• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    አቡነ አኖሬዎስ


    በአባቱም ቤት እያለ ሐራንኪስ የሚባል መጸሕፍትንና የያሬድን ማኀሌት የሚያውቅ ስው መጣ፡፡ በአባቱ ቤት አደረ፣በዚህም ተቀመጠ፡፡ አቡነ አኖርዮስ ከእርሱ ማህሌተ ያሬድን በትኅትና በትዕግስት በማስተዋልና በመረዳት ተማረ፡፡ አዝወትሮም ይጸልይ ነበር መዘመርንም አያቆርጥም ነበር፡፡እየተማረ በትህትና ኖረ እንጂ፡፡ ጾምንና ጸሎትን ወደደ፣ ንጽሕናንና ትዕግሥትንም ገንዘብ አደረገ፡፡

    ጌታችን በወንጌል ‹‹በትዕግሥታችሁ ነፍሳችሁን ገንዘብ ታደርጓታላችሁ›› እንዳለ ፡፡ ደግመኛም አለ ‹‹ስለ እኔ ብሎነፍሱን የተዋት ያገኛታል›› ይህንን ሁሉ ከልጅነቱ ጀምሮ ያስብ ነበር፡፡ ስለ ጽድቅም ሲል ነፍሱን ተዋት፡፡ ደግሞም ጻድቅ አቡነ አኖርዮስ ዓለም እንደሚያልፍ ሀብትም እንደሚሻርና እንደሚጠፋ ወርቅና ብርም እንደሚዝግ አሰበ፡፡ ምንኩስናውም ወደደ፡፡ የሲራክ ትምህርት በልቦናው ሰምቷልና በጸጥታ ይኖር ዘንድ ፈለገ፡፡ ‹‹አግዚአብሔር የመትፈራው ነፍስ ሕያው ትሆናለች፣ወደ እርሱም ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው የሚያስፈራው የሚያስደነግጠው የለም ፡፡ እርሱ ተስፋው ነውና፡፡ እግዚአብሔርን የምትፈራ ነፍስ ብጸዕት ናት፣የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፡፡››

    ምንኩስና መፈለጉ እናትና አባቱ አላወቁም ነበር፡፡ እነርሱ እንደ ሕጉ ሚስት ሊያጩለት አስበው ነበር፡፡ ቅዱሱም ይህንን ነገር እንዳወቀ ከአባቱና ከእናቱ ጋር ሳይማከር በጸጥታ ተነስቶ ወደ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘንድ ደረሰ፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም ባየው ጊዜ ብዙ ምርኮን እንዳገኘ ሁሉ ተደስተ፡፡ ተነስቶም ሳመውና ‹‹የመንፍስ ቅዱስ ቤት ሆይ ስላም ላንተ ይሁን›› አለው፡፡ አባታችንም ከእርሱ ተባረከ፡፡ በየዋህትም በትህትናም እንዲህ አለው ‹‹አባት ሆይ ዜናህን ሰምቼ ወዳንተ መጣሁ፣የቅዱሳንን የምንኩስና ልብስ ትሰጠኝ ዘንድ››፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖትም መለሰለት እንዲህ ሲል ‹‹ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን፣ልጄ ሆይ ጥቂት ጊዜ ጠብቅ ፣የቅዱሳንንም ሁኔታቸውን ታይ ዘንድ ተቀመጥ፣ ከዚህም በኋላ የምንኩስናን ልብስ እሰጥሃለሁ››፡፡ ቅዱሱም አቡነ ተክለሃይማኖት ቃሉን ሰምቶ ከመነኮሳት እንዳየው በብዙ ጾምና ጸሎት ተጠምዶ  ከርሱ ጋር ተቀመጠ፡፡

    ከጥቂት ጊዜም በኋላ አቡነ ተክላሃይማኖት አቡነ አኖሬዎስን የንጽሕናና የቅድስና ልብስ የሚሆነውን ልብስ ምንኩስናን አለበስው፣አሰታጠቀውም፡፡ በመልካም ምግባሩ የተነሳሣ በአቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ዲቁና ይሾሙት ዘንደ መረጡት፡፡ እንደ ሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስም በዚያ ሾሙት፡፡ እርሱም በሕግና በሥርዓት ፍጹም ሆነ፡፡

    መልካምነቱን ባዩ ቅዱሳንም ሁሉ አንድ ሆነዉ በዚያች ገዳም ላይ ከአቡነ ተክለሃይማኖት በታች መጋቤ አድርገዉ ሾሙት፡፡ ለእርሱም ታዘዙለት፡፡ እርሱም በግዴታ አያስተዳድራቸዉም ነበር ፡፡ በየዋህ ቃል ያዛቸው ነበር እንጅ፡፡ መልካም ጠባይ ያለው ነበረና በዚያ የተነሳ የተከበረ ሆነ ፡፡ ቅዱሳንም ሁሉ ይወዱት ትእግስቱንም ያደንቁ ነበር፡፡ መነኮሳትንም ‹‹አትታክቱ ተግታችሁ ጸልዩ፣ በመገዛት ተጋደሉ፣ ሰለ  ሥጋ ነገር ከማሰብ ለእግዚአብሔር መገዛት ይበልጣልና›› ይላቸው ነበር፡፡ ጻድቅ በሕይወት ሳለ ይከብራል ይወደሳልም፣ ከሞተ በኋላም እጅግ ከፍ ከፍ ይላል፡፡

    በሔደበት፣ በተቀመጠበት ‹በተኛበትም የምተከተለው አንዲት ሴት ነበረች አንድ ቀን በመኝታው እያለ መጥታ በላዩ ላይ ወደቀች ፡፡ እርሱም ‹‹ነብር ነብር››ብሎ ጮኸ፡፡ ያቺም ሴት በፍርሃት የተነሣ ሸሸች፡፡ ጩኸቱንም በሰሙ ጊዜ ቅዱሳን ወደ እርሱ መጡና‹‹ ምን ሆንክ›› አሉት፡፡ እርሱም ‹‹በተኛሁ ጊዜ ነብር ወደ እኔ መጣ ስጮህም ከእኔ ዘንድ ሄደ›› አላቸዉ፡፡ ወንድሞቹም በእዉነት ነበር የታየዉ መሰላችው፡፡ የሴቲቱን መምጣት አልነገራቸውም፡፡

    ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያቺ ሴት ከሌላ ሰው ፀነሰች ፡፡ ከማን ነው የፀነሽዉ ሲሉዋት ዋሽታ ‹‹ከአኖሬዎስ ነዉ›› አለች፡፡ በምግባር የተትረፈረፈ አቡነ ተክለሃይማኖት ይህንን ሲሰማ ልጁ አኖሪዎስን ‹‹ልጄ ሆይ ሴቲቱ ካንተ ነው የጸነስኩት የምትለዉ እውነት ነውን?›› አለዉ ያም ቅዱስ ልጅ ለአባቱ ‹‹ አባት ሆይ ከኃጢአት ንጹሕ የሆነ የለም ›› አለዉ፡፡ በዚህም ጊዜ የአባቶቻችን አባት (ተክለ ሃይማኖት) መሪር ልቅሶን አለቀሰ፡፡ የሚያደርገዉንም አጣ ፡፡ ንስሐንም ሰጥቶ አሰረዉ፡፡ ባልሠራው ሥራ ታሥሯልና ቅዱሱ ደስ አለዉ፡፡

    የመውለጃዋ ጊዜም በደረሰ ጊዜ ማኅፀኗ ተዘጋ፣ከባድ ህማምም ያዛት፡፡ በጽኑ ሕማሟም የተነሣ ‹‹ይህች ሕመም በምን ምክንያት አገኘችሽ?›› ብሎ ተናግሯት፡፡ ያቺ ሴት ‹‹በጻድቁና ቅዱሱ ሰዉ አኖሬዎስ ላይ የሐሰትን ነገር ስለተናገርኩ ነው›› አለቻቸው ፡፡ ይህም ነገር ካለፈ በኋላ ሴትየዋ ያለችውን ለአቡነ ተክለሃይማኖት ነገሩት፡፡ ወደ እርሱም ዘንድ ሔዶ ‹‹ባላደረከዉ ነገር ታሠርክ፣ እንግዲህስ ይፈቱሃልና ደስ ይበልህ›› አለዉ፡፡ ብጹዕ የሚሆን የአባቶቻችን አባትም ለመነው፡፡ አለዉም ‹‹ባንተ ላይ የሚመሰክር ማን አለ?››፡፡ከዚያም ‹‹ተፈታ›› አለዉ፡፡ በዚህ ጊዜም ማሰሪያው ወለቀ፣ ከእግሩም ተፈታ፡፡ (መሠርያዉም ) ሁለትና ሦስት ጊዜ ዘለለ፡፡ የአባቶቻችንን አባትም ይህንን ባየ ጊዜ ለእሱ ተንበረከከ፡፡‹‹ልጄ ሆይ ይቅር በለኝ››አለዉ ፡፡ ሁለቱም ቅዱሳን ተላቀሱ፡፡ የእግዚአብሔርን የታላቅነቱንም ነገር እርስ በርሳቸው ‹‹ምስጋና ለእርሱ ይሁን›› እያሉ ተነጋገሩ፡፡አቡነ አኖሬዎስም ተነሳና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ‹‹አባት ሆይ የመነኮሳትን ማኅበር ከመነኮሳዪት  ማኅበር መለየት የተሻለ ነው፡፡ መነኮሳት ብቻቸዉን ይኑሩ፣ የመነኮሳዪያትን ማኅበር መለየት የተሻለ ነዉ፡፡ መነኮሳት ብቻቸዉን ይኑሩ፣ መነኮሳዩያትም ለብቻቸዉ ይቀመጡ፡፡ አባት ሆይ ስማ እሳት በእጨቶች መካከል ተደብቆ እንዴት ይቀመጣል? እንዳይታወኩ በየራሳቸው ይቀመጡ፡፡ በልቶም አመድ ያደርገዋል፡፡ ያጠፋዋልም ፡፡ እርስ በርሱ የተፋተገዉም ራሱን ብቻ ሳይሆን ታላቁንም ታናሹንም ያቀጥላል፡፡ በፊቱም ሊከላከለዉ የሚቻለዉ የለም፡፡ እሳት ፈጣሪው ሰይጣንም እሳት ባለበት ኅሊና ይሠለጥናል፡፡የዝሙት አሳትም ሥጋና ነፍስ ይበላል፡፡ ሴቶችንና ወንዶችንም ከመለያየት በቀር ሊያቆመዉ የሚችል የለም፡፡››
    የነፍሳት ጠባቂ የሆነ አባታችንም ለልጁ እንዲህ አለዉ፣ ‹‹ይህ ሥርዓት መልካም ነዉና ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም ድረስ እንደምትለው ይሁን፤››አለው፡፡

    ሹመትም እምቢ አለ፡፡ በዚህ ጊዜም ተነሳና ወደ ሩቅ ሀገር ወደ ትግራይ ሄደ፡፡ እርሱም ጸዓዳ አምባ ነዉ፡፡በዚያም አቡነ አኖሬዎስ ለብቻዉ ተቀመጠ፡፡ከቅዱሳን መከራዎችም ብዙዎችን መከራዎች ተቀበለ፡፡ ከዚያም ወደ አባቱ ገዳም ተመለሰ፡፡

    ጋት ይነሥን ከተባለ ልጇጋር አብራ የምትገዛ አዉሬ ገዘባ የተባለችዉን ጠንቋይ አገኛት፡፡ የሀገሩም ሰዎች ሁሉ ከእግሮቿ በታች ይሰግዱላት ነበር፡፡ በየቀኑም አሥራ ሁለት ላሞች ያርዱላት ነበር፡፡ አቡነ አኖሬዎስም የሀገሩ ሰዎች ሁሉ እንደሚስግዱላት፡ እንደሚያርዱለትም በሰማ ጊዜ ወደ እርሷ መጣ፡፡ ቀርቦም አላት‹‹ሴትዮ ሆይ በምን መክንይት የሠዉልሸል ?በምንስ ምክንያት ከእግርሽ በታች የሰግዱልሻል?አንቺ አምላክ አይደለሽም››አላት፡፡

    ፍሡሕ ከሆነ ከዚህ አባታችን ቃል የተነሣ የቺ ጠንቋይ ፈራች፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍትም ነገራት፡፡የሃይማኖትም ቃል አስተማራት፡፡ በእየሱስ ክርሰቶስም ስም አሳመናት፣ልጇንም አሳመነዉ፡፡ ከጥቂት ጊዜም በኋላ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃት፡፡ሰሟንም ማርያም ኃይላ ብሎ ጠራት ፡፡ ልጇንም አጥምቆ መርቆሬዎስ አለዉ፡፡ በዚያም በቀርሜሎስ መካከል ትንሽ ቤተክርስቲያን ተከለ፡፡ ያቺንም ጠንቋይ አመነኮሳትና መነኩሲት ሆነች፡፡

    አንድ ቀንም ቅዱስ በቤቱ እያለ ዘካርያስና ዘርዐ አብርሃም ወጡ፡፡ አነርሱም የዱር አራዊትን የሚያድኑ ወንድማማቾች ነበሩና፡፡ አንዲት ሚዳቋም አገኙና አብርሃም በቀስት ወጋት፡፡ የደሟን ፈለግ እየተመለከቱም ተከተሏት፡፡ በበረሐዉም መካከል አደባባይ የመሰለ መልካምን ቦታ አገኙ፡፡ ሚዳቋዋንም ትተው‹‹ ሰባታችንን እንንገረው፣ቤተ ክርስቲያን የምታንጽባት ቦታ አገኘን እንበለው‹ ልብ ቆራጥ ነውና ተነሥቶ ሲመጣ የሐራስን ሰዎች ቢያገኛቸው ከሀገራችን ያሳድዳቸዋል፡፡ ይህንንም ተነጋግረው ወደ አባተታችን ዘነድገቡ፡፡ እንዲህ ብለውም ነገሩት ‹‹ አባት ሆይ ለንተ‹ ካንተም በኋላ ለልጆችህ የሚበቃ መልካም ቦታ አገኘንልህ፡፡

    ቅዱስም ይህንን ሲሰማ ተደስተ፣ ሐሴትም አደረገ፡፡ ‹‹ ለጆቼ ሆይ ኑ አሰዩንኝ›› አላቸው ቅዱሱም ተነሳና በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት ከሁለቱ ወንድሞችና ከጥቂቶቹ ልጆች ጋር ሄደ፡፡ ወደዚያች ቦታም ደረሰ፡፡ ብዙ ዛፎችና ድንጋዩችም ነበሩበት፡፡ በዚያም የሐራስ ሰዎች ይኖሩ ነበር፡፡ ያቺን ምድርም እንደ አደባባይ የከበረች መሆንዋን ባየ ጊዜ በዚያ ቆሞ ምስራቅንና ምዕራብን፣ ሰሜንና ደቡብን አየ፣በመስቀሉም ባረካት፡፡ በዚያች ይኖር ዘንድም ወደዳት፡፡ ‹‹ይህቺ ለዘላለም ማረፊያዬ ናት፣ መርጫታለሁና በዚች አድራለሁ›› ሲልም ትንቢት ተናገረ፡፡

    ወዳጆቼ ሆይ ተመልከቱ፡፡ አባታችን አቡነ አኖሬዎስ በላዩ ባደረ በመንፈስ ቅዱስ ነቢይ ነዉ፡፡ ከመሆኑ በፊት ያዉቅ ነበርና ፡፡ ጳዉሎስ ‹‹መንፈስ ያለበት ሁሉን ያውቃል››እንዳለ፡፡ የርሱን የልጆቹ ርስት መሆንዋን ዐወቀ፡፡ ዘካርያስና አብርሃምን‹ ያለበሳቸውን ያስታጠቀቸውንና ቆብ የጫነላቸውን መነኮሳት ሁሉ፣‹‹እዚህ መኖር ይሻለናልና መነጥሩት ጥረጉም››ብሎ አዘዛቸው፡፡ አብርሃምና ዘካርያእም በማጭድና በምሣር መጥረግ ጀመሩ፡፡በሰይፎቻቸውም እንጨቶችን ቆርጡ፡፡ለቅዱሱም መንገድን ጠረጉለት፡፡ በዚያም ዘጠኝ ቤቶችን ሠሩ፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም እንደ ቀድሞው በአንዲት ቀን ሠርቶ ፈጸመ፡፡

    ቅዱሱም በዚያችም በሜዷ በቀኟና በግራዋ ወዲያና ወዲህ ሲል የውኃ ምንጭን አገኘ፡፡ደስም አለው፡፡ አንድ እጨትም ቆርቶ ፈለጠው፡፡ ቁመቱም በሰው ክንድ ሰባ ክንድ ሆነ፡፡ ለቤተ ክርስቲያንም አደረገው፡፡በብዙም መከራ በዚያ መልካም ገድልን እየተጋደለ ተቀመጠ፡፡ 
    የጌታችንን የእግዚአብሔርን ነገር ለሚሰማዉ ድንቅ ነዉ፡፡ ምክሩ ከሰው ኀሊና  የራቀ ነው የበጎች አረኛ ሆኖ ያለ ዋጋ ለተሾመ ለካህኑ አኖሬዎስ ኃይልና ጽንዐትን የሰጠ፣ነብይ ‹‹ እግዚአብሔር ጻድቃንን ይደግፋችዋል፡፡›› እንዳለ፡፡ አኖሬዎስ በእውነት በአምላኩ ኃይል ጸና፡፡ የሐራስንም ሰዋች በጸሎት አሳደዳቸው፡፡በዚያም ቦታውን አደረገ፡፡ ገዳሙም እጅግ በረታች፡፡

    ይቀጥላል፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አቡነ አኖሬዎስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top