• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday, 11 November 2015

    በዓለ ጰራቅሊጦስ

    በዓለ ጰራቅሊጦስ ወይም በዓለ ጰንጠቆስጤ ከዘጠኙ የጌታችን ዐበይት በአላት አንዱ ሲሆን መንፈስ ቅዱስለሐዋርያት የወረደበትን ቀን የምናስብበት በዓል ነው። ጰራቅሊጦስ የግሪክ ቃል የሆነ የመንፈስ ቅዱስ መጠሪያ ነው። ትርጉሙም በጐን የሚቆም፣ የሚረዳ፣የሚያጽናና ማለት ነው። አበው መንጽሂ /የሚያነጻ፣የሚቀድስ/ መጽንሂ /የሚያጸና፣ የሚያበረታ/ በማለት ይገልጹታል። ጰንጠቆስጤ የሚለውም የግሪክ ቃል ሲሆን “ፔንዲኮንዳ” ሃምሳ “ፔንዲኮስቲ” ሃምሳኛ ማለት ነው። በዓሉ ጌታችን ባረገ በአሥረኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ በተነሳ በሃምሳኛው ቀን ይከበራል።

    የበዓሉ የትመጣ

    እስራኤል ከግብጽ ከወጡና ሕገ ኦሪት ከተሰጠቻቸውጊዜ ጀምረው በዓለ ፋሲካን ለማክበር በኢየሩሳሌምይሰበሰባሉ። ፋሲካ ለእስራኤል የነፃነት በዓላቸው ስለሆነ በስደት ምክንያት ወደ ተለያዩ ሀገሮች ከተበተኑ በኋላም እንኳን ካሉበት በመምጣት በዓሉንየሚያከብሩ ሲሆን ከፋሲካ ማግስት ጀምረው ሃምሳውን ቀን በዓል አድርገው አገር የቀረበው በየአገሩ እየሄደ አገር የራቀበት ስንቁን ይዞ ከዚያው ከኢየሩሳሌም ይሰነብታል። በሃምሳኛው ቀን በዘፀ ፴፬፥፳፪፣ በዘሌዋ ፳፫፥፲-፲፯ በታዘዙት መሠረት  በዓለ ሰዊትን /የእሸት በዓልን/ ካመረቱት ምርት በኩራቱን ለመሥዋዕት በማቅረብ ያከብራሉ። በዓለ ፋሲካን ለማክበር ከዝርወት ተሰብስበው የነበሩ አይሁድ ሁሉወደየመጡበት የሚመለሱት ይህን በዓለ ሰዊትን ካከበሩ በኋላ ነው። በዓለ ሰዊትን በዝርወት. የተሰበሰቡና በዚያውም የሚኖሩ አይሁድ አብዛኛውንጊዜ በዓል የሚያከብሩት በደብረ ጽዮን ነው።

    በዚሁ ልማድና ሥርዓት መሠረት ጌታችን በመሥቀልተሰቅሎ ድኅነተ ዓለምን በፈጸመበት ዓመት እስራኤላዊያን በዚች በደብረ ጽዮን በዓለ ሰዊትን ለማክበር ተሰብስበው እንዳሉ ሐዋርያት ደግሞ ጌታችን የነገራቸውን ተስፋ እየተጠባበቁ በዚሁ በደብረ ጽዮን በቅዱስ ማርቆስ እናት ቤት ውስጥተሰብስበው ነበር። ይህች ቀን ጌታ ባረገ አሥረኛው. ቀን ነበረች። በዚህች ዕለት ጠዋት አይሁድ የቀድሞውን በዓል ሲያከብሩ ለሐዋርያት ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ተፈጸመላቸው፤ መንፈስ ቅዱስ ተሰጣቸው /ሐዋ ፪፥፩-፬/ በማለት በሐዋርያት ሥራ ላይ ጽፎልናል። ስለዚህም ቅዱሳን ሐዋርያት በዲድስቅሊያ 31 “ከዕርገቱ ቀን በኋላ ታላቅ በዓል ይደረግ፤ በዚህች ቀን በሦስተኛው ሰዓት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጰራቅሊጦስን ልኮልናልና እኛም በእርሱ ስጦታዎች ተሞላን አዳዲስ ቋንቋን ተናገርን” በማለት በዓሉን በቤተ ክርስቲያን እንድናከብር ሥርዓትን ሠርተዋል።

    በዚህም መሠረት በነቢያትና በሐዋርያት ትምህርት ላይ የታነጸችው ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንኑ በዓል ዛሬም ድረስ ታከብራለች።

    ትንቢት

    በቅዱስ መጽሐፍ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተገለጠውን ስናይ የአብና የወልድ ሕይወታቸው የሆነ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለዓለሙ ሁሉ ሕይወትን የሚያድል ስለሆነ ምሉዕ ሆኖ በሁሉ ቦታ እንዳለ“የእግዚአብሔርም መንፈስ በውሃ ላይ ሰፍፎ ነበር´’ /ዘፍ ፩፥፪/ በማለት ይገልጻል። ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ በዘመናት ሁሉ ከእግዚአብሔር ወዳጆች ጋርበመሆን ምግባር ትሩፋት እንዲሠሩ ያደርጋል። ሆኖምግን የሰው ልጆች ኃጢአትን በሰሩ ጊዜ በዓለም ላይ ምሉዕ የነበረው የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰው እንደራቀ ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጽልናል። እግዚአብሔርም መንፈሴ በሰው ላይለዘላለም አይኖርም፥ እርሱ ሥጋ ነውና፤ ዘመኖቹምመቶ ሃያ ዓመት ይሆናሉ አለ /ዘፍ ፮፥፫/። ኋላም ሰውን ወዳጅ የሆነው ልዑል አምላካችን የሰውን ልጅበሞቱ ሊያድነውና በቅዱስ መንፈሱም ሊያጸናውና. ሊያጽናናው መፍቀዱን በነቢያት አድሮ ትንቢት. አናግሯል። ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “ከእሴይ ግንድበትር ይወጣል። ከሥሩም ቁጥቋጥ ያፈራል።የእግዚአብሔር መንፈስ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ የምክርና የኃይል መንፈስ የዕውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።” /ኢሳ፲፩፥፪/ በማለት ተናግሯል። በተለይም የመንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት መውረድ “መንፈሴን በሥጋ ለባሽሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁምትንቢትን ይናገራሉ፥ ሽማግሌዎችሁም ሕልምን ያልማሉ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ…” /ኢዩ ፪፥፳፰/የሚል የነቢይ ቃል ነበረ።

    የትንቢቱ ፍጻሜ

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ የመረጣቸው ደቀ መዛሙርት በመጀመሪያ አካባቢ ይከተሉት የነበረው ምድራዊ ሹመትና ሥልጣን ከመፈለግ አንጻር ነበረ። ይሁን እንጂ እየዋሉ እያደሩ ቃሉን ሲሰሙ ለምድራዊ ክብር ሳይሆን ለሰማያዊ ክብር መጠራታቸውን ነግሯቸዋል። ይሁንእንጂ ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣበትን የሰውን ልጅ ከዘላለማዊ ሞት የማዳን ዋነኛ ዓላማ ለመፈጸም ተቃርቦ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ደቀ መዛሙርቱየፍርሃትና የመታወክ ልብ ነበራቸው። ይህ የሚታወክ ልቦና ሊረጋጋ የሚችለው በሚኖራቸው ፍጹም እምነት እንደሆነ ለማስረገጥ “ልባችሁ አይታወክ በእግዚአብሔር እመኑ በእኔ ደግሞ እመኑ” /ሐዋ፲፬፥፩/ ብሏቸዋል። ፍጹም የሆነ እምነት ያለው ሰው አይረበሽም አይታወክም። የሚያስፈራው የሚያስደነግጠው ነገር አይኖረውም።

    ጌታ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ደቀ መዛሙርቱን  “ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ቆዩ” /ሉቃ ፳፬፥፵፱/ ባላቸው መሠረት የተገባላቸውን ቃል ኪዳን በተስፋ ሲጠብቁ ቆይተዋል። ይህ ኃይል መንፈሳዊናሰማያዊ ኃይል ነው ይህም የሚገኘው ከእግዚአብሔር ብቻ ነው። ይህንን ኃይል ለማግኘትእግዚአብሔርን በትዕግስት ሆኖ ደጅ መጥናት ያስፈልግ ነበረ። ስለዚህም ደቀ መዛሙርቱ “ሁሉምበአንድ ልብ ሆነው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ ዐውሎነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፣ ተቀምጠው የነበረበትንቤት ሞላው እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጡባቸው በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር” እንዲል /ሐዋ ፪፥፪-፬/። ሁሉም በአንድ ልብነበሩ፤ የተከፋፈለ ሃሳብ አልነበራቸውም። ዛሬ የብዙዎቻችን ልብ ቀርቶ የእያንዳንዳችን ልብ እንኳንአንድ አይደለም። በብዙ ነገር ልቦናችን ይከፋፈላል።እግዚአብሔር ኅብረትና ፍቅር ከሌላቸው ሰዎች ጋርምንም አይሠራም።

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ “አብ በስሜ የሚልክው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው ኣጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል።እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።” /ዮሐ፲፬፥፳፮/ ባለው መሠረት ደቀ መዛሙርቱን የሚያጽናና፣ የሚያረጋጋና ምሥጢርን የሚገልጽ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል። ደቀመዛሙርቱ ይህንን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ በበዓለ ሃምሳ ካገኙበት ጊዜ ጀምሮ የተሰጣቸውን የምሥራችየሆነውን ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ ለመስበክና ኃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት ራሳቸውን ለእግዚኣብሔር የተቀደሰ አድርገው አቅርበዋል። በዚሁ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ከወረደላቸውና የመንፈስ ቅዱስ ማደርያ ከሆኑ በኋላበመንፈስ ብርቱ ሆነዋል፣ በዕውቀት ጎልምሰዋል፣ከብልየት ታድሰዋል።

    በዕለቱ ከተለያዩ የዓለም አገራት በዓለ ሃምሳ የተባለውን ታላቅ በዓል ለማክበር ኢየሩሳሌም የተሰበሰቡ ብዛት ያለው ሕዝብ ሐዋርያት በቋንቋቸው ወንጌልን ሲሰብኩ በመስማታቸው ተደንቀዋል። “እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋቸው ሲናገሩ ይሰማ ስለነበር የሚሉትን አጡ ተገርመው ተደንቀውም እንዲህ አሉ፥ እነሆ እነዚህ ሁሉ የሚናገሩ የገሊላሰዎች አይደሉምን እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን” /ሐዋ ፪፥፯-፰/ በማለት በመገረም ይናገሩ ነበር።በዚህ ዕለት ቅዱስ ጴጥሮስ በሕዝቡ መሐል ተገኝቶ አይሁድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት አድርገውመከራ እንዳጸኑበት፣ በመስቀል ላይ እንደሰቀሉት፣እንደገደሉት እርሱ ግን ሞትን ድል አድርጎ ተነሳ እኛደግሞ ለዚህ ምስክሮች ነን ብሎ ማንንም ሳያፍርና ሳይፈራ ያስተምር ነበር። ባስተማረው ትምህርት ልባቸው የተነካ ብዛት ያላቸው ሰዎች ሐዋርያትን ወንድሞች ሆይ ምን እናድርግ ሲሉ ጠይቀዋል። ቅዱስ ጴጥሮስ “ንስሐ ግቡ ኃጢያታችሁም ይሰረይዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስምተጠመቁ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ” በማለት ንስሐ እንዲገቡና የተስፋው ቃል ተሳታፊዎችእንዲሆኑ አስተምሯቸዋል።

    ቃሉን ሰምተው ንስሐ የገቡና የተጠመቁ ሰዎች ቁጥራቸው ሦስት ሺህ ያህሉ ነበር። ቃሉንም የተቀበሉተጠመቁ፥ በዚያን ቀን ሦስት ሺህ የሚያህል ነፍስተጨመሩ፤ በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቁረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር። /ሐዋ ፪፥፵፩-፵፪/። ያመኑት ሁሉ አብረው በኅብረት ይኖሩ ነበር ያላቸውን ሀብት ንብረት ሳይቀር አንድ ላይአደረጉ። በመካከላቸው መለያየት አልነበረም። ሀብታም ደሃ ትንሽ ትልቅ የሚል ልዩነት አልነበረም።ሁሉም እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪነበሩ። ሁለት ሦስት ሆናችሁ በስሜ በምትሰበሰቡበት በመካከላችሁ እገኛለሁ ብሎ ነበረና በስሙ አንድሆነው በፍቅር በመገኘታቸው “ስጦታን ለሰው ልጅ ሰጠህ” /መዝ ፷፯፥፲፰/ የሚለው የዳዊት ቃል በእነርሱ ላይ ተፈጽሟል። ሰማያዊ በረከትንና ጸጋውንሊቀበሉ ችለዋል። በዚህም ስጦታ የመንፈስ ልዕለናን ይዘው ጨለማውን ዓለም በወንጌል አብርተዋል። ኃይለ አጋንንትን ድል አድርገዋል። አላውያን ነገሥታትን አሳፍረዋል።

    ቤተ ክርስቲያን በዚህ ቀን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታለች። ልጆች የሆንን ሁላችንም በአርባና በሰማንያ ቀን ስንጠመቅ ነው ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ የተወለድነውና ከሥላሴ ልጅነት ያገኝነው። ይህን በጥምቀት ጊዜ ያገኘነውንጸጋ አክብረን ልንይዘው ይገባናል። “በትሕትና ሁሉናበየዋህነት በትዕግስትም እርስ በርሳችሁ በፍቅር ታገሱ በሰላም ማሰማሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” /ኤፌ ፬፥፪-፫/ እንዲል እንደተሰጠን የጸጋ ስጦታ መጠን ቤተ ክርስቲያንን በፍቅር በአንድነት ሆነን ልናገለግል ይገባናል። እርሱ በማይታበለው ቃሉ ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ያለ ጌታ ዛሬም በደሙ የዋጃትን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆችን አይተዋቸውም።ብቻ እኛ በቤቱ ጸንተን በፍቅር እንኑር። ሁሌም እርሱ ከእኛ ጋር ይኖራል። ለዚህም የእግዚአብሔር መንፈስቅዱስ ጸጋ የእመቤታችን ኣማላጅነት የሐዋርያት ረድኤት በረከት አይለየን። አሜን!

    በዲ/ን ዶ/ር ንዋይ ገሠሠ

    ***ወስብሐት ለእግዚአብሔር***

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በዓለ ጰራቅሊጦስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top