• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት በምን ይለያል?

    መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት በምን ይለያል?

    1. ትንቢቱ የተረጋገጠ እውነት በመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር በመረጣቸው ነቢያት የራሱን አምላካዊ ፈቃድ የገለጠበት ፍጻሜውንም በወሰነው ጊዜ እንዳከናወነ የተመዘገበበት ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተስፋና የፍጻሜ መጽሐፍ ነው፤ በብሉይ ኪዳን አዶናይ ለሕዝቡ የሰጠውን ተስፋ በአዲስ ኪዳን ፈጽሟልና፡፡ በብሉይ ኪዳን በትንቢት የተነገሩት ከሰው አእምሮ እና ከተፈጥሮ ሕግ በላይ የሆኑት አምላካዊ እቅዶች በአዲስ ኪዳን በትክክል ተፈፅመዋል፡ “ድንግል ትጸንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” የሚለው የትንቢት ቃል ለተርጓሚው ለስምዖን አረጋዊ አእምሮ ቢከብድም ጌታ እንደቃሉ ከድንግል ማርያም ያለ ወንድ ዘር በመወለድ ፈጽሞታል፡፡ ኢሳ. 7፡14፤ ማቴ. 1፡23፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገሩ የትንቢት ቃሎች ለጸሐፊዎች ቢከብዱም ተፈጽመዋል፡፡ ያልተፈጸሙትም በጊዜያቸው ይፈጸማሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜ ያገኙና ያላገኙ ትንቢታትመዝገብ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ስለሚሆነው በእርግጠኝነት የሚናገር ብቸኛ መጽሐፍ ነው፡፡ መዝ. 49፡2

    2. ስለፍጥረታት አፈጣጠር በእርግጠኝነት ስለሚናገር፡- መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረታት አፈጣጠር ሲናገር በመላምታዊ አመክንዮ አይደለም፤ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ በማለት በእርግጠኝነት ይናገራልና፡፡ ዘፍ. 1፡1፡፡

    3. የሰው ፈጠራ (ልብ-ወለድ) ባለመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የጠቢባን ምርምር ውጤት የሆነ ፍልስፍና፤ የደራሲያን የምጥ ፍሬ የሆነ ልብወለድ አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነትና ጥረት የደረሱት የፈጠራ ድርሰት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች መግባቢያ ቋንቋና ፊደል የተጻፈ ቢሆንም እንኳ ቃሉ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ኤር. 1፡9፤ ዘካ. 6፡9፤ዮሐ. 2፡22፤ ራዕ. 20፡12፡፡

    4.በእግዚአብሔር መንፈስ የተመሩ (የተነዱ) ቅዱሳን ሰዎች የጻፉት በመሆኑ፡-መጽሐፍ ቅዱስ የተለዩና የተመረጡ ሰዎች የጻፉት ቅዱስ መጻሕፍት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የቅድስና ጥሪ ሰምተው፣ በበጉ ደም ተዋጅተው፣ በፈቃዱ ተመርተውና በኑሮ ሥርዓታቸው አክብረውት ያረፉ ሰዎች ቅዱሳን ይባላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ባከበራቸው ቅዱሳን ያጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ 2ኛጴጥ. 1፡20፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በተመረጡ ጣቶች የተጻፈ ምርጦችንም የሚያፈራ አምላካዊ ቃል ነው፡፡

    5. ዘመን የማይለውጠውና የማይሽረው በመሆኑ፡- ብዙ መጻሕፍትን ዘመን ሽሯቸዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡ በዘመን ብዛት የተረሱ በርካታ መጻሕፍት አሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በየዘመናቱ እጅግ ተፈላጊ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የተረሳውን የሚያስታውሰው አምላክ ቃል በመሆኑ አይዘነጋም፤ በየጊዜው ተሽሎ ለሚነሳው ትውልድ የሕይወት ሥርዓት መሪ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና፡፡ ኢሳ. 40፡8፡፡

    መጽሐፍ ቅዱስ በየዘመናቱ የገጠሙትን የአመለካከት ጽንፎችና የኢ-አማንያንን ጦርነቶች አልፎ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታትን ያስቆጠረው አምላካዊ ቃል ስለሆነ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብርቱ ተቃውሞዎችን አልፎ ለዚህ ትውልድ የደረሰው እግዚአብሔር በረዳቸው የታመኑ ምስክሮች መስዋእትነት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመን የማይሻርና በትውልድ የማይሻሻል ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉም መጻሕፍት በላይ የእድሜ ባለጠጋ (አረጋዊ) ነው፡፡ 

    6. ለሁሉም የሚናገር መጽሐፍ ስለሆነ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ድሀና ሀብታም፣ የተማረና ያልተማረ፣ ትንሽና ትልቅ ሳይልሁሉን በየአድራሻው ይናገራል፡፡ ፊት አይቶ የማያደላው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ የላከው የፍቅር ደብዳቤ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስማንነትን በግልጥ በስልጣን ቃል ይናገራል፡፡

    7. የሚያነቡትንና የሚሰሙትን የሚባርክና የሚያንጽ በመሆኑ፡- በዓለማችን አንባቢያንን የሚያንጹ መጻሕፍት ሊኖሩቢችሉም እንኳ ከመጽሐፍ ቅዱስ በላይ ውስጣዊ ማንነትን የሚሠራ መጽሐፍ የለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ የሕይወት መምህር ነው፡፡ አንባቢያንና ሰሚዎች ከመታነጽ አልፈው የሚባረኩበትም መጽሐፍ ነው፡፡ መዝ. 22፡4፣ 2ጢሞ. 3፡17፣ ራዕ. 1፡3፡፡መጽሐፍ ቅዱስ የሚያንጻቸውና የሚባርካቸው የታላቅነትን ምስጢር በማወቅ ስኬትን ይጎናጸፋሉ፡፡ ንግሥት ቪክቶሪያ “የእንግሊዝ አገር ታላቅነት ምስጢሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የታላቅነትን ምስጢር እንደሚያጎናጽፍ መስክራለች፡፡ 

    8. የሁሉ ምንጭ በመሆኑ፡- መጽሐፍ ቅዱስ የሃይማኖትና የስነ-ምግባር፣ የኪነጥበብና የስነ-ጽሁፍ፣ የሥራ-አመራርና የፍትሕ፣ የግብርናና የጤና፣ የእውነተኛ መጻሕፍትና የእውነተኛ ትምህርቶች ምንጭ ነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ባለመጥፋት ከሚወዱት ጋር ይሁን!!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት በምን ይለያል? Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top