• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    አጨብጫቢ – ክፍል አንድ


    ጭብጨባ ለተለያዩ ነገሮች ይደረጋል። በጣም የተለመደውና በየቦታው የሚታየው ጭብጨባ የዘፈን ጭብጨባ ነው። የመዝሙርም ጭምር። ይህ የዜማውን ፍጥነት ወይም ምት ለመጠበቅ የሚረዳና ማዳመቂያም ነው። ሌላው ጭብጨባ የአድናቆት መግለጫ ነው። የኳስ ግብ ሲገባ፥ ነጥብ ሲቆጠር ይጨበጨባል። አለቃ ወይም መሪ ወደ አዳራሽ ሲገባም ይጨበጨባል፤ ይህ ለሙሽራም፥ ለአርበኛም ይሆናል። ዲስኩር አድራጊ ኃይለ ቃል ሲናገር ወይም ንግግሩን ሲጨርስም ይጨበጨባል።  በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለጭብጨባ የሚናገሩ ጥቅሶች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጭብጨባ ይናገር እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩት ጭብጨባዎች መላቅጣቸው የጠፋ ሆነዋል። በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጭብጨባ የሚናገርባቸውን ሁኔታዎች እንይ። በጠቅላላው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወደ አሥራ አምስት ጊዜያት ያህል ጭብጨባ ተጠቅሶአል።  በመጀመሪያ ለእግዚአብሔር የተጠቀሱትን ጥቂት እንይ። በመዝ. 98፥8 ያለው፥ ወንዞችም በአንድነት በእጅ ያጨብጭቡ የሚል ቃል አለ። በኢሳ. 55፥12 ላይም የሜዳ ዛፎችም እንደሚያጨበጭቡ ይናገራል። ይህ ሰዎችን አይመለከትምና እንለፈው። ምሳሌያዊ አገላለጥ ሆኖ ግን የፍጥረትንና የተፈጥሮን ተገዥነት ያመለክታል። ሌላው በመዝ. 47፥1 ላይ የምናገኘው አሕዛብ ሁሉ አጨብጭበው ለእግዚአብሔር እልል እንዲሉ የተነገረ ቃል ነው። ይህ ጥቅስ ይመስለኛል ዘመነኞች ሰባኪዎች ጉባኤን የሚያስጨበጭቡበት። መዝሙሩን በሙሉው ስናየው ግን እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ የሚለው ስንኝ ያለበት፤ ማስተዋልን የተላበሰ አምልኮን የሚጋብዝ ነው። ባለማስተዋልና ሰባኪዎች ጉባኤው ጭር ያለ ሲመስላቸው አጨብጭቡ የሚሉትን አይመስልም። ሁለተኛው አሳብ ከላይ ለመሪ ወይም ለአድናቆት እንደጠቀስኩት የመሰለ ጭብጨባ በ[1]ነገ. 11፥12 እናገኛለን። ጨቅላው ኢዮአስ በነገሰ ጊዜ በዚያ የነበሩት ሰዎች፥ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ ያጨበጨቡት ጭብጫባ ነው። የደስታ፥ የይታወቅ፥ የይሰማ ጭብጨባ ነው። በቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባቦች ሁሉ ጭብጨባ የተጠቀሰው በአሉታዊ መልኩ ነው። ለምሳሌ፥ በዘኁ. 24፥10 ባላቅ በንዴት አጨበጨበ። በሕዝ. 21፥17 እና 22፥13 የተጠቀሰው ማጨብጨብ እግዚአብሔር ቅጣቱን ሊያሳርፍባቸው እና በቁጣው መነሣቱን ያሳያል። በሌሎችም ስፍራዎችም ቅጣትን፥ ንቀትን፥ በመፍረስ መደነቅን እና የመሰሉትን ያሳያል፤ ኢዮ. 27፥23፤ 34፥37፤ ሰቆ. 2፥15፤ ሕዝ. 6፥21፤ 21፥ 14-17፤ 22፥13፤ 25፥6፤ ናሆ. 3፥19።

    ከዚህ በተለየ መልኩ የሚደረግ ማጨብጨብ ደግሞ አለና ያንን ማየትና ማሳየት እፈልጋለሁና ወደ አጨብጫቢዎችና አጨብጫቢነት ልምጣ። አንድ ነገር ሲደረግ አድራጊዎች አሉ፥ ተደራጊዎች አሉ፥ አስደራጊዎች አሉ፥ አደራራጊዎች አሉ። ይህ የኋለኛው ቃል ይኑር ወይም ልፍጠረው አላውቅም። አደራራጊዎች ያልኩት ሲደረግ አበረታቾችን ነው። አጨብጫቢዎች የምላቸው እነዚህን ነው። ዘፈን በደመቀበት አጨብጫቢ እንዲሉ። የደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት የአጨብጫቢን አንዱን ትርጉም፥ ያጨበጨበ፥ የሚያጨበጭብ ብሎ ሁለተኛውን ደግሞ የነገር ረዳት አዳማቂ ይለዋል።2 ሁለተኛውን ትርጉም ነው የፈለግሁት።

    አንዳንዶች አዳማቂዎች መልካም ያደርጋሉ። ማበረታታት ነው፥ ማስቀጠል፥ ማስጨረስ። ማጨብጨብ፥ “ቀጥል፥ በል፥ ይመርብህ፥ አድርግ፥ በርታ. . .” ማለት ነው። ማድነቅን፥ እንዲጨርስ ማበርታትን፥ ማደፋፈርን ያሳያል። አጨብጫቢ ሲባል ግን ጊዜ ትርጉሙ አሉታዊ ነው፤ አሉታዊው አተረጓጎሙም ትክክለኛ አተረጓጎም ነው። አጨብጫቢነት ትክክል ያልሆነ ነገር ሲደረግ አውቆ ወይም ሳያውቁ ማበረታታትና ማደፋፈርን ያመለክታል።

    ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ አሸን እየፈሉ ለመጡት የስሕተት ልምምዶች ዋናዎቹ ምክንያቶች ስሕተተኞቹና የሚንነዱበት መንፈስ እና/ወይም ግፊት ቢሆኑም በሁለተኛ ደረጃ ተመልካችና አጨብጫቢ አድማጮቻቸውም ናቸው።


    ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ አሸን እየፈሉ ለመጡት የስሕተት ልምምዶች ዋናዎቹ ምክንያቶች ስሕተተኞቹና የሚንነዱበት መንፈስ እና/ወይም ግፊት ቢሆኑም በሁለተኛ ደረጃ ተመልካችና አጨብጫቢ አድማጮቻቸውም ናቸው። የተመልካቾችና አድማጮች ሚና ቀላል አይደለም። አጨብጫቢነት ትልቅ ጉዳት አለበት። እንዲህ ያሉ ነገሮች የሚከሰቱት አእምሮአቸውን ከቃሉ ጋር በማያቀናጁት እና እየሆኑ ያሉትን ነገሮች በማያስተውሉ ከቃሉ ጋር በማያስተያዩ ሰዎች ዘንድ ነው። አእምሮአቸውን የተቀሙ፥ ሁሌ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ የማይደርሱ ሰዎች ያኔ እንደነበሩ ዛሬም አሉ። እነዚህ በቀላሉ አጨብጫቢ የሚሆኑ የአድናቆት ረሃብተኞች ሰለባዎች ናቸው። አጨብጫቢዎች አገልጋዮችን ወደ ጥፋት የሚያነጉዱና አብረዋቸው የሚነጉዱ ናቸው። ዛሬ በአማካይ ቤተ ክርስቲያን አምልኮም እንኳ ጭብጨባ እጅ እጅ እያለ የመጣ፥ ከመስመር የወጣ ነገር እየሆነ ነው።

    ሰንበሌጥ ክርስቲያኖች

    ይህን ስል የጥንት ክርስቲያኖች ሁሉ ድንቅዬዎች የዘንድሮዎቹ ደግሞ ድንክዬዎች ማለቴ አይደለም። ብቻ እስኪገርም ድረስ ሳይበቅሉና ስር ሳይሰድዱ ከአንድ መደብ እየተነቀሉ በሌላ ቦታ እንደሚተከሉ ችግኞች እየተነቀሉ የሚተከሉ፥ አሁንም እየተነቀሉ የሚተከሉ፥ ስር ሳይኖራቸው ወደ ላይ ብቻ የሚያድጉ የጭንጫ ሰንበሌጥ ክርስቲያኖች በገፍ ተወልደውልናል። ብዙዎች የዘንድሮ ክርስቲያኖች ቆም ብለው እንደ ቤርያ ሰዎች፥ “ነገሩ እንዲሁ ይሆንን?” ብሎ በመጠየቅ ፈንታ፤ ቁሙ ሲባሉ መቆም፥ ተቀመጡ ሲባሉ መቀመጥ፥ አጨብጭቡ ማጨብጨብ፤ አሜን በሉ አሜን፤ ጩኹ ማጓራት፤ ሳቁ ሲሏቸው መንከትከትና መገልፈጥ፤ ገና ሳይገፏቸው መገንደስ፤ (ሲገፏቸውማ ከወለሉ በታች መስጠም ይቃጣቸዋል)፤ ዝለሉ ሲሏቸው እንጣጥ፤ የቢልቃጥ ውኃ ግዙ መግዛት፤ የዝተት ጥብቆ ቁራጭ ግዙ፥ መግዛት። “ለምን?” ብሎ መጠየቅ ነውር ይመስላቸዋል። ‘እውነት ይህ የእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ሥራ ነው?’ ብሎ መጠየቅ መንፈስ ቅዱስን መቃወምና እግዚአብሔርን የተገዳደሩ አንገተ ደንዳኖች መሆን ይመስላቸዋል። የሚያሳዝነው አንዳንዶቹ እንደዚያ የተማሩ ናቸው። መናፍስትን ለመለየት መጣር መንፈስ ቅዱስን መናቅ ነው ብለው ያምናሉ። ሰይጣን ወይም ሰይጣናዊ አሠራር የቤተ ክርስቲያንን መድረክ የሚረግጥ አይመስላቸውም። ሌሎች ደግሞ በፍርሃት፥ በይሉኝታና በአቻዎች ጉንተላ ወይም አቻዎችን ለመምሰል በሚደረግ ግፊት (peer pressure) ነው አጨብጫቢ የሚሆኑት። እነዚህ ራሳቸውም በዋል ፈሰስ የሆኑና እንደ ቦይ ውኃ ወደቀደዱላቸው የሚፈስሱ በመልካሙ መሬት ሳይሆን በመንገድ ዳርና በጭንጫ ላይ እንደወደቀው ፍሬ የሆኑ ክርስቲያኖች ናቸው። እነዚህ ናቸው ዘንድሮ በጣም የበዙልን። የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን ይህ ችግር የራሳቸው ችግር ብቻ ሆኖ የሚቆም ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ማወቅ የሚፈልጉና ክርስቶስን ማወቅ የሚፈልጉትን ጠያቂዎችና ፈላጊዎች ከሩቅ እያስቀራቸው መሆኑ ነው። አንዳንዶቹንም የክርስቶስ ተቃራኒ ወደሆነ አቅጣጫ ፊታቸውን እንዲያዞሩ እያደረጋቸው ነው። ይህ ያሳዝናል። እነዚህ ናቸው የሐሰተኛ ነቢያትና ሐዋርያት አሳቢና ቀላቢ፥ መጋቢና አንጋቢ፥ እንዲሁም አጃቢና አጨብጫቢ በመሆን የሚያገለግሉት። የዕድገት ዘመናት እያስቆጠርንም በጥቅሉ ስንታይ ከጭብጨባ ባህል ገና ያልወጣንና ያልጸዳን ዛሬም መፈክራም ትውልድነን።

    ከዩቱብ የተገኘ ምስል ‘ነብይ’ በላይ

    በቅርብ የአንድ ‘ነቢይ’ የዩቲዩብ ቁራጮች ተላኩልኝና አየሁት። [2] ሌሎችም ይህንን የሚመስሉ በዩቲዩብ የተንጠባጠቡ ብዙ ናቸው።         ከተላኩልኝ ሁለቱን ብቻ እንይ። ስፍራዎቹን ከታች ከግርጌ ማስታወሻ ላይ ወስዶ ማየት ይቻላል። ሁለት ሴቶች ወደ ፊት ወጥተው ስለ እነርሱ ‘የተገለጠለትን’ የቤተ ዘመድ ስሞች፥ ስልክ ቁጥሮችና ወዘተ፥ ነው የሚናገረው። አቀራረቡ ፍጹም ተውኔታዊ ነው። ሴቶቹ ወደ ፊት ወጥተው ንግርቱ ይነገርላቸዋል። እነርሱም፥ ‘የእግዚአብሔር ሰው’ እያሉና እየተቅለሰለሱ ትክክልነቱን ያረጋግጣሉ። እየተገረሙ ወይም የተገረሙ እየመሰሉ ያረጋግጣሉ። ሕዝቡም ያወካል፥ ያጨበጭባል፤ ብድግ ቁጭ እያለ ይስቃል። እንደ ጳውሎስ ዘመን ዛሬም ሁልጊዜ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉ ሞኞች ሴቶች እልፍ ናቸውና ይህ ብቻ ሳይሆን ብዙ ‘ነቢያት’ ሴቶች ላይ ነው ትኩረት የሚያደርጉት። እነሆ አንድ ናሙና፤

    ነቢይ በላይ፡-የባለቤትሽን ስም ልንገርሽ?
    ሴቱቱ፡- አዎን የእግዚአብሔር ሰው
    ነቢይ በላይ፡- ገብረጊዮርጊስ
    ሴቱቱ፡- አዎን የእግዚአብሔር ሰው ፍጹም ትክክል ነው
    ነቢይ በላይ፡-የባለቤትሽን ወንድም ስም ልንገርሽ?
    ሴቱቱ፡-አዎን የእግዚአብሔር ሰው ንገረኝ
    ነቢይ በላይ፡-ገብረክርስቶስ
    ሴቲቱ፡ አዎን የእግዚአብሔር ሰው እውነት ነው
    ነቢይ በላይ፡-እሺ አንዲት የምትቀርቢያት ጎረቤት አለቺሽ። ስሟን ልንገርሽ?
    ሴቱቱ፡-አዎን የእግዚአብሔር ሰው ንገረኝ
    ነቢይ በላይ፡-ይህች ጎረቤትሽ መልኳ ቀይ ነው። ስሟ ደግሞ ፀሐይ ይባላል
    ሴቱቱ፡- አዎን የእግዚአብሔር ሰው ፍጹም ትክክል ነው (በመገረምና በመደነቅ ውስጥ ሆና እልልታዋን ታቀልጠዋለች)
    ነቢይ በላይ፡- ሌላም ነገር ልንገርሽ። ባለቤትሽ ሞቷል። ከዚህ በፊት ምግብ ቤት ነበረሽ። አሁን ምግብ ቤቱ በኪሳራ ተመቶ ተዘግቷል። ሦሰት ልጆች አሉሽ፤ አንዷ ድሬዳዋ ነው ያለቺው። አንዷ አዲስ አባ ናት፤ አንዱ ደግሞ እዚሁ ናዝሬት ነው ያለው።
    ነቢይ በላይ፡- የእኔ እናት በውኑ ይሄ የተናገርኩት ሁሉ ትክክል አይደለምን?
    ሴቱቱ፡-የእግዚአብሔር ባሪያ ሆይ ሁሉም ትክክል ነው (ጉባኤውና ሴቲቱ በታላቅ ደስታያጨበጭባሉ፣በመገረም ይስቃሉ፣ ይጮሃሉ…)

    ነቢይ በላይ፡-አንቺ እናት በእርግጥም የእግዚአብሔር ነቢይ እንደሆንኩኝ እንድታውቂ የባለቤትሽን እህት ስም ልንገርሽ?
    ሴቱቱ፡-ንገረኝ የእግዚአብሔር ሰው
    ነቢይ በላይ፡-በውኑ የባለቤትሽ እህት ስም አስቴር አይደለምን?
    ሴቱቱ፡-አዎ የእግዚአብሔር ሰው ትክክል ነው![3]
    በቃለ ምልልሱ ውስጥ ያሰመርኩበትን ክፍል እንደገና እናስተውል። ጭብጨባ፥ መገረም፥ ሳቅ፥ ጩኸት። በጉባኤው ውስጥ የጠረጠረ፥ የጠየቀ፥ የመረመረ፥ ‘ይህ ከየት መጣ?’ ያለ፥ የተቆጣ ይኖር ይሆን? መቼም ያን በሚያህል ጉባኤ ጥቂት አይጠፉም። መገረምና መደነቅ ብቻውን የነቢይ አገልግሎት ምልክት አይደለምም፥ ሆኖም አያውቅም። ነቢያት ነን የሚሉ ሰዎች ነቢይ የሚለውን ቃል ወይም ተጓዳኙን ትንቢት የሚለውን ቃል፥ ወይም ይህን ሰው የሾሙት ሰዎች በሾሙት ወይም በቀቡት ቀን የጠቀሱትን የነቢያት ቢሮ ያሉትን ቢሮ በግልጽ ተርጉመው አስቀምጠውት ከሆነ አላውቅም። የዚህ ‘ነቢይ’ ድረ ገጽ ላይ ትንቢትን ወይም ነቢይን ተርጉሞት ከሆነ ብዬ ብፈትሽ የለም። በድረ ገጹ ከጸጋ ስጦታዎች መካከል ያለው አንድ ስጦታ ብቻ ሆኖ ያም፥ ‘ያለ መድኃኒት የሚደረግ መለኮታዊ ፈውስ’ ተብሎ ተቀምጦአል። ትንቢትን በተመለከተ፥ Prophecy in the Church በሚል ርዕስ ስር የተቀመጠው ሳነብበው ስላለመሳደብ ወይም አለመራገም፥ ዳንስ ቤት እና ዳንኪራ ቤት የመሳሰሉ ቦታዎች ስላለመሄድ የተጻፈ እንጂ ከቶም ከትንቢት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ነው። እንዲህ ያለው የዳንስ ቤትና ዳንኪራ ቤት ነገር በእምነት አቋም ውስጥ መጻፉ ራሱ እያስገረመኝ ነው ያነበብኩት። ከዓመታት በፊት ይህ እንኳን ሊጻፍ ሊታሰብም ስፍራ የሌለው ነገር ነበረ። ሰው እንዲህ ገብስ ከሆነ መጻፉ አስፈላጊ ነው ማለት ነው።  እነዚህ የዘመናችን ነቢያትና የነቢያቱ ሿሚዎችም ለራሳቸውና ለሌላውም ሲሉ ይህን ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ በመነሣት በግልጽና በማያሻማ ትርጉሙ ሊተረጉሙትና ሊመልሱት የተገባ ነው። የተገባበት ዋና ምክንያት ራሳቸው ይህ አገልግሎት ምን መሆኑን እንዲያውቁት ነው። በግልጽ እንደሚታየው ምንነቱን በማያውቁትና ከሌሎች ሰምተው በተለምዶ በቀሰሙት መስክ ነው እየተንደፋደፉ ያሉት። በዚህ ምክንያት ትርጉሙን አውቀው ካላሳወቁ ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ መሆናቸው ይቀጥላል። ዛሬ ለአንዱ ትንቢት ማለት ምስጢር መግለጥ፤ ለሌላው፥ የዛሬ ወር የሚሆነውን መናገር፤ ለሌላው፥ የሰው ዘመዶች ስም መጥራትና ማስጨብጨብ፤ ለሌላው የስልክ ቁጥር ማውጫ ይመስል ቁጥር መንገር፤ ለዚህ ይህ፤ ለዚያ ያ እየሆነ ማንም የፈለገውን እየሆነና እያደረገ፥ እየቀደደና እየደረተ ሊኖር ወለል ያለ በር መበርገድ ነው። የለም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነቢይና ትንቢት እንደደፈረሰ ውኃ ያለ መልክ የለውም። በጣም ግልጽ ነው።  የብሉይ ኪዳንም ሆነ የአዲስ ኪዳን ነቢያትን አገልግሎቶች፥ ተግባሮችና ትምህርቶች፥ በእስራኤልም፥ በቤተ ክርስቲያንም በቅዱሳን ላይ፥ በደነዘዙቱ አማኞች ላይ፥ በእግዚአብሔር ጠላቶችም ላይ የፈጠረው ለውጥ ተጽፎልን በቃሉ ውስጥ አንብበናል። ስለዚህ የነቢያት አገልግሎት መልክ ምን መምሰል እንዳለበት ለዚህ ዘመን ክርስቲያኖች እንግዳና ዱብ ዕዳ መሆን አይችልም። ደግሞም የቀደሙት ነቢያት ቀድመው እንዲሄዱ የተደረጉት የኋለኞቹ አዲሶቹ መንገዷን እንዲያውቋት ጭምር ነው። የእግዚአብሔር ማንነት አልተለወጠም። የሰው ባህርይም አልተለወጠም። ቃሉም አልቀጠነም። የኃጢአት ደመወዝም ኃጢአት ቢበዛም አልተቀነሰም። ኃጢአት ረከሰ፤ ዋጋው ግን አልቀነሰም።

    ነቢያትና ሐዋርያት ለማስገረምና ለማስጨብጨብ አይደለም የተጠሩት። ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱና አሕዛብን አስገርሙ፥ አስደንቁ፥ አስጨብጭቡ አልተባሉም። ማንም የእግዚአብሔር ነቢይ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ሰዎችን ሲያስገርም አናይም። የተላኩት የእግዚአብሔርን እውነት ለማወጅ ነው። ቃሉን ለመግለጥ ነው። ወንጌልን ለመስበክ ነው። ወንጌል ደግሞ የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት ለሰው ልጆች የከፈተው የዕርቅና የይቅርታ መንገድ ነው። መስቀሉ የኃጢአት ስርየት የሆነበት ደሙ የፈሰሰበት የመሥዋዕት ሥራ ነው። ከዘላለም የነበረው ቃል ሥጋ የሆነበት ምክንያትም ይህ ነው። ወንጌል ይህንን የዕርቅ የምሥራች ማወጅ ነው። ወንጌል ወንጀል አይደለም። ክርስቶስ ሥጋ መሆኑን፥ በመስቀል መሞቱን፥ ደሙን ማፍሰሱን የሚያጎላና የሚያውለበልብ ሳይሆን ሰዎችን አደሳስቶና አስቆ፥ አዝናንቶና አስገርሞ ወደ ቤት የሚልክ አገልግሎት ለማገልገል ጌታ ያኔ እነዚያንም አልላካቸውም፤ ዛሬም እነዚህንም እኛንም አልላከንም። እንዲህ የሚያደርጉ የዘመናችን ‘ነቢያት’ ያልዳኑትን ከጥፋት ጎዳና የማይመልሱ ብቻ ሳይሆኑ የዳኑትንም እውነትን የተቀሙ ሆነው እንዲኖሩ የሚያደርጉ ሐሳውያን ናቸው። ከውጭ ሆነው ለሚታዘቡና የክርስትናን ስም ለማጉደፍ ለሚጠባበቁ ደግሞ ቀዳዳ በመፍጠር የስድብ ምክንያት መሆን ነው።

    ይልቅስ ጠንቋዮች ናቸው በማስደነቅና በማስገረም ሰዎችን በመዳፋቸው ውስጥ ማኖር የሚፈልጉ። በሐዋ. 8፥9 ሲሞን የሚሉት አንድ ሰው ግን፥ እኔታላቅ ነኝ ብሎ፥ እየጠነቈለ የሰማርያንም ወገንእያስገረመ ቀድሞ በከተማ ነበረ። ይላል። ሐዋርያት ሰዎችን የማስገረም ስጦታ አልተቀበሉም። ወንጌልን መስበክ አስደናቂ ለውጥ በልብ ውስጥ የሚፈጥር ሥራ ቢሆንም የአስደናቂነት ሙያ ግን አይደለም። በራእ. 13፥3 ምድርም ሁሉ አውሬውንእየተከተለ ተደነቀ ይላል። ማስደነቅ ትኩረትንና አድናቆትን ከአድናቂ ወደ አስደናቂ የሚያቀብል ግርግር ነው። የምናየውንና የምንሰማውን ሁሉ ጉድ እያልን የምንቀበል ከሆነ ጉድ እያልን እስከ ሲዖል ደጅ ልንሄድ እንችላለን። ፍጻሜያችን አያምርም። እንደ ቤርያ ሰዎች መርማሪዎች እንሁን።  ከላይ የተጠቀሰው ‘ነቢይ’ ታሪክ የቀረበበት መጽሔት ዛሬ አገራችን በነቢያት እየተንበሸበሸች መሆኗንና ይህም የመባረኳ ዋና ምልክት እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ፥ ‘ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የነቢያት ድምጽ ታፍኖ ነበር፤ አሁን እግዚአብሔር አምላክ የነቢያትን አገልግሎት ለቤተክርስቲያን በተሃድሶ መንፈስ እየለቀቀ ይገኛል።’ ብሎአል። [4] ጸሐፊው ይህንን አባባል ከሌላ ምንጭ እንደጠቀሰው በቅንፍ  አስቀምጦታል። ግን አፋኙ ማን መሆኑና የታፈኑት ነቢያት እነማን መሆናቸው አልተመላከተም። ይህ ጥቅልል አነጋገር ከተሰጣበት ሜዳ የተወሰደ እንጂ በታሪክ ጥናት ያልተደገፈ እንደሆነ በግልጽ ይታያል። ደግሞም፥ “ቤተክርስቲያን ያለ ወንጌላዊ እድገቷ የተገታ እንደሆነ ሁሉ፥ ያለ ነብይም ኃጢያትን የመቋቋምኃይሏ ደካማ ነው።” ይላል የጽሑፉ አዘጋጅ።

    ይህ ማለት እኮ እነዚህ ነቢያት የተባሉ ሰዎች ክርስቲያኖች ኃጢአትን እንዲቋቋሙ የሚያስችል ውስጣዊና የራሳቸው ኃይል አላቸው ማለት ነው። በኢትዮጵያ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ ከአንድ ምዕት ዓመት ጥቂት የዘለለው ነው። በነዚህ ዓመታት እንደ አሁኖቹ ያሉት ነቢያት አልነበሩምና ቤተ ክርስቲያን ኃጢአትን መቋቋም ሳትችል ኖራለች ነው የሚለን። በአንጻሩ፥ አሁን ደግሞ፥ ነቢያት እንደ እንጉዳይ እየፈሉ፥ አንጓው ተቆርጦ ሲተከል እንደሚበቅል ሸንኮራ በየማሳው እየበቀሉና እየበዙ ስለሆኑ ቤተ ክርስቲያን ኃጢአትን መቋቋም ችላለችና ምንም ኃጢአት አይሰማም፥ አይደመጥም ማለት ነው? እውነቱ ግን ይህ አይደለም። አንዳንዶቹ (ምን አንዳንዶቹ?) ‘ነቢያት’ የሰዎችን መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊና ስሜታዊ ፍላጎት እያዳበሩ መሆናቸውን ከሚናገሯቸው ትንቢቶች ማወቅ ይቻላል። የማይጨበጡ የተነገሩ ‘በረከቶችን’ ለማግኘት ወደ ማጭበርበርና ሥጋዊ ብልሃቶች የገቡና ትንቢቱን በጉልበታቸውና በዘዴያቸው ሊያገኙ በመጣር ይስሐቅን ሳይሆን እስማኤልን እየወለዱ ያሉት ቁጥር ጥቂት አይደለም። የኅሊና መብራታቸውን አጥፍተው አጭበርብረው ያገኙትን ንዋይ እግዚአብሔር እንደባረካቸው እየቆጠሩ ኃጢአትን እየተዳፈሩ ያሉቱ ጥቂት አይደሉም። ማንም ክርስቲያን ከኃጢአት ፈተና እስኪሞት ድረስ የጸዳ አይሆንም። ያለነብይም ኃጢያትን የመቋቋም ኃይሏ ደካማ ነው።” ማለት ግን ሽንገላ ብቻ ሳይሆን አሳች ትምህርትም ነው። ቤተ ክርስቲያን ኃጢአትን የምትጋፈጠውና ፈተናን የምትቋቋመው ደግሞ በዘመነኛ ‘ነቢያት’ ፈንጠዝያ ሳይሆን ክርስቲያኖች ዕለት ዕለት በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ ኑሮ በመኖርና ቃሉን በመመርመር መታዘዝን ሲለማመዱ ነው። ቤተ ክርስቲያን ኃጢአትን የምትቋቋመው በነቢያት ከሆነ ነቢያት መንፈስ ቅዱስ ናቸው ማለት ነው? እንደዚህ ያሉ ባለማስተዋል የሚነገሩ የስንፍና ንግግሮች የዘመናችንን ‘ነቢያት’ ከስፍራ አስፈንጥረው ጣራ የሚያስበረቅሱ የመሆናቸው ጉዳት ቀላል አይምሰለን። ‘ነቢያቱ’ የሚያደርጉትን ካላወቁ የሚጽፉቱ ተጠንቃቂ እንጂ ልቅ መሆን የለባቸውም። ነቢያት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲታዩ ኃጢአትን ሲወቅሱ እንጂ ኃጢአትን የመቋቋሚያ ኃይል ሲሆኑ አይደለም። ነቢይ ነን ከሚሉቱ አንድም የወቀሳና የተግሳጽ ቃል የሌለበት የዚህ ዘመን ትንቢት የሚያሳየን እውነትም ኃጢአት ከቤተ ክርስቲያንና ከየክልሉ ውስጥ ተጠራርጎ የወጣ ያስመስለዋል። ስለ ኃጢአት አለመናገራቸው ግን ኃጢአት የለም ማለት ነው ብለን አንሳት።  ይህንን እውነት ሳናስተውለው የቀረን ካለን እገረማለሁ። በግልም ይሁን በጉባኤ፥ በቴሌቪዥን ይሁን ወይም በስልክ፥ የሚነገረው ‘ትንቢት’ በሙሉ የመሳካት፥ የመሻገር፥ ጠርምሶ የመውጣት፥ የቪዛ፥ የበር መከፈት፥ የተራራ መናድ፥ ልጅ የመውለድ፥ መኪና የመግዛት፥ የሥልጣን ማግኘት፥ የመቀባት፥ የምኑ ቅጡ ነው። ይሄ ሆኗል ወንጌሉ። ይህ ሆነ ቅድስና፥ ይህ ሆነ መስቀሉ። ኃጢአት አይወቀስም። ውስጥ አይፈተሽም፤ የስልክ ቁጥር ይነገራል። የዘመናችን ሰነፍ ነቢያት ‘ጎርፍ አይመጣም፤ አትስጉ’ ብለው ክርስቲያኖች የውሃ ዋና እንዳይማሩና እንዳይለማመዱ የሚያሰንፉ የሰላም ብቻ ሰባኪዎች ናቸው። በሕዝ. 13፥10-15 ሰላም ሳይኖር ሰላም እያሉ ስለሚሰብኩ የተናገረው የነቢዩ ቃል ከዚህ የሚመሳሰል ነው። ሰላም ሳይኖር፥ሰላም እያሉ ሕዝቤን አታልለዋልና፤ አንዱም ሰውቅጥር ሲሠራ፥ እነሆ፥ ገለባ በሌለበት ጭቃይመርጉታልና። ገለባ በሌለበት ጭቃ ለሚመርጉትሰዎች፥ ይወድቃል በላቸው። የሚያሰጥም ዝናብይዘንባል፥ ታላቅም የበረዶ ድንጋይ ይወድቃል፥ዐውሎ ነፋስም ይሰነጣጥቀዋል። እነሆ፥ ግንቡበወደቀ ጊዜ፥ የመረጋችሁት ጭቃ ወዴት አለ?አይሉአችሁምን? ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔርእንዲህ ይላል፦ በመዓቴ በዐውሎ ነፋስእሰነጣጥቀዋለሁ፥ ያጠፋውም ዘንድ በቍጣዬየሚያሰጥም ዝናብ፥ በመዓቴም ታላቅ የበረዶድንጋይ ይወርዳል። ገለባም በሌለበት ጭቃየመረጋችሁትን ቅጥር አፈርሳለሁ ወደ ምድርምእጥለዋለሁ፥ መሠረቱም ይታያል። እርሱም ይናዳልበመካከሉም ትጠፋላችሁ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። መዓቴንም በግንቡ ላይገለባም በሌለበት ጭቃ በመረጉት ላይ እፈጽማለሁእኔም፥ ግንቡና መራጊዎቹ የሉም እላችኋለሁ።ገለባ ወይም ጭድ ሳይኖር በጭቃ መምረግ ይቻላል? (ወይም ገለባና ጭድ እና ጭቃ ለማታውቁ፥) ሲሚንቶ በሌለበት አሸዋ መግረፍ ይቻላል? በትክክል ይቻላል። ግን ያ ምርጊት ጊዜያዊ ብቻ ነው። ታላቅ መነቃቃት በነበረባቸው የብሉይ እና የአዲስ ኪዳን ዘመናትም እንኳ፥ እንዲሁም በታሪክ ውስጥ በታዩ መነቃቃቶች ውስጥ በወንጌልና በቅድስና ተግባር ላይ ያላተኮረ ትምህርት ሲሰጥ አልታየም። በኢዮስያስ ወይም በነህምያ ዘመን ስለነበረው መነቃቃት ብናጤን፥ ወይም መንፈስ ቅዱስ በወረደበት የሐዋርያት ዘመን ስለነበረው ብናይ፥ ወይም በተሃድሶው ዘመን፥ ወይም የታላቁ የመነቃቃት ዘመናት ስለሚባሉት፥ ወይም ስለ አገራችን የመጀመሪያ የወንጌል አዝመራ ዘመናት ብንመረምር አገልጋዮቹ ጭድ በሌለው ጭቃ እንዳልመረጉ ማስተዋል አይሳነንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸው ነቢያትቃሉን ሲገልጡ እንጂ ወደ መድረክ ሰውን ጠርተውያንን ሰው ሲገልጡ፥ ወይም የአባት፥ የአያትና የምንጅላት ስም እየጠሩ ‘የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ልክ ነህ’ ሲባሉ አይደለም። በነገራችን ላይ፥ ይህ፥ ‘የእግዚአብሔር ሰው’ የሚለው አጠራር ቲ. ቢ. ጆሹዋና መሰል የዘመናችን ነቢያት ነን ባዮች እንዲጠሩበት የሚያደፋፍሩት ቃል ነው። ቃሉ በራሱ ምንም ችግር የለበትም፤ በብሉይ ኪዳን ሳሙኤል፥ ኤልያስ እና ኤልሳዕ ተጠርተውበታል። የሶምሶን ወላጆችም መልአኩን እንዲህ ጠርተዋል። ሙሴም ተጠርቷል ግን በእግዚአብሔር ባሪያነት ነው የሚታወቀው፤ በተለይ ከሞተ በኋላ በዘዳግም እና በኢያሱ መጻሕፍት፥ ‘የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ’ ነበር መጠሪያው። ነገር ግን፥ አንድን ሰው እንደ ማዕረግ አድርጎ ‘የእግዚአብሔር ሰው’ ማለት ሌላውን ወይም ራስን ከዚያ ያነሰ ማድረግ መሆኑ አይዘንጋን። እንዲህ ያለው የማበላለጥ ወይም የማወራረድ ተግባር የአዲስ ኪዳን ወይም የክርስቲያኖች ቋንቋ አይደለም። ይህ ሐረግ በአዲስ ኪዳን ሁለቴ የተጠቀሰ ሲሆን (1ጢሞ. 6፥ 11 እና 2ጢሞ. 3፥16-17) በተለይ ሁለተኛው፥የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉየተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞይጠቅማል። ይላል። የእግዚአብሔር ሰው ማለት የክርስቲያን መጠሪያ እንጂ የ’ነቢያት’ ማዕረግ አይደለም። ይህ ከላይ ያነበብነው ዓይነት ለ’ነቢዩ’ የተገለጠለት መረጃ ነገር እውነት ነው ቢባል ምንጩምን ሊሆን ይችላል? በጉባኤው ውስጥ የመደረጉጥቅምስ ምንድር ነው? ሁለቱንም እንይ።

    ይቀጥላል….

     

    [1] ደስታ ተክለ ወልድ፤ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ 598፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፥ 1962 ዓመተምሕረት፥ዐዲስአበባ።

    [2] http://www.youtube.com/watch?v=ll7CbUeyr7o  https://www.youtube.com/watch?v=3KDQqELnFvw

    [3] ዱናሚስ፥ ቁ. 12፤ ሰኔ 2006 ዓ. ም.

    [4] እላይ የተጠቀሰው፤ ገጽ 2።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አጨብጫቢ – ክፍል አንድ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top