• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    ነገረ ድኅነት - (ክፍል 1)

    ከይስሐቅ አበባየሁ

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

    ይህ ጽሑፍ ተከታታይ ኮርስ ሲሆን በሳምንት አንዴ ይለጠፋል፡፡ በተቻለን መጠን አጠርና ቀለል አድርገን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡ እናንተም ሳትሰላቹ እንድትከታተሉን በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችን ነው፡፡

    መግቢያ፡- ‹‹ድህነት›› የሚለው ቃል በሃሌታው ሀ ሲጻፍ ‹‹ማጣትን ችግርን›› የሚያሳይ ሲሆን በብዙኃኑ ኀ ‹‹ድኅነት›› ተብሎ ሲጻፍ ግን መዳንን ያሳያል፡፡ በዚህ ሰዓት ኑፋቄዎች ሁሉ ፊታቸውን ወደ ነገረ ድኅነት አዙረዋል፡፡ ምን ያህል ስር እንደሰደደ የተረዳውት 2007 ክረምት ለአሰላ ጊቢ ጉባኤ ተማሪዎች ‹‹ነገረ ድኅነት›› ኮርስ ለመስጠት መጻሕፍትን በማገላብጥበት ወቅት ነበር፡፡ ባለንበት ሰዓት የድኅነት ትምህርት ላልተረዱት ድህነት እየሆነ መጥቷል፡፡ ታዲያ ለምን በዳረጎት ግንዛቤ አልፈጥርም ብዬ ተነሳሁ፡፡

    እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤ/ክ ይህ ‹‹ትምህርተ ድኅነት›› ‹‹ነገረ ድኅነት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በሌሎች ዘንድ የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፤- ለምሳሌ በካቶሊክ ቤ/ክ “እርቅ”(reconciliation) ወይም “ቤዛ” (redemption) ሲባል  በፕሮቴስታቶች ደግሞ “መቀደስ”(Justification) ተብሎ ይጠራል፡፡ ነገር ግን በቤ/ክ እነዚህ ቃላት በክርስቶስ የተፈጸመልንንየማዳን ሥራ አሟልተው ሊያስረዱን የሚችሉ ቃላት አይደሉም፡፡ እርቅ ስንል በሁለት ጠበኞች መካከል የተደረገን መስማማትንና ወዳጅነትን የሚያስረዳን ቃል ሲሆን ቤዛ ስንል ደግሞ አንድ እስረኛን ወይም ባለእዳን ዋጋ ከፍሎ ማስለቀቅ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቃላት በውጭ ሊፈጸሙ የሚችሉትን ድርጊቶችን ሊያስረዱ የሚችሉ ቃላት እንጂ አንድ አካል ወደ መሆን መምጣትን የሚያስረዱ ሆነው አናገኛቸውም ወይም በድኅነት ሥራ የሁለቱን ወገን ተሳትፎ አሟልተው የሚያስረዱ ቃላት አይደሉም፡፡መቀደስም ቢሆን ኃጢአትን ከመሥራት ተከልክሎ በቅድስና ሕይወት መመላለስን የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ እንደውም እንደ ፕሮቴስታንቱ ዓለም አስተምህሮ አንድ ሰው ሊጸድቅ የሚችለው በእምነት ብቻ ነው ስለሚሉ ክርስቶስን በተግባር ላለመምሰል ፈቃደኞች አለመሆናቸውን እንረዳለን ፡፡

    እኛ ኦርቶዶክሳውያን ግን ሰው ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው ፤ ነገር ግን ጸጋውን ለመቀበል የግድ እምነትን ከምግባር ይዘን ልንገኝ ያስፈልገናልን ብለን እናስተምራለን፡፡ ስለዚህም ቤተክርስቲያችን ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ ጋር ያለንን የእኛን ተሳትፎ እና ከእርሱ ጋር የተፈጸመውን ፍጹም አንድነት ለማስረዳት ስትል ድኅነት(Salvation or Sotoria) የሚለውን ቃል አብዝታ ትጠቀማለች፡፡  

       የመዳን ትምህርት የቤ/ክ ትምህርት ማዕከል ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክረው እግዚአብሔር በኀጢአት የወደቀውን ሰው ከማዳን የበለጠ ዓላማ የለውም፡፡ አንድ ልጁንም አሳልፎ የሰጠበት ከዚህ የበለጠ አላማ ስለ ሌለው ነው፡፡ አበውም ‹‹እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ሰውን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል›› ሲሉ የሰው ድኀነት በእግዚአብሔር ዘንድ ትልቁ ጉዳይ መሆኑን መግለጣቸው እንደ ሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሁሉም ዘንድ ‹‹እንዴት ነው የምድነው? ›› ከሚለው ጥያቄ የበለጠ ጥያቄ አለ ማለት ያስቸግራል፡፡ ሰዎችም የተለያዩ ሃይማኖት ተከታይ የሚሆኑት ይህን ዋና ጥያቄ ለመመለስ ነው፡፡

    ማብራሪያ፡- ‹‹ነገረ›› የሚለው ቃል በቤ/ክ ትምህርት የአንድ ትምህርት መስክ መግለጫ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በዚህ ይዘቱ/LOGY/2የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ይተካል፡፡ ‹‹ድኀነት›› ስንል በኃጢያት ምክኒያት የወደቀውና የጎሰቆለው የሰው ልጅ ከደረሰበት ውድቀትና ሞት ሙሉ በሙሉ ነፃ መውጣትና በሞት ምክኒያት አጥቶት የነበረውን ጸጋ ማግኘቱን መጀመሪያ ከመበደሉ በፊት ወደ ነበረበት ጸጋው(ማንነቱ) መመለሱን ማለታችን ነው፡፡ የድኀነት ትምህርት ባንድ ወገን አባታችን አዳም ከወደቀበት የኀጢአት ማጥ ወጥቶ እንዴት ዳነ? እኛስ ልጆቹ እንዴት እንድናለን? የሚለውን ነጥቦች የምናይበት ትምህርት ነው፡፡ የነገረ ድኀነት መነሻው የአዳም ውድቀት ጉዳይ ነው፡፡ ምክኒያቱም ኀጢአትን የሠራ፣ ይድን ዘንድ ቃል ኪዳን የተገባለት እርሱ ነውና፡፡ በመሆኑም ጽሑፋዊ ኮርሳችንን የምንጀምረው በዚሁ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ስለ አዳም ውድቀት ከመነጋገራችን በፊት ስለ አፈጣጠሩ ማጥናቱ ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ 

    እንግዲህ በሚቀጥለው ክፍል  የአዳም አፈጣጠር፣ የአዳም አወዳደቅ፣ ለአዳም መሳሳት ተጠያቂው ማነው? የሚለውን ይሆናል!

    ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    2 comments:

    1. ቃለ ህይወት ያሰማልን ሌሎች ክፍሎች የሉም ወይ

      ReplyDelete
    2. ንዑ ኃቤየ ይበለን

      ReplyDelete

    Item Reviewed: ነገረ ድኅነት - (ክፍል 1) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top