• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    ‹‹የሚጠፋውን አሮጌ ሰው አስወግዱ ›› ኤፌ 4 ፥23


                    ከመ/ር ዳንኤል ተካ

    ሁሌም የጳጉሜ ወር ሲመጣ ሰው ሁሉ ያለፉትን ወራት በህሊና ሚዛንነት መዝኖ የትላንቱን ጠንካራ ጎን ለማስቀጠል፤ ደካማውን ለማረም ጊዜ ሰጥቶ፤ ሰዓት ሰፍሮ የሚመረምርበት ወቅት ነው፡፡ አስገራሚው ነገር ሁሌም ለቀጣይ ዓመት እንዲህ እሰራለሁ፣ ይህን አደርጋለሁ ማለት የየዓመት ተግባራችን ሆኗል፡፡ እኔም እንዲህ ከሚያደርጉት ሰዎች መካከል አንዱ ነኝና በጳጉሜ ወር ላይ ሆኜ ያሳለፍኳቸውን ወራቶች በቃለ እግዚአብሔር መስታወትነት ለመመልከት መጽሐፍ ቅዱሴን ስገልጥ ሐዋርያው ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን መልዕክት ተመለከትኩ ‹‹የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ››፤ ዓይኔ ከዚህ ኃይለ ቃል ጋር ተሰክቶ ያሳለፍኳቸውን የ2007 ዓ.ም ወራቶች ማሰላሰል ያዝኩ፤ ከመስከረም እስካለሁበት ጳጉሜ ወር ድረስ ደስ የሚያሰኙ ግን የመከኑ ዕቅዶች የበዙበት፤ የተበላሹ የሕይወት ውጣ ውረዶች የተሞሉበት፤ ሃሳቦች ግባቸዉን ሳይመቱ የሚሻገሩ ብሎም የሚዘነጉበት፤ ዕቅዶች በዝተው በሕይወቴ ውስጥ የተዝረከረኩበት፤ የነበሩት የተበላሹ ማንነቴ ወይ ባሉበት አልያም ብሰው ተመለከትኩ፡፡ ዕቅዶቼን ፈተሸኳቸው .. ችግር የለባቸውም፤ እንዲያውም ለሌሎች አካፍያቸው ተጠቅመውበት ከኔ በተሻለ ማንነት ላይ ሲሆኑ፤ እኔ ግን ነገ እንዲህ አደርጋለሁ፣ ከዚያም ይኽን እሰራለሁ እያልኩ ዛሬን ማቀጃ ብቻ እንጂ መሥሪያ ሳላደርገው 365ቱን ቀን አባክኜ ዛሬ ላይ ደረስኩ፡፡ ውጤቱ ሰውነቴ ደክሞ፣ መንፈሳዊነቴ ዝሎ፣ መንፈሳዊ ቃል እንጂ መንፈሳዊ ሕይወትን ሳልኖር ይኽው ሌላ አዲስ ዓመት መጣ፡፡ 

     

    ያልተስተካከለ ሕሊና፤ ያልነጻ ልቦና፤ ያልተስተካከለ ሕይወት፤ ያልተቀናጀ ወዳጅነት፤ የነበሩኝን ነገሮች አሰብኳቸው፡፡ ያለሁት ቤተክርስቲያን ግን ቤተክርስያንን የምተች፤ ጉድለቷን መሙላት ሲገባኝ እኔ ራሴ የማደክማት ፤ መድረኳን ለፖለቲካ ፍጆታ ካልሆነ በቀር ባድራሻዬ የማልገኝ፤ ሁልጊዜ ችግሬን እንጂ  ችግሯን እንዳልተረዳው ተሰማኝ፡፡ ቤተክርስቲያን የኔ ናት? ታዲያ እኔ የማን ነኝ? ከወዳጆቼ ጋር ያደረኳቸውን ውይይቶች፣ የዋልኳቸውን ውሎዎች ፈተሸኳቸው፡፡ ያኔ ለአገልግሎት ስንጣደፍ ከቃለ እግዚአብሔር በቀር የማያውቁ አንደበቶቻችን ዛሬ ላይ ለዛቸው ጠፍቶ፤ ወሬና ጨዋታችን ሁሉ የተገላቢጦሽ ሆኖ በዓለሙ እንኳ የማይደፈሩ ቃላቶች መገኛ ምንጫቸው የኛ አንደበት ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ከቤተሰቤ ጋር የነበረኝ የጠነከረ ግኑኝነት በአዳዲስ ወዳጆች ተተክቶ፤ ቤተሰቤ ስለ እኔ ምን አገባው በሚል ፈሊጥ ጊዜ ሳልሰጣቸው ሀሳቤን ተናግሬ ሃሳባቸውን ሳላዳምጣቸው ይኸው ድፍን አንድ ዓመት ሞላኝ፡፡ አምና ያቀድኳቸው ሁሉ ሳይፈጸሙ ተደመሩና መንፈሳዊ ሕይወቴን አዝለው ከቤተክርስቲያን አገልግሎት ነጠሉኝ፡፡ በቤቱ ሆኜ የቤቱን ምግብ (ሥጋ ወደሙን) ሳልበላ፤ በቤቱ ሆኜ የቤቱን ዜማ (ቅዳሴ) ሳልሰማ፤ በቤቴ ሆኜ ቤቴን ሳላስከብር ጊዜው ነጉዶ ሰውነቴ ገርጥቶ አሮጌ ሰው ሆኜ አገኘሁት፡፡ 

    ሁል ጊዜም ጠባዬ ይገርመኛል፤ ምን ነካኝ? የምለው በዓመቱ መጨረሻ ነው፡፡ ይኽን ባላደርግስ? እዲህ ነበር መሆን የነበረበት? የዓመቱ የጸጸት መዝጊያዎቼ ሆኑ፤ ለዚያ ነው ‹‹የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ›› ከሚለው ቃል ላይ ዓይኔ ተሰክቶ የቀረው፡፡ ዕውነት የምን አዚም ተጫነን? ያሰብነውን እንዳንፈጽም አቅም ያሳጣን ምንድነው? በምትለውጥ ቤት ተቀምጠን ለመለወጥ ያልፈቀድነው ምክንያቱ ምንድነው? ሁሌ አቃጆች ግን የማንፈጽም ደካሞች የሆነው ለምንድነው? መረመርኩት፤ ብዙ አወጣሁ አወረድኩ፤ ችግሩ ዕቅዱ ላይ ሳይሆን አተገባበሩ ላይ ነው፡፡ ያውም ነገ የምትለው ቃል ሳላስበው ዛሬን እንዳሳጣችኝ ተገነዘብኩ፡፡ ነገ ተስፋ፤ ዛሬ ደግሞ በእጃችን ያለች ናት፡፡ በእጃችን ባለችው በዛሬ ካልሰራን ተስፋ በሆነችውና ባልጨበጥናት ነገ እንደምንሠራ በምን እርግጠኞች ሆንን? ነገ ስትመጣ ዛሬ ሆኗ ነው፡፡ ዛሬ ከሆነች ደግሞ እኔ ዛሬን ለማቀጃ ብቻ ሳይሆን ለመተግበሪያ ስላላዋልኳት፤ ዓመቱን ሁሉ አቃጅ ሆኜ በድክመት ፈጸምኩት፡፡ የሚራራው መላኣክ ግን ‹‹በዚህች ዓመት ተዋት›› በሚለው የምልጃ ቃል ዓመቱን ያለፍሬ ብፈጽምም፤ ለከርሞ አማልዶኝ፤ የከርሞን ዕቅድ ለማቀድ ከዘንድሮ ጫፍ ላይ ሆኜ ራሴን እየመዘንኩኝ ነው፡፡ የአገልግሎት አጋሬ የሆንከው አንተም በዚህ ሚዛን ላይ ከሆንክ፤  ራስህን መዝነህ የደረስክበት ካለ በዚሁ ገጽ ላይ ጠቁመኝ፤ ያንተን ተቀብዬ የኔንም ጨምሬ በአዲሱ ዓመት ‹‹አዲስ››ለመሆን እተጋለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በቸርነቱ ይርዳን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ‹‹የሚጠፋውን አሮጌ ሰው አስወግዱ ›› ኤፌ 4 ፥23 Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top