ባሕታዊ ዘበህድአት! ገዳማዊ ሕይወት በመነኰሳት
አንድ ሰው ኅሊናውን ለምናኔ አነሣሥቶ ወደ ገዳም በሚገባበት ወቅት የሚያጋጥሙት ፈተናወች እጅግ በጣም ብዙዎች ናቸው፡፡ በዓለማችን እንደ ገዳም ያለ ፈተና የሚበዛባት ቦታ የትም የለም፡፡ ሰብአዊ ፈተናዎች በሙሉ ተሰባስበው የሚገኙት በገዳም ነው። ምክንያቱም ብዙኅ ሕማሞሙ ለጻድቃን ማለት የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው በተባለው መሠረት፣ በዚህ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ይልቅ በምናኔ ወደ ገዳም በገቡ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ፈተና የበለጠ ክብደት አለውና።
ገዳማውያን አበው መነኰሳትና እማት መነኰሳይያት በገዳማዊ ሕይወታቸው የሚዋጉት ከዚህ ዓለም ካለው ከሚታየው፤ ከሚጨበጠው፤ ከሚዳሰሰውና ከሚሰማው ፈተና ብቻ ሳይሆን ከማይታዩ፤ ከማይዳሰሱ፤ ከማይጨበጡ ረቂቃን አጋንንት ጋርም ከመዋጋት አቋርጠው አያውቁም። ውጊያውም እስከ ዕለተ እረፍተ ሥጋ ድረስ የሚያቆም ውጊያ አይደለም፡፡ ስለዚህ በገዳም በመናንያንና በመናንያት ላይ የሚደርሰው ፈተና ስፍር ቁጥር የለውም።
በመጀመሪያ ደረጃ በገዳማዊ ሕይወት የሥራን ክቡርነት መረዳት፤ የተለያዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙ መታገስን፣ ሲታዘዙ ያለማጕረምረምና ያለመታከት የታዘዙትን መፈጸም፣ ጾምን፣ ጸሎትን፤ ስግደትን፤ ሕርመትን መለማመድና ገንዘብ ማድረግ የግድ ነው። ምክንያቱም ገዳም የትጉሃን መናኸሪያ እንጂ የሰነፎች መኖሪያ፤ መጦሪያ ወይም መደበቂያ አይደለምና፡፡
ገዳማዊ መነኩሴ ወይም ገዳማዊት መነኩሲት በገዳማቸው ውስጥ በተለያዩ የሥራ ክፍሎች ሲመደቡ ማለትም አትክልትን መትከል፣ መኮትኮትና ውኃ ማጠጣትን፤ እርሻ ማረስን ሌሎችንም አስፈላጊና ተገቢ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን፤ በገዳሙ ውስጥ ከሚኖሩ መሰሎቻቸው ጋር በመስማማትና ማንኛውንም ዓለማዊና ሥጋዊ ፈቃድን በማስወገድ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ጸንቶ ማገልገል መንፈሳዊ ግዴታቸው ነው። ይህም ተግባርና አገልግሎት ደግሞ የአንድ ገዳማዊ ወይም ገዳማዊት ጠባይ፤ ችሎታ፤ ፍቅረ ቢጽነት የሚመዘንበት የምናኔ መስፈርት ነው። ልክ እንደ አባ ዮሐንስ ሐፂር ትዕግስትን መላበስ ይጠበቅባቸዋል።
አባ አሞይ የደረቀ እንጨት ተክሎ ለምልማእስክታፈራ ድረስ ውኃ እንዲያጠጣት ለአባዮሐንስ አዘዘው አባ ዮሐንስም ያለማጕረምረምበትሕትና በመቲረ ፈቃድ ዐሥራ ሁለት ምዕራፍያህል ከሚርቅ ቦታ በቀን ሁለት ጊዜ ውኃእያመላለሰ ያጠጣ ጀመር፡፡ በሦስተኛው ዓመትያች እንጨት ለምልማ አብባ ያማረ ፍሬአፈራች።
አባ አሞይ በዮሐንስ ታዛዥነት እጅግ ተደሰተ። ፍሬውን ለቅሞ ለገዳሙ ማኅበር እንካችሁ ይህ የታዛዥነት ፍሬ ነው እያለ ሰጣቸው። ዮሐንስም በልቡናው ዘወትር እግዚአብሔርን ያስብ ነበር። ለአንድ ደቂቃ እንኳ ፈጣሪውን ከማሰብ አቋርጦ አያውቅም
የመነኰሳት ምግብ አትክልት፤ቅጠላ ቅጠል እንዲሁም እንደ ገዳሙ ሥርዓትና ሕግ እህልም ይመገባሉ፡፡
እንደየ ገዳማቱ ሥርዓትና ሕግ መሠረት የአኗኗርና የአመጋገብ ልዩነት አለ፡፡ ለምሳሌ አትክልት የሚመገቡ መነኰሳትና መነኰሳይያት እንደየ ችሎታቸው እየተመደቡ አትክልቱን በፈረቃ ሌሊትና ቀን ውኃ ያጠጣሉ። እንደ ዋልድባ ገዳም አጠራር አትክልተኛው /ወንዘኛ/ ተብሎ ይጠራል፡፡ ታዲያ በዚህ ድምጸ አራዊት ጸብአ አጋንንት በበዛበት ገዳም ያውም በሌሊት ውኃ ሲያጠጡ ማደር በጣም ከባድ ነው፡፡ በሌሊት ተነሥቶ ባትሪን በመጠቀም ሙሉውን ሌሊት አትክልት ውኃ ሲያጠጡ ማደር አንዱ የገዳማዊ ሕይወት ቁልፍ ተግባር ነው። አንዳንድ ጊዜም ባትሪ በሚያልቀበት፤ጨረቃም በሌለችበት ወቅት በጨለማው እየዳበሱ፤በዳሰሳ ሥራ ሢሠራ ከተለያዩ የምድር አራዊት ማለትም ከእባቡ፤ ከዘንዶው፤ ከነብሩ፤ ከአንበሳው፤ ከአሳማው፤ ከጅቡ ወዘተ ጋር በመታገል የሕይወት መሥዋዕትነትን በመክፈል የሚኖርበትና የሚሠራበት ቦታ ገዳም ነው። ታዲያ አንዳንድ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በዓለማዊ ኑሯቸው ዕለታዊ ችግር ሲያጋጥማቸው ገዳሜን ነው ሂጀ የምገባ ብለው ሲዝቱ ይሰማሉ፡፡ ምንአልባት ገዳም የጠንካራ ሰዎች መኖሪያ፤ የትጉሃን መናኸሪያ፤ በትግዕስት ፈተና እግዚአብሔር ፈጣሪ የሚገኝበት ቦታ መሆኑን አልተረዱት ይሆን
ማንኛውንም ገዳማዊ መነኩሴ ወይም ገዳማዊት መነኩሲት ሥራ በሚሠሩበት ጊዜ አፉቸው/አንደበታቸው ቃለ እግዚአብሔርን ከመናገር አያቋርጥም፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ በጋራ ሥራ በሚሠሩበት ውኃ በሚያጠጡበት ጊዜ ድምጻቸውም አይሰማም። በነገራችን ላይ አብዛኛን ጊዜ አትክልቱን ውኃ የሚያጠጡት በመሸከም ሳይሆን በመስኖ ነው።
መናንያንና መናንያት በወጣኒነት ጊዜያቸው ፆር ሳይጠፋላቸው ሰይጣን ዲያብሎስ በልዩ ልዩ ዓይነት ፆር እንዳይዋጋቸው ማለትም በትዕቢት ፆር ይህንን ሠርተናልና አክብሩን አመስግኑን ሳይሉ በጥብአት ሰይጣን ዲያብሎስን ድል በማድረግ የምንኩስናን ሥርዓትና ጠባይ ሀ ብለው ይማሩታል። ራስን የመግዛት ጠባይ መላ ሕዋሳትን ጠብቆ በልቡና ተዘክሮተ እግዚአብሔርን ሲያዝ ነው። በተለይ ለወጣኒ አፍአዊና ውስጣዊ ሕዋሳትን መሰብሰብ የሚገባ መሆኑን አበው መነኰሳትና እማት መነኰሳይያት በደንብ ይመክራሉ፤ ያስተምራሉ።
ሰው አብዝቶ ሕዋሳቱን በገዛ ቁጥር በልቡናው የሚመላለሱ እኩያን ምክንያቶች ሁሉ ከውስጡ እየጠፋ ይሄዳሉ። በአንድነት ገዳማት ከዕለት ምግብ ጀምሮ ምንም ዓይነት የግል ንብረት አይፈቀድም። ልብስም እንኳ ለአንድ መናኝ መነኩሴ ወይም መነኩሲት በየስድስት ወሩ ግማሽ ጣቃ አቡጀዴ ይሰጣል እንጂ ሌላ ትርፍ የሚያገኘው/የምታገኘው የለውም/የላትም።
ከላይ እንደተገለጸው ሥራ ፈት ሆኖ መቀመጥ በገዳም በጥብቅ የተከለከለው ነው። ያለበቂ ምክንያትና ያለመጋቢው ፍቃድ ከገዳሙ ወጥቶ ከቦታ ቦታ መዘዋወርም አይፈቀድም። አመጋገብንም በተመለከተ የገዳሙ ቀኖና የሚፈቅደውን የምግብ ዓይነት መጠን ተላልፎ መመገብ ክልክል ነው፡፡ በተለይ በሥራ መለገም፣ ስሕተትን መደበቅ፣ በጠቅላላ ለዓለማዊና ሥጋዊ ፍላጐት ተገዥ መሆን የገዳማዊ ሕይወት ገጸ ባሕርይ አይደለም። ከመገልገል ይልቅ ለማገልግል ፈጣን መሆን የገዳሙ ኑሮ ሌላው ግዴታ ነው። በመሆኑም ገዳማቱ የትጉህ መነኩሴ ወይም የትህግት መነኩሲት መኖሪያ እንጂ የማይሰራ የሰነፍ ሰው መጦሪያ ቦታ ያለመሆናቸው ግልጽ ነው።
ሀ. የምንኲስና ሥርዐት
ወጣኒ መናኝ ምንኩስናን ለመቀበል በገዳማት ትምህርት ቤት የኖረ ድንግል ከሆነ ሦስት ዓመት በረድእነት ማገልግል አለበት። ይኸውም ጠባዩና ችሎታው የሚመዘንብት አነጋገሩ፣ አለባበሱ፣አረማመዱ፣ ትሕትናን፣ ፍቅረ፣ ቢጽን፣ ሕዋሳትን መግዛት፣ በፈተና መታገስ ያለማጐረምረም ያለመታከት መታዘዝን እነዚህን ሁሉ መለማመድ አለበት። በዓለም ከሚኖሩ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ወደ ገዳሙ ለምናኔ ሲመጡ ደግሞ አንድ ሰው ከምንኩስና በፊት ሰባት ዓመት ሳይመነኩስ በረድእነት ማገልግል አለበት። ምክንያቱም ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋልና ነው።
ከገዳም ውጭ ባሉ አድባራት በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት የኖረ ሰው በቀጥታ ወደ ገዳም ቢገባ በረድእነት ከምንኩስና በፊት ከሦስት ዓመታት በላይ ማገልግል አለበት። ምክንያቱም ይህም ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋልና ነው፣
ምንኩስናን ለመቀበል የሚያስብ ሰው አሰቀድሞ ስለምንኩስና ሕይወት እንዴት ሊያስብ እንደቻለ ራሱን መጠየቅ አለበት፡፡ ከባለቤቱ ጋር ተጣልቶ ወይም ከባለቤቷ ጋር ተጣልታ ሊሆን ይችላል ወይም ከልጆቹ/ቿ ጋር ተቀያይሞ/ማ እንደሆነ/ች አይታወቅምና አመጣጡን በጥንቃቄ ማጥናት ይገባል። ምንአልባት እየቆየ በሄደ ጊዜ ልጆቼ ታዩኝ/ናፈቁኝ ባለቤቴ ናፈቀችኝ/ናፈቀኝ ብሎ/ላ ወደዓለም ቢመለስ/ብትመለስ ሊከሰቱ የሚችሉ ፈተናዎችን ለመቋቋም የምንኩስናን ምንነትና ዓላማ በሚገባ፤ በስፋት፤ ማስረዳት፤ ግዴታ መሆኑን የምንኩስና መርሆች አጥብቀው ያስረዳሉ።
ገዳም የጥበብ፣ የዕውቀትና የፍልስፍና ምንጭ ነው። ቀዳሚሃ ለጥበብ ፈሪሃ እግዚአበሔር›› በተባለው መሠረት በገዳም መጀመሪያ የሚያጠኑት የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት፣ መጋቢነት፤ አዳኝነት፤ አዛኝነትና ርኀራኄ ነው። በዚህ የተመሠረተ ምናኔ ለሁሉም ነገር አይጎመጅም። ራስ ወዳድነትም አያጠቃውም።
ዛሬ በገዳማት የሚገኙት ብርቅና ድንቅ የሆኑ መጻሕፍት፣ ሥዕላት፣ ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅዱሳትና ቅርሶቻችን በሙሉ በጥንት ጊዜ የነበሩ አበው መነኰሳት የጿፏቸውና የቀረጹዋቸው ናቸው። የዛሬ ዘመን ትውልድ አንጀተ ባዶ ሆኖ እየሸጠ የሚበላቸው ስለሆነ ማመላከት ይሆንብኛል እንጅ ያሉበትን ቦታ እናገር ነበር። የብዕራቸው አጣጣል፣ የብራና ጽሕፈቱ፣ የሥዕላቱ ውበት ልዩ ነው። ዛሬ ኦርቶዶክሳዊ ሥዕልና አሣሣል የለም፣ የጥንቱ አሣሣል ጠፍቶአል፤ ዝብርቅርቁ ወጥቷል ማለት ይቻላል። ይህም የሆነበት ምክንያት ጸሐፊና ሠዓሊ መነኰሳት ስለጠፋና ሥራውም ለትሩፋትና ለተአዛዚነት ሳይሆን ለገንዘብ ብቻ የሚሠራ በመሆኑ ነው። ቀድሞ ግን ሥራውን እንዲሠሩ ሲታዘዙ በሱባዔ፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር፤ በጸሎት ስለሆነ ሥራቸው እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ዕፁብ ድንቅ ሁኖ ይገኛል።
እንግዲህ የገዳም መሠረቱ፣ የኑሮ ሕይወቱ ከላይ እንደተገለጠው የምርምርና የፍልስፍና፤ የትምህርትና የተአምራት፣ የፈውስና የበረከት፣ የሰላምና የአንድነት፣ የፍቅር ቦታ መሆኑ ነው።
ለ የምንኲስና መዐርግ መቀበል
ይህ ክፍል በአርእስቱ እንደተገለጸው በምንኲስና ገዳማዊ ሕይወትን መቀበል ነው። ይህም የገዳማዊ ሕይወት ምንኲስና በምናኔ ከዓለማዊ ግብር ተለይቶ እግዚአብሔርን ለማገልገል የሚያደርጉት ታላቅና ጽኑዕ መንፈሳዊ ጉዞ ነው። ምንኲስናም ማለት በንጽሕናና በድንግልና በቅድስና በገዳም ውስጥ ሆኖ በጾም፤ በጸሎት፤ በስግደት፤ በአጽንዖ በዓት፤ በትህርምትና በማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ተወስኖ በመኖር ፈጣሪ እግዚአብሔር ዓለሙን በሙሉ እንዲራራለት ማማለድ ነው።
ከእነዚህ ገዳማውያን አበው መነኰሳትና እማት መነኰሳይያት በምንኩስና ሥርዓትና ቀኖና መሠረት በእንጦርስ ወመቃርስ አስኬማ የተወለዱ አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ቅዱሳት አንስት መነኰሳይያት ዋነኛዎቹ ናቸው። ከራሳቸው ላይ የሚደፉት አስኬማም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ በቀራንዮ አደባባይ ለሰው ልጅ ነፃነት ሲል የተቀዳጀውን አክሊለሦክ በማሰብ ነው። ገዳማውያን ለሰው ልጆች በሙሉ አጥፊ የሆነውን ነገር የማይሠሩና ለእንስሳት እንኳ ሳይቀር የሚራሩና የሚያዝኑ ናቸው። ጸሐፍት ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን የተባሉ ሁሉ ከነቢያትም ወገን እነ ኤልያስና እና ዮሐንስ መጥምቅ የእነርሱ የመናንያን ወገን ናቸው። ዮሐንስ መጥምቅም ይከታተል የነበረው የመናንያን ሕግና ሥርዐት ነበር።
1ኛ. ራሳቸውን የማይላጩ፣ የሚያሰክር መጠጥ የማይጠጡ፣ ከሁሉም የማይገባ መጥፎ ነገር የተከለከሉ፣ ናዝራውያን ነበሩ። ናዝራዊ ማለት ከክፉ ነገር ሁሉ የተከለከለ ማለት ነው። ቋንቋው የዕብራይስጥ ነው፣ ናዚር ወይም ናዛር ማለት ከክፉ ነገር ሁሉ የተከለከለ፣ ስእለት ወይም ብፅዓት ያደረገ፣ ሕይወቱን በሙሉ ለእግዚአብሔር የሰጠ፣ በሰውነቱም የተቀደሰና የተለየ ሰው ማለት ነው።
እንደነ ሶምሶን፤ እንደነ ሳሙኤል እንደነ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ናዝራውያን ተብለው ይጠሩ ነበር። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱሰ ክርስቶስ ግን በተወለደበትና ባደገበት ናዝሬት ኢየሱስ ናዝራዊ ተብሏል ወይም ተብሎ ይጠራል፡፡ ናዝራዊ መባሉ ናዝሬት በመኖሩ ነው።
2ኛ. አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ከኲነኔና ከዘለዓለማዊ ሞት እንዲያድነው ጽኑ ተስፋና ብፅዐት ሰጥቶ የነበረ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ናዝራዊ ተባለ፡፡ ወቦአ ናዝሬተ ኀበ ተሐፅነ ከመ ይሰመይ ናዝራዊ። ናዝራዊ ይባል ዘንድ ናዝሬት ገብቶ አደረ፡፡ ማቴ. 2፥23 ለእኛም ተባሕትዎውንም ሆነ በገዳም መወሰንን፣ መጾም መጸለይን፤ መስገድን፣ በገዳም መኖርን የአስተማረን እርሱ ራሱ ሊቀ ካህናት መድኀነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ክርስትናንም የመሠረተ እርሱ ነውና ወእምዝ ወሰዶ መንፈስ ቅዱስ ለእግዚእ ኢያሱስ ገዳመ ከመ ይትመከር እምኀበ ዲያቢሎስ›› ማቴ 4፥1
‹‹ ወጾመ አርብዐ መዓልተ ወአርብዐ ሌሊተ ዐርባመዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾመ።›› ሠራዔ ሕግ ነውናሥራውን በገዳም መሠረተ። በገዳም ምን መደረግእንዳለበት አስተምሮና ሠርቶ ካሰየ በኋላ ዓለሙንለማስተማር ‹‹በዓለም በሚገኙት ሁሉ አስተማሪእንዲሆኑ ሐዋርያትን መረጠ። መጀመሪያ ቅዱስጴጥሮስንና ቅዱስ እንድርያስን ቀጥሎም ቅዱስያዕቆብንና ቅዱስ ዮሐንስን ጠራቸው። ‹‹ዓለሙንተውት እኔን ተከተሎኝ›› ማቴ.4$1-2 ማቴ.4፥18-22።
አባቱንና እናቱን፤ እኅትና ወንድሙን፤ ዘመድ አዝማዱን ትቶ ያልተከተለኝ የእኔ ደቀ መዝሙር ሊሆን አይችልም አላቸው። እነሱም ሁሉንም ትተው ተከተሉት፡፡ ማቴ.4፥22 ማቴ.19$27፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም የጠየቀው ስለዚህ ነበር፤ እንዲህ ሲል እኛ ሁሉን ትተን ተከተልንህ። ‹‹ናሁኬ ኀደግነ ኲሎ ወተሎናከ ምንተ እንከ ንረክብ› ሁሉን ትተን ተከተልንህ የምናገኘው ጥቅም ምንድን ነው? አለው ጌታም እንዲህ ሲል መለሰለት‹‹ አማን እብለክሙ አንትሙ ተለውክሙኒ አመ ዳግም ልደት አመ ይነብር ወልደ እጓለ እመሕያው ዲበ መንብረ ስብሐቲሁ አንትሙኒ ትነብሩ ዲበ ዐሠርቱ ወክልኤቱ መናብርት ወትኴንኑ ዐሠርተ ወክልኤተ ሕዝበ እስራኤል። ማቴ 19፥28›› እውነት እላችኃላሁ እናንተስ የተከተላችህኝ በዳግመኛ ልደት የሰው ልጅ በክብሩ ዙፋን በሚቀመጥበት ጌዜ እናንተ ስትፈርዱ በዐሥራ ሁለቱ ዙፋን ትቀመጣላችሁ።
ይህም ማለት በዳግም ምጽአት ፍርድ ሲሰጥ በክብር ሁናችሁ ትፈርዳላችሁ አላቸው። ደስታችሁና ዋጋችሁ የምናኔያችሁና ያስተማራችሁት የትምህርት ፍሬ በዚያን ጊዜ ይገለጣል አላቸው። የሐዋርያት ጥሪና ምርጫ ወይም ተልእኮ ገዳም ገብቶ፣ በዓት አጽንቶ፣ መንኖ፣ ከዓለም ርቆ መኖር አልነበረም። ዓለሙ አስተማሪ መካሪ የሚፈልግበት ሰውንም ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፣ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ የሚመልሱበት ጊዜና ዘመን ስለነበር ከዓለሙ ተለይተው በዓለሙ ውስጥ እንዲኖሩ ወንጌልን አንግበው እንዲጓዙ አደረጋቸው። ትእዛዙም በጣም ከባድ ነበር፣‹‹ኢትንሥኡ በትረ ወኢአሣዕነ፣ ወኢቁናማተ፣ በትርም አትያዙ፣ጫማም አታድርጉ፣የሥንቅ አቅማዳም አትያዙ፣ በእግዚአብሔር እመኑ፣ ሁሉም እንደ እናት እንደ አባት እየሆኑ ይቀበሏችኋል፣ በሄዳችሁበትም ቦታ ሰላም የሚገባው በዚሀ አካባቢ ማን ነው ብላችሁ ጠይቁ እንጂ ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት አትዘዋወሩ።›› ይደልዎ ዐስቡ ለዘይትቀነይ እንዳለ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ላገለገለ የዕለት ምግቡ ይገባዋልና ሲል 12 ሐዋርያትን መርጦ ላካቸው።››
የሐዋርያት ምናኔ ወንጌልን በዓለሙ ሁሉለማዳረስ፣ በትምህርት በተአምራት በሰዎች ላይያለውን ጭንቀት ድንቁርናና ጥፋት ለማስወገድ፣እንቅፋት እንዳይሆንባቸው ከዓለሙ እንዲለዩአደረጋቸው። ለሚስት፣ለልጅ፤ ለሀብት፣ ለንብረትማሰብና መጨነቅ እንዳይኖር ምን ላብላቸው፣ ምንላጠጣቸው፣ በምን ላስደስታቸው እንዳይሉ ነውከዓለሙ ነጻ ያወጣቸው። ስለዚህ የጌታ ትምህርትየገባው ሐዋርያው እንዲህ ሲል ተናገረ ‹‹እስመዘኢያውሰበ ይኄልዮ ለእግዚአብሔር በዘያሠምሮለእግዚአብሔር ወዘሰ አወሰበ ይኄሊ ንብረተ ዝንቱዓለም በዘያሠምራ ለብእሲቱ፣ ይህም ያላገባእግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው ገንዘብ ደስየሚሰኝበትን ያስባልና ያገባ ግን ሚስቱን ደስየሚያሰኝበትን ገንዘብ ያስባልና ››1ኛ. ቆሮ.7፥32
ሐዋርያው ንዋየ ኅሩየ ረሰይኩከ ከመ ትጹር ስምየ በውስተ አሕዛብ ስሜን በአሕዛብ ዘንድ እንድታስተምር ልዩ መሣሪያ አድርጌ መርጨሃለሁ ባለው መሠረት ወአንሰ ሐሰ ሊተ ኢይዜኀር ዘእንበለ በመስቀሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እኔ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መከራ መስቀል እንጂ በሌላ አልመካም ‹‹ወበኀቤየሰ ምውት ዓለም›› ዓለም በእኔ ዘንድ የሞተ ነው ወአነሂ ምውት በኀበ ዓለም እኔም በዓለም ዘንድ የሞትኩ ነኝ በማለት የዓለም ጭንቀትና ጥበት የሌለበት መሆኑን ገለጠ ገላ.6፥14። የወንጌል ገበሬ የሆኑ ወንጌላውያን ሐዋርያት ዛሬም ያስፈልጋሉ። የት ይገኙ? መሳዮችና አስመሳዮች ሞልተዋል፣ ሆነው የተገኙ ግን የሉም። ካሉም መልካም ከሌሉም እንዲኖሩ ማድረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ድርሻ ነው፤ ከመንበሩ ላይ አለንና ‹‹ ሤመክሙ እግዘአብሔር ጳጳሳተ ከመ ትርዐዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለክርስቶስ እንተ አጥረያ በደሙ ወዐተባ በዕፀ መስቀሉ ተብሎ ተጽፏል፡፡ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድረጎ ሾማችሁ፡፡ የሐ.ሥራ 20፥28 ሐዋርያት ከዓለም የተለዩበትን ግዳጅን ተወጡ። በሮማ ከተማ ወንጌልን ሲሰብኩና አምላክነቱን ሲመሰክሩ በነኔሮን ቄሣር አንገታቸው ተቆረጠ፣ ደማቸው ፈሰሰ፣ አለአግባብ ተሰቅለው ሞቱ፡፡ እነ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ለዘፈነች ሴት ወለተ ሄሮድያዳ፣ አንገቱ ተቆረጠ፣ ሐዋርያት ሁሉም የየሀገረ ስብከታቸውን የምናኔ የአገልግሎት ተግራቸውን ፈጸሙ ‹‹ ሰማዕተ ኮኑ በሃይማኖት ወበፅንዐ ትዕግሥት›› እንዲል።
ሐ. የአበው መነኰሳትና የእማትመነኰሳይያት መመሪያ ሥርዐተ ሕግ፤
የምንኲስና ሕይወት በትሩፋት የበለጸገ ቢሆንም የሁሉም መነሻ የሚሆኑ መመሪያዎች አሉት። ከእነዚህም ዋና ዋናዎቹ፦
ንጽሕና እና ቅድስናተአዝዞ/ኦሆ በሃሊትን (መታዘዝን፣እሺ ማለትን)መንኖ ጥሪትን (ለራስ ወይም ለግል የራስ የሆነ ሀብት አለማስቀመጥን)ለጾም፣ ለስግደት ለጸሎት በጠቅላላው ለትሩፋት ጽሙዳን መሆን፣ ለሁሉም ነገር በሰዓት መገልገል ናቸው።
የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ግን ፦ ፍቅር፣ ደስታ ሰላም ትዕግሥት ቸርነት በጎነት እምነት የዋህነት ራስን መግዛት ነው። ይህንን ቃል መመሪያ በማድረግ ሥራውን ይጀምራል። የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ (ገላ.5፥22) ተብሎ ተጽፎቸልና።
ሥራ አለመፍታት ራሱ የምናኔ ሕይወት ሌላው ገጽታ ሲሆን ሥራ ፈትነት ደግሞ የዚህ ተቃራኒ የሆነ ኢገዳማዊ ጠባይ ነው፡፡ በእርጅና ወይም በሕመም ምክንያት ለመሥራት የማይችል አቅመ ደካማ ካልሆነ በቀር ማንኛውም ገዳማዊ/ገዳማዊት በተረጅነት እንዲኖር አይፈቀድለትም። አቅመ ደካማ እንኳን ቢሆን ማኅበሩ ድካሙን አይቶ ከሥራ ነጻ እንዲሆን ካለደረገው በቀር እሱ ደክሜያለሁ፣ ልረፍ ብሎ አይጠይቅም። ከሁሉ በላይ በገዳማቱ መንፈሳዊ ፍቅር በዝታ፤በርክታ ትገኛለች። አፍቅሮ ቢጽ በቅዱስ ዮሐንስ መልእክት በተነገረው ቃል መሠረት ወዳጄ ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል ትላለች።
እግዚአብሔርን ማንም አላየውም እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ይሆናል›› (1ዮሐ.ም 4፥11) በሚለው ቃል መሠረት በአበው መነኰሳት አንደበት ለወጣኒዎች ምክር ይሰጣቸዋል።
በየገዳማቱ ሥርዓተ ምንኲስና የሚሰጠው በገዳሙ ፈቃድ ነው። ከዚህ በኋላ በማኅበር ጸሎት በአበምኔቱ ቡራኬ መስቀለ ሞት የተባለ አስኬማ ይሰጣቸዋል፡፡ የአበ ምኔቱ ምክር እንደሚከተለው ነው። በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበረታችሁ ሁኑ የሰይጣን ዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንደ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ካለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዥዎች ጋር በሰማያዊ ስፍራ ካሉ ከከፉት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።
ስለዚህ በከፋ ቀን ለመቃወም፣ ሁሉንም ፈጽማችሁ ለመቆም እንድትችሉ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ አንሡ፤ እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ በሰላም ወንጌል በመዘጋጀት እግሮቻችሁን ተጫምታችሁ ቁሙ የክፉን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበት የእምነት ጋሻ አንሡ የመዳን ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።
ይህም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ ዘኢፆረ መስቀለ ሞትየ ኢይክል ይጸመደኒ›› መስቀሉንም የማይዝ በኋላየም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም ባለው መሠረት እነሆ እነዚህ አበው መነኰሳት ቃሉን ትእዛዙን እንደፈጸሙ ያሳስበናል። (ማር 8፥34። ሉቃ 9፥23።)
ነገር ግን ውጫዊ ማንነታችን እንኳ ቢጠፋ ውስጣዊ ሕይወታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል። የማይታየውን እንጂ የሚታየውን ባንመለከት ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘለዓለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና የሚታየው የጊዜው ነውና የማይታየው ግን የዘለዓለም ነው። (2ኛ. ቆሮ 4፥16)
ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ወይጽልኣ ነፍሶ ወያጥብዕ ወይፁር መስቀለ ሞቱ ወይትልወኒ አበው መነኰሳት በገዳም ሲኖሩ ዋዕየ ፀሐይን ችለው፤ ብርዱንና ረሀቡን ታግሰው፤ ለዚች ለምታልፈው ጊዜያዊት ዓለም ምንም ሳያስቡና ከምንም ሳይቆጥሩ በሰው ዘንድ የተናቁ ከምንም የማይቆጠሩት ሰዎች በፈጣሪ ዘንድ ግን ከወርቅና ከዕንቊ ይልቅ የጠሩና የከበሩ ከብርሃናት ይልቅ ሰባት እጅ የሚያበሩ ናቸው።
አበው መነኰሳትና እማት መነኰሳይያት እንደ አባት ቅድስት ሥላሴ፤ እንደ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ወንድም እንደ እኅት ቅዱሳን መላእክት እንደ ርስት እንደ ጒልት የማታልፍ ርስተ መንግሥተ ሰማያት አለቻቸውና ደስተኞች ናቸው። በገዳማዊ ሕይወት የሚገባ ኃዘን አለ፤ ይኸውም የራስን ኃጢአት አይቶ፤ ግፍዐ ሰማዕታትን ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን አስቦ፤ ፈጣሪ ዓለሙን በሙሉ በምሕረት ዐይኑ እንዲገበኘው መጸለይና በስሕተት ለሚጠፋው ፍጥረት ማዘን የምንኲስና ዐቢይ ተግባር ነው፡፡ በገዳም ውስጥ የሚኖሩ ገዳማውያንና ገዳማውያት የሱባኤያቸው ትርጉም ይህ ነው። የራስን ኃጢአት እያሰቡ ማዘን እንደ አዳም እንደ ቅ/ዼጥሮስ እንደ ዳዊት ነው። መልካቸው ሳይለወጥ ሳይሰቀቁ እንባቸው እንደ ሰን ውኃ ይወርድ ነበር።
ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን አስቦ ማዘን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ነው። የጌታችንን መድኅነ ዓለም ክርስቶስን የዕለተ ዓርብ መከራውን እያሰበ ሰብዓ ዘመን ቊጹረ ገጽ ሁኖ ኑሯል። ብፁዓን እለ ይላህው ይእዜ እስመ እሙንቱ ይትፌሥሑ፡፡ ዛሬ በንስሓ የሚያለቅሱ ንዑዳን ክቡራን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና፡፡ማቴ. 5$4፡፡ አበው መነኰሳትና መነኰሳይያት በእውነትና በመጸጸት በእግዚአብሔር ፊት ልቡናቸውን አቅርበው ከዓለማዊ ኑሮ ፈጽሞ ሕይወታቸውን በማግለል በፈጸሙት ገድልና ትሩፋት የቃል ኪዳን ቅዱሳን ለመሆን የበቁ ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው።
መ. ባሕታዊ ዘበህድአት
ሐዋርያው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ‹‹ ጻድቃን ወዔሉ በሠቅ ወበሐሜለት ወበዘብድወ ጠሊ ተጸነሱ ተመንደቡ ሐሙ›› ሁሉን እያጡ የበግና የፍየል ለጦ ለብሰው ዞሩ፡ ዓለም አልተገባውቸምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ። ዕብ.11፥37
በየክፍለ ዘመኑ የነበሩ አሁንም ያሉ ባሕታውያን ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ቤት ንብረታቸውን ጥለው የዚህን ዓለም ተድላና ደስታ ንቀው በየገዳማቱ እየገቡ በጾምና በጸሎት ተወስነው በመኖርና እንዲሁም በየዋሻውና በእየዱሩ ቅጠልና ውኃ ብቻ ለቁመተ ሥጋ ያህል በመመገብ ከዚህች ዓለም ተለይተው በገዳም ተሰውረው የሚኖሩ ቅዱሳን ስፍር ቁጥር እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡
እንግዲህ ከብዙ ብሕትዋን አበውና ብሕትዋት እማት ሕይወት እንደምንረዳው ያንድ መናኝ በሥርዓተ ምንኲስና ሕጋዊ ህልውና በጾም በጸሎት ተወስኖ በሱባኤ ተጠምዶ ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ ከሚኖርባት ገዳም ወይም ዋሻ ውጭ መንቀሳቀስ አይችሉም።
ወተግሕሡ እምነጽሮታ ወዘክሮታ በዓይን ከማየትበልብ ከማስሰብ በጆሮ ከመስማት ፈጽመውተከለከሉ። ከሰው ተለይተው ዳባ ለብሰው ዳዋጥሰው ድንጋይ ተንተርሰው ጸብአ አጋንንትን፣ ግርማሌሊትን፣ ድምፀ አራዊትን፣ ችለው በብሕትውናየሚኖሩ አያሌ ቅዱሳን፣ ከዚህ ዓለም ጊዜያዊተድላና ደስታ ራሳቸውን ሰውረው በገዳም ይኖራሉ።
እግዚአብሔርን የሚያፈቅሩ ሕጉንና ትእዛዙን አክብረው በንጽሕና እና በቅድስና ሕይወት የሚኖሩ፤ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ሰማያዊ ምስጢርን የሚያውቁ፤ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ያስገዙ ባሕታውያን፤ ፈቃደ ሥጋን በፍጹም ቆርጦ በመጣል መሪያቸው እግዚአብሔርን፤ መሣሪያቸው ጸሎትን፤ ጋሻቸውን የትሩፋት ሥራ በማድረግ ባማረና በሠመረ መንፈሳዊ ትጋትና ፍቅር የሚኖሩባት ቦታ ገዳም ናት። ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ እንዳለን እናውቃለን።( 2ቆሮ 5፥1)
ባሕታውያን እና ባሕታውያት በትዕግሥት በኅቡእ ሆነው ከበዓት ሳይናወጡ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት ተወስነው ከመኖር በቀር በማንኛውም የገዳሙ አስተዳደር ውስጥ ጣልቃ አይገቡም። የባሕታውያን ግዴታዎች ቀንና ሌሊት በየሰዓታቱ ስለ አርድዕት ስለ ምእመናን ስለ ሀገርና ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጸሎት ማድረስ አለባቸው። የገዳማቱ ሕግ ግዴታም ነው።
‹‹ ብፁዓን እለ ይርኅቡ ወይጸምዑ በእንተ ጽድቅ እስመ እሙንቱ ይጸግቡ›› ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው ይጠግባሉና፡፡ አበው መነኰሳት አብዝተንማ ከተመገብን ሰውነታችንን ገቶ ማኖር እንደምን ይቻለናል ብለው ከሚበሉት ከሚጠጡት ከፍለው የሚራቡ ንዑዳን ክቡራን ናቸው። (ማቴ.5፥6)
የሁሉም አብነቱ አበው መነኰሳት ናቸው። እንዲህ ያለ የትሩፋት አበጋዞች በሰውነት ያለ አእምሮ ጠባይዕ ሥራ ሠርቶ ሊገለጽ ነው እንጅ ተሰውሮ ሊቀር አይደለም፡፡ ሰውነታቸው በዚህኛው ዓለምም ሆነ በወድያኛውም ዓለም የከበረች ነች፡፡‹‹ ወጻድቃንሰ ውስተ ሕይወት ዘለዓለም›› ሥራውን ሠርተው ክብሩን ይወርሱ ዘንድ ጻድቃንስ ሁልጊዜ በዘለዓለም ሕይወት ውስጥ ናችው።
በየገዳማቱ በአርምሞ የሚኖሩ ባሕተውት ብዙ ናቸው። ማለትም ምንም ሳይናገሩ፤ አፋቸው የሚከፈተው ለጸሎት ለምስጋና ብቻ ነው። ጸጥታንና ዝምታን ገንዝብ በማድረግ ይታወቃሉ።
‹‹ ወይበውኡ ውስተ ልበ ሰብእ›› አባቶች መነኰሳት በሰው ልቡና ውስጥ ገብተው ምን እንዳሰብክና ምን እንደ ሠራህ ያውቃሉ፡፡ ልክ ዳዊት በኢዮአብ፣ ኢዮአብ፣ በዳዊት ልብ፣ ሳኦል በአበኔር፣ አበኔር በሳኦል ልቡና ምን እንዳለ እንዳወቁ ሁሉ ባሕታውያንም በሰው ልቡና ያለውን በሚገባ ያውቃሉ።
እንግዲህ አስተውሉ! የአባቶች መነኰሳት መዓርግ እስከዚህ ድረስ ነው። የሰውን ልቡና ይመረምራሉ፣ ያለፈውንም የሚመጣውንም ያውቃሉ፣ በእግዚአብሔር ኃይልና ቸርነት ይመካሉ። ለዚህም ነው አርድእት ከገዳም ወደ ገጠር ሲላኩ ከባሕታውያን አበው እግር ወድቀው ጸሎት የሚቀበሉት ከፈተና እንዲሰውራቸው ወደ አባቶች ሄደው እንዲጸልዩላቸው፣ ሲጠይቋቸው ኃይለ አጽራርንና ኃይለ አጋንንትን እንዲያደክምላቸሁ ሰይጣን ያደረበት ሰውም እንዳግጠማችሁ ወደ ገዳማችሁና በዓታችሁ በሰላምና በደህና ይመልሳችሁ ብለው ይጸልዩላቸዋል።
ሌላው የሚያስገርመውና የሚያስደንቀው ደግሞ የመነኰሳት ሕይወት ነው። የመጀመሪያው መነኲሴ ሁለተኛውን፤ ሁለተኛው ሦስተኛውን፤ ሦስተኛው ዐራተኛውን እንዲህ እያለ ከሕገ ሥጋ ወደ ሕገ ነፍስ፤ ከወጣኒነት ወደ ማእከላዊነት ከማእከላዊንት ወደ ፍጹምነት ይደርሳል ማለት ነው። እነዚህም ዐሥሩ መዓርጋት
ጽማዌ፦ መላእክት ሲወጡ ሲወርዱ ማየት ነገር ግን የሚወጡበትንና የሚወርዱበትን አለማወቅ ነው።ልባዊ፦ መላእክት የሚወጡትንና የሚወርዱበትን ማወቅ ነው።ጣዕመ ዝማሬ፦ ከዚህ መዓርግ ሲደርሱ ውዳሴ ከንቱ ይቃወማቸዋል።አንብዐ ንሰሓ፦ እንደ ሰን ውኃ እንባቸው ሳያቋርጥ መፍሰስ ነው።ኲነኔ፦ ሥጋን ለነፍስ ማስገዛት ነው።ዑቃቤ፦ በዚያው ጸንቶ መኖር ነው።ንጻሬ፦ ከአለት ሆኖ መላእክትን በየከተማቸው ማየት ነው።ሑሰት፦ እንደእግረ ፀሐይ ከሁሉ መድረስ ነው።ተሰጥሞ፡- በባሕረ ብርሃን መዋኘት ነው።ፍቅረ ደቂቀ ዕጓለ እመሕያው፦ አማኒ ኢአማኒ፣ ኃጥእ ጻድቅ፣ባዕድ ዘመድ፣ ሳይሉ የሰውን ዘር ሁሉ አንድ አድርጐ አስተካክሎ መውደድ ነው።
እነዚህ መዐርጋት የሚገኙት ከሰው ለተለዩ፣ በዱር በገደል ለሚኖሩ ቅዱሳን ነው። ሁሉን አስተካክሎ ማየት የሚቻለው ማነው ? ከዚህ መዓርግ የሚደርስ ሰውስ ማን ነው? እንደተጠቀሰው ለዐሥረኛው መዓርግ እንዲበቃ አይጠበቅበትም። የሚጠበቅበት ዋናው የእግዚአብሔር ሰው መሆን መቻሉ ነው።የፍጹማኑ መነኰሳት ሕይወትም ይህንን ይመስላል።
ሶበ ኀለየ ልብየ፤ ልቡናዬ የንጽሐ ነፍስን ነገር ባሰበ ጊዜ ከንጽሐ ነፍስ ማዕረግ ደረስሁ እንደ አዳም ከስምንተኛው ማዕረግ ደረስሁ ዳግመኛ ከንጹሐ ነፍስ ወደ ንጽሐ ልቡና ወጣሁ ከንጽሐ ልቡና ማዕረግ ለመድረስ ይተጉ ስለነበሩ ስለ ጻድቃን ነገር አንክሮየ በዛ ንጽሐ ነፍስ ተሰጥታቸው ሳለች ከንጽሐ ልቡና ለመድረስ ገና የመሻት ፈቃድ አለባቸውና ለካ ጻድቃን ለትሩፋት ይተጉ የነበረ ከንጽሐ ልቡና ለመድረስ ነው ብዬ አንክሮዬ በዛ በልቡናዬ አድራ ያለች ፍቅረ እግዚአብሔርም እንደ እሳት ትቀጣጠላለች። አቤቱ ሁልጊዜ አንተን ማሰብ በልቡናው ያደረበት ሰው ንዑድ ክቡር ነው።
አበው መነኰሳት ዘወትር አምላካቸውን በዕንባ፤ በስግደት፤ በቁመት፤ በጸሎት ይማጸኑታል። አንድ ስለራሳቸው ሁለት ስለገዳማቸው ሦስት ስለሕዝባቸው አራት ስለ አገራቸውና ስለዓለም በሙሉ ያለ ዕረፍት ቸርነትህ በኛ ይብዛ በማለት ይማጸኑታል። ቸር ፈጣሪያችን ሆይ በኃጢአት የጐሰቆለ ሰውነታችንን ይቅር በል ይሉታል።
ቸርነትህና ርኀራኄኅ የበዛ ፈጣሪያችን ሆይ ደከመን፤ የሠራነውን ኃጢአት ይቅር በለን አንተን መለመንንና ማመስገንን አንወድምና በግድ ሥራ አሠርተህ ወዳንተ እንድንቀርብ አድርገን፡፡ በፈቃዳችን ከታሰርንበት ግዞት ቤት ሰውነታችንን ነፃ አውጣን አቤቱ ከሀሊነትህ ፍቅርሕ ዓለምን ድል ይነሣልን ዘንድ በወረድንበት በዚህ ዓለም ፍቅር ሰጥመን ከመቅረት አውጣን፡፡ አንተን ከማወቅ ዐይነልቡናችንን የሚሸፍነውን የኃጢአት ኀልዮ ከገጸ ልቡናችን አርቅልን እግዚአብሔር አምላካችን።
ይቆየን……
ከብፁዕ አቡነ ሳሙኤል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን
የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን
ሊቀ ጳጳስ
0 comments:
Post a Comment