የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንኳን ለባዕታ ለማርያም ዓመታዊ ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሳችኁ አደረሰን፡፡
ደጋግመን እንደምንነጋገረው በዓላትን የምናከብረው እንዲኹ በልምድ አይደለም፡፡ ከእያንዳንዱ በዓል የምንማረውና ለራሳችን የምጠይቀው ነገር አለ፡፡ እስኪ ዛሬም ነፍሳችንን እንዲኽ ስንል እንጠይቃት፡- ነፍሴ ሆይ! እመቤትሽ ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበትን በዓል እያከበርሽ ነው፡፡ አንቺስ መቼ ይኾን ወደ ቤተ መቅደሱ በዘልማድ ሳይኾን በእውነት የምትገቢው? እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በሦስት ዓመቷ ገባች እያልሽ እያከበርሽ ነው፡፡ አንቺስ በስንት ዓመትሽ ይኾን የምትገቢው? ነፍሴ ሆይ! እስኪ ተጠየቂ፤ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብታ ሰማያዊ መ ና ሰማያዊ መጠጥ ጠጣች እያልሽ እያከበርሽ ነው፡፡ ታድያ አንቺስ መቼ ነው ከዚኹ ሰማያዊ መናና ሰማያዊ መጠጥ ተካፋይ የምትኾኚው? መቼ ነው በአንቺ ወደ ቤተ መቅደሱ መግባት በእነ ቅዱስ ፋኑኤል ዘንድ ታላቅ ደስታ የሚኾነው?
ተወዳጆች ሆይ! ራሳችንን እንመልከት፡፡ ክርስትና ዕውቀት አይደለም፡፡ ክርስትና መረጃ አይደለም፡፡ ክርስትና መኖር ነው፡፡ ይኽን ከማንም ሰው በላይ ያሳየችን ታላቋ የሕይወታችን መስታወት ደግሞ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ስለዚኽ ርሷን ልንመስል ይገባል፡፡ በኹለንታናችን የእውነት ልጆቿ ልንኾን ያስፈልጋል፡፡ እመቤታችን ባለችበት መገኘት ያስፈልጋል፡፡
አማላጂቱ ሆይ! ደካሞች እንደኾንን ታውቂያለሽ፡፡ የዓለም ጓዝ ይዞን እንዳይቀር፥ ወደ ቤተ መቅደሱ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድም ወደ ደብተራ ብርሃን እንድንገባ፥ ከኅብስተ ሕይወት ከስቴ ሕይወት አንድም ከጣዕመ መንግሥተ ሰማያት እንድንሳተፍም በምልጃሽ ደግፊን፡፡ መቅደስ ሰውነታችንን ከኃጢአት ድር ይወለወል ዘንድ ልጅሽንና ወዳጅሽን ቅድስት ሆይ ለምኚልን፡፡
0 comments:
Post a Comment