• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday, 10 November 2015

    “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን “ ራዕየ ዮሐንስ ምእራፍ ፪ ፥ ፲


    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን! 

    “ካለውና ከነበረው ከሚመጣውም በዙፋኑም ፊት ካሉት ከሰባቱ መናፍስት ከታመነውም ምስክር ከሙታንም በኩር የምድርም ነገሥታት ገዥ ከሆነ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን አሜን!””

    “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን “ ራዕየ ዮሐንስ ምእራፍ  ፪ ፥ ፲

    በዘላለማዊ የኪዳን ደም ሊታደገንና ለነፍሳችን ፍጹም እረፍትን ሊሰጠን፡ ወደ ክብሩ ዙፋን ሊያደርሰንና ወደ ቅዱሳን ሕብረት ሊደምረን በቀራንዮ ለቤዛነታችን መስዋዕት የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ለታመነው ሐዋርያ በፍጥሞ  ደሴት በግዞት ሳለ ወደፊት በቤተክርቲያን ላይ ሊደርስ ስላለው መከራ፦ ስደትና ፈተና እንዲሁም ለቤተክርስቲያን መሪዎችና ለማህበረ ምእመናን ፦ ከእነርሱ ስለሚጠበቀው ኃላፊነትና ክርስቲያናዊ ግዴታ ምን እንደሆነ በአጽንኦት የሚያመላክት፤ አማናዊ ቃሉን ለሚጠብቁ እና እንደ ፈቃዱም ጸንተው ለሚኖሩት ያዘጋጀላቸው ፍጹም የሆነ ሰማያዊ ክብር እና ጸጋ በማስረገጥ በራዕይ የገለጠለት ምስጢራዊ የትንቢት ቃል ነው።

    በራዕየ ዮሐንስ ምዕራፍ ሁለት እና ሦስት የተጻፉት ትንቢታዊ መልዕክቶች በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በእስያ (በዛሬዋ የቱርክ ክፍለ ግዛት) አካባቢ በቅዱሳን ሐዋርያት ትምህርት የተመሰረቱ እና ታላቅ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጥባቸው የነበሩ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ፦ የአገልግሎት ጥንካሬ እና ድክመት ምን እንደሆኑ በዝርዝር ከማስረዳታቸውም ባሻገር የእነዚያ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ምእመናን በተለያዩ ምክንያቶች በወቅቱ ከደረሱባቸው ወደ ፊትም ሊመጡባቸው ከሚችሉ ፈተናዎች እና መከራዎች እንዴት ማምለጥ እንደሚችሉ ከእግዚአብሔር የተላከላቸውን መልዕክት ሰምተው፦ በእምነትም ጸንተው፦ በመንፈሳዊ ተጋድሎ በርትተው በእግዚአንሔር ኃይል እና መንፈስ በመታገዝ በአሸናፊነት መጓዝ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያሳዩ መልዕክቶች ናቸው። ለዚህም ነው በእያንዳንዷ መልዕክት መዝጊያ ላይ “ መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን  ጆሮ ያለው ይስማ።” በማለት ያሳሰበው።

    ከሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከልም ከወቀሳው ቃል የዳኑት ሰምርኔስ እና ፊላዴልፊያ  ሲሆኑ የአምስቱ አብያተ ክርስቲያናት አለቆች እና ምዕመናን ወቀሳ እና ተግሳጽ ደርሶባቸዋል። “እስከሞት ድረስ የታመንህ ሁን.....” የሚለው ቃል በወቅቱ የተነገረውም በሰምርኔስ ቤተ ክርስቲያን ተሹሞ ለነበረው ለቅዱስ ሄሬኔዎስ ነው። በእርሱ እና በምእመናን ላይ እስራት እና  ጽኑ የሆነ መከራ እንደሚደርስባቸው እያሳሰበ በዚህ ሁሉ ግን ሊደርስባቸው በሚችለው ነገር ሳይሳቀቁ ፍርሃትን በእምነት አስወግደው እስከ ሞት ድረስ እግዚአብሔርን በመታመን እንዲጸኑ፦ ይህንን ቢያደርጉ የሕይወትን አክሊል እንደሚቀዳጁ በማስረገጥ ነው መልዕክቱን ያጠቃለለው።

    የእግዚአብሔር ቃል እና መልዕክት ዘመን የማይሽረው እና ዘላለማዊ በመሆኑ ዘመናትን አልፎ አሁንም በዚህ ዘመን ላለነው ትውልዶች በእግዚአብሔር ቤት ስንኖር፦ በክርስትና መንገድ ስንመላለስ ሊኖረን ስለሚገባው ክርስቲያናዊ ሕይወት፦ በሥጋችን ምኞት እና በስሜቶቻችን ከሚመጡብን ፈተናዎች፦ በሌሎች ሰዎች ምክንያት ከሚደርሱብን ችግሮች፦ ከዲያብሎስ የሚወረወርብን የጠላት ፍላጻ እንዴት መመከት እንዳለብን ያስተምረናል። በሁለቱ ምዕራፎች ላይ የተዘረዘሩት ችግሮች ዛሬም ቤተ ክርስቲያንን እያስጨነቋት ያሉ፦ የአገልጋዮችንና የምእመናንን ሕይወት ለከፋ አደጋ ላይ የጣሉ መሆናቸውን በየእለቱ የምንመለከተው ነው። የጥፋት ሰለባ እንዳንሆን ፍጹም ፈቃዱ የሆነ እግዚአብሔር ያሉብን ችግሮች ምን እንደሆኑ በዝርዝር ከማስረዳቱም ባሻገር፣ችግሮቻችንን መፍታት የምንችልበትን መንገድ ሊገባን በሚችል ቋንቋ አስቀምጦልናል፡፡

    አንዳንዶች እንደሚያስቡት የክርስትና ጉዞ “አልጋ በአልጋ” አይደለም በየጊዜው መልኩን እየቀያየረ የሚመጣ መከራ ያለበት፦ መትጋትን የሚጠይቅ፦ “ንበሩ ድልዋኒክሙ” እንደተባለው ሁል ጊዜ ዝግጁ ሆነው የሚመላለሱበት የሕይወት መንገድ ነው። መንገደኛ ለጉዞ  የሚያስፈልገውን ስንቅ እና እንደየመንገዱ ሁኔታ የሚይዛቸው ነገሮች ይኖሩታል። አንድ ወታደርም ብቁ ወታደር የሚያሰኘውን ትምህርት አግኝቶ ፦ የሚይዘውን መሳሪያ አጠቃቀም በሚገባ አውቆ፦ጠላቱን ማሸነፍ የሚችልበትን ስልት ተረድቶ ፦ በቂ የሆነ የአካል እና የስነ ልቦና ስልጠና  ተሰጥቶት ነው ወደ ውጊያ  የሚሰማራው። ክርስትናም እንደዚሁ ነው።

    በክርስትና  ጉዞ ሦስት ዓበይት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው።

    አንደኛው እምነት ነው። ከምንም በፊት እምነት አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልምና። ዕብራውያን ፲፩፡ ፮ በእምነት ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊ የሆነውን ተስፋ እናደርጋለን። በእግዚአብሔር ስንታመን እርሱም ይረዳናል። ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ ምዕራፍ ላይ ብዙዎች እግዚአብሔርን በማመን ለሰው የማይቻለውን ነገር ማድረግ እንደቻሉ በዝርዝር ያስተምራል። ንጉሥ ዳዊትም “አባቶቻችን አንተን ተማመኑ፤ተማመኑ አንተም አዳንካቸው።” መዝ ፳፩፡ ፬ በማለት ዘምሯል። ስለ እምነት ነቢያትም ሐዋርያትም ብዙ ጽፈዋል። ጌታችንም “በእግዚአብሔር አብ እመኑ በእኔም እመኑ” በማለት አስተምሮናል ዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፬፡፩

    ሁለተኛው ቃሉን በመጠበቅ በእውቀት እና በማስተዋል መመላለስ ነው። ክርስቲያን ስለሚያምነው እግዚአብሔር ፦ስለ ጥልቅ ፍቅሩ፦ ምህረቱ እና ወሰን ስለሌለው ቸርነቱ ማወቅ ይጠበቅበታል። ሐሰትን ከእውነት መለየት እና የእግዚአብሔርን ቃል ከሌላ ትምህርት ጋር ቀላቅለው የሚያስተምሩትን በጥንቃቄ ለይቶ መረዳት ያስፈልጋል። ጌታችን በትምህርቱ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ” ዮሐ ወንጌል፲፬፡፲፭ በማለት እንደተናገረው ትእዛዙን ወይም ቃሉን መጠበቅ በረከትን ያሰጣል። በሌላ በኩልም ጌታችን የተናገረውን ቃል የማያስተውሉትን ይወቅሳል ዮሐ ወን ፰፡፵፫ “ንግግሬን የማታስተውሉ ስለምንድን ነው?” በማለት። ቅዱስ ጳውሎስ በጻፋቸው መልዕክቶች ሁሉ የሚያምነውን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ፦ ከዚህም የተነሣ ከሁሉ የሚበልጠውን ሰማያዊ ክብርን ለማግኘት አብዝቶ እንደሚጋደል ደጋግሞ አስተምሯል። ጠቢቡ ሰለሞን “ቅዱሱን ማወቅ ማስተዋል ነው።” መጽ ምሳሌ ፱፡፲ በማለት የምክር ቃሉን አስፍሯል። ትእዛዙን መጠበቅም በህይወት እንደሚያኖር ይገልጣል ፤ መጽ ምሳሌ ፯፡፪ ቅዱስ ጳውሎስም “ያመንሁትን አውቃለሁና” በሚደርስብኝ መከራ አላፍርም ይላል ፪ኛ ጢሞቴዎስ ፩፡፲፪ በፊላዴልፊያ ቤተ ክርስቲያን ተሹሞ ለነበረው ለቅዱስ ዲሜጥሮስ “ቃሌን ጠብቀሃል.....የትእግስቴን ቃል ስለጠበቅክ..... በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።” ራዕይ ዮሐ ፫፡፲ በማለት የእግዚአብሔር ጥበቃ እንደማይለየው አስረግጦ ነግሮታል፡፡

    ሦስተኛው ተግባር ነው። ክርስቲያን እግዚአብሔርን በማመን እና በማወቅ ሲኖር ሥጋዊ እና መንፈሳዊ ህይወቱ ጤናማ እንዲሆን ክርስትናውን በሥራ መግለጥ ያስፈልጋል። ክርስትና በሥራ  እና በእውነት የሚገለጥ እንጂ በእምነት እና በእውቀት ብቻ አይደለምና። ያዕቆብ ፪፡፳፬ ክርስትናንን የሰጠን ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ታሪክ የለወጠው በትምህርቱ ብቻ ሳይሆን በሥራውም ጭምር ነው። ከሁሉ በላይ ደግሞ በእርሱ ሕይወት መስዋዕት መሆን ነው ዓለም ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገረው። በመሆኑም በክርስቶስ ሞት ያገኘነውን ሕይወት እስከ ሞት ድረስ ልንጠብቀው ያስፈልጋል። መታመናችን እስከ ሞት ድረስ መሆኑም ክብርንና ጸጋን እንድናገኝ፦ የሕይወትን አክሊል እንድንቀዳጅ፦ ከሕይወት ዛፍ እንድንበላ፦ በሕይወት መጽሐፍ እንድንጻፍ፦ ሰማያዊት ኢየሩሳሌምን እንድንወርስ እና ከክርስቶስ ጋር በዘለዓለም  መንግስት እንድንኖር ነው።

    ለዚህም ነው አበው ነቢያት እና ሐዋርያት፦ ከእነርሱም በኋላ የተነሡት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፦ በሰማዕታት ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች፦ በሐገራችንም በተለያዩ ወቅቶች በተነሡ ወረራዎች እና የጥፋት ዘመቻዎች ብዙ ክርስቲያኖች እስከ ሞት ድረስ በመታመን ተጋድሎአቸው የፈጸሙት። እንደ ቀዳሜ ሰማዕት እስጢፋኖስ፦ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ጳውሎውስ፦ እንደ ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ፦ ቅዱስ ቶማስ፦ እንደነ አግናጢዮስ ምጥው ለአንበሳ፦ ቅዱስ ጊዮርጊስ፦ ቅዱስ መርቆሬዎስ፦ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ እና  እናቱ ቅድስት እየሉጣ፦ እንደ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ፤ በአጼ ሱስንዮስ ዘመን በደንቀዝ እንደተሰዉት ስምንት ሺህ ክርስቲያኖች፤ በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ በፋሺስቶች ግፍ ለሐገራቸው እና ለቤተ ክርስቲያትን መስዋዕት እንደሆኑት እንደ ሰማዕቱ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ፤ ሊደርስባቸው ካለው የመከራ ብዛት ወደኋላ ሳያፈገፍጉ ሰውነታቸውን እንደ ንጹህ የመገበሪያ ስንዴ ለመስዋዕት ያዘጋጁት። እስከሞት ድረስ መታመን እንዲህ ነው።

    እንደሚታወቀው ባልፉት ሃያ ምዕት ዓመታት ቤተክርስቲያን ያለፈችባቸው ፈተናዎች፣በምእመናን ላይ የደረሰው ስደት እና መከራ እጅግ ብዙ እና አስከፊ እንደሆኑ ከቤተክርስቲያን የታሪክ ማኅደር የምንረዳው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ጠላቶች መጠኑ ይለያይ እንጂ በቤተክርስቲያንኗ አስተዳደርም ይሁን በምዕመናኑ ክርስቲያናዊ ሕይወት ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ቤተክርስቲያን የተመሰረተችው በጽኑ አለት ላይ በመሆኑ የሲዖል ደጆች በጋፏትም፣ “እግዚአብሔር ውስተ ማዕከላ ኢትትሀወክ፣ወይረድአ እግዚአብሔር ፍጽመ” መዝሙር ፵፭፡፭  ትርጓሜውም “እግዚአብሔር በመካከልዋ ነው፣አትናወጥም፣እግዚአብሔርም ፈጥኖ ይረዳል፡፡”እንደተባለው በተደጋጋሚ ከደረሰበት አደጋ በእግዚአብሔር ትድግና፣እንዲሁም እግዚአብሔርን ይዘው በእምነትና በተጋድሎ በፀኑ፣ እስከሞትም ድረስ በታመኑት ልጆቿ መስዋዕትነት እስከ ዛሬ ድረስ፣ ትውፊቷንና ሥራዓቷን ጠብቃ ኖራለች፤እስከዓለም ፍፃሜም በተጋድሎ ጸንታ ትኖራለች፡፡

    እኛም የቀደሙት አበው እምነታቸውን እና ተጋድሎአቸውን እያሰብን እግዚአብሔር በሠራልን የመዳን ጉዞ እስከሞት ድረስ በመታመን ለቤተክርስቲያን ያለንን ፍቅር በሥራና በእውነት በማሳየት ለሰማያዊ ክብር የሚያበቃ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት ይጠበቅብናል፡፡ ይህንን ለማድረግም የእግዚአብሔር ቸርነት የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት የቅዱሳን ምልጃ የመላዕክት ጥበቃ አይለየን፡፡ አሜን፡፡ 

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር!

    እግዚአብሔር ሐገራችንን እና ቤተክርስቲያናችንን ይጠብቅልን! አሜን!

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ማኅበረ በዓለ ወልድ ትምህርት ክፍል

    ሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ሐምሌ ፳፩ ፳፻፬ ዓ.ም.

    አትላንታ 

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን “ ራዕየ ዮሐንስ ምእራፍ ፪ ፥ ፲ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top