• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    ሰሞነ ሕማማት ረቡዕ

                                                                   አስቻለው አሸናፊ

      የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች የሰሞነ ሕማማት ሶስተኛ ቀን የሆነው ረቡዕ እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ መሰረት

    ፩   የምክር ቀን

    ፪   የመልካም መዓዛ ቀንና

    ፫ የእንባ ቀን  በመባል ይታወቃል፡፡

         ይህ ስያሜ የተሰጠው መጽሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ እግዚአብሔር አምላክ እንደረዳን መጠን ስያሜው የተሰጠበትን ፍሬ ሀሣብ ለመረዳት እንሞክራለን፡፡ የቃሉ ባለቤት ሚስጢሩን ለሁላችን ይግለፅልን፡፡ አሜን!!!!

    ፩  የምክር ቀን   ማቴ 26÷1-5 ማር 14÷1-2 ሉቃ 22÷ 2-6

      ይህ ቀን የምክር ቀን የተባለበት ዋነኛው ምክንያት የካህናት አለቆችና የህዝቡ ሹማምንት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሊፈፅሙ ስላሰቡት ሤራ ለመመካከር የተሰበሰቡበት (ሸንጎ የተቀመጡበት)  ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ሸንጎ ‹‹ሲኒሃ ድርየም›› በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ሸንጎ ላይ በአብዛኛው የተሠየሙት ሰዱቃውያን ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ፀሀፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጎው  በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ግቢ የተካሄደ ሲሆን መሪውም ሊቀ ካህኑ ቀያፋ ነበር፡፡ ሸንጎው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት (72) ተሳታፊዎች ነበሩት፡፡

       በወቅቱ ህዝቡ ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት እንዲሁም በሚያደርጋቸው ተአምራት እየተማረከ ስለነበር የካህናት አለቆቹ ልባቸው ውስጥ ታላቅ የሆነ ስጋት ተፈጥሮባቸው ነበር፡፡ ስጋታቸውንም በሸንጎው ላይ እንዲህ በማለት ገልፀዋል፡፡ ‹‹ይህ ሰው ብዙ ተአምራትን ስለሚያደርግ ምን ብናደርግ ይሻላል? እንዲሁ ብንተወው ሰው ሁሉ በእርሱ ያምናል፤ ሮማውያንም መጥተው ቤተ መቅደሳችንንና ህዝባችንን ሁሉ ይደመስሳሉ፡፡››   ሊቀ ካህኑ ቀያፋም ‹‹ እናንተ ምንም አታውቁም፤ ህዝቡ ሁሉ ከሚጠፋ  አንድ ሰው ስለህዝቡ ቢሞት ለእናንተ የሚሻል መሆኑን ከቶ አልተገነዘባችሁምን?›› አላቸው፡፡ ይህን የተናገረው ግን ከራሱ አመንጭቶ አልነበረም፡፡ይልቁንም በዚያን ዓመት ኢየሱስ ስለህዝቡ መሞት እንደሚገባው ሲያመላክት ይህንን ተናገረ፡፡   ዮሀ 11÷49-52

        በዚህ ሸንጎ ላይ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዘው በመግደሉ ሀሳብ ቢስማሙም እንዴት ሊይዙት እንደሚችሉ ግን በጣም ጭንቅ ሆኖባቸው ነበር፡፡ምንክያቱም በወቅቱ የፋሲካ በዓላቸው ( ዘፀ 12÷1-27 )ተቃርቦ ስለነበርና ህዝቡም ጌታችንን በመቀበሉ በበዓሉ ጌታን መያዝ ከባድ መስሏቸው ‹‹በበዓል ቀን ይህንን አናደርገውም›› አሉ፡፡  ማር 14÷12

     ነገር ግን ዲያብሎስ ለክፉ ስራው ተባባሪ አያጣምና ከአስራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ዐቃቤ ንዋይ የነበረው አስቆሮታዊው ይሁዳ ወደ ካህናት አለቆች ዘንድ ሄዶ፤ እሱ ክርስቶስን አሳልፎ ሊሰጣቸው ፣እነሱ ደግሞ የሰላሳ ብር ክፍያ ሊሠጡት ተስማሙ፡፡ (ሉቃ 22÷3 ማቴ 26÷14-16 ማር 14÷10-11) ይሁዳ ጌታውን አሳልፎ ለመስጠት የሚያበቃ በቂ የሆነ ምንክያት አልነበረውም፡፡እሱም እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ ከጌታ እግር ስር ቁጭ ብሎ ትምህርቱን ተምሯል፤ አብሮት በልቷል፤ ጠጥቷል እንዲሁም ጌታችን ብዙ ተአምራትን ሲያደርግ አብሮት ነበር፡፡ከዚህ በተጨማሪም ጌታችን ከሐዋርያት መካከል እሱን ዐቃቤ ንዋይ( ገንዘብ ያዥ) አድርጎ ሾሞት ነበር፡፡ ይሁዳ ግን በልቡ ታላቅ የሆነ የገንዘብ ፍቅር ስለ ነበር ከተሰበሰበው ብር መሀከል የሚወስደው አልበቃ ሲለው፤ የካህናት አለቆች ክርስቶስን መያዝ እንደሚፈልጉ ሲያውቅ፤ ብዙ ብር እንደሚሰጡት አስቦ ጌታውን አሳልፎ ሊሰጣቸው ተስማማ፡፡ ምክንያቱም‹‹ ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥርነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖትተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።››ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ በ 1ኛ ጢሞ 6÷10  የገንዘብ ፍቅር ክፉ መሆኑን ገልፆልናል፡፡ስለዚህም ይሁዳ ከጌታው ይልቅ ገንዘብን በማስበለጥ አምላኩን በ ሰላሳ ብር ሸጠው፡፡ በዚህም ምክንያት የካህናት አለቆችና የህዝብ ሹማምንት ክርስቶስን ለመግደል የተማከሩበት ቀን ስለሆነ የምክር ቀን ይባላል፡፡

    ፪ የመልካም መዓዛ ቀን    ማቴ 26÷6-13 ዮሐ 12÷1-9

     በዚህ እለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስምኦን ዘለምጽ ቤት ለማዕድ ተቀምጦ ሳለ ህይወቷን ሙሉ በዝሙት አሳልፋ የነበረች ስሟ ማርያም እንተፍረት የተባለች ሴት ወደ እርሱ ዘንድ መጥታ፤ በህይወት ዘመኗ የሰራችውን ኃጢያት እንዲምራትና ለንስሀም እንዲሆናት ዋጋው እጅግ የከበረ ሽቶ ገዝታ፤ ጌታ ኃጢያትን የሚያስወግድ፣ ዘለዓለማዊ ህይወትን የሚያድል አምላክ መጣ ስትል፤ ሶስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቶን ይዛ እርሱ ለማዕድ ወደተቀመጠበት ቤት መጣች፡፡ ሽቶውንም በእራሱ ላይ አፈሰሰች፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳም ሽቶው ውድ መሆኑን ተመልክቶ ‹‹ይህ ሽቶ በከንቱ ባከነ፡፡›› በማለት ተናገረ፡፡ ጌታችንም ‹‹እርስዋ ይህን ሽቶ በእኔ ላይ ማፍሰሷ እኔን ለቀብር ለማዘጋጀት ነው፡፡›› በማለት ለሞት እየተቃረበ መሆኑን ነገራቸው ፡፡ ሽቶውም መልካም መዓዛ ያለው በመሆኑ ይህ እለት የመልካም መዓዛ ቀን ይባላል፡፡

    ፫ የእንባ ቀን     ማቴ 26÷6-13 ማር 14÷3-9 ዮሐ 12÷1-9

     የጌታችንን እራስ ሽቶ የቀባችው ይህችው ሴት፤ ክርስቶስ ኃጢያትን ይቅር የሚል አምላክ መሆኑን በማመን ፤ኃጢያቷን ይምራት ዘንድ በፊቱ አልቅሳለች፤ በዕንባዋም እግሩን አጥባለች፤ በጠጉራም እግሩን  አብሳዋለችና ይህ ቀን የእንባ ቀን ይባላል፡፡

       እኛ  የአሁን ዘመን ክርስቲያኖች በዚህ ዕለት ልንማርና ልንረዳ የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር በሰው ልጆች ላይ ክፋትን ለማድረግና በደልን ለመፈፀም መተባበር እንደሌለብን እንዲሁም ጌታችን በመጽሐፍ ‹‹ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።›› ማቴ 6÷24  እንዳለው ይህን የጌታን ቃል መሰረት በማድረግ በውስጣችን ያለውን የገንዘብ ፍቅር ትተን ኃያል ለሆነው አምላክ መገዛትና ቃሉን የህይወታችን መመሪያ ልናደርገው እንደሚገባ ነው፡፡የአስቆሮታዊውን ይሁዳ ታሪክ እንኳን ብንመለከት ከጌታው ይልቅ ገንዘብን አስበልጦ ከሸጠው በኋላ መጨረሻ ላይ የሄደው እራሱን ወደ ማጥፋት ነበር፡፡

    ‹‹በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፥ ሠላሳውንም ብርለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ፤ንጹሕ ደምአሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ። እነርሱ ግን።እኛስ ምን አግዶን? አንተው ተጠንቀቅ አሉ፡፡ብሩንምበቤተ መቅደስ ጥሎ ሄደና ታንቆ ሞተ።›› ማቴ 27÷3-5  እኛም ከእግዚአብሔር ቃል ይልቅ ዓለማዊ የሆነውን ገንዘብን በማሠብ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩ የሰው ልጆች ላይ ክፋትን የምናበዛ፤ በደልን የምናስከትል፤ እርስ በርስ ከመዋደድ ይልቅ እርስ በርሳችን የምንጠፋፋ ከሆነ ወደፊት የሚጠብቀን ዘለዓለማዊ ሞት መሆኑን ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡ መቼም የሰው ልጆች ስንባል እንደ ስማችን ብዛትና ልዩነት የምንሰራው ኃጢዓት ብዛትና ልዩነት አለው፡፡ስለዚህም ስለሰራነው ኃጢዓት ዕለት ዕለት ማልቀስ፤ እንደ ማርያም እንተፍረትም ይቅር ባይነቱን አምነን ተቀብለን፤ ክርስቶስ የማሰርና የመፍታት ስልጣን ወደሰጣቸው( ማቴ 16÷19) ወደ ቤተክርስቲያን ካህናት ዘንድ በመሄድ ንስሀ መግባትና እራሳችንን ለስጋ ወደሙ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቃሉን ተረድተን እራሳችንን በቤቱ ተክለን ለመኖር ያብቃን!! ሟዕለ ፆሙን አሳልፎ ለብርሀነ ትንሳኤው ያድርሰንን!!!      አሜን !!

                                                                                                ወስብሀት ለእግዚአብሔር!!    

                                                    ይቆየን!!!!  

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሰሞነ ሕማማት ረቡዕ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top