• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 12 November 2015

    የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ (ቃና ዘገሊላ)


    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

    “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ”
    (ቃና ዘገሊላ)

    የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ የሚለው ትእዛዝ ሥልጣን ካለው አካል ቢነገር ውጤታማ ሲሆን፤ ሥልጣን ከሌለው ሰው ቢነገር ሰሚ ያጣ ነበር፤ ነገር ግን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ባለ ሞገስ፣ ባለ ጸጋ እመቤት በመሆንዋ ድምጽዋ (ቃልዋ) ተሰሚነት ያለው በመሆኑ አድርጉ በማለት ለአገልጋዮች ትእዛዝ አስተላልፋለች፡፡

    ይህ ቦታ ቃና ዘገሊላ (ከገሊላ አውራጃ አንዷ ቃና) በተባለ ቦታ ነው፡፡ ዶኪማስ ሰርጉን ባደረገበት ወቅት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጠራት፡፡ በአገራቸው ልማድ ወላጅ ከተጠራ፣ ልጅ አብሮ ይመጣል፡፤ ልጅ መምህር ከሆነ ደቀ መዛሙርቱን ጠቅላላ ይዞ ነው የሚመጣው ስለዚህም ሁሉም በቦታው ታድመዋል፡፡

    ከሰው ብዛት የተነሣ ተጠምቆ የነበረው የወይን ጠጅ ግን ሳይታሰብ አልቆአል፡፡ አገልጋዮች ወደ ወይን ጠጅ ክፍል ይገባሉ፤ ነገር ግን ይዘው የሚመጡት የወይን ጠጅ የለም፡፡ የሚጨንቅ ሰዓት ነው፡፡ ሰውን ሰርግ ጠርቶ የሚበላ ወይም የሚጠጣ የለም ማለት አሳፋሪ ነው፡፡

    እመቤታችን “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው”፣ “በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻል” የሚባሉትን ሞገስ ያላት መሆንዋን ሕዝቡ አያውቅም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እርስዋ የማን እናት መሆንዋንም ጭምር የተገነዘበ የለም፡፡ ባለ ተአምራት ልጅ እንዳላት ያመነ፣ ሁሉን ካለ መኖር ወደመኖር ያመጣ ፈጣሪ እንደወለደች ከጥቂቶች በስተቀር በሠርጉ ያሉት ሁሉ አያውቁም፤ ደቀ መዛሙርቱ እንኳ እንዲያምኑበት የቻሉት ይህን የምልክቶች መጀመሪያ ካደረገ በኋላ ነው በእርሱ የአመኑት (ዮሐ 2፡11)፡፡ ስለዚህ አማልጅኝ፣ ጠይቂልኝ፣ ብሎ የሚለምናት አይኖርም፡፡ ባለ “ጸጋ” መሆንዋን አያውቁምና፡፡

    ሁሉም የሚያውቁት ግን አንድ ነገር አለ፡፡ “እናት” ናት፡፡ እመቤታችን ጌታችንን የወለደችው በአሥራ ስድስት ዓመትዋ ነው፡፡ ጌታ ተወልዶ ሰላሣ ዓመት አልፎታል፡፡ ስለዚህም እርስዋ አሁን የአርባ ስድስት ዓመት እመቤት ናት፡፡ እስራኤላውያን “እናት” የሆነችን ማክበር ዕድሜ የሚያረዝም፣ ተስፋ ያለው መሆኑን አጥብቀው ይረዳሉ “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት” (ኤፌ 6፡2-3)፡፡

    ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አገልጋዮቹን በመጥራት “የሚላችሁን አድርጉ” በማለትዋ፤ እነርሱ የሚታዘዝዋት ዕድሜያቸው እንዲረዝም ካላቸው መልካም ምኞት ነው ማለት እንችላለን፡፡ ከዚሁም ጋር አስተዳደጋቸው የእናት ትእዛዝ ንቆና ትቶ መሄድ የማይሞክሩት አይደለም፡፡ እመቤታችን የአርባ አምስት ዓመት እናት በመሆንዋ “እናትህም ባረጀች ጊዜ አትናቃት” (ምሳሌ 23፡22) የሚለውን ትእዛዝ ንቆ እንደመሄድ ስለሆነ ምንም ይሁን የምታዛቸውን ለማድረግ ፍቃደኞች መሆናቸውን መገመት አያዳግትም፡፡

    ድንግል ማርያም ዶኪማስ በሰርግ እንዲያፍር አልፈለገችም፡፡ በተሰጣት ጸጋ ወይን ጠጅ እያለቀ መሆኑን አውቃለች፡፡ ርኅርኅት በመሆንዋ እና ሁሉን ማድረግ የሚችለውን የእግዚአብሔርን ቃል በመውለድዋና ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነሥቶ ከእርስዋ ጋር አማኑኤል (እግዚአብሔር ራሱ) ተቀምጦ፤ ስለ ጭንቀታቸው ዝም ማለት አልፈለገችም፡፡ ስለዚህም ለምልጃ ወደ ፈጣሪዋ ቀረብ ብላ “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” አለችው፡፡

    የፈጣሪዋ መልስ ምንኛ በሚያስደስት ቃላት የተዋቡ ናቸው!፡፡ አንቺ “ሴት” በማለት አዳም ሔዋን ከእርሱ የተካፈለችውን አጥንትና ሥጋ ሊያስታውስ “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ያለውን ተናግሮ አጥንቴ ከአጥንትሽ ነው፤ ሥጋዬም ከሥጋሽ ነው የተገኘው አላት፡፡ እውነትም ድንቅ ነው፡፡

    ቀጥል አደረገና ያልሽኝን ላላደርግልሽ፣ የምታዢኝን ላልፈጽምልሽ እንዴት እንቢ እላለሁ በማለት “ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” የሚል የባህላቸውን ንግግር ተናገረ፡፡ ይህ አነጋገር ምን ጠብ አለን? የሚል የእስራኤላውያን የተለመደ አነጋገር ለመሆኑ ቀጥሎ ያሉትን ጥቅሶች ብትመለከቱ በቂ ነው (2ኛ ሳሙ 19፡22፣ 1ኛ ነገሥ 17፡18፣ 2ኛ ነገሥ 3፡13፣ ማር 5፡7፣ ሉቃ 8፡28)፡፡

    ሁሉን አዋቂ የሆነው አምላካችን ኢየሱስ፣ ከእናቱ ጋር የመጣበት፣ የራሱ የሆነ ምክንያት አለው፡፡ እንዲያው ለከንቱ አይደለም፡፡ ስለዚህ የለመነችውን ልመና ሊያደርግላት ጥቂት ጠብቂኝ ለማለት “ጊዜዬ ገና አልደረሰም” አላት፡፡ እርሱ በአንድም በሌላም ቢናገርም ለተነሣንበት ርዕስ ለመማር በወቅቱ ወይን ጠጁ በድንጋይ ጋኖቹ ውስጥ ሙጥጥ…. ብሎ አላለቀም፡፡ እነርሱ ማለቅ አለባቸው፡፡ የዚህም መሟጠጥ ትልቅ ምክንያት አለው፡፡

    ባልተሟጠጠ የወይን ጠጅ ላይ ውኃ ጨምሮ ተአምር ቢሠራ አምላካችን አይደነቅም፣ ለአምላክነቱም ገላጭ አይሆንም ነበር፡፡ ይህንን ነቢያትም ይሠሩታልና፡፡ ነቢዩ ኤልሣዕ በዕዳ ለተያዘች ሴት በቤትዋ ያለውን የዘይት ማሰሮ አበርክቶላት ከጐረቤቶችዋ በሰበሰበችው ማድጋዎች ሁሉ ዘይቱን እያንጣፈፈች በመሙላት አበርክቶ ተአምር እንደ ሠራላት እስራኤል ሁሉ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ጌታም እንዲሁ ጥቂቱን ወይን ጠጅ ቢያበረክት እንደ ነቢይ ከመቁጠር ውጪ ሊያደንቁትና ሊያምኑበት አይችሉምና ጥቂት ጊዜ እንድትጠብቅና ያለችውን እንደሚያደርግላት ነገራት፣ በዚህም እጅግ አስደሰታት፡፡

    ከደስታዋ የተነሣም ጊዜው ሲደርስ ወይኑ ተሟጥጦ በነበረበት ወቅት እናታችን እመቤታችን ለአገልጋዮቹ የሚላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ አዘዘቻቸው፡፡ እርስዋ ሳታዝዛቸው፤ ራሱ ጌታ ጠርቶ “የምላችሁን አድርጉ” ቢላቸው ኖሮ ምን እንደሚፈጠር መገመት አያዳግትም፡፡

    ጌታ በዚህ ጊዜ ሰላሣ ዓመቱ ነው፤ አስተናጋጆቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት እርሱ በሕዝብ ሁሉ ፊት ተአምር አድርጎ አያውቅም፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለን “ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ” በማለቱ በሕዝቡ እውቅና ባለማግኘቱ ወጣቶቹን የሠላሳ ዓመት እኩያቸው ቢያዛቸው፤ ምናልባትም ወይን ጠጅ በማለቁ ምክንያት፣ ተናድደው ባሉበት ሰዓት ውኃ ቅዱ ቢላቸው፣ በእኩያነታቸው አልታዘዝ ብለው ለተአምሩ እንቅፋት ሊሆኑ ይችሉ ነበር፤ በሰው ሰውኛ አሁን ቀድቶ አሁን ጠምቆ ወይን መሥራት አይቻልምና፡፡

    ነገር ግን “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” ያለቻቸው “እናት” ናት፡፡ “የእናትህንም ሕግ አትተው” (ምሳሌ 6፡20) የሚለውን አጥብቀው የሚከተሉ አማኞች ስለሆኑ፤ ምንም አሥራ ሁለት እንስራ ወይም አስራ ስምንት እንሥራ ያህል ወንዝ ወርደው ከምንጭ ቀድተው መሙላት በእነርሱ “ምን ሊያደርግ ይሆን” የሚል ጥያቄ በአእምሮአቸው ቢመላለስም ቃሉ “የእናትህንም ሕግ አትተው” ስለሚል በእናቱ ትእዛዝ መሠረት አምላካችን ክርስቶስ ያላቸውን ሁሉ ያውም እስከ አፍ ገደፋቸው ድረስ በመሙላት ከብዙ ድካም በኋላ ፈጽመዋል፡፡

    የዚህ ሁሉ የመታዘዛቸው ውጤት ምንድን ይሆን? አሁንም ሌላ የሚላቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ በአምላካዊ ሥልጣኑ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ የቀየረበትን ተአምሩን ከፈጸመ በኋላ፤ ቀጠሎ ሌላ ትእዛዝ “አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት” አላቸው፡፡ ሲቀዱት ምን ያህል ያስፈነድቃቸው?፣ ምን ያህል እየፈጠኑ ለአሳዳሪው እንዲቀምሰው ሮጠው ይሰጡት?፣ ድንቅ አድራጊውን ጌታ ላይ ዓይናቸውን ሳይነቅሉ፤ በደስታ ይመለከቱታል፡፡ ይህን ያደረገ እርሱ መሆኑን የሚያውቁት አገልጋዮቹ ናቸውና፡፡ ጭንቀታቸው ያቃለለችው፣ ትእዛዟን በማክበራቸው ደስታ አግኝተዋል፡፡ አልታዘዛትም ቢሉ ኖሮ የሚያጡት ይህንን ደስታ ነበርና፡፡

    የመታዘዛቸውን ውጤት አሳዳሪው በመቅመስ የሙሽራው ወይን መስሎት በማድነቅ “ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው።”

    በፍጹም ሙሽራው አልጠመቀውም፡፡ የእርሱም አይደለም፡፡ የድንግል ማርያም የምልጃ ውጤት፣ የአገልጋዮቹ የመታዘዝ ትጋት፣ ዕንቁ የሆነው የአዳኛችን፣ የፈጣሪያችን፣ የአምላካችን የኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር ነው፡፡

    ቃና ዘገሊላ ለሕዝብ ሁሉ በመጀመሪያ ጊዜ ድንቅ ሥራ ተፈጸመባት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት ታወቀባት፣ የእግዚአብሔር ወልድ ኤልሻዳይነት ተመሰከረባት፣ የደቀ መዛሙርቱ እምነት ተጀመረባት፡፡

    አሁን የእኛ ቃና ዘገሊላ ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡ በዚያ ጌታ ሰርግ ጠርቶናል፣ በዚያም እናቱ በአማላጅነት አለች፣ ሐዋርያት በቅዳሴው ይታደማሉ፣ ስቡህ፣ እኩት፣ ውዱስ ቅዱስ ይላሉ፤ ካህናት ቅዳሴውን ጀምረው ለዓለም የሚሆን ሥጋ ወደሙን ለመፈተት፣ ከሕዝቡ ጋር “እግዚኦ፣ እግዚኦ” እያሉ ጌታን ይለምኑታል፡፡ እርሱም የቀረበውን ኅብስት እና ወይን፤ ወደ ሥጋውና ደሙ ይቀይራል፡፡ “ሁሉም ተዘጋጅቶአል፤ ወደ ሰርጉ ኑ” ተብለናልና ንስሐ ገብተን ጸድተን ወደ ክርስቶስ ሥጋውና ደም እንቅረብ፡፡ ለዚህም እመቤታችን በአማላጅነትዋ አትለየን፡፡

    አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእናቱን ልመና ሰምቶ ለመንግሥቱ የበቃን ያድርገን፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ (ቃና ዘገሊላ) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top