• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 12 November 2015

    “የድንግል ማርያም ልጅ” ነው ወደ ሰማይ ያረገው


    ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይሁንና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ኃጢአት ሲል የተሰቀለው በሥጋው ነው፣ የሞተውም በሥጋው ነው፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣው በሥጋው ሲሆን፣ ወደ ሰማይ ያረገውም በሥጋው ነው፡፡

    በዚህ ዘመን ያሉ ሐሰተኛ ወገኖቻችን መካከል፤ ጥቂቱ በሥጋው አልሰቀሉትም ሲሉን፤ ከፊሉ ደግሞ በሥጋውስ ተሰቅሎአል፣ ነገር ግን የቀብሩ ቦታ ሥጋው ስለ ጠፋ የተነሣው መንፈሱ ነው ይሉናል፤ ይህ ደግሞ ሠርቀውታል ከሚለው ከአይሁድ ሐሰተኛ ስብከት የማይተናነሥ ነው፡፡ ስለሆነም ከእነዚህ ሐሰተኞች ልንርቅ ይገባናል፡፡ ክርስቶስ የሚሰቀለው በሥጋው፤ የሞተው በሥጋው፤ የተነሣው በሥጋው፤ እንዲሁም ወደ ሰማይ ያረገው በሥጋው ነውና፡፡

    – “ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው…እርሱ ግን ስለ ሰውነቱ ቤተ መቅደስ ይል ነበር” (ዮሐ 2፡19-21)
    – “ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” (ዮሐ 3፡14-15)
    – “ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፥ ስለ ሰው ልጅም በነቢያት የተጻፈው ሁሉ ይፈጸማል፡፡ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታልና፥ ይዘብቱበትማል ያንገላቱትማል ይተፉበትማል፤ ከገረፉትም በኋላ ይገድሉታል፥ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል” (ሉቃስ 18፡31-33)
    – “የሰው ልጅ በኃጢአተኞች እጅ አልፎ ሊሰጥና ሊሰቀል በሦስተኛውም ቀን ሊነሣ ግድ ነው እያለ ገና በገሊላ ሳለ ለእናንተ እንደ ተናገረ አስቡ” (ሉቃስ 24፡6-7)

    እነዚህ ጥቅሶች የሚያስረዱት የክብር ባለቤት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነቱ እንደተሰቀለልን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ የሞተውም እንዲሁ በሥጋ መሆኑንና የተነሣውም በመለኮቱ (በመንፈሱ) ኃይል እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲህ ያስረዱናል፡-

    – “ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ” (1ኛ ጴጥ 4፡1)
    – “መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም” (1ኛ ቆሮ 15፡3)
    – “ስለ ዓመፀኞች አንድ ጊዜ በኃጢአት ምክንያት ሞቶአልና፤ በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” (1ኛ ጴጥ 3፡18)

    በአምላክ የሕይወት ቃሎች እንደምንረዳው በሥጋ የሞተው ክርስቶስ በመለኮት ኃይል፣ በአምላክነቱና በሁሉን ቻይነቱ ከሙታን ተለይቶ ሕያው ሆኖ የታየው ክርስቶስ በዚያው ሥጋ ተቀብሮ በዚያው ሥጋ እንደተነሣ እንድናምን ይረዱናል፡፡ ከሃይማኖታችን የወጡ ወገኖች ግን “በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ” የሚለውን ቃል ይዘው በመንፈስ ነው የተነሣው ወደ ማለት አዘንብለዋል፡፡ ይህ በመንፈስ ተነሣ የሚል አመለካከት በሐዋርያትም ተፈጥሮባቸው በነበረበት ጊዜ ራሱ ጌታ እንጂ ሌላ መንፈሳዊ ፍጡር እንዳልሆነ ምላሽ ሰጥቶአቸዋል፡፡ “ጌታ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ። ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው፡፡ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው፡፡ እርሱም፦ ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እጆቹንና እግሮቹን አሳያቸው፡፡” ከዚህ ከጌታ ቃል “መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውም” የሚለው በመንፈስ እንዳልተነሣ ሲያመለክት “እኔ ራሴ እንደ ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ” የሚለው ደግሞ ራሱ የተሰቀለውና የሞተው እንደተነሣ ያስገነዝበናል፡፡ በራሱ ሥጋ እንደተነሣ የሚያስተምሩን ተጨማሪ ጥቅሶችን ይመልከቱ፡-

    – ሴቶቹ ወደ መቃብሩ የመጡት ማንን ፈልገው ነው? የተሰቀለውን ሥጋውን፣ ምኑን ሽቱ ሊቀቡት ነው የመጡት? ሥጋውን፣ መልአኩ የተኛበትን ሥፍራ እዩ ከዚህ የለም ያላቸው ምኑን ነው? ሥጋውን ነው፡፡ “መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው። እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና፡፡ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ” (ማቴ 28፡5-6)
    – “የተሰቀለውን የናዝሬቱን ኢየሱስን ትፈልጋላችሁ፤ ተነሥቶአል፥ በዚህ የለም፤ እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ” (ማር 16፡6)
    – ከተነሣም በኋላ ሲገለጥላቸው ከተናገራቸው ንግግር ማስተዋል የምንችለው ነገር አለን፡- “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸውበዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፡፡ እንዲህም አላቸው፦ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል” (ሉቃስ 24፡44-46) በዚህ ውስጥ ከእናንተ ጋር ሳለሁ የሚለውን ስናጤነው፣ በምንድን ነበር፣ ከእነርሱ ጋር የነበረው? በሥጋ ስለሆነ፤ አሁንም የሚናገራቸው ያው የተነሣው ሥጋ መሆኑን አእምሮአችንን ከከፈትን ግልጽ የሆነ ቃል ነው፡፡
    – ከተነሣ በኋላ የሚሰወረውና በዝግ ቤት የሚገባው መንፈስ ስለሆነ የሚመስላቸው ደግሞ አንዳንዶች ስላሉ፤ ለዚህም መልስ መስጠት ይገባናል፡፡ ይህ የመሰወሩ ተአምር ድንቅ አድራጊነቱን ከሃሊነቱን ያሳያል እንጂ ረቂቅ ሆኖ መነሣቱን አያመለክትም፡፡ ምክንያቱም በሥጋም ሣለ ይህንኑ ተአምር እንደሚሠራ “የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃን ሳለላችሁ በብርሃኑ እመኑ አላቸው። ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ሄደና ተሰወረባቸው” ይላል ይህ ሳይሞትም በፊት ያደረገው ተአምር ነውና አምላክነቱም የሚያመለክት ብቻ ነው (ዮሐ 12፡36)፡፡ ስለሆነም በሥጋ የተነሣው የሰው ልጅ (የድንግል ማርያም ልጅ) ያው እርሱ ተአምር አድራጊ መሆኑን የሚያስገነዝበን ነው፡፡

    በዚሁም አንጻር የሞተውና የተነሣው በሥጋ እንደሆነ ሁሉ ወደ ሰማይም ያረገው የሰው ልጅ ኢየሱስ ከርስቶስ በሥጋው ነው፡፡ ይህንን ገና ወደ ሰማይ ወጥቶ በሥጋ በዙፋኑ እንደሚኖር የተተነበዩ ትንቢቶች አሉ፡፡

    አዳም የፈለገው ከሥላሴ እንደ አንዱ ሆኖ በአምላክነት መኖር ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለተኛው አዳም ሥጋን ለበሶ ከሦስቱ እንደ አንዱ የአምላክነት ሥልጣን እንደሚያገኝ እንዲህ ተጽፎአል፡- “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” (ዘፍ 3፡22)፡፡ ይህም “አዳም” የሔዋንን ባል እንዳልሆነ የምናስተውልበት ምክንያት አዳም ፍሬውን በመብላቱ ምክንያን እንኳን መልካምንና ክፉን ሊያውቅ የሞት ቅጣት ደርሶበታል “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና” (ዘፍ 2፡17) የሚለው ሁሉን ታውቃለህ ሳይሆን ብትበላ ሞትን ትሞታለህ ነው፡፡

    ታዲያ “እነሆ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ” የሚለው እንዴት ነው የተፈጸመው ቢባል፤ በሁለተኛው አዳም ነው፡፡ “ፊተኛው ሰው አዳም ሕያው ነፍስ ሆነ ተብሎ ተጽፎአል፤ ኋለኛው አዳም ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ሆነ” (1ኛ ቆሮ 15፡45) ስለሚል ኋለኛው አዳም መልካምንና ክፉን ያውቃል፤ ይህም ከእኛ ከተባሉት ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ እንደ አንዱ የሆነው የሰው ልጅ ክርስቶስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ወደ ሰማይ ያረገውና በዙፋኑ የተቀመጠው ወልድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ ብሎ አምላክ ትንቢት የተናገረው፡፡

    “አምላክ በእልልታ፥ እግዚአብሔር በመለከት ድምፅ ዐረገ” (መዝ 46/47/፡5) የሚለው እና “ወደ ሰማይ የወጣ የወረደስ ማን ነው? ነፋስንስ በእጁ የጨበጠ ማን ነው? ውኃንስ በልብሱ የቋጠረ ማን ነው? የምድርን ዳርቻ ሁሉ ያጸና ማን ነው? ይህን ታውቅ እንደ ሆንህ፥ ስሙ ማን የልጁስ ስም ማን ነው?” (ምሳሌ 30፡4) ላይ ያለው የእግዚአብሔር ልጅ የተባለው የድንግል ማርያም ልጅ ወደ ሰማይ ማረጉን አስቀድሞ መነገሩን ያስታውቀናል፡፡

    “ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ 3፡13) በዚህ ቃል ውስጥ “ሰማይ” የሚለው ቃል ጠፈርን አይወክልም በትንቢተ ኢሳይያስ 66፡1 “ሰማይ ዙፋኔ ነው” በማለቱ ይህ “ሰማይ” ተብሎ የተነገረው “ዙፋን” የሚለውን ነው፡፡ በመሆኑን ጥቅሱ በማነጻጸር ስንተካው እንዲህ ይሆናል፡-

    “ከዙፋኑም ከወረደ በቀር ወደ ዙፋን የወጣ ማንም የለም፥ እርሱም በዙፋን የሚኖረው የሰው ልጅ ነው” (ዮሐ 3፡13) የሚለውን ስለሆነ አሁን በዙፋኑ ያለው የድንግል ማርያም ልጅ እርሱም “የሰው ልጅ ነው” የተባለው ነው፡፡ ይህም እንዲታወቅ “በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ” (ራእይ 5፡13) በማለቱ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው በጉ እንዲህ ሲመሰገን የሚኖረው ወደ ሰማይ የወጣው ስለ እኛ የተሰቀለው ራሱ ክርስቶስ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ” (1ኛ ጴጥ 3፡22) ያለው፡፡

    በሥጋ አልወጣም ለሚሉን መጽሐፍ ቅዱስን አለማንበባቸውን ያስገነዝበናል እንጂ የድንግል ማርይም ልጅ የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ “ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ” (ማር 16፡19) በማለቱ ዐረገ የተባለው ኢየሱስ ነው፡፡ ይህ ስም ደግሞ ከድንግል ማርያም በተወለደ ጊዜ የተሰጠው ስም ነው፡፡ “ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ” (ማቴ 1፡21) የተባለው ያው በሥጋ የተወለደውና በሥጋዌ ስሙ በሚጠራበት ስሙ በዚያው ኢየሱስ ተብሎ እየተጠራ ነው ወደ ሰማይ የሄደው “ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ” (ሉቃስ 24፡51) በዚህን ጊዜ ነው በሥጋ ከሞት መነሣቱን መላእክት እንዳበሠሩት አሁንም በዕርገቱ ጊዜ “እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፡፡ እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው” (ሐዋ 1፡9-11)፡፡

    “ይህን የሚመሰክር። አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና፡፡
    የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችን ጋር ይሁን፤ አሜን፡፡”
    (ራእይ 22፡ 20-21)

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: “የድንግል ማርያም ልጅ” ነው ወደ ሰማይ ያረገው Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top