• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    ይቅርታ

    ለጤናማ ግንኙነት ይቅርታ ወሳኝ ነው!

    በየትኛውም የኑሮአችን ክፍል ውስጥ ሰላም ያለውን ጤናማ ግንኙነት እስከ ሕይወታችን ፍጻሜ ድረስ ይዘን የምንዘልቀው ይቅርታ መድኀኒትን የምንጠቀም ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ኑሮ ውስጥ ትልቁም ከባዱም ነገር ግንኙነት ነው፡፡ ብዙ ወገኖች በዚህ መንገድ ይፈተናሉ፡፡ በአንድ የጦር ሜዳ ላይ ከጠላት ትልልቅ ዒላማዎች መካከል የግንኙነት መስመሩን ማቋረጥ ቀዳሚ አጀንዳው ነው፡፡ እግዚአብሔር እንኳን በሰናዖር ሜዳ ላይ በጠላትነት በተነሡት ሕዝቦች ፊት የወሰደው እርምጃ ቋንቋቸውን መደባለቅ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር የግንኙነት መስመራቸውን አቋረጠው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ና የተባለው እየሔደ፣ ሒድ የተባለው እየመጣ፣ ውጣ የተባለው እየገባ፣ ቁም የተባለው እየተቀመጠ ጤናማ ግንኙነት ጠፋ፡፡ እናም መጨረሻቸው ጥፋት ሆነ፡፡በእውነት ከልቤ ልንገራችሁ ውጣ ውረድ በበዛበት፣ መውጣትና መግባታችን በብዙ  እንቅፋቶች በተሞላበት ዓለም ሰው በሰላም ለመገናኘቱ ዋጋ ቢሰጥ አይበዛበትም፡፡ ምክንያቱም መገናኘት ቀላል አይደለምና፡፡ እኛ ስንተያይ ሌሎች ጋ መለያየት፣ እኛ ሰላምታ ስንለዋወጥ ሌሎች ጋ መነካከስ፣ እኛ ጤና ይስጥልኝ ስንባባል ሌሎች ቀብር ላይ መሆናቸውን አንዘንጋ፡፡ ይህን እውነት የዘነጋ ሰው የኑሮ ምሥጢሩ አልገባውም ማለት ነው፡፡ እስቲ ሌሊት ስንት አንቡላንስ ጮዃል? ስንቶች ያለበደላቸው በሌሊት ሞተዋል? ስንቶች ከጨለማና ከሰው ጅብ ጋር ሲታገሉ አድረዋል? በሌሊት ለስንቶች ሲለቀስ ታድሯል? ተነፋፍቃችሁ በሰላም የተገናኛችሁ እንኳን ለዚህ አበቃችሁ፡፡ ወጥታችሁ የገባችሁ፣ ተሰማርታችሁ የተሰበሰባችሁ ሐሴት አድርጉ፡፡ ደግሞ ተከፍታችሁ ብቸኝነት የሚያሰቃያችሁ፣ የሰው ክፋት የወዳጅ ክህደት ያቆሰላችሁ፣ ሰው በነፍሱ ተወራርዶ ለሥጋው የተዋጋችሁ እና እንደ ድካማችሁ ያልተከፈላችሁ ተመስገን በሉ፡፡ ይህም የሆነው በሕይወት ስለኖራችሁ ነውና፡፡

    ሰው ከራሱ ጋር መኖር በተቸገረበት በዚህ ዘመን ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር ስኬት ነው፡፡ በተለይ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ የሥጋና የዲያብሎስ ተፅዕኖ ስለሚያይል ጤናማ ግንኙነት በማጣት የሚንገላቱ ብዙ ናቸው፡፡ የአቤል ዕጣ ፈንታ በቃየል ወንድማቸው የደረሰባቸውም በዙሪያችን እንደ ክረምቱ ደመና ናቸው፡፡ ዛሬ ክርስትና ውስጥ ልዩነቱን የሚያጠቡ ጠፍተው መለያየትን የሚያጸድቁትም እንደ አሸን መበርከታቸው ወይ ጉድ ያሰኛል፡፡ ለአብያተ ክርስቲያናት መከፋፈል ምክንያቱ ምን ይሆን? ምዕራብና ምሥራቅ፣ ሰሜንና ደቡብ በሚል ተቀጽላ እናት እና ልጅ ተነጣጠሉ፡፡ ለመሆኑ ከራሳችን ጋር የምንታረቀው መቼ ይሆን?

    ከፍጻሜ የማይደርስ መልካምነትን መጀመር ወረተኛ ስለሚያደርገን ግንኙነታችንን ያበላሸዋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ደግሞ ሽልማትና ክብር ያለው በፍጻሜ ላይ እንጂ በጅምሩ ላይ አይደለም፡፡ ማኅበራዊ ኑሮም ጅማሬ እና ፍጻሜ ያለው የዓላማ ሕይወት ነው፡፡ ዛሬ በሕይወታችን ውስጥ ያለው መጠላላት እና መወነጃጀል ምንጩ አብረን እንዳለቀስን አብረን መኖር ስላቃተን ነው፡፡ ‹‹በረሀብ፣ በችጋር፣ በጤናማጣት ብንማቅቅ፣ ምኑ ነው የሚደንቅ? አብሮ መሥራት እንጂ አብሮ መብላት አናውቅ›› ሆኖ በችግራችን ዘመን አብረውን የተቸገሩ፣ ልቅሶአችንን በእውነት ያለቀሱ ጥሩ ሰዎች በደስታችን ግን ተቃዋሚዎች ይሆናሉ፡፡ ባይቃወሙንም እንኳን እውነተኛ አልቃሽ እንጂ እውነተኛ የደስታ ተካፋይ አይሆኑንም፡፡ መልካምነታቸው መሠረቱን አውጥቶና ትንሽ ጡብ ደርድሮ፣ ጉልላቱን ሳያይ ያልቃልና፡፡

    አንድ የከተማ አውቶብስ ብዙ ሕዝብ ጭና ትነሣለች፡፡ የጫነችውን ሰው በሙሉ ይዛ ግን ጉዞዋን አታጠናቅቅም፡፡ በየፌርማታው የሚወርዱ ብዙ መንገደኞች ሲሆኑ ጥቂቶች ግን ይፈጽማሉ፡፡ በማኅበራዊ ሕይወትም ሲኖር የጀመሩ ሁሉ አይፈጽሙትም፡፡ በመንገድ ወራጅ የሚሉ ብዙዎች ናቸውና፡፡ እግዚአብሔርን ግን የምናገኘው በጽናት ነው፡፡ የጽናትም ቤቱ እምነት ሲሆን መሠረቱ ግን ፍቅር ነው፡፡ ደግሞም መንገዱን የሚያረዝመው ድልድይ መሆኑን አንርሳ፡፡ ታዲያ የእኛንም ማኅበራዊ ኑሮ በጤንነት የሚያረዝመው ይቅርታ ነውና ይቅር እንባባል፡፡ ለአሉባልታ ጆሮ አንስጥ፡፡ ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› ይከፋልና፡፡ ይጠቅሙናል ብለን ከምናስባቸው ነገር ግን ከወዳጃችን ይልቅ ለእኛ አሳቢ ባልሆኑ ሰዎች ከንቱ ወሬአቸውን ሰምተን የቀደመ ፍቅራችንን መተው የለብንም፡፡

    ክፉ አማካሪዎች /መናፍቃን/ በክርስቲያኖች ማኅበራዊ ግንኙነት ላይ ከሚያደርሷቸው ጥፋቶች መካከል አንዱ ፍቅራቸውን ማቀዝቀዝ ነው፡፡ በአንድ በኩል ምእመናን በአሳብ ተከፋፍለው ፍቅራቸው እንዲጠፋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምእመናን ለዘብተኞች ሆነው ለእግዚአብሔር የነበራቸው የጋለ ፍቅር እንዲቀዘቅዝ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያዪቱን ቤተ ክርስቲያን ፍቅር ገንዘብ እንድናደርግ ይጠበቅብናል፡፡ ‹‹በየቀኑ በአንድ ልብ ሆነው በመቅደስ እየተጉ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ በደስታና በጥሩ ልብ ምግባቸውን ይመገቡ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው›› ተብሏልና /ሐዋ.2.#7/፡፡ ቤተክርስቲያን ሕይወታችን ሞገስን የምታጣው የቀድሞ አንድነቷንና ጤናማ ፍቅሯን ስትከስር ነውና በፍቅራችን ሌሎችን መማረክ እስክንችል ድረስ ከልብ እንዋደድ፡፡

    በጾመ ፍልሰታ ለማርያም ካህኑ ሰዓታት ቆመው በጥዑመ ዜማ ‹‹ንዒ›› እያሉ ሲያዜሙ የድምፃቸውን ቅላጼና የዜማውን መርዘም መታገሥ ያልቻሉት ሰው ‹‹እንኳን እርሷ ልትመጣ እኔም ልወጣ ነው›› አሉ ይባላል፡፡ ዛሬ የይቅርታ ቤት ጠፍቶ ፍቅራችን እንኳን ሌሎችን ሊማርክ ይቅርና ብዙዎችን ከውስጥ እየገፈተረ ነውና ‹‹ቤታችሁ የተፈታ ሆኖ ይቀርላችኋል›› ያለው የጌታ ቃል እንዳይደርስብን ያሰጋል /ማቴ.!3. !8/፡፡ ደግሞስ በዓለም ላይ ያለው ጥላቻና መለያየት በእኛም ዘንድ በተመሳሳይ መልኩ ካለ ልዩነታችን ምኑ ላይ ነው? መንፈሳዊነታችን ከወዴት አለ? ስለዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ለጤናማው ግንኙነታችን ይቅርታ አስፈላጊ መሆኑን ስላወቀልን ‹‹የቀድሞ ፍቅርህን ትተሃልና ከወዴት እንደወደቅህ አስብ፤ እንግዲህ ንስሐ ግባ›› እያለ ይወቅሰናል /ራእ.2.4-5/፡፡

    ሰዎች ጤናማ ግንኙነታችንን የሚያውኩት /የሚበድሉን/ በማወቅ ብቻ ሳይሆን ባለማወቅም ነው፡፡ የሕንዱ መሪ የነበሩት ጋንዲ በ፲፱፻፰ ዓ.ም በአንድ ጽንፈኛ እስላም ከተተኮሰ ጥይት ከሞት ለጥቂት ተረፉ፡፡ ያ ሰው ተይዞ እንዲፈረድበት ሲጠየቁ ግን ጋንዲ በፍጹም እምቢ አሉ፡፡ በሞትና በሕይወት መካከል እያጣጣሩ ሳለ ተከታዮቻቸውን ጠርተው በዚያ ሰው ሕይወት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳያደርሱ አደራ ካሉ በኋላ “ይህ ሰው የሚያደርገውን አያውቀውም፡፡ በእርሱ ግምትና አስተሳሰብ እኔ ጋንዲ የምሠራው ሁሉ ትክከል ሆኖ አልታየውም፡፡ ስለዚህ በዚህ ሰው ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳታደርሱበት፡፡ በዚህ ሰው አምንበታለሁ፤ እወደዋለሁ፤ ላሽንፈውም የምፈልገው ለእርሱ ባለኝ ፍቅር ብቻ ነው” አሉ ይባላል፡፡ በእውነት የሌሎችን ችግራቸውን ሳይሆን የችግራቸውን መንሥኤ ማወቅ ይቅር ባይ ያደርገናል፡፡ ሰዎች ለምን እንዳጠፉ፣ ለምን እንዳላደረጉልን፣ ለምን ምላሽ እንዳልሰጡን ከአንደበታቸው ሳንሳማ ፈጥነን አንፍረድ፡፡ ፈርደንባቸው ከሔዱ በኋላ እውነቱን ስናውቅ ለይቅርታ እንኳ ጊዜ እናጣለንና፡፡

    መቼም ያለ ሰው መኖር አንችልም፡፡ ያስቀየሙንን ሰዎች ብንተዋቸው ሌሎችን መፈለጋችን አይቀርም፡፡ ስለዚህ አዲስ ወዳጅ ከምናለምድ ጠባያችንን የሚያውቁልን ወዳጆቻችንን ይቅር ብንል ይሻለናል፡፡ “ድንገተኛ ወዳጅ እንደርሱ አይሆንምና የቀድሞ ወዳጅህን አትተወው” እንዲል፡፡ /ሲራ. ፱፥፲/ በአንድ ወቅት ዐፄ ምኒልክ ከሠራዊቶቻቸው መካከል ስመ ጥር የሆኑ የጦር ሰው እርሳቸውን የሚያሳዝን ጥፋት በመሥራታቸው መኳንንቶቻቸውን ሰብስበው “በድሎኛልና ይህን ሰው አንድ በሉልኝ” አሉ፡፡ መኳንንቱም በየተራ እየተነሡ “እምዬ ምኒልክን ከበደለማ ሞት ይገባዋል” እያሉ የፍርድ አሳብ አቀረቡ፡፡ እርሳቸው ግን ከዛሬ ጥፋቱ የትላንት መልካምነቱን፣ ከዛሬ ወንጀሉ የትናንት ወዳጅነቱን አስበው “እናንተ የዋሆች እርሱን እዚህ ደረጃ ለማድረስ  ሃያ ዓመት ፈጅቶብኛል” ብለው ይቅርታ አደረጉ፡፡ እኒያ ራስም ከቀድሞ ይልቅ ታመኗቸው ይባላል፡፡

    ፈርጀ ብዙ በሆነችው በጥቂቷ ዕድሜያችን ተለሳልሰው ገብተው በቤታችን ከተደላደሉ በኋላ በማያቋርጥ ሙግት አድክመውን ይሆናል፡፡ ችግራቸው እስኪያልፍ ተጠግተውን ሲያገኙ ተረከዛቸውን አንሥተውብን ይሆናል፡፡ በቅቤው ምላሳቸው ሸንገለውን በመርዛማው ልባቸው ጐድተውን ይሆናል፡፡ ሳንፈልግ ያለልክ አክብረውን ጊዜያቸው ሲያልቅ ደግሞ ስማችንን በምናልፍበት ሁሉ አጥፍተውት ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች እንደ ጥንቱ አልሆን ብለው ተለዋውጠውብን ይሆናል፡፡ ለእነዚህም ሰዎች ይቅርታን ልናደርግላቸው ይገባናል፡፡ ቸሩ አምላካችን እኛን ከነስንት ጉዳችን ተሸክሞን የለምን? ዛሬ የሰው ልጅ ኃጢአት ዜና ተብሎ በገበያ ላይ ይሸጣል፡፡ የሚደብቅልን ሰው፣ የምንደብቅለትም ወዳጅ የለንም፡፡ እግዚአብሔር ያየብንን ቢያሳይብን፣ የሰማብንን ቢያሰማብን ኖሮ እንደሰው እንኳን የማንቆጠር፣ አንድ ቀንም ለማደር የማይፈቀድልን በሆንን ነበር፡፡ የእኛ ነገር የማይገርመው እርሱን ብቻ ነው፡፡ ቅዳሴያችን “አንተ ተአምር ድካሞ ለሰብእ፤ የሰውን ድካሙን አንተ ታውቃለህና” እንዲል፡፡

    በሰዎች ላይ የመፍረድ ዝንባሌ ካለን ጤናማ ግንኙታችንን ጉዳት ላይ ይጥለዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ መንገድ የመተያየት ልማድ ይስተዋላል፡፡ ነገሩን በዚህ መንገድ ሰዎችን ለማስተካከል እንኳን ብናስብ አይቻልም፡፡ ደግሞም አብዝተን በምንፈርድባቸው ነገሮች ዘግይቶም ቢሆን ራሳችን እናገኘዋለን፡፡ ታድያ እውነተኛ ነን ካልን እኛ በደከምን ለድካማችን የምናሳየውን ርኅራኄ ለሌሎችም ውድቀት እንዲሁ የምናሳይ እንሆናለን፡፡ ለመፍረድ አለመቸኮል ያበላሸ እንዲያስተካክል ዕድል መስጠት ነው፡፡ አለመፍረድ የወደቀ እንዲቆም መደገፍ ነው፡፡ እስቲ በዛላችሁባቸው ወራቶች በቁስላችሁ ላይ እንጨት የሰደዱባችሁን አስቡ፡፡ ምን ያህል ከባድ ነበር? እናንተ ግን ፈጽማችሁ እንዲህ አታድርጉ፡፡ “እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” ይላልና፡፡ /፩ኛ ቆሮ. ፲፥፲፪/

    ይቅር ያልናቸው ሰዎች ከበደሉን በላይ ይክሱናል፡፡ በክፋት እየመረረች ያለችውንም ዓለም የሚያጣፍጣት ቅመም ይቅርታ ብቻ ነው፡፡ ትዕግሥት ማጣት፣ ክፉውን በክፉ መመለስ ደካማነት ነው፡፡ ብርቱዎች ግን ይቅርታ የሚያደርጉና በመልካም የሚያሸንፉ ናቸው፡፡ “ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት” እንዲል፡፡ /ማቴ. ፭፥፴፱/ ቂምን መንከባከብ አረም ስንዴ ላይሆን መልፋት ነው፡፡ ይህን ሐቅ ክረምቱ አልፎ በጋው ሲመጣ እናየዋለን፡፡ ይቅርታ ግን አዲስ የሕይወት ታሪክን ያስነብብልናል፡፡ እንዲሁም በይቅርታ ሊማሩ የማይፈልጉ ብዙዎችን እናስተምርበታለን፡፡ ታድያ ለጤናማ ግንኙነት የይቅርታን አስፈላጊነት አስተዋላችሁን?

    እንግዲህ ነገሮችን በሚዛናዊነት ለመዳኘትና ከተለያየ አቅጣጫ ለማየት ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ሁሉም ጥሩ ወይም ሁሉም መጥፎ አይደለምና፡፡ ሁሉም መጥፎ እንደሆነ በምናስብበት ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ደጉን ነገር ለመመልከት ጭፍኖች እንሆናለን፡፡ ሁሉም ጥሩ እንደሆነ በምናስብበት ሁኔታ ደግሞ ኑሮአችን ጥንቃቄ የጐደለው “በሬ ከአራጁ ጋር ይውላል” እንደሚባለው ዓይነት ይሆንብናል፡፡ ስለዚህ ጥበበኞች እንሁን፡፡ የበደልንም እንሁን የተበደልን፣ ሁላችንም ለይቅርታ ከልባችን እንታረቅ፡፡ የዘገየ ይቅርታ ደግሞ ይቅር ካለማለት አይሻልምና ፈጥነን ይቅር እንባባል፡፡ “ከባላጋራህ ጋር ፈጥነህ ተስማማ” ተብሏልና፡፡ /ማቴ. ፭፥፳፭/ ለፍቅር፣ ለይቅርታና ለምሕረት ምንም ክፉ ነገር፤ ለጥላቻ፣ ለቂምና ለበቀል ምንም ጥሩ ነገር የለውም፡፡ በመሆኑም ለጤናማ ግንኙነት ይቅርታ ማለትን ልመዱ፡፡

    እኛ ክርስቲያኖች ነን፡፡ ክርስቲያኖች ደግሞ የእግዚአብሔር ሰዎች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ይቅር ባይ አምላክ ነው፡፡ ክርስትና ደግሞ የይቅርታ አስተማሪ ነው፡፡ ስለዚህ ክረስቲያን እስከሆንን ድረስ ያለ ይቅርታ መኖር አንችልም፡፡ ክርስቲያን ለመሆን፣ የይቅርታ ባለቤት የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል ይቅር ባዮች መሆን አለብን፡፡ ይቅር ባዮች ካልሆንን እግዚአብሔርን መምሰል አንችልም፡፡ እግዚአብሔርን ካልመሰልነው ደግሞ እናንተ የአባቴ ቡሩካን ብሎ እጃችንን ይዞ ሊቀበለን አይችልም፡፡

    ይቅርታ ካለ መቀያየም የለም፤ ይቅርታ ካለ ጠብና ጥላቻ የለም፤ ይቅርታ ካለ ሰውን መክሰስ ድንበር ማፍረስ የለም፡፡ ይቅርታ የነደደን ያበርዳል፤ የመረረን ያጣፍጣል፤ የደበቀን ይገልጣል፤ የራቀን ያቀርባል፤ ከቅዱሳን ጋር አንድ ያደርጋል፡፡ ይቅርታ ያገናኛል፤ ያቀራርባል፤ በፍቅር ያስተሣሥራል፤ ያስተሳስባል፡፡ በመሆኑም ዝርዋን የሆነው እንድንሰበሰብ፣ የተራራቅነው እንድንቀራረብ፣ ሥራችን በረከትን እንዲያገኝ፣ አምልኮታችን ዋጋ እንዲኖረው፣ የተፈጠርንበት ዓላማ ግቡን እንዲመታ የይቅርታ ባለቤቶች መሆን ይጠበቅብናል፡፡

    ታላቅ ጥፋት ለሠራው የሰው ልጅ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ የይቅርታ ብሥራት ያሰማው የይቅርታ ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅር የምትልን አንደበት፣ ይቅርታ የምታስብን ልብ፣ ለይቅርታ የሚንበረከክን ጉልበት፣ ለይቅርታ የሚዘረጋን እጅ፣ ስለ ይቅርታ የሚያነባን ዐይን ያድለን፡፡ ያለፈውን ዘመን በሰላም እንዳሳለፈልን መጨውን ዘመንም በይቅርታ የምንኖርበት ጊዜ እንዲያደርግልን መልካም ፈቃዱ ይሁን፡፡

     

    ስብሐት ለእግዚአብሔር

    አባ ሳሙኤል

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

    የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

    አዲስ አበባ

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ይቅርታ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top