• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ

    ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ፤

    ወይጸግቡ ጠላተ ገዳም፤

    ወይረውዩ አድባረ በድው (መዝ. 64÷11-12)፡፡

    “አእትቱ እምላዕሌክሙ ግዕዘክሙ ዘትካት በእንተ ብሉይ ብአሲ ዘይማስን በፍትወተ ስሒት፤ ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ፡፡ ወልበስዎ ለሐዲስ ብእሲ ዘሐደሶ እግዚአብሔር በጽድቅ ወበርትዕ ወበንጽሕ” በተሳሳተ ምኞት የተበላሸውን አስቀድሞ ትኖሩበት የነበረውን አሮጌውን ሰውነት ከእናንተ አርቁ፡፡ ልቡናችሁን በእውቀት አድሱ፤ በእውነት፣ በጽድቅና በንጽሕና እግዚአብሔርን ለመምሰል የተፈጠረውን አዲሱን ሰውነት ልበሱ” (ኤፌ. 4÷22-24)፡፡ ስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘአብጽሐነ እስከ ዛቲ ዕለት፤ ከዚህ ዘመን፣ ከዚህ ዕለትና ከዚህ ያደረሰን ልዑል እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን፡፡ እንኳን ከዘመነ … ወደ ዘመነ … በሰላምና በጤና ሁላችንንም አደረሰን፡፡ ፈጣሪያችን ቸሩ መድኃኔዓለም ዘመኑን የሰላም፣ የዕድገት፣ የጤናና የብልጽግና ዘመን ያድርግልን፡፡ ለሀገራችን ለቤተ ክርስቲያናችን እንዲሁም ለመላው ዓለም እውነተኛውን ሰላምና ፍቅር ያውርድልን፡፡

    ዛሬ በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር 2008 ዓ.ም ሲሆን በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2015 ነው፡፡ ይህ ልዩነት የመጣው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የምዕራብ አብያተ ክርስቲያናት የተለያየ የዘመን አቆጣጠር ስለሚከተሉ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሌላው የክርስትና ዓለም የተለየ የራስዋ ብቻ የሆነ የዘመን አቆጣጠር መንገድ አላት፡፡ ይህም የዘመን አቆጣጠር መጽሐፍ ቅዱስን በተለይም መጽሐፈ ሄኖክንና ኩፋሌን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ጥንታዊው የጁሊያን የዘመን አቆጣጠር ከአሁኑ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር ተመሳሳይነት ነበረው፡፡ ሆኖም የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን በ6ኛው መቶ ዘመን ላይ የጁሊያን የዘመን አቆጣጠር የተባለ ሌላ የዘመን አቆጣጠር ጀመረች፡፡ ይህም የግሪጎርያን የዘመን አቆጣጠር ቢሆን የ4 ዓመት ስሕተት እንዳለው ራሳቸው አውሮፓውያን ያምናሉ፡፡

    ያም ሆነ ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዚህ በያዝነው ባሕረ ሀሳብ በተባለው የዘመን አቆጣጠር ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ አገልግሎት እያቀረበች ትገኛለች፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ዝም ቢሉ ለዓመቱ የዘመን መቁጠሪያ ካሌንደር ማዘጋጀት የሚችል ሰው ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ለሚመጣው ዓመትም የዐቢይ ጾም፣ የሰኔ ጾም መቼ እንደሚገባ እንዲሁም የሆሳዕና፣ የስቅለት፣ የፋሲካና የዕርገት በዓሎች መቼ እንደሚውሉ ለመናገር የሚችል ሰው አይኖርም፡፡ የእኛ ሊቃውንት የመሬትን፣ የፀሐይንና የጨረቃን እንቅስቃሴና ዑደት በልዩ የባሕረ ሀሳብ አቆጣጠር እያሰሉ የዕለታትን፣ የወራትን፣ የዓመታትንና የበዓላትን ቀናት ለመናገር ይችላሉ፡፡

    “እግዚአብሔር መንፈስ ለተማረኩትም ነጻነትን እሰብክላቸው ዘንድ፣ ያዘኑትንም ወደ አሰኛቸው ዘንድ፣ ዕውሮችም ያዩ ዘንድ፣ የተገፉትንም አድናቸው ዘንድ፣ የቆሰሉትንም እፈውሳቸው ዘንድ፣የተመረጠችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት እሰብክ ዘንድ ላከኝ፤” (ኢሳ. 61÷1-2)፡፡ ከዚህም ቀጥሎ ጌታችን የዚህ መጽሐፍ ትንቢት እንደ ደረሰና እንደ ተፈጸመ ለሕዝቡ በግልጥ ተናገረ፡፡ በእርግጥ ጌታችን ሥጋውን ለብሶ የመንፈስ ደስታን አግኝተዋል፤ በኃጢአት ምክንያት የዲያብሎስ እስረኞች የነበሩትም ነጻነትን አግኝተዋል፡፡ በኃጢአት ምክንያት በተፈጥሮ የነበራቸውን ክብር አጥተው ሐዘንተኞች የነበሩት ሁሉ ደግሞ በክርስቶስ ክብራቸውን እንደገና በማግኘታቸው የዘለዓለም ደስታን ተጐናጽፈዋል፡፡ በኃጢአት ዕውራን የነበሩ መንፈሳዊና ሥጋዊ ብርሃንን አግኝተዋል፡፡ በደዌ ኃጢአትም ቁስለኞች የነበሩ የሥጋና የነፍስ ፈውስን አግኝተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ድኅነት፣ ይህ ሁሉ ፈውስ፣ ይህ ሁሉ ነፃነትና በረከት የተገኘው በመድኃኔዓለም ክርስቶስ ስለሆነ፣ ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ይህችን ዘመን “የተመረጠችው የእግዚአብሔር ዓመት” ብሏታል፡፡

    የዘመን መለወጫን በዓል፣ የአዲሱን ዓመት በዓል ያከበርነው በዚሁ ሳምንት ውስጥ ነው፡፡ ዛሬም የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያው ቀዳሚት ሰንበት ስለሆነ ዛሬ የምንነጋገረውና ስለ ዘመን መለወጫ ነው፡፡

    በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት “የተመረጠችው የእግዚአብሔር ዓመት፣” “የተወደደችው ሰዓት” እና “የመዳን ቀን” (2ቆሮ. 6÷2) የተባለው ይህ እኛ የምንኖርበት የክርስትና ዘመን ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እያንዳንዱ ዓመት “የተመረጠ የእግዚአብሔር ዓመት” ነው፡፡ ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር ወደዚህ ወደ አዲሱ ወደ “ተመረጠው የእግዚአብሔር ዓመት” በሕይወት፣ በጤናና በደስታ ጠብቆ፣ ከማናቸውም ችግር፣ ከማናቸውም መከራና አደጋ ሰውሮ እንኳን አደረሰን! እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ! ልዑል እግዚአብሔር አዲሱን ዓመት የፍቅርና የሰላም፣ የደስታና የጤና፣ የሀብትና የብልጽግና ዘመን እንዲያደርግልን፣ እንዲያደርግላቸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምኞቷን ትገልጻለች፡፡

    አዲስ ዓመት ብዙ ነገሮችን ያስታውሰናል፡፡ በዚህ በአዲሱ ዓመት ባለፈው ዓመት የተደረገውን ነገር ሁሉ እናስታውሳለን፡፡ በአዲሱ ዓመት ባለፈው ዓመት የተሠራው ሥራ ሁሉ ይገመገማል፡፡ በአለፈው ዓመት ስለተሠራው ሥራ ሪፖርት (ዘገባ) ይቀርባል፡፡ እያንዳንዱም ሠራተኛ በአለፈው ዓመት ውስጥ ስለሠራቸው ሥራዎች ሁሉ ሪፖርት (ዘገባ) ለቅርብ አለቃው ያቀርባል፡፡ ይህ የሰለጠነው ዓለም አሠራር ነው፡፡ በዚህ ዓይነት የእያንዳንዱ ሠራተኛ ሥራ በአዲሱ ዓመት ይገመገማል፡፡

    ባለፈው ዓመት መልካም ሥራ ከተሠራ፣ ይህ መልካም ሥራ በሚቀጥለውም ዓመት በተሻለና በበለጠ ሁኔታ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ባለፈው ዓመት 1ኛ) ስሕተት ከተሠራ፣ 2ኛ) እንዲሠራ በታቀደው መሠረት ሥራው ካልተከናወነ፣ 3ኛ) ሥራው ግቡን ካልመታ በአጠቃላይ ያለፈው ዓመት ስሕተትና ያለፈው ዓመት ድክመት በሚመጣው ዓመት እንዳይደገም ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ስሕተት ወይም ጉድለት የሠሩ ሁሉ ያ ስሕተት፣ ያ ድክመት፣ ያ ጉድለት በአዲሱ ዓመት እንዳይደገም የሚመለከታቸው ሁሉ ታላቅ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፤ ቃልም ይገባሉ፡፡ ሠራተኞች ሁሉ፣ አለቆችም ሆኑ ተራ ሠራተኞች እንደገና በአዲሱ ዓመት መልካምና የተሻለ ሥራ ለመሥራት አዲስ የሥራ ዕቅድና አዲስ የሥራ ፕሮግራም ያወጣሉ፡፡ እንዲሁም ለሥራ ማስኬጃ፣ ለወጭ መሸፈኛ የሚሆን ባጀት ይዘጋጃል፡፡ ይህ እንግዲህ በሥጋዊ ሕይወታችን፣ በሥጋዊ ሥራችን የምንፈጽመው ተግባር ነው፡፡

    በመንፈሳዊ ሕይወታችንስ ምንድን ነው የምናደርገው? መጀመሪያ ባለፈው ዓመት ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ምን ሠርተናል? ምን አከናውነናል? እያንዳንዳችን ባለፈው ዓመት ስለሠራነው ለፈጣሪያችን ወይንም ለሕሊናችን ሪፖርት (ዘገባ) ማቅረብ አለብን፡፡ ለሚመጣውም ዓመት ዕቅድ ማውጣት አለብን፡፡ ምናልባት ባለፈው ዓመት በመንፈሳዊ ሕይወታችን ተገቢ ሥራ አልሠራን ይሆናል፡፡ በእግዚአብሔር ሕግና ትእዛዝ አልሄድን (አልተጓዝን) ይሆናል፡፡ ይህንን ሁሉ ገምግመንና መርምረን ያለፈውን ዓመት መጥፎ ሥራዎቻችንን በአዲሱ ዓመት ደግመን እንዳንሠራ መጠንቀቅና ለእግዚአብሔር ቃል መግባት አለብን፤ ጥንቃቄም ማድረግ አለብን፡፡ በአዲሱ ዓመት መልካም ሥራና የጽድቅ ሥራ እንድንሠራና እግዚአብሔርን እንድናስደስት ዕቅድ ማውጣት አለብን፡፡ ከምናገኘውም ገቢ ሁሉ ለእግዚአብሔር አሥራት ለመክፈል ዕቅድ ማውጣት አለብን፡፡ ይህንንም ለማድረግ ለፈጣሪያችን ቃል መግባት አለብን፡፡

    እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች የሆናችሁ የተጠራችሁበት ጥሪ ሠርታችሁ በረከት ታገኙበት ዘንድ ኃረየ ፲ወ፪ተ ሐዋርያተ ሴሞሙ ኖሎተ ወወሀቦሙ ሀብተ ይስብኩ ቃላተ ፫አስማተ ፩መንግሥተ

    ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ

    ልዑለ ባሕርይ ቸሩ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ቅዱስ ሉቃስ ወደ ዘመነ ቅዱስ ዮሐንስ ፳፻፰ ዓ.ም በሰላም፤ በጤና፤ በሕይወት አደረሳችሁ

    በግብርና ሙያ ላይ ላላችሁ ገበሬዎች “እግዚኦ ባርክ ፍሬሃ ለምድር፡፡ መሐሪ ወጻድቅ መኑ ከማከ ዘታርኁ ክረምተ በጸጋከ፡፡ ነፍስ ድኀንተ ወነፍስ ርህብተ እንተ ጸግበት ተአኩተከ፡፡”

    አቤቱ የምድርን ፍሬ ባርክ፡፡ በስጦታህ ክረምትን መልሰህ የምታመጣው ሆይ! እንደ አንተ ያለ ጻድቅና ርኀሩኀ አምላክ ማን ነው? የታመመች ሰውነት በተፈወሰች ጊዜ የተራበች ሰውነት በጠገበች ጊዜ ታመሰግንሃለች፡፡

    ባሮ ፪÷፮

    ለብፁዓን አባቶችና (ሊቃነ ጳጳሳት) “ወእከውነክሙ አባክሙ ወአንትሙኒ ትከውኑኒ ደቂቅየ ወአዋልድየ ይቤ እግዚአብሔር ዘኲሎ ይመልክ”

    እኔም እቀበላችኋለሁ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል፡፡                         ፪ቆሮ. ም፮÷፲፰፬

    የዘመነ ኦሪት መጨረሻ የዘመነ ሐዲስ መነሻ፤ ነቢይም፣ ሰማእትም፣ ሐዋርያም በአጥማቂነቱ ካህን፤ የዓለምን ኃጢአት ይቅር የሚል ከእኔ በኋላ ይመጣል በማለቱ ነቢይ፤ ስለ ክርስቶስ ሕይወቱን በመስጠቱ ሰማዕት ከሆነው ከቅዱስ ዮሐንስ በረከት ረድኤት እግዚአብሔር አምላካችን ያድለን አሜን!!

     

    እግዚአብሔር አምላክ ዘመኑን የሰላም፣ የጤና፣ የበረከት፣ የልማት፣ የእድገት ዘመን ያድርግልን!

     

    አባ ሳሙኤል

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

    የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

    አዲስ አበባ

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top