• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 9 November 2015

    ቅዱስ አትናቴዎስ


    ሐዋርያትን የመሰለ የተመሰገነ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አትናቴዎስ ስለ እግዚአብሄር ቃል ሰው መሆን ነገሩን ከኒቅያ ማህበር 318 ሊቃውንት ጋር አስተባብሮ በተናገረበት ድርሳኑ እንዲህ አለ ፦

    ኢየሱስ ክርስቶስ አንዱ አምላክ ነው ፤ በመለኮት የእግዚአብሄር ልጅ በሥጋ የአዳም ልጅ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ልጅ የአዳም ልጅ ስለሆነም ለወልድ ዋህድ ለአንዱ የምንሰግድለት ለአንዱ ደግሞ የማንሰግድለት ሁለት አካል ሁለት ባህርይ አለው የምንል አይደለንም፡፡ ሰው የሆነ የእግዚአብሄር  አካሉ ባህርዩ አንድ ነው እንጂ ፤ ከስጋው ሳንለይ አንድ አድርገን አንዲት ስግደትን እንሰግድለታለን እንጂ፡፡

    ሁለት ነው ፤ አንዱ ከእግዚአብሄር የተገኘ የባህርይ አምላክ ነው ፡ ለእርሱ እንሰግዳለን ፤ ሁለተኛውም ከማርያም የተገኘ ሰው ነው ፡ ለእርሱ አንሰግድም አንልም፡፡ እርሱ ከሰው ቢወለድም በፀጋ የእግዚአብሄር ልጅ   አይደለምና ፤ አስቀድሜ እንደተናገርኩ ከእግዚአብሄር የተገኘ እግዚአብሄር ነው እንጂ፡፡

    እርሱ የእግዚአብሄር አንድያ ልጅ ነው ፡ ዳግመኛም በኅላ ዘመን በሥጋ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደ ያው እርሱ ነው ፡ ሌላ አይደለም፡፡ ዮሐ 1 ፡ 1-18

    ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው የእግዚአብሄር የባህርይ ልጅ ነው ፤ እርሱም የባህርይ አምላክ ነው፡፡ መለኮት ቢያድርበት በፀጋ የከበረ አይደለም ፤ ስጋን በመንሳት ሰው የሆነ እርሱ ብቻ ነው ፤ በመለኮት የእግዚአብሄር ልጅ ነው ፤ አምላክም ነው ፤ እርሱ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ብቻ ነው፡፡

    የእኛን መከራ ተቀበለ ፤ በመለኮቱ መከራ ሳይኖርበት ክርስቶስ ስለእኛ በሥጋ መከራ ተቀበለ ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ዳግመኛም ስለእኛ ስለሁላችን ቤዛ አድርጎ ለሕማም ለሞት ሰጠው እንጂ እግዚአብሄር ላንዱ ልጁስ እንኳን አላዘነም ብሎ እንደተናገረ፡፡ 1ጴጥ 3፡18፣19 ፤ ሮሜ 8 ፡ 32

    እንደቀድሞው መታመም መለወጥ የሌለበት ሁኖ ኖረ፡፡ በነቢይ አድሮ የማይለወጥ

    አምላክ እኔ ነኝ ብሎ እንደተናገረ ፡ በመለኮቱ መለወጥ የለበትም፡፡ ሚል 3፡6

    ሃጢአታችንን ስለማስተስረይ ለእኛ የሚገባ ሞትን ሞተ ፤ ቤዛችን በሚሆን ሞቱ ሞትን ያጠፋው ዘንድ ሞተ ፤ ሞት በመሽነፍ ባህር ተሰጠመ ፤ ሞት ፅናትህ የት አለ?መቃብርስ ማሽነፍህ የት አለ? ብሎ ሐዋርያው እንደተናገረ፡፡ ኢሳ 25፡8  ፤ ሆሴ 13፡14 ፤ 1ቆሮ 15፡54

    እንደተፃፈ ሃጢአታችንን ለማስተስረይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞተ ፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት ቀድሞ እንደነበረ ለዘለዓለሙ ይኖራል ፤ በሞትም አይያዝም ፡ የማይታመም የእግዚአብሄር አብ ሃይሉ ነውና፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረ ሞት ሊይዘው አልቻለምና ፡ ወደ ሰማይ አረገ ፡ በአብ ዕሪና ተቀመጠ ፡ ይኅውም ዕርገት ነቢር ቃል ከአዳም ነስቶ በተዋሃደው ሥጋ የፈፀመው ነው፡፡ ራእ ዮሃ 1፡18 ፤ ግብ ሐዋ 2፡24 ፤ 1ጴጥ 3፡22

    የእግዚአብሄርን ቃል ሲያመለክት ጌታ(አብ) ጌታየን(ወልድ) በቀኜ ተቀመጥ አለው ብሎ ነቢዩ ዳዊት በመፅሃፉ እንደተናገረ፡፡ መዝ 16 ፡(15) 7-11 ፤ ግብ ሐዋ2፡25 -28 ፤ ማቴ 22፡41 ፤ ቃል በመለኮቱ አይወሰንምና እርሱ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ሰማይን ምድርን ይወስናል እንጂ ከቀዳማዊ አብ የተገኘ እርሱ ከዘመን አስቀድመው ከነበሩ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የነበረ ቀዳማዊ ነው፡፡መዝ 95(94)1-7 ፤ ኢሳ 26፡1 ፤ ዮሃ 1፡1-4

    ክርስቶስ የእግዚአብሄር ኅይሉ ነው ፤ የእግዚአብሄር ጥበቡ ነው ብሎ ሐዋርያ ጳውሎስ እንደተናገረ የማይመረመር የእግዚአብሄር አብ ኅይሉ ነውና፡፡1ቆሮ 1-24 በሙታን በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ይህ አንድ አምላክ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የእግዚአብሄር ልጅ ይመጣል ፡ እመጣለሁ ብሎ እንደተናገረ፤ በስውር የተሰራውን መርምሮ የሚፈርድ የልቡናን ሃሳብ የሚገልጥ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ በክብር ይመጣል ፤ ለሁሉም እንደስራው ይከፍለዋል ብሎ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደተናገረ፡፡ማቴ 25፡1-46 ፤  1ቆሮ 4-5

    እግዚአብሄር ካፃፋቸው መፃሕፍት ከተገኘ ከዚህ ትምህርት ሌላ የሚያስተምረውን የእግዚአብሄር ልጅ ፡ ከማርያም ከተወለደው ልዩ ነው የሚለውን አንዱ አካል የእግዚአብሄር ልጅ ፡ አንዱ ከማርያም የተወለደ በፀጋ የከበረ ዕሩቅ ብእሲ ነው ብሎ ሁለት እስከማለት ደርሶ እንደእኛ በፀጋ የከበረ የፀጋ ልጅ ነው የሚለውን ፤ ጌታችን የነሳው ስጋ ከሰማይ እንደተገኘ ፡ ከድንግል ማርያምም እንዳልተገኘ አድርጎ የሚናገረውን ወይንም መለኮት ስጋ ወደመሆን ተለወጠ ፡ ወይም ከእርሱ ጋር ተቀላቀለ ፤ ወይም መለኮት በባህርይው ታመመ የሚለውን ወይም መለኮት ያልተዋሃደው የዕሩቅ ብእሲ ሥጋ ነውና ጌታችን ለተዋሃደው ስጋ አልሰግድለትም የሚለውን የጌታችን ሥጋ አምላክ ነውና እሰግለታለሁ የማይለውን እንዲህ እንዲህ የሚሉትን የእግዚአብሄር ልጅ የሾመው ሐዋርያ እኛ ካስተማርናችሁ ሌላ ትምህርት የሚያስተምራችሁ ሁሉ የተወገዘ ፡ የተለየ ይሁን ያለውን ቃል ይዛ ቅድስት ቤተክርስቲያን ታወግዛቸዋለች ፡ ትለያቸዋለች፡፡ ገላ 1፡6-10

    መናፍቃንም ሰው ሆነ ስለማለት ፋንታም ራሳቸውን ለመጉዳት ልብወለድ ነገርን ፈጥረው “እግዚአብሄር በሰው አደረ” አሉ ፤ መለኮትና ትስብእት እርስ በርሳቸው አንድ ሆነው ተዋሃዱ ስለማለት ፋንታ ሰው ሰራሽ ነገርን ፈጥረው ተናገሩ ፤  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካል አንድ ነው ስለማለት ፋንታ ሁለት ባህርይ ፡ ሁለት አካል ፡ ሁለት ገፅ ብለው አመኑ ፤ በሶስቱ አካላት ስለማመን ፈንታም ሊያምኑበት ሊያስተምሩበት በማይገባ ሥራ አራት ብለው አመኑ፡፡

    ይህም የማይገባ የማይጠቅም ክህደት ነው ፤ ፍጡርን ከፈጣሪ ጋር አቆራኝተዋልና ፤ ተገዥንም ከገዥ ጋር አንድ አድርገዋልና ፤ ካልተፈጠሩ አካላት ጋር ልዩ አራተኛ አካል አለ ብለዋልና፡፡በክህደታቸው በሶስቱ አካላት ላይ ከመላእክት በኅላ የተፈጠረ ሌላ አንድ አካል ይጨምራሉና ሶስት ስለማለት ፋንታም አራት ብለው ይሰግዳሉ፡፡ 1ጢሞ 2፡16-19 ፤ 2ጴጥ 2፡1-13 ፤ እነዚህ የተረገሙ ናቸው ፤ ትምህርታችውንም የያዘ የተረገመ ነው፡፡ ማቴ 25፡41 ፤ 2 ጴጥ 2፡14-22

    ከሃድያን ጳውሎስ ሳምሳጢና መርቅያን እንደተረጎሙላቸው መጠን ይልቁንም እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሰው ሁሉ ለስላሴ ይሰግዳል ፡ ያገለግላል ፡ ይገዛላቸዋል  ይላሉ እንጂ ለእርሱ አይሰግዱም ፤ ሐዋርያት ያስተማሯቸው አምላክ አዝዞ ያፃፋቸው መፃህፍት ያልተናገሩትን የማይገባ ነገርንም ይናገራሉ አሉ፡፡

    ከመምህራን ተለይተው በምክር አንድ ሆነው ሥጋን ሳይዋሃድ ሰው ከመሆን አስቀድሞ በጌትነት በምልአት የነበረ ፤ ሰው በሆነ ጊዜም በጌትነት  በምልአት ያለ ሲሆን በሁሉ ለሁሉ ገዥ ይሆን ዘንድ ሁሉን ባስገዛለት ጊዜ ሁሉን እንዲገዛለት ላደረገ ለአብ ወልድም ይገዛል እያሉ እንደ ወደዱ ይተረጉሟቸዋል፡፡ ያደረበት ሰው ግን ከፍጡራን ሁሉ እንደአንዱ ነው ፡ ለእግዚአብሄር ይሰግዳል ፡ ይገዛል ፡ አሉ ፤ እንዲህ ባለ ድንቁርና እንደተያዙ ዕወቁ ፤ ራሳቸው አዋቆች እንደሆኑ ያስባሉ ፡ የወደቁበትን ይህን የአእምሮ ማጣትና የስንፍና ብዛትን እዩ ፡ በመፃህፍት የማይገኘውን ከልቡናቸው አንቅተው እስከመናገር ደርሰዋል፡፡ ኢሳ 5፡19 ፤ ዮሃ 8፡44(45)

    ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሄር የባህርይ ልጅ ሲሆን ሰው ይባላል ፤ ዳግመኛም የአዳም ልጅ ይባላል ፤ ሰማያዊ ሲሆን በፈቃዱ ምድራዊ ሆነ ፤ በመለኮቱ መከራ መቀበል ሳይኖርበት ሰው በመሆኑ መከራ ተቀበለ ፤ ፈፅሞ አንዱ በአንዱ ያደረ ነው አይባልምና ፡ ለአንዱ ለእግዚአብሄር ልጅ ሁለት አካል ሁለት ገፅ ሁለት ባህርይ የለውም፡፡ ዮሃ 3፡12(13) ፤ ዮሃ 5፡27 ፤ ሮሜ 5፡8-11 ፤ 1ቆሮ 5 ፡ 14

    እኛ ኢየሱስ ክርስቶስን የማይታመም ሰማያዊ አምላክ እንደሆነ እናውቀዋለን ፡ ዳግመኛም በሥጋ ከዳዊት ባህርይ የተገኘ የሚታመም ምድራዊ ሰው ኢንደሆነ እናውቀዋለን ፤ እንደምን ባለ ስራ ፡ እንደምን ባለ ነገር የሚታመም የማይታመም ሆነ? ብለን አንጠራጠር ፡ አንድ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አምላክ ነው ፡ ሰውም ነው፡፡

    የመለኮትና የትስብእት ተዋህዶ እንደምን እንደሆነ ምሳሌ በመሻት አንመራመር  ፡ አንሳት  ፡ አንጠራጠር ፡ ተዘጋጅቶልን ካለ ከመንግስተ ሰማያት ክብር እንዳንለይ፡፡ ከሁሉ የሚበልጥ በዚህ ሃይማኖት በልቡናህ ታምን ዘንድ ይገባል፡፡ ዳግመኛም በዚህ ሃይማኖት ትፀና ዘንድ በአርያም ያለ እግዚአብሄርን ለምነው  ፡ ከስጋዊ ከደማዊ ፡ ከምድራዊ ፈላስፋ ይህን ልትማር ለአንተ አይገባም ፡ በአርያም ካለ ከእግዚአብሄር ዘንድ ነው እንጂ፡፡ እርሱ ራሱ ጌታችን ሰማያዊ አባቴ ነው እንጂ ይህን ስጋዊ ደማዊ መምህር የገለጠልህ አይደለምና ነተ የዮና ልጅ ስምኦን ሆይ ብፁህ ነህ ፡ አንተ መሰረት ነህ ፡ በአንተ መሰረትነት ቤተክርስቲያንን አንፃታለሁ ፡ የሲኦል አበጋዞች አጋንነትም ድል አይነሷትም ብሎ እንዲህ ተናግሯልና፡፡

    የእግዚአብሄር ቸርነት ፡ የእመቤታችን አማላጅነት ፡ የአባታችን የቅዱስ አትናቴዎስ በረከትና ረድኤት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱስ አትናቴዎስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top