ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማለት ለመረዳት እንዲመቸን እያንዳንዳቸውን ቃላት ለመተንተን እንሞክራለን፡
ክርስቲያን ማለት የክርስትና ሃይማኖት መሥራችና ባለቤት በሆነው በክርስቶስ ኢየሱስ አምላክነትና አዳኝነት አምኖ የተጠመቀና የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሰው የሚጠራበት በክርስቶስ የወረስነው ስም ነው፡፡ ይህም ስም ምንም እንኳን የሚጠሩበት ሁሉ በነጻ የተቸራቸው ስጦታ ቢሆንም የስሙ ባለቤት ክርስቶስ ግን ይህንን ስም ለሚሹ ሁሉ ለመስጠት የከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት በፊደል ድርደራና በቃላት ቅንብር መግለጽ አይቻልም፡፡ ‹‹ስለ ጽድቅ የሚሞት በጭንቅ ሊገባ ይችላል ስለ ቸር ሰውም የሚሞት ምናልባት ሊገኝ ይችል ይሆናል፡፡›› ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቷልና በዚህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል፡፡ ሮሜ 3፥5-7
ይህ ክርስትና ክርስቶስን የመምሰል ሕይወት በመኖር ቅድስና ክብርን ለማግኘት የተዘጋጀ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች የሚጠሩበት ስም ነው፡፡ ‹‹ለተቀበሉትና በስሙ ላመኑ የእግዚአብሔር ልጆች የመሆንን መብት ሰጣቸው›› ዮሐ. 1፥12
‹‹ክርስትና›› ሰዎች በፍቅረ እግዚአብሔር ተስበው ፈጣሪያቸውን አውቀው በነፍሳቸውም እረፍትን ሽተው በሕጉና በትዕዛዙ ጸንተው ለመኖር ሲሉ ራሳቸውን ከዓለም ፈቃድ ነጥለውና ሁለንተናቸውን ለእርሱ የሰጡ ሆነው የሚኖሩበት ሕይወት ነው፡፡ ‹‹ዓለምና ምኞቱም ያልፋሉ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘለዓለም ይኖራል›› 1ዮሐ. 2፥17
ሥነ ማለት ሠናየ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ማማር’ መዋብ ማለት ነው፡፡ምግባር ማለት ገብረ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጕሙም ተግባር ክንውን ማለት ነው፡፡ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ማለት የክርስቲያን መልካም ሥራ ያማረ ተግባር የተዋበ ክንውን ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና አዳኝነት ያመነ ሰው የሚሠራው መልካም/ያማረ ተግባር ማለት ነው፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሕገ ልቦና
ሕገ ልቦና ማለት እግዚአብሔር አምላክ በልቦናቸው ሕግ እየደነገገላቸው ምንም የተጻፈ ሕግ ያልኖራቸው ወይም በቃል ሳይነግሯቸው መልካም የሆነውን በልቦናቸው አውቀው የሚሠሩት ሕግ ነው፡፡
ይህ ሕግ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ያለው 2256 ድረስ ነው፡፡ በሕገ ልቦና የነበሩ አባቶች መልካም ሥራ ይሠሩ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡ ለምሳሌ ጻድቁ አብርሃም ከመልካም ሥራዎቹን ውስጥ ቤቱ እንግዶችን እየተቀበለ በፍጹም ትሕትና እግራቸው እያጠበ ምግብን መጠጡን እያቀረበ ያስተናግድ እንደ ነበር ተገልፃል፡፡ ‹‹ እግራችሁን የምትታጠቡበት ውኃ እስካመጣላችሁ ድረስ በዚህ ጥላ ሥር እርፍ በሉ . . . ጥቂት ምግብ ይምጣላችሁ እንዳስተናግዳቸሁ ፍቀድልኝ›› ዘፍ. 18፥4 ይህንንም ሥርዓት የአብርሀናም ዘውድ የነበረው ሎጥ እንደሚፈጸም ዘፍ. 19፥1 ስር ተገልፀዋል፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግብር በሕገ ኦሪት
ኦሪት ማለት የሱርስት ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ብርሃን ማለት ነው፡፡ ‹‹ ከዘመነ ኦሪት ከሙሴ ዘመን ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ጊዜ ድረስ የነበረ ሕግ ነው፡፡ ይህ ሕግ የተፃፈ ሕግ ሲሆን እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን ያስተላለፈው ሕግ ነው እግዚአብሔር ለምን ይህን ሕግ ሰጣቸው ቢሉ? እስራኤላውያን በአረማውያን መካከል በሚኖሩበት ጊዜ እንዲለይበት እንዲቀደሱበት እራሳቸውንም ልጆቻቸውንም ከኃጢአት እንዲታቀቡበት በጽድቅ ላይ ጽድቅ በትሩፋት ላይ ትሩፋት የሚያገኙበት እራሳቸውን ከአሕዛብ ይለዩበት ዘንድ የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ በዚህ ኦሪት መጽሐፍ ላይ እስራኤላውያን በማኅበራዊ አኗኗራቸው ጊዜ እንዲፈጽሙ ከተነገራቸው ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው፡፡
በአለባበሳቸው ዘዳ. 22፥5 ዘዳ. 22፥11-12 በአመጋገባቸው ዘዳ. 14፥3-21 የለቅሶ ልማድ ዘዳ. 14፥1-2
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሕገ ወንጌል
ወንጌል ማለት የምሥራች ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የምንመራበት ሕግ ነው፡፡ የሕገ ወንጌል መሥራች ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን ሥርዓቶች በሐዲስ ኪዳን ሥርዓቶች እየለወጠና እየፈጸመ በተግባር ያሳየን ያስተማረን አምላካችን ነው፡፡‹‹ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ›› በማለት በሁሉ እርሱን አብነት በማድረግ እንዲገባን የነገረን፡፡ ማቴ. 11፥29
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment