• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    ምሥጢረ ቁርባን

    ቁርባን የምንለው የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው፡፡ የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ የዘላለም ሕይወት ሊኾን የተሰጠ ነው፡፡ ሥጋውን ደሙን የተቀበለ የዘላለም ሕይወት አለው፡፡ (ዮሐ 6. 53-56) የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ በምን ምክንያት ይገኛል፤ የሚገኝበትስ በምን ቦታ ነው ቢባል መልስ በትምህርት ይሰጣል፡፡

    የክርስቶስ ሥጋውና ደሙ የሚገኝበት ቦታ በቤተ መቅደስ ነው፡፡ የሚገኝበትም በኅብስትና በወይን ነው፡፡ በኀብስትና በወይን መገኘቱም እንዲህ ነው፡፡ በቤተ መቅደስ ውስጥ መንበረ ታቦት አለ፣ ታቦቱ በመንበሩ ላይ ይኖራል፡፡ ጸሎተ ቅዳሴ በሚደረግበት ጊዜ ቄሱ (ቀዳሹ ቄስ) ኅብስት በጻህል፣ ወይኑን በጽዋዕ አድርጎ በታቦቱ ላይ ለእግዚአብሔር ያቀርበዋል፤ እግዚአብሔር እንዲባርከው እንዲቀድሰው ነው፡፡ በታቦቱ ላይ ያቀርብና “አሐዱ አብ ቅዱስ፣ አሐዱ ወልደ ቅዱስ፣ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ”ብሎ ሃይማኖትን ይመሰክራል፡፡ ሕዝቡም (ምእመናኑም)የቀሲሱን ቃል ተከትለው “በአማን አብ ቅዱስ፣ በአማን ወልድ ቅዱስ፣ በአማን ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” ብለዉ ሃይማኖት ይመሰክሩበታል፡፡ ከዚህ አያይዞ ሙሉ ጸሎተ ቅዳሴ ይደርስበታል (ይጸለይበታል)፡፡

    በጸሎተ ቅዳሴው ውስጥ ቡራኬ የሚደረግበት ጸሎት አለ፣ ቄሱ እንደ ሥርዓቱ እየጸለየ በኅብስትና በወይኑ ላይ ቡራኬ ያደርጋል፣ ጸሎተ ቅዳሴውንም ሲጸልይ “አቤቱ ወደዚህ ኅብስትና ወደዚህ ወይን መንፈስ ቅዱስንና ኃይልን እንድትልክ እንለምንኃለን፣ የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን ያደርገው ዘንድ” የሚለዉን ጸሎት እየጸለየ ቀዳሹ ሕብስቱንና ወይኑን ይባርካል፣ ይህን ጊዜ (ይህን የሚጸለይበት ጊዜ) በመንፈስ ቅዱስ ኃይል (በመንፈስ ቅዱስ ሥራ)ኅብስቱ የክርስቶስ ሥጋ፣ ወይኑ የክርስቶስ ደም ይሆናል፡፡ ይህም ጸሎት ይረስዮ ይባላል፡፡ (ኅብስቱንና ወይኑን የክርስቶስ ሥጋውንና ደሙን ያድርገው ማለት ነው)፡፡ ይህም በቅዳሴ ሐዋርያትና በቅዳሴ እግዚእ ነው ያለው፣ በሌሎቹ ቅዳሴዎችም ይህን የመሰለ ጸሎት አለ፣ ከዚህ ቀጥሎ አያይዞ ቄሱ እየመራ፣ ሕዝቡ እየተከተለ “ሀበነ ንኀበር በዘዚአከ መንፈስ ቅዱስ ወፈውሰነ በዝንቱ ጵርስፎራ…” እያሉ ይጸልዩበታል፡፡ቀጥሎ ጸሎተ ፈትቶ (እየቈረሱ የሚጸለይ) አለ፣ ቄሱ ያን እየጸለየ እንደ ሥርዓቱ ሥጋውን ይቈርሰዋል፡፡ ፍታቴውን ሲፈጽም ቄሱ እየመራ ሕዝቡ እየተቀበሉ አርባ አንድ ጊዜ እግዚኦታ (እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ) ያደርሱበታል፡፡ ቀጥሎ ቄሱ “አአምን፣ አአምን፣ አአምን፣ ወእትአመን …እያለ ሥጋውን በደሙ”“ቡሩክ እግዚአብሔር አብ…ወብሩክ ወልድ ዋሕድ…ወቡሩክ መንፈስ ቅዱስ…”እያለ ደሙን በሥጋው ሦስት፣ ሦስት፣ ጊዜ ይባርከዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በቅድሚያ ቀዳሾች ካህናት፣ ቀጥሎ ሕዝቡ በቄሱ እጅ እንቈርበዋለን (እንቀበለዋለን)፡፡

    ደሙን በጣት ለማቀበል ስለማይቻል በዕርፈ መስቀል እንቀበለዋለን፡፡ ማቀበያው በዕርፈ መስቀል ስለኾነ ደሙ በዲያቆኑ እጅ እንዲሰጥ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ያዝዛል፡፡ የምንቀበለውም ሥጋውና ደሙ በዕለተ ዓርብ (የስቅለት ዕለት) ነፍስ የተለየው መለኮት ያለተለየው ነው፡፡ ነፍስ የተለየው መለኮት የተዋሐደው ነው ብንልም ይኾናል፡፡ቁርባንን በኅብስትና በወይን ማቅረብ የጀመረ ማን ነው?ወይም ቁርባን በኅብስትና በወይን እንዲቀርብ ያዘዘ ማን ነው? ብንልመልሱ ለመጀመርያ ቁርባንን በኅብስትና በወይን ምክንያት የሰጠ፣ ቁርባን በኅብስትና በወይን እንዲቀርብ ያዘዘ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

    ትምህርቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በትምህርቱ ዘመናት ሲያስተምር፡- “ከሰማይ የወረደ ሕያው ኅብስት /እንጀራ/እኔ ነኝ ከዚህ እንጀራ የሚበላ ለዘላለም ሕያው ይኾናል፣ ለዘላለም ሕይወት እኔ የምሰጠውም እንጀራ ሥጋዬ ነው፡፡ ”ሥጋዬን የበላ ደሜን የጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው፣ እኔም በመጨረሻ ዕለት አስነሳዋለኹ፡፡ ሥጋዬ እዉነተኛ የጽድቅ መብል ነውና ደሜም እዉነተኛ የጽድቅ መብል ነውና ደሜም እውነተኛ የሕይወት መጠጥ ነውና፣ ሥጋዬን የበላ፣ ደሜን የጠጣ በእኔ ይኖራል፣ እኔም በእርሱ እኖራለሁ ሲል አስተምሯል፡፡ ይህን ትምህርት በወንጌል ዮሐንስ እናገኘዋለን፡፡ (ዮሐ6.51 እና ቁጥር54-56)

    ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ትምህርቱን አስተምሮ ሲፈጽም ለመድኃኒተ ዓለም ዓርብ ዕለት ሊሰቀል ሐሙስ ማታ ከመያዙ በፊት ባንድ በደገኛ ሰው ቤት ልዩ አዳራሽ ተዘጋጅቶለት ገብቶ ለእራት ተገኘ፡፡ በዚያ ተገኝቶ በኦሪቱ ሕግ ለደቀ መዛሙርቱ የፋሲካን መሥዋዕት አደረገ (ሉቃ.22.7-18)፡፡ በዚያን ጊዜ ለፋሲካ ካቀረበው አንዱን ኅብስት አንስቶ ያዘና ጸለየ፣ ጸለያና ባርኮ ቈርሶ “እንኩ ብሉ ይህ ስለ እናንተ የሚሰጥ ሥጋዬ ነው” ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፡፡ እንዲሁም ወይኑን በጽዋ ይዞ ጸልዮ ባርኮ “እንኩ ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፣ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ እና ስለብዙ ሰዎች ለኃጢአት ሥርየት የሚፈስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው”ብሎ ሰጣቸው፣ ሰጣቸውና መታሰቢያዬን እንዲህ አድርጉ ብሏቸዋል፡፡ ይህንን ትምህርት በወንጌል ተጽፎ እናገኘዋለን (ማቴ.26.26-27፤ ማር 14.22-24፤ ሉቃ.24.19-20)፡፡ ደቀመዛሙርቱም (ሐዋርያትም) ጌታ ባሳያቸውና “መታሰቢያዬን እንዲህ አድርጉ” ብሎ ባዘዛቸው መሠረት ብሎ ባስተማሩበት ቦታ ሁሉ ቁርባንን በኅብስትና በወይን ያቀርቡ ነበር፡፡ ለዚህም (1ኛቆሮ 10.16ና ምዕ. 11.23-26) ተመልከቱ፡፡

    ሐዋርያት ለቤተ ክርስቱያንም ቁርባን በኅብስትና በወይን እንዲሆን በሲኖዶሳቸው አስተላልፈዋል፡፡ ጥቅስ “ወኢያዕርጉ ላዕለ ምሥዋዕ ዘእንበለ ኀብስተ ሰርናይ ንጹህ ወማየ ወይን ንጹህ”ማለት “ከንጹህ ከስንዴ ኀብስትና ከንጹህ ከወይን ውኃ በቀር ሌላአያቅርቡ በመሥዋዕት ላይ” ፍትሕ መንፈሳዊ ጴጥ ረሰጠጅ (ጴጥ ማለት ጴጥሮስ አለ፣ ለማለት ነው፣ “ረሰጠጁ” ሦስተኛ ሲኖዶስ ለማለት ነው)፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን ቁርባን በኀብስትና በወይን መቅረቡ ትምህርቱን ከዚህ በላይ እንደወሰነው ጌታ ባደረገው፣ መታሰቢያዬን እንዲህ አድርጉ ባለው እና በሐዋርያት ትምህርት መሠረት ነው፡፡ ስለ ቁርባን ከሃይማኖተ አበውም እንጠቅሳለን፡፡ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ አትናቴዎስ ስለ ቁርባን እምነት የተናገረው እንዲህ ይለል፡፡“ደግሞ እናምናለን በቅዱስ ቁርባን፣ ሕይወት የሚሆን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንደሆነ፣ ይኸውም ካህኑ ሳይቀድሰው (ሳያከብረው)ኀብስትና ወይን የነበረ፣ ካህን ሲቀድሰው ግን መንፈስ እላዩ ላይ ይወርዳል፣ ኅብስትም ከመሆን የእግዚአብሔር ልጅ የአካላዊ ቃል እውነተኛ ሥጋ ወደ መሆን ይለወጣል፣ እንዲሁም በጽዋ ያለው ወይንም ከወይንነት የወልደ እግዚአብሔር የአምላክ ደም ወደ መሆን ይለወጣል ከሥጋው ጋር ሲዋሐድ ባለበት እያለ”ብሏል፡፡ ሃይማኖተ አበው ድርሳን ዘአትናቴዎስ ክፍል 16፡ ምዕ. 28፣ ገጽ. 87 ተመልከቱ፡፡

    ኀብስቱና ወይኑ የክርስቶስ ሥጋና ደም ሲሆን ተመሳሳይ ሁኔታ የለውም፡፡ ለቁርባን በመንበረ ታቦት ላይ የሚቀርበው ኀብስትና ወይን የክርስቶስ የወልደ እግዚአብሔር ሥጋና ደም ሲሆን፣ በአኳኋኑ ተለውጣ ጨው እንደሆነች እንደ ብእሲተ ሎጥ እና ተለውጦ ደም እንደሆነ እንደ ማየ ግብጽ አኳኋን እይታይም፣ እንደዚሁም ተለውጦ ወይን እንደ ሆነ እንደ ማየ ቃና አኳኋን አይታይም፣ በእነዚያ ኹኔታ አይመስልም፣ ከእነዚያ ሁኔታ ጋር አይነጻጸርም፣ (ዘፍ 10.17እና 26፤ ዘዳ.7.17-21፣ ዮሐ.2.7-10)፡፡ ለቁርባን የሚሆነው ኀብስትና ወይን የሚዘጋጅበት ቦታ፡፡

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ለቁርባን የምናደርገው ኅብስት ወይንም በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ በሚገኘው ቤተልሔም በሚባለው ቤት ውስጥ በካህናት ተልእኮ ነው የሚዘጋጀው፣ በውጪ የተሠራ ግን ለቁርባን አይሆንም፡፡

    መደምደሚያ
    ስለ ቁርባን በአጭርና በግልጽ ቃላት የተዘጋጀው አጭር ትምህርት በዚህ አለቀ፡፡ ክብር ይሁን ለእግዝአብሔር

    ምንጭ ፈለገ ጥበብ 4ኛ ዓመት ቁጥር 10

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ምሥጢረ ቁርባን Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top