• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    በዓታ ለማርያም

    ታህሳስ 3 ቀን በዓታ ለማርያም ድንግል "ሰአሉ ወይትወሀበክሙ ለምኑ ይሰጣችሁማል ማቴ 7፡7"
    አባ ሳሙኤል ወ/ሐዋርያት

    ኢያቄም እና ሐና አንድ ወንድ አንድ ሴት በሚለው በተከበረው ጋብቻ የጸኑ በሀገራቸው የተከበሩ፤ በመልካም ሥነ ምግባር የታወቁ ሰዎች ነበሩ በእግዚአብሔር ፊትም እውነተኞች ነበሩ ትእዛዙም ሁሉ ይፈጽሙ ነበር ይሁን እንጂ በዚህ በተከበረ ጋብቻ ጸንተውና ተወስነው እያሉ ነገር ግን እንደሌሎች ሰዎች ወልደው የሚሰሙት አይቶው የሚደሰቱበት ልጅ ባለማግኘታቸው እጅግ ያዝኑና ይተክዙ ነበር፡፡ በጾምና በጸሎት እግዚአብሔርንም ይጠይቁ ነበር፡፡ ስዕለትም ይሳሉ ነበር ስዕለታቸውም ወንድ ልጅ ብንወልድ እርሱ ወጥቶ ወርዶ ያበላናል አንልም ያንተ ቤት ቤተ እግዚአብሔር ያገለግላል እንጂ ሴትም ብትሆን ጋግራ ታብላን ፊትላ ታልብሰን አንልም ሀርና ወርቅ እየፈተለች መሶበ ወርቅ እየሰፋች ቤተክርሲያን ታገለግላለች እንጂ ብለው ተሳሉ፡፡

    የለመኑትን የማይነሳ የነገሩትን የማይረሳ እግዚአብሔር ልመናቸውን ሰምቶ እጅግ የምታስደስት እና ልዩ የሆነች ልጅ አገኙ፡፡ ሌሎች ሰዎች ቢወልዱ ሰው የሚወልዱ ልጆች ነው፡፡ እነሱ ግን የወለዱት ፈጣሪዋን የምትወልድ ልጅ ነው፡፡ የወለዱት በስዕለታቸው መሠረት በ3 ዓመቷ ገና አይተው ሳይጠግቧት ይህች ልጅ አንድ ነገር ብትሆን ከእግዚአብሔርም ከልጃችንም ሳይሆን እንዳንቀር ሆዷ ዘመድ ሳይወድ አፏ እህል ሳይለምድ ወስደን እንስጥ ብለው መባዕ ጨምረው ወደ ቤተ መቅደስ ይዘዋት ሄዱ፡፡

    ሊቀ ካህናቱ ዘካርያስ መጥቶ ሕዝቡን ሰብስቦ የምግቧ ነገር ይያዝልኝ አለ፡፡ ወዲያው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ ይዞ ረቦ ታየ፡፡ ቅዱስ ዘካርያስ ለእርሱ የመጣ መስሎት ዛሬስ ክብሬን በሰው ፊት ሊገልጸው ነው ብሎ ሊቀበል ተነሣ፡፡ መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ወደ ላይ ራቀበት የእርሱ ተወራጅ ስምዖንም እንኪያስ ለኔ የመጣ ይሆናል ብሎ ቀረበ ራቀበት ካህናቱም ሕዝቡም በተራ ቢቀርቡ ራቀባቸው፡፡ "ምናልባት ጥበበ እግዚአብሔር አይመረመርም ለዚህች ልጅ ብላቴና የመጣ እንደሆነ እንይ ቅድስት ሐና ትተሻት እልፍ በይ" አሏት ትታት እልፍ አለች ድክ ድክ እያለች እናቷን ስትከተል መልአኩ ቅዱስ ፋኑኤል ፈጥኖ ወርዶ አንድ ክንፍን አንጽፎ አንድ ክንፍ ጋርዶ በሰው ቁመት ልክ ከመሬት ከፍ አድርጎ መግቧት አረገ፡፡ የምግቧ ነገር ከተያዘልንማ ትግባ እንጂ ብለው ከመካነ ደናግል አስገቧት፡፡ "ከመዝ ነበርኪ ውስተ ቤተ መቅድስ ወመላእክት ወትረ ያመጽኡ ሲሳየኪ ከመዝ ነበርኪ ዐሰርተ ወክሊኤተ ዓመተ እንዘ ትትናዘዚ እምኅበ መላእክት" ይላል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕሰማያዊ እየተመገበች ቅዱሳን መላእክት እየጎበኟት አስራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ኖረች፡፡

    በስዕለት የተገኙ ቅዱሳን አባቶችና እናቶች እነ ቅድስት ሐና እመ ሳሙኤል የታላቁ ነቢይ ሳሙኤል እናትና አባቱ ሕልቃና ይባላል የእነ ቅዱስ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ የቅዱስ ኢያቄምና ሐና ለዚህ ነው መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ይፈራል የተባለው ቀደም ብሎ በብሉይ ኪዳን የተነገረ ነው "አቡየ ፈነወኒ አነ ተፈነውኩ" የወይን አትክልት የተከለ ባለ ቤት ሰው ነበረ ቅጥርም ቀጠረለት መጥመቅያም ማሰለት ግንብም ሠራና ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ የሚያፈራበትም ጊዜ ሲቀርብ ፍሬውን ሊቀበሉ ባርያቹ ወደ ገበሬዎች ላከ ባሮቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት አንዱንም ገደሉት ሌላውን ወገሩት ደግሞ ከፊተኞች የሚበዙ ሌሎች ባሮችን ላከ እንዲሁም አደረጉባቸው በኋላ ግን ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ ልጁን ላከባቸው፡፡ ገበሬዎቹ ግን ልጁን ባዩ ጊዜ እርስ በርሳቸው ወራሹ ይህ ነው ኑ እንግደለውና ርስቱን እናግኝ ተባባሉ ይዘውም ከወይኑ አትክልት አወጡና ገደሉት የመጀመርያዎቹ ባሮያዎች ዓበይር ነቢያት ናቸው እነሱም ኢሳያስ ኤርምያስ ሕዝቅኤል ዳንኤል ናቸው፡፡ ከእነርሱ የሚበዙ የተባሉ ደቂቀ ነቢያት ናቸው ኢዮኤል ዮናስ አምፅ ሆሴዕ ሚክያስ ናሆም ሶፎንያስ ዕንባቆም አብድዩ ሐጌ ዘካርያስ ሚልክያስ ልጅ የተባለ አቡየ ፈነወኒ አነ ተፈነውኩ ላኪ እግዚአብሔር አብ ነው ተላኪ እግዚአብሔር ወልድ ነው፡፡ ዓበይት ነቢያትና ደቂቀ ነቢያት የተደበደቡ በአሕዛብ በእነ ፊርዖንና ናቡኪዶነፆር አስራውያን ተገርፈዋል ታስረዋል ተሰደዋል፡፡ ልጁም በፈሪሳውያን በሰዱቃውያን መጸብሐን ጸሐፍት ካህናት መገብተ ምኩራብ መላሕቅተ ህዝብ ረበናት ተማካክረው ሰቀሉት ገደሉት ስለዚህ ከመልካም ዛፍ የተገኙ ዓበይት ነቢያት ደቂቀ ነቢያት ሐዋርያት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ቃሉን የጠበቁ ሕጉን የጠበቁ ፈጣሪያቸውን የተከተሉ በንስሐ የታጠቡ ሁሉ እግዚአብሔር የመረጣቸው የመልካሚቷ ዛፍ ፍሬዎች ናቸው፡፡

    እኛን ስለወደደን ካለመንኖር ወደ መንኖር አምጥቶ የፈጠረን አንድነቱን ሦስትነቱን ካለማወቅ ወደ ማወቅ ካለመሰማት ወደ መሰማት ካለመማር ወደ መማር ፈጥሮ ሳያጠፋን በከሃሊነቱ ችሎ ታግሶ እድሜ ሰጥቶ ያቆየን እግዚእትነ ማርያም እመቤታችን ከመከራ ሥራ ከመከራ ነፍስ የምታድነን እመቤታችንን ከማኅፀነ ሐና ፈጥሮ ከአንስት አለም መርጦ ከሁሉ አልቆ የእናት አማላጅ የሰጠን እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን አሜን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በዓታ ለማርያም Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top