• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday, 11 November 2015

    ምሥጢረ ተክሊል ምዕራፍ ፩


               ክፍል አንድ (1)

    በዚህ ክፍል አንድ ትምህርታችን ምሥጢረ ተክሊል ምንድን ነው? የሚለውን ከብዙ በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡ 

    1. ምሥጢረ ተክሊል ምንድን ነው?
    ቤተክርስቲያን የክርስቲያን ቤት ናት ፤ጥበብ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤በሰባቱ ምሶሶዎቿ ቤቷን አንጻለች፡፡ እነዚህ ምሶሶዎች ደግሞ የምድር ሥርዓት እስከ ሚጠናቀቅበት ድረስ የማይናዱ፤ የማይፈርሱ፤የማይለወጡ፤የማይሻሩ እና አላፊ ያልሆኑ ዘላለማዊ እና ሰማያዊ ጸጋዎችን የሚያሰጡ በሚታይ ነገር ፤ የማይታይን ሀብት ለሁላችን እንድንካፈል የሚያደርጉ ቤተክርስቲያንን በምሶሶነት የሚደግፉ ምሥጢራት ቤተክርስቲያን ናቸው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ ሲል እግዚአብሔር ስላዘጋጀልን ምሥጢራት ይገልጣል፡-" ጥበብ ቤትዋን ሠራች፤ሰባቱንም ምሶሶችዋን አቆመች፡፡ ፍሪዳዋን አረደች፤የወይን ጠጅዋን ደባለቀች፡፡" ምሳ 9፡1

    ወዳጆቼ ሁላችን እንደምናውቀው በምሶሶ የተመሰሉት ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን፡-
    1. ምሥጢረ ጥምቀት
    2. ምሥጢረ ቁርባን
    3. ምሥጢረ ሜሮን
    4. ምሥጢረ ንስሐ
    5. ምሥጢረ ክህነት
    6. ምሥጢረ ተክሊል
    7. ምሥጢረ ቀንዲል ናቸው፡፡ 

    እነዚህ ለቤተክርስቲያን ምሶሶዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ምሶሶዎች መካከል ደግሞ ዛሬ የምንማማረው ምሥጢረ ተክሊል ነው፡፡ ምሥጢር መባላቸው፡-
    1. ለሚያምን ብቻ የሚፈጸሙ ምሥጢራት በመሆናቸው ነው፡፡
    2. በሚታየው ነገር የማይታየውን ሀብተ መንፈስ ቅዱስን የሚያሰጡ በመሆናቸው ነው፡፡

    ተክሊል ማለት ከለለ ፤ አከበረ ካለው ግሥ የወጣ ሲሆን ትርጉሙ ክብር ማለት ነው፤ ቅዱስ ጳውሎስ ፡- "ሴት ግን የወንድ ክብር ናት" እንዳለ፡፡ 1ቆሮ11፡7 ወንድ እንዲህ የተመሰከረላትን ረዳቱን በቃል ኪዳን/በማይፈርስ ውል/ የሚቀበልበት በመሆኑ የተክሊል ጋብቻ የከበረ ነው፡፡ ሌላው ይኸው ሐዋርያ ፡-"መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ሴሰኞችና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡" እንዳለ፡፡ዕብ13፡4 በእግዚአብሔር ስለሚቀደስና ስለሚከብር የተክሊል ጋብቻ ክቡር ነው፡፡

    ወዳጆቼ ምሥጢረ ተክሊል ማለት አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር በማይመረመር የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አንድ የሚሆኑበት ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ገና በሥነ ፍጥረቱ የአፈጣጠር ሥርዓት የተማርነው ሕያው እውነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ብቻ መፍጠሩ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት አንድ ወንድ ለአንዲት ሴት፤አንዲት ሴት ለአንድ ወንድ ብቻ መሆን እንዲገባቸው ሲያመለክተን ነው፡፡ ለምሳሌ ሙሴ በጻፈልን መጽሐፍ ፡- "ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን የተዋል፤በሚስቱም ይጣበቃል" አለ እንጂ በሚስቶቹ ይጣበቃል አላለም፡፡ ይህ ምሥጢረ ተክሊል አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ብቻ (ጋብቻ) የሚያድርጉት ምሥጢር ነው፡፡
    ወዳጆቼ ጋብቻን በሁለት ዓይነት መልኩ ልንፈጽም እንችላለን 1ኛ. አግዚአብሔር ረድቶን ድንግልናችንን ጠብቀን ከተገኘን ከመጽሐፈ ተክሊል ጸሎት ተደግሞልን ቃልኪዳን ገብተን፤ ሁሉ ይህን ሕይወታችንን(ክብራችንን) አይቶ እንዲናፍቅ እና በድንግልና ጸንቶ ለዚህ ክብር እንዲበቃ ቤተክርስቲያን በደስታ ይገባችኋል ብላ ሥርዓቱን በመፈጸም አክሊልን ታቀዳጃቸዋለች፡፡ 2ኛ. በልዩ ልዩ ምክንያት ድንግልናችንን ሳንጠብቅ ብንገኝ ደግሞ ቤተክርስቲያን ቃልኪዳን ገብተን በሥርዓተ ቁርባን በመፈጸም ካባውን ብቻ አድርገን አክሊሉን ባለማድረግ ጋብቻችንን እግዚአብሔር እንዲባርክልን አደራ በመስጠት ከዚህ ምሥጢር እንድንካፈል ታደርገናለች፡፡ በሥርዓተ ተክሊል ለማግባት መስፈርቱ ምንድን ነው?...ይቀጥላል ይቆየን

                ክፍል ሁለት(2)

    ወዳጆቼ ስለ ምሥጢረ ተክሊል ትርጉም እና ምሥጢራዊነቱን በክፍል አንድ ትምህርታችን ተመልክተናል፡፡ እግዚአብሔር ቢፈቅድ የጋብቻ ሦስቱ ዓላማዎችን እና በዚህ ዙሪያ የተጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች እንዲሁም አስተምሮዎች ከብዙ በጥቂቱ እርሱ እንደፈቀደ እናያለን እግዚአብሔር ምሥጢሩን እንዲገልጥልን የተቀደሰ ፍቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን

    2. የጋብቻ ዓላማ ምንድን ነው?

    2.1. ለመረዳዳት ነው፡፡ አዳም ለእንሰሳት ሁሉ ስም ያወጣ፤ በምድር እንሰሳትም ላይ ስልጣን ያለው ሰው ነበር፤አስቀድሞ እግዚአብሔር ለአዳም ረዳት እንደሚያስፈልገው ስላወቀ "...ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት፡፡" ዘፍ2፡18 አለ፡፡ ምክንያቱም " አዳም እንደ እርሱ ረዳት አልተገኘለትም ነበርና፡፡" ዘፍ2፡21 አዳም እግዚአብሔር በጥበቡ ከጎኑ አጥንት የሰራትን ሴት ሲያመጣለት በጣም በመደሰት "ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ናት ፤ሥጋም ከሥጋዬ ናት እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል፡፡" ዘፍ2፡23 ሴት ምትክ ናትና፡፡
    ይህ ብቻ አይደለም ሰው በመጀመሪያ የሚያውቀው እናትና አባቱን እንደመሆኑ የሚረዳውም እነርሱን ነው፤ይሁንና እነርሱን ትቶ ከሚስቱ ጋር እንደሚረዳዳ አንድ አካል አንድ መንፈስ አንድ ልብ እንደሚሆን ምክንያት የሚሆነው በሥጋ ብቻ ሳይሀን በመንፈስም ጭምር ትስስር ስላለው ነው፡፡ ይኸውም በሥጋ ሴት ከወንድ ተገኝታለች፤ በመንፈስ ደግሞ አንድ ናቸው፡፡ እንዲህ በማለት ሊቀ ነብያት ሙሴ ያረጋግጥልናል፡-"...ስለዚህ ሰው አባቱን እና እናቱና ይተዋል፤በሚስቱም ይጣበቃል፤ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፡፡" ዘፍ 2፡24

    ወዳጆቼ መረዳዳት ስንል ከሁለት በኩል የሚፈስ መልካምነትን ነው፡፡ ይኸውም ስለ ጋብቻ ሕግ እና ሥርዓት የሚነግረን መጽሐፈ ተክሊል እንዲህ ሲል ያመጣዋል፡- "ወንድ ለሚስቱ የሚገባትን ሁሉ መጠበቅ፤ማድረግ ይገበዋል፤ሴትም ለባሏ የሚገባውን መጠበቅ፤ማድረግ ይገባታል፡፡ ትእዛዝ፤ለሴት ባሏ የሚገባውን ያድርግላት፤እንደዚሁም ሴት ለባሏ የሚገባውን ታድርግለት(1ቆሮ7፡3)" (መ.ተክሊል.ገጽ 73)

    ወዳጆቼ እርስ በእርስ ሊተዛዘዙ የተገባ ነው፡፡ እርሱም እርሷን ፤እርሷም እርሱን እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ በሆነ ነገር ሁሉ ሊያዙ ሥልጣን እግዚአብሔር ለሁለቱም ሰጥቷቸዋል፡፡ የግል ሥልጣን ማለትም በእየግላቸው ግን ሥልጣን የላቸውም፡፡ "ሴት ባሏ ያዘዛትን ልትፈጽም እንጂ በባሏ ላይ የሌለ ትእዛዝ ፈጻሚ ልትሆን የወደደችሁን ልታደርግ በራሷ ሥልጣን የላትም፤በእሷ ላይ ሥልጣን ያለው ባሏ ብቻ ነው፤ እንዲሁም ወንድ ሚስቱ ላይ የሌላይቱ ታዛዥ ሊሆን፤የሌላይቱን ፍቃድ ሊፈጽም በራሱ የማዘዝ ሥልጣን የለውም፡፡ በእሱ ላይ ሥልጣን ያላት የምታዝዝበት ሚስቱ ናት፡፡ ትእዛዝ፤ ሴት በራሷ ሥልጣን የላትም፤ሥልጣን ለባሏ ነው እንጂ፤ እንደዚሁም ወንድ በራሱ ሥልጣን የለውም ፤ሥልጣን ለሚስቱ ነው እንጂ 1ቆሮ7፡4" (መ.ተክሊል.ገጽ 74) 

    2.2. ዘርን ለመተካት ነው፡፡ "...እግዚአብሔርም ባረካቸው እንዲህም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ግዙአትም..."ይህ አምላካዊ ትህዛዝን እርሱ በፈቀደው መልኩ ለመፈጸም የምንጠቀምበት መንገድ ቅደስ ጋብቻ ነው፡፡ ዘፍ1፡27

    2.3. ከዝሙት ለመራቅ ነው፡፡ ይህ ሲባል ጋብቻን ለዝሙት እንጠቀምበታለን ለማለት ሳይሆን ቅዱሱን ጋብቻ ባለመፈጸማችን ከሚመጣብን የዲያብሎስ የዝሙት ጾር ለመዳን ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ "ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንጹሕ ይሁን" ዕብ13፡4 ያለው በቤተክርስቲያን በካህናት ፀሎት በእግዚአብሔር የተቀደሰውን ጋብቻ እስከመጨረሻው በንጽህና መጠበቅ እንደሚገባን ለማስተማር መሆኑ የታመነ ነው፡፡ 
    ወዳጆቼ ግልጽ በሆነ የምርጫ ሕይወት እንዳለንና ነገር ግን ከዝሙት እሳት ለመዳን ቅዱስ ጋብቻ ምርጫ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ያመጣዋል፡-" ስለ ጻፋችሁልኝ ነገር፤ከሴት ጋር አለመገኛኘት ለሰው መልካም ነው፡፡ ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት፡፡"1ቆሮ 7፡2 

    ወዳጆቼ ይህ ታላቅ እና ክቡር ጋብቻ መቼ እና ማን መሰረተው ለሚለው ጥያቄ አስራት ገብረማርያም ሲመልሱ፡- "እግዚአብሔር የጋብቻን ምሥጢር የመሰረተው ገና የሰው ልጅ በዔደን በነበረ ጊዜ ነው፡፡ "እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤እግዚአብሔርም ባረካቸው እንዲህም አላቸው ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሉአት ግዙአትም... እግዚአብሔር አምላክም ከአዳም የወሰዳትን አጥንት ሴት አድርጎ ሠራት ወደ አዳምም አመጣት አዳምም እንዲህ አለ፤ ይህቺ አጥንት ከአጥንቴ ናት ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል፡፡ ስለዚህ ሰው አባቱን እና እናቱን ይተዋል፤ በሚስቱም ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ይሆናሉ" ዘፍ 1፡27-28፤ 2፡18-24"
    ይህንኑ አባባል ነው መድኃኒታችን "እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለየው ሲል ያጸደቀው (ማቴ19፡6) ጌታችንም የጋብቻን ተዋሕዶ በቃሉ ብቻ ያስተማረው ሳይሆን በቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ ተገኝቶ ባርኮታል፤ቀድሶታል፡፡ ስለዚህ ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ጋብቻ በሁሉም ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹህ ይሁን" ያለው፡፡ (ዕብ 13፡4) (ትምህርተ መለኮት ገጽ200-201) 

    ወዳጆቼ ምሥጢረ ተክሊል እግዚአብሔር የሰጠውን ትሕዛዝ በሕጋዊ መልኩ የምንፈጽምበት ምስጢር ስለመሆኑ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን "ምሥጢረ ተክሊል ሁለት የተለያየ ጾታ ያላቸውን ሰዎች አንድ በማድረግ ፈጣሪ"ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት"ዘፍ1፡28 ሲል የሰጠውን ፈቃድና ቡራኬ በሕጋዊ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈጸም ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ምሥጢር የሚፈጸመው በካህን ሲሆን ሥርዓቱ ሊፈጸም የሚችለውም ለመጀመሪያ ጋብቻ ብቻ ነው፡፡" በማለት ገልጸዋል፡፡ (መድብለ ትምህርት ኦርቶዶክሳዊ ገጽ 21)
    ወዳጆቼ ምሥጢረ ተክሊል የማይመረመር የእግዚአብሔር መንፈስ ሁለቱን አንድ የሚያደርግበት ምስጢር መሆኑን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፡- "ምሥጢረ ተክሊል ማለት አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር በማይመረመር የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ አንድ የሚሆኑበት ምሥጢር ነው፡፡

    ሀ. ጌታችን በቃና ዘገሊላ በጋብቻ ጊዜ በመገኘት በገነት ፈርሶ የነበረውን ጋብቻ እንደ ገና ባርኮታል፡፡(ዮሐ2፡1-10)"

    ለ.ማቴ19፡14 ፈጣሪ በመጀመሪያ ወንድ እና ሴት አደረጋቸው፡፡ አለም፡-ስለዚህ ሰው እናት እና አባቱን ይተዋል፤ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ስጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን? ስለዚህ አንድ ስጋ ናቸው እንጂ ወደፊት ሁለት አይደሉም፤ እግዚአብሔር ያጣመረውን እንግዲህ ሰው አይለየው"በማለት አስተምሯል፡፡

    ሐ.ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም "ጋብቻ ቅዱስ መኝታውም ንፁሕ ይሁን" ብሎ አስተምሯል፡፡ በማለት ገልጾታል፡፡ (ዕብ13፡4) (ኦርቶዶክስ መልስ አላት ገጽ 20-21)

    ወዳጆቼ ያለ ድንግልና ተክሊል ማድረግ እንደማይገባ ዲያቆን ኅብረት የሺጥላ በንጽጽር ሲገልጥ "ድንጋሌ ሥጋ ላላቸው ሰዎች በጋብቻቸው ጊዜ የሚደረግላቸው ጸሎት ለመዓስባን(ድንግል ላልሆኑ) ሰዎች ከሚደረገው ይለያል፡፡ በሥርዓተ ቤተክርስቲያን ቀኖና መሠረት አንድ ሰው ድንግልናውን ጠብቆ ለመኖር ከተሳለ በኋላ እንደ ገና ወደ ማግባት ቢመለስ ጋብቻው ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚያገባ ሰው ተቆጥሮ ሥርዓተ ተክሊል አይፈጸምለትም፡፡ (ፍት.ነገ.አን.24) ይህ ሰው ንጽሐ ሥጋውን ሳያጠፋ ስእለት ተስሎ ስላፈረሰ ብቻ ክብረ ተክሊል ከቀረበት ንጽሐ ሥጋውን ሳያጠፋ ስእለት ተስሎ ስላፈረሰ ብቻ ክብረ ተክሊል ከቀረበት ንጽሐ ሥጋውን ያፈረሰ ሰው እንዴት ይልቅ ተክሊል ከማድረግ አይከለከልም?" (ሕይወተ ወራዙት (የወጣቶች ሕይወት) ክፍል አንድ ገጽ152-153)
    ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን በተመለከተ በማጠቃለያ ትምህርቱ ላይ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ እንዲህ ብሏል፡-" በአጠቃላይ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ቤዛነት የተገኙት የመዳን ጸጋዎች ተጠብቀው የሚገኙባቸውና እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ለሚነሡ ሰዎች የሚሰጡባቸው መንገዶች ናቸው፡፡ ለስም አጠራሩ ለአምላክነት ክብሩ ምስጋና ይግባውና መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን መዳን እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ለሚነሳው ለእያንዳንዱ ሰው የሚደርስለትና የሚፈጸምለት በምሥጢረተ ቤተክርስቲያን አማካኝነት ነው፡፡ 

    ጌታችን ራሱን በእረኛ መስሎ ባስተማረበት ትምህርት "በሩ እኔ ነኝ፤በእኔ የሚገባ ቢኖር ይድናል ይገባልም ይወጣልም፤ መሰማሪያም ያገኛል" ሲል የተናገረው ምሥጢረተ ቤተክርስቲያንን እንደሚመለከት መምህራነ ወንጌል ገልጸዋ፡፡ዮሐ10፡9 "በእኔ ይገባል" ማለት በምሥጢራት አማካኝነት ወደ መዳን ወደ እርሱ (ወደ ክርስቶስ) አንድነት ይገባል ማለት ነው፡፡ በጥምቀት በሜሮን፤በቁርባን አማካኝነት ወደ መዳን ፤ወደ ሕይወት ይገባል፡፡ "ይገባልም ይወጣልም" ማለትም ከዚህ ዓለም ሕይወት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት የሚሄደው በእነዚህ ምሥጢራተ አማካኝነት ነው፡፡(መድሎተ ጽድቅ (የእውነት ሚዛን) ገጽ 178-179)

    ጋብቻ በእግዚአብሔር የተገነባ ትልቅ የሕይወት ተቋም እና የትውልድ ምንጭ መሆኑን ዲ.በሪሁን ወንደሰን ሲገልጽ፡- "ጋብቻ ሰው ሰራሽ ያልሆነ በእግዚአብሔር የተገነባ ትልቅ የሕይወት ተቋም ነው፡፡ ሀገር ቤተክርስቲያን ቤተሰብና በዓለም ውስጥ ያለ እያንዳንዱ መንፈሳዊም ይሁን ማህበራዊ ተቋም የተመሰረተው በጋብቻ ላይ ነው፡፡ ጋብቻ ባይኖር በሰው ልጅ ታሪክ ምንም አዲስ ነገር አይፈጠርም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ጋብቻን የተውልድ ምንጭ እንዲሆን አስቀድሞ ከወሰነ በኋላ ለአዳምና ለሔዋን ባርኮ ሰጣቸው፡፡ (ጋብቻዬን ከማን ጋር ልፈጽም? ገጽ5)...ይቆየን ይቀጥላል


                 ክፍል ሦስት

    ጌታችን እየረዳን በክፍል አንድ ምሥጢረ ተክሊል ምንድን ነው? በክፍል ሁለት ደግሞ የጋብቻ ዓላማ ምንድን ነው? ስለ ምሥጢረ ተክሊል በልዩ ልዩ መምህራን የተጻፉ ከሰባት ያላነሱ መጻሕፍትን በመዳሰስ ጥቂት ትምህርቶችን ቃርመናል፤ ዛሬም እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ በክፍል ሦስት ትምህርታችን ቅድመ ጋብቻን ከብዙ በጥቂቱ እንማማራለን፤ እግዚአብሔር አምላካችን በከንቱ በፌስ ቡክ ላይ ከምናባክነው ጊዜያችን ላይ በጎንውን ብቻ ለማየት፤ ለመስማት፤ ለማንበብና ለመረዳት ባገኘናት ፍንጭ ደግሞ ለሌሎች የምናስተምር እንደ ቤሪያ ሰዎች ልበ ሰፊዎች እንዲያደርገን ቅዱስ ፍቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን

    ወዳጆቼ ምሥጢረ ተክሊል የፍቃደኝነት ማረጋገጫ ምሥክርነት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ምክንያቱም በተክሊል የተጋቡትን ቤተክርስቲያን ሕጋዊ ጋብቻ ብላ በይፋ ትመሰክርላቸዋለችና፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ታላቁን ምሥጢር ዓይንተ እግዚአብሔር በሆኑት ካህናት አባቶቻችን በምሥጢር ቁርባን የሚጸና የማይደገም በአደባባይ የሚፈጸም ምሥጢር ነው፡፡ በአደባባይ መፈጸሙ ደግሞ ሁለተኛ ጋብቻ እንደሌለ ለማረጋገጥ ነው፡፡ 

    አንዳንዶቻችን እግዚአብሔር እንደማያይ ዝም ቢለን ሀገር እና ደብርን በመቀየር የማይደገመውን ምሥጢረ ተክሊል እየደጋገምን ከሥርዓቱ ይልቅ ለራሳችን ክብርን እየሰጠን ሰውንም እግዚአብሔርንም በማሳዘን በማይገባ የድፍረት ኃጢአት እንመላለሳለን፤ የከበደንን ሥርዓት ቢሻሻል ብለንም በድፍረት እንሰብካለን በተለያዩ ድህረ ገጾቻችን ይህ አያድንም በሚለው ብሒል ተጠምደን ለራሳችን ስተን ሌሎችንም እናስታለን፡፡ በእውነት እርሱ እርም የሆነብንን ነገር ከሕይወታችን ያርቅልን፡፡

    ወዳጆቼ የእግዚአብሔርን የማዳን ጸጋ ከምናጸናባቸው ምሥጢራት መካከል አንዱ እንደመሆኑ የማይታይ ጸጋ ይልቁንም ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምሥጢረ ቁርባንንም የምንካፈልበት በመሆኑ የማይታየው ጸጋ ሁለት የሆነውን አካላችንን አንድ ያደርገዋል፡፡ በእርግጥ ሁሉም ምሥጢራት በሚታይ የማይታይ ጸጋ የሚያሰጡ በመሆናቸው ምሥጢራት ይባላሉ ብለን በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ውስጥ መማማራችን ይታወቃል፡፡ እውነት ነው! ምሥጢረ ተክሊል በሚታይ (መሐላ፤ጸሎት፤ቀለበት፤ቅዳሴ፤አክሊል፤ካባ…የመሳሰሉት) ሁለት የተለያዩ አካላት አንድ የሚሆኑበት የማይታይ(የእግዚአብሔር ጸጋ፤ አንድ የሚሆኑበት፤ የሚጸኑበት፤ የሚፋቀሩበት፤ የሚረዳዱበት...የመሳሰሉት) በመሆኑ ምሥጢር መባሉ ትክክል እና ሁሉ ሊቀበለው የተገባ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሥርዓት ነው፡፡ 
    ወዳጆቼ ምንጊዜም ሥርዓተ ተክሊል በሚፈጽሙ ሁለት ጥንዶች ጋብቻቸውን ለመባረክ እና ለማጽናት ከሌሊት ጀምሮ የሚጸለይላቸው የተክሊል ጸሎት(ጸሎተ ተክሊል) ይባላል፡፡ ጸሎተ ተክሊል ማለት አንድ ወንድ ከአንዲት ሴት ጋር ተስማምተው በነጻ ምርጫቸው እና ፈቃዳቸው በሚያደርጉት ጋብቻ ላይ ካህናት ስምምነታቸውን በማጽናት ስለአንድነታቸው ጸጋውን ያገኙ ዘንድ የሚፈጽሙት አገልግሎት ፤የሚያስተላልፉት ጸሎትና ቡራኬ ነው፡፡

    3. ቅድመ ጋብቻ

    ከቅዱስ ጋብቻ በፊት የምናደርገው ቅድመ ዝግጅት ቅድመ ጋብቻ ይባላል፡፡ ይኸውም መተጫጨት ፤መመራረጥ፤ መፈቃቀድ፤ መስማማት በቅድመ ጋብቻ ሊጠናቀቁ የሚገባቸው አበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡ ይህ መተጫጨት በሁለት ዓይነት መልኩ ሊፈጸም ይችላል፡፤ አንደኛው አብርሃም ለይስሐቅ ርብቃን እንዳጨለት በቤተሰብ የሚደረግ መተጫጨት ሲሆን ዘፍ24፡2፤ ሁለተኛው ደግሞ እንደ ያዕቆብና እንደ ራሔል በተጋቢዎች ብቻ የሚደረግ መተጫጨት ነው፡፡ ዘፍ 29፡18

    ወዳጆቼ ከማግባታችን በፊት ያለው ይህ ወቅት እጅግ ከባድ እና በጥንቃቄ ልናስተውል እና ፈቃደ እግዚአብሔርን በማስቀደም አብዝተን ልንጸልይበት የሚገባ ነው፡፡ ምክንያቱም በስህተት ጎዳና የጀመርነው ጋብቻ ትውልድንም የሚያበላሽ እና የመልካሙን ትውልድ ምንጭ የሚያደርቅ ነው፡፡ ከዚህ ለመዳን ፍቃደ እግዚአብሔርን ማስቀደም ለሐሳባችን ስኬት ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ መዝ 36፡5
    እውነት ግን ፈቃደ እግዚአብሔርን ማወቅ ይቻላል? ብላችሁ እንደምትጠይቁኝ አልጠራጠርም፤ጥያቄው መሰረታዊ አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው፤ በነገራችን ቀላልም አይደለም!በቀላሉም በጸሎት ነው ብለን ብቻ መልሰን የምንተወው ጉዳይ አይደለም፤እርግጥ ጸሎት የማይመልስልን ጥያቄ ፤የማይፈታልን የሕይወት እንቆቅልሽ የለም፡፡ ይሁንና ከጸሎት ጋር የእኛም ድርሻ ከግምት ሊገባ ይገባዋል፡፡ በመተጫጨት ውስጥ ሁለት ነገሮች እንደ ምሣሌ ብንመለከት ፈቃደ እግዚአብሔርን ለማወቅ ሊረዱን ይችላሉ፡-
    1. ትክክለኛ አመለካከት፡- በሁኔታዎች፤ፍላጎት ለፍላጎት፤ ዓላማ ለዓላማ፤የተስማሙ ከሆነ እና በተጨማሪም ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይጋጨን ሲሆን ይህ ፍቃደ እግዚአብሔር ያለበት ነው ማለት እንችላለን፡፡
    2. የተሳሳተ አመለካከት፡- በሕልም ምልክት መፈለግ፤ዕጣና የመሳሰሉትን በመሞከር የእግዚአብሔርን ፍቃድ ለማወቅ መሞከር የተሳሳተ አመለካከት በመሆኑ ይህን በማስወገድ ፍቀደ እግዚአብሔርን ማወቅ እንችላለን፡፡

    ወዳጆቼ ሌላው በምንተጫጭበት ወቅት ልንመረመር እና ልናጤን የሚገቡን ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ናቸው ፡-

    1. በሃይማኖት ሊመሳሰሉ ይገባል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ ነው የሚመክረን እንኳን ለትዳር ለባልነጀርነት እንኳን መምረጥ እንደሚገባን ሲገልጽ፡-“ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል፡፡” እንዲል፡፡1ቆሮ15፡33

    አንዳንዶች ምን ችግር አለው ክርስቲያን ከሆንን እኔ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነኝ ተሐድሶ መናፍቁን ባገባ ዋናው ፍቅር አይደል? በማለት ከማናውቀው አዠቅት ውስጥ ወድቀን የጨለማ ሕይውን ለመግፋት እንገደዳልን፤ በሁለት ቀናት ውስጥ ጓደኛዬ ሙስሊም ነው ችግር አለው ወይ? ከተፋቀርን ብንጋባ ምን አለበት ያላችሁኝም አላችሁ በዚህ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ዘፋኙ “አንቺም በሐይማኖሽ እኔም በሐይማኖቴ…” በማለት አቅሉን የሳተ አስተሳሰብን የሚያራምድ ሳይሆን ይልቁንም አይደለም ለቅዱሱ ጋብቻ በልዩ ልዩ መስተጋብሮቻችን ከማይማኑ ጋር በማይመች አካሄድ ሳይቀር እንዳንጠመድ አስጠንቅቆ ይነገረናል፡- ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ምን ኅብረት አለው?...” 2ቆሮ 6፡14 
    ወዳጆቼ ማህበራዊ ሕይወት እና መንፈሳዊ ሕይወት የሆድና የጀርባ ያህል የማይገጣጠሙ አካሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሰላም ከመሐመድ ጋር አይደለም ለመተጫጨት እና ለመጋባት ለጉርብትናው እንኳን ጥንቃቄ ሊወሰድበት የሚገባ የመጽሐፍ ቅዱስንም ሆነ የቤተክርስቲያንን ሕግ የሚጻረር የዲያብሎስ ወጥመድ ነው ፡፡ 
    2. ወንዱ ከ18 ሴቷ ከ15 ዓመት በታች መሆን ይገባል፤ ከዚህ በታች ቢተጫጩና ቢጋቡ ጋብቻቸው አይጸናም፡፡ የጋብቻ ሕጉ የሚፈቅደው ይህንን ነው፡- “ከ15 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላት ድንግል(ቆንጆ) ከ18 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ድንግል (ጎበዝ) ተጫጭተው ጋብቻን መፈጸም ይችለሉ፤ በውዴታ የሰጡት ቃላቸውም ይጸናል፡፡(መጽሐፈ ተክሊል ገጽ 75-76) 
    3. ዝምድና ሊኖራቸው አይገባም፡፡ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ ዝምድና እንዳይኖር በፍትሐ ነገስት ተደንግጓል፡፡(ፍት.ነገ28፡8-42) በመሆኑም ሥጋዊ ዝምድና ሊኖር የማይገባው ሲሆን ከዚህም በላይ መንፈሳዊ ዝምድናንም ይከለክላል፡፤ ለምሳሌ የክርስትና አባቱን ሚስት እንዲሁም የክርስትና ልጁን እናት የመሳሰሉትን ማግባት ስለማይችል በመተጫጨት ጊዜ ሊተኮርባቸው ይገባል፡፡
    ይቆየን …ይቀጥላል

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ምሥጢረ ተክሊል ምዕራፍ ፩ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top