• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday, 11 November 2015

    ምሥጢረ ተክሊል ምዕራፍ ፪



                      ክፍል አራት (4) 
    እግዚአብሔር አባታችን የሚረባንን የሚጠቅመንን እያስተማረን በመንገዳችን ሁሉ እየመራን ረዥሙን ጉዞ አንድ ብለን ጀምረን ይኸው አራተኛው ምዕራፍ ላይ ደረስን አሁንም በቃሉ ምግብነት የተራበችዋን ነፍሳችንን እንዲመግብልን የተቀደሰ ፍቃዱ ይሁን፤ እንደምናስታውሰው በክፍል አንድ የምሥጢረ ተክሊል ምንነትን፤ በክፍል ሁለት የጋብቻ ዓላማን? እንዲሁም በክፍል ሦስት ቅድመ ጋብቻን ጀምረን እንዳይበዛ በማሰብ ይቀጥላል ብለን ማቆማችንን ከወዲሁ ላስታወሳችሁ እወዳለሁ፡፡

    ዛሬም እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ በክፍል አራት ትምህርታችን የጀመርነውን የቅድመ ጋብቻን ትምህርት እናጠቃልልና ድንግልና እና ተክሊል በሚል ርዕስ ደግሞ በክፍል አምስት እርሱ እንደፈቀደ እንማማራለን፤ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡አሜን

    ወዳጆቼ የቀድሞዎቹ ነገስታቶች ክርስትናቸውን አጥብቀው ይይዙ የነበሩ በመሆኑ ይተዳደሩበት የነበረውን መጽሐፍ ፍትሐ ነገስት ማለታቸውን መቅድሙ ይገልፃል፡፡ ይህ መጽሐፍ ለሀገራችንም ሆነ ለዓለም ሕዝብ የሕግ ምንጭ ሆኖ አሁን ደረስ የሚያገለግል ታላቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ከአረበኛ ወደ ግእዝ ቀጥሎም በእንግሊዝኛ እንዲሁም በ1962 ዓ.ም በግእዝ እና በአማረኛ የታተመው መጽሐፍ አገልግሎቱን የዋለው ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን(ዓፄ ዘርአያዕቆብ 1444-1468) ጀምሮ ሲሆን የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት እስከ ረቀቀበት(1948 ዓ.ም) ድረስ በዚህ የሕግ መጽሐፍ ኢትዮጵያ ትተዳደርበት እንደነበረ የታሪክ ሕያው ምስክርነትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
    ወዳጆቼ ቅድመ ጋብቻ ላይ (በምንተጫጭበት ወቅት) ብዙ ጊዜ የማናስተውላቸው እና ከገባንበት በኋላ የምንነቀባቸው ስህተቶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው ጊዜያዊ ሀብትን ተመልክተን የምናደርገው መተጫጨት ብሎም በቅዱስ ጋብቻ እስከ መወሰን የምንደርስበት የሕይወት ስህተት ነው፡፡ 

    ይህ ሀብት አገኛለው፤የምፈልገውን እበላለው፤እለብሳለው፤ሕይወትን በተሻለ ሁኔታ እመራለው፤ነፍሴ ሆይ ብይ ጥገቢ እንዳለው ሰነፍ በመሆን ጋብቻን ለጥቅም መፈለግ፤ፍቅርን እንዳናይ እንደተጋረደብን ዘመናችንን ሁሉ በተሰላቸና ፍጹም በተረበሸ መልኩ በጨለማ እንድንመራ ከማድረጉም በላይ ሰማያዊውን የእግዚአብሔርን ጸጋ በምድራዊው ገንዘብ ለውጠናልና ደስታ የሰማይ ያህል ይርቅብናል፤የሕይወት ትርጉሙ የማይገባን ከእንሰሳዊ ሕይወት ያልተሻለ በራሳችንም በፍሬዎቻችንም የማንደሰት እንሆናለን፡፡ እንዲህ ከመሆን እርሱ ይጠብቀን፡፡ 

    ለዚህ ስህተት የሚዳረጉትን ሰዎች በተመለከተ፡- "...ከእነርሱም ወገን ስለ ገንዘብ ብዛት ጋብቻን የሚሻ አለ፡፡ ... ስለዚህም ስለ ገንዘብ ፍቅር የሚስቱን መልከ ጥፉነት የሚታገሥ አለ፡፡..." (ፍት.ነገ.ትርጓሜ አን.24፡839 ገጽ211) ካስተዋልን ግን ገንዘብ እኮ ድግስን እንጂ ጋብቻን አያሳካም፤ፍቅርን አይገዛም፤ይልቁንም ደገኛ ሀብት ቢኖረን ባለጸጋውን አምላክ እንደማምለካችን መመካታችን በእርሱ ብቻ ይሆን ዘንድ ልባችን ቢመካ ሰላማችን እንደ ወንዝ በሆነ ነበር፡፡ ምክንያቱም ብንመካበት የተገባ የዘላለም መኖሪያች እና የሕይወታችን ትርጉም፤የመኖራችን ዋስትና የሚሆን እንደ እግዚአብሔር ያለ ለእኛ ማንም የለም፡፡ ዘዳ33፡26 ክብር ላከበረን ጌታችን ይሁን፡፡አሜን

    ወዳጆቼ መመካት በእግዚአብሔር መሆን እንዳለበት ነብየ እግዚአብሔር ኤርሚያስ እንዲህ በማለት ያመጣዋል ፡-"እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፡፡ ጠቢብ በጥበቡ አይመካ፤ኃያልም በኃይሉ አይመካ፤ባለ ጠጋም በብልጥግናው አይመካ ፤ነገር ግን የሚመካው፡- ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ ደስ የሚያሰኙኝ እነዚህ ናቸውና፤ይላል እግዚአብሔር፡፡"ኤር9፡23-24 ስለዚህ መመካት ያለብን በእግዚአብሔርን እና እርሱን እንድናውቅ በሰጠን ማስተዋል እንጂ ለራሳችን በሚመስለን ኃላፊ ገንዘብ መሆን የለበትም፡፡ ማስተዋሉን ይስጠን፡፡

    ዛሬ የአመለካከት ድኅነት ሰማይን በነካበት ዘመን ሰው መሆናችን እስኪረሳን፤ጊዜያዊው ኑሮአችን ዘላለማዊ ኑሮ እስኪመስለን ድረስ ያወረን እና እግዚአብሔርን እንዳናይ ታላቅ ጋሬጣ የሆነብን ገንዘብ ነው፡፡ ሰው ለመጥላታችን፤ሰው ለመውዳዳችን ሚዛኑ እግዚአብሔር ሳይሆን ገንዘብ ሆኗል "ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ" የሚለውን አባባል የሕይወታችን መርሕ አድርገን እንደ ስምዖን መሰሪ ሰማያዊውን ጸጋ በገንዘብ ለማግኘት የምንሯሯጥ ያላስተዋል ስንቶች ነን? ለእኛ ተክሊል ማድረግ የጓደኞቻችን የድፍረት ኃጢአት መመዘኛ የሆነብን፤ እነ እገሌ አድርገዋል አይደል?ምን ሆኑ? በማለት የእግዚአብሔር የምህረት ባለጠግነትን እንደ ሞኝነት የምናይ ስንቶቻችን ነን?፡፡ ይህ ግን መንፈስ ቅዱስን ማታለል ነውና ለጊዜው የተሳካልን ቢመስለን ቀናተኛው እግዚአብሔር የስራችንን ሊሰጠን ዋጋውን በእጁ ይዞ ዘወትር በሕሊናችን በኩል ይቆማል፡፡ 

    ሰው ሰው ሆነ የሚባለው እንደ ሰው መኖር ሲችል ብቻ ነው፤ይኸውም የእግዚአብሔር ፍቅር የተሞላ ሰው ሲሆን ነው፤ እግዚአብሔር ያሉት ሁሉም ነገሮች አሉት፤ዳዊት ልጁ ሰሎሞንን ሰው ስላልሆነ አይደለም "ልጄ ሆይ ሰው ሁን" ያለው ነገር ግን ሰው ማለት በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ክቡር እና የእግዚአብሔር ፍቅር የሚንጸባረቅበት የክብሩ ማደሪያ ነው፤ በመሆኑም በዚህ የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ መንገስ ያለበት እግዚአብሔር ብቻ እንጂ በደባልነት ገንዘብ ሊሆን አይገባም፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ ቤተመቅደስ ልባችንን ከተቆጣጠረው ክፋትን ብቻ የሚያበቅል ፍሬ የሌለው ሕይወትን እንድንመራ እንገደዳለን፡፡ 

    እዚህ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ለወለደው ለልጁ ለጢሞቴዎስ የመከረውን ቃል ማስታወስ ወደድኩኝ፡- "ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ስቃይ ራሳቸውን ወጉ አንተ ግን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከዚህ ሽሽ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም፤ መጽናትንም፤ የዋህነትን ተከታተል፡፡ መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ፡፡" 1ጢሞ6፡10-12 ገንዘብን መውደድ ይህን ያህል ክፉ እና ከሐይማኖት መንገገድ የሚያስወጣ ቀይ መስመር ነው፡፡ 
    ሌላው ወጪያዊ ውበት(ተክለ ሰውነት) ነው፤ ነገር ግን ይህን ብቻ እንደ መስፈርት በመቁጠር ስንቱን ቆንጆ ላናገባቸው በእጮኝነት ጊዜ አስነወርናቸው? አንገታቸውን አስደፋናቸው? አላማውያን የማያደርጉትን ነውር እርም የሆነ ነገር ፈጸምን? ጋብቻን ለመመስረትም ለመተጫጨትም ተክለ ሰውነት አይከለከልም፤በተክለ ሰውነትም ምክንያት ጋብቻ አይፈርስም፡፡ምሳ31፡30 ሁሉም ውብ ነው፤በእግዚአብሔር ጣቶች የተዘጋጀ የእግዚአብሔር ውጤት ነው፡፡ በዝሙት የምናይ ከሆነ"ቆንጆና እሸት አይታለፍም" እያልን ካገኘነው ጋር አንሶላ እየተጋፋን እግዚአብሔርን እናሳዝናለን፤ባለማስተዋል እንዲህ የምናደርግ ይህ የእግዚአብሔር ድምጽ ነውና ንሠሐ ገብተን ሰው ልንሆን ይገባናል፡፡

    አንዳንዴ እጅግ የማዝንባቸው አባባሎች አሉ፡፡ እንደ እኛ ዓይን ቆንጆዎቹን ለማድነቅ ሰሪውን እናንቋሽሻለን፡- "እግዜር እጁን ታጥቦ ነው የሰራህ/ሽ" ፤ "በማር ሰራሽ ሆይ" እስኪ ተመልከቱ አፈር አፈርን ንቆ በክህደት በማር ነው የተሰራኸው ሲል እንደመስማት የሚያሳዝን ምን ነገር አለ? እንዲህ ያለውም ያለላትም ሁለቱም ከከበረ አፈር ነው የተፈጠሩት ሁለትም አፈር ነው የሚሆኑት፤ እዚው ላይ እግዚአብሔር እኛ እንዳልነው እጁን መታጠብ የሚገባው አምላክ ነው፤በዚህ ውበት ተሳስበው የተተጫጩ ጥንዶች እግዚአብሔርን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ አላከበሩምና ለዝሙት ለማይረባም አእምሮ ተላልፈው ላለመሰጠታቸው ዋስትና አይኖራቸውም፡፡
    ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔርን ለማያከብሩ እና ተክለ ሰውነትን ተመልክተው አብረው ለመኖር ላቀዱ ጥንዶች እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል፡-"ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ ነገር ግን በሀሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ፡፡ ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮወች ሆኑ..."ሮሜ1፡20፤21 

    ይህ ብቻ አይደለም ለመመለስ እና እግዚአብሔርን ለማወቅ ባለመውደዳቸው ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ እንደሰጣቸው ሲናገር፡-" እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ሰጣቸው ዓመፃ ሁሉ ግፍ መመኘት ክፋት ሞላባቸው፤ ቅናትን ፤ ነፍስ መግደልን ክርክርን፤ተንኮልን፤ክፉ ጠባይን፤ተሞሉ፤የሚያሾከሹኩ፤ሐሜተኞች አምላክን የሚጠሉ..."ሮሜ1፡28-32 

    ወዳጆቼ በእጮኝነት ከምንስትባቸው አንዱ ተክለ ሰውነት በመሆኑ ከዝሙት የጸዳ እይታ እግዚአብሔር ሁሉንም ውብ አድርጎ እንደሰራ በማመን ይንን እንደ መስፈርት እንዳንቆጥረው በመጠንቀቅ የእጮኛ ምርጫችንን ከወዲሁ ልናስተካክል ይገባል፤ ውበት ሐሰት ነው ደምግባትም ከንቱ ነው እግዚአብሔርን የምትፈራ እርስዋ ትመሰገናለች ነውና የሚለው ቃሉ የእኛ መስፈርት ከተሳሳተው ተክለ ሰውነት ወደ ትክክለኘው እግዚአብሔርን ወደ መፍራት ሊሸጋገር ይገባል፡፡ ደግሞም አባቶቻችን "የሚያብለጨልጭ ሁሉ ወርቅ አይደለም" የሚሉት ምክር ልብ ልንለው ይገባል፡፡
    የእጮኝነት ጊዜ የጋብቻ ጊዜ እንዳለመሆኑ መጠን የተቃራኒ ጾታ ግንኙነትን ሳናደርግ፤ በሐሳብ የምንግባባበት፤ ጠባይ ለጠባይ የምንጠናናበት፤ በማናቸውም ጉዳዮች ሳንተፋፈር የምንነጋገርበት፤ ጠንከርም ሲል ቤተሰቦቻችንን የምናስተዋውቅበት የቅድመ ጋብቻ አንዱ ክፍል ነው በመሆኑም ቅድስናን(ክብረ ንጽሕናን) የሚያሳጡንን የረዘመ የእጮኝነት ጊዜ ማስቆጠር፤በምንገናኝበት ጊዜ ከሰው የተደበቀ ቦታን መምረጥ እንዲሁም ፤ሕይታችንን የሚያለመልመውን ቃለ እግዚአብሔር በሕብረት አለመመገብ ናቸው፡፡ 
    ሌላውና የመጨረሻው የእጮኝነት ጊዜአችንን የተሳካ የሚያደርግልን እና ለቅዱሱ ጋብቻ የሚያበቃን
    1ኛ.እግዚአብሔር እንደሚያየን ማመን እርሱ እንደሚያየን ካመንን እርስ በእርሳችን ሰው ኖረ አልኖረ አንዳራም፡፡ 1ጴጥ41
    2ኛ. የሚገባን ልብስ ማድረግ አካልን የሚግልጥ ልብስን አለማድረግ፡፡ 2ሳሙ13፡19 ከጋለሞታ ልብስ የተለየ ምሳ 7፡10፤ ባትን ከሚያሳይ ልብስ የተለየ ኢሳ 47፡2፤ የተገባ አለባበስ ጌጠኛ (ንጹሕ) እና ደገኛ ልብስ ኢሳ 52፡1፤ ነብዩ ኤርሚያስ ሴቶች ስለምን የተገላለጠ ልብስ እንደሚያደርጉ ሲገልጥ፡-" በልብሽም እንዲህ ያለ ነገር ስለምን ደረሰብኝ ብትይ፤ ከኃጢአትሽ ብዛት የተነሳ የልብስሽ ዘርፍ ተገልጦአል ተረከዝሽም ተገፍፏል፡፡" ኤር13፡22
    3ኛ.የሥጋ ስሜታችንን የሚያነሳሱ ፊልሞችን እና የመሳሰሉትን ነገሮች አለማየት
    4ኛ. የዝሙት ጾርን በጾምና በጸሎት ማሸነፍ የእጮኝነት ጊዜአችንን የተሳካና ጣፋጭ እግዚአብሔር ያለበት ያደርግልናል፡፡

                     ክፍል አምስት (5)

    እግዚአብሔር አባታችን የቤቱን ሥርዓት በፍቅር እያስጨነቀ፤ ያስተማረን ሁሉ ለበጎ እንድናውለው እየፈቀደ በክፍል አንድ የምሥጢረ ተክሊል ምንነትን፤ በክፍል ሁለት የጋብቻ ዓላማን? በክፍል ሦስት ቅድመ ጋብቻን፤በክፍል አራት የቅድመ ጋብቻን የመጨረሻ ክፍል አስተማረን፤ እነሆ ዛሬ በክፍል አምስት ትምህርታችን ድንግልናና ተክሊል በሚል ርዕስ እንማማራለን፤የሐር ነጋዴዋን የልድያን ልብ የከፈተ አምላካችን የእያንዳንዳችንን የልቦና ጓዳ እያንኳንኳ እንዲያስተምረን የተቀደሰ ፍቃዱ ይሁን፡፡ አሜን

    4. ድንግልና እና ሥርዓተ ተክሊል
    ድንግልና የሚለውን ቃል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሲተረጉሙት፡- "በቁሙ ድንግልነት፤ ድንግል መሆን፤ ክብርና ማኅተመ ሥጋ፤ ንጽሐ ሥጋ፡፡" ብለዋል፡፡ ግልጽ ሲያደርጉት ደግሞ በደንገለ ትርጉም ላይ እንዲህ ብለዋል፡-" ደነገለ፤አጥብቆ ጠበቀ፤ከለከለ፤ከሴት አራቀ ራሱን ወይም ሌላውን፡፡" ይላል፡፡ 

    ድንግልና የሚለውን ዐዲስ የአማረኛ መዝገበ ቃላትን ያዘጋጁት ሊቁ ደስታ ተክለወልድ ሲገልጹ፡- " ድንግልና ፡-ድንግል መሆን፤መጠበቅ ወይም ክብርና" መጽሐፍ ቅዱስም ስለ ድንግልና በብዙ ስፍራ ክብር መሆኑን ይገልጣል፡- "እርሱም ሚስትን በድንግልናዋ ያግባ" ዘሌ21፡13 ገለዓዳዊው ዮፍታሔ አሞናውያንን በእጁ ይጥልለት ዘንድ ለእግዚአብሔር ከድሉ በኋላ የሚያገኘውን መስዋዕት አድርጎ ሊያቀርብ ስለት በመሳሉ ከበሮ እየመታች የተቀበለችው ልጁ ነበረችና መስዋዕት አድርጎ ከማቅረቡ በፊት ይህቺ ሴት ስለድንግልናዋ ሁለት ወር ታለቅስ ዘንድ ወደ ተራራዎቹ መውጣቷ ለድንግልና ምን ያህል ክብር መስጠት እንዳለብን የምንማርበት ሕይወት ነው፡፡ "ሁለት ወርም አሰናበታት ከባልንጀሮቿም ጋር ሄደች በተራራዎችም ላይ ለድንግልናዋ አለቀሰች" ይህን ያህል ነው ድንግልና ሊከበር የሚገባው፤ለሞት እንኳን የተዘጋጀንበት የሚያስጨንቅ ጊዜ ቢሆን ድንግልና ሊጠበቅ ይገባዋል ምክንያቱም ክብር ነውና፤የጌታ ቤተመቅደስ ከጋብቻ በፊት በሚደረግ ዝሙት ይፈርስ ዘንድ የተገባ አይደለምና፡፡መሳ11፡28-40፤1ቆሮ6፡18-20
    ደስታ ተክለወልድ ስለ ድንግል ትርጓሜ ሲተነትኑ በማይሰበር ብዕራቸው ድንግል "ሴት ያላወቀ ወንድ ወንድ ያላወቃት ልጃገረድ(ዘሌ 21፡13)" ማለት ነው፡፡ ይሉና ቀጠል አድርገው ድንግልናን ከእናትነት አስተባብራ የያዘች ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያምን ፡-"ድንግል ማርያም ከመውለድ አስቀድሞ፤በመውለድ ጊዜ፤ከመውለድ በኋላ ድንግል የሆነች ማርያም...በማለት ለደናግላን የዘላለም ምሳሌ መሆንዋን ጥልቅ በሆነ የነገረ ማርያም ምሥጢር ይገልጣሉ፡፡እውነት ነው ድንግል ማርያምን ከፈጣሪ በታች የሚመስላት አንዳች ፍጡር የለም፡፡ 

    ሥርዓተ ተክሊል ያለ ድንግልና የማይፈጸም ምሥጢር ነው፡፡ ስለዚህም ለተክሊል ክብር እንድንበቃ ድንግልናችንን ልንጠብቅ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን ራሱን የብርሐን መልአክ እስኪያደርግ ድረስ የሚለወጠው ዲያብሎስ በልዩ ልዩ ዝንጋዬ እንድንወድቅ ያደርገናል፡፡ቅዱስ ጳውሎስ ያለንን መንፈሳዊ ሀብት መጠበቃችን ዋጋ የሚያሰጥ መሆኑን በገለጸበት አውድ ፡-"…መልካሙን ገድል ተጋድያለው ሐይማኖትን ጠብቄአለው…የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፡፡”2ጢሞ4፡7 እንዳለ፡፡ ለሐይማኖት መቆም፤ለሐይማኖት መቀደስ፤ ለሐይማኖት መጋደል እንዲገባ በስፋት ይገልጥልናል፡፡

    እዚህ ላይ ማወቅ የሚገባን ድንግልና ሥርዓተ ተክሊሉን ለማክበር ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ከመፍራት አንጻር እንደ ዕንቁ አክብረን በመጠበቅ በዚህ ጉዳይ የሚመጣብንን የዲያብሎስ የሽንገላ ከንፈር ፤የመከራ ገፈት ፤የሥጋ ፈቃድ ጦርነት፤ ከዓለም ብልጭልጭነት የተነሳ ከሚያመጡብን ሥቃይ እና መከራ በመጋደል እንደ ሐዋርያው የጽድቅ አክሊላችንን ስለመቀበላችን የምናገኘውን ሕይወት ቤተክርስቲያን በሚታይ አክሊል የማይታየውን የጽድቅ አክሊል በምሥጢረ ተክሊል መፈጸሟ የሠማይ ሥርዓት በምድር ተሰራ የሚለውን በተግባር ማየታችን መሆኑን ነው፡፡

    እንደ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ድንግልና በሁለት ዓይነት መልኩ እንዳለ በተለያዩ ሉቃውንተ ቤተክርስቲያን የብዕር ውጤቶቻቸው በስፋት ተገልጧል፡፡ ድንግልናን የሥጋ እና የነፍስ በማለት በሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡የደናግላን ምሳሌ የሆነች እመቤታችን ድንግል ማርያም በሥጋም በነፍስም ድንግል ናት፡፡ አንዳንዴም የሕሊና ድንግልና የነፍስ ድንግልና ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፡-“ድንጋሌ ሥጋ ለድንግሌ ነፍስ መገለጫ፤ጥላ ወይም አምሳል ነው፡፡” በማለት የሥጋ እና የነፍስ ድንግልና ያላቸውን ትስስር በሚገባ ገልጽዋል፡፡ ይኸውም፡- ድንጋሌ ሥጋ ከግብረ ሥጋ ግንኙነት በመራቅ የምንኖረው የቅድስና ሕይወት ሲሆን፤ ድንጋሌ ነፍስ ደግሞ ኃጢአታችንን ለካህናት አባቶቻችን በመግለጽ በንሰሐ እየተመላለስን የምንኖረው ሰማያዊ ሕይወት ነው፡፡ እዚህ ላይ ከድንግል ማርያም በስተቀር ሰው በሕሊናው ይበድላልና ዕለት ዕለት ንሰሐ ካልገባ በዚህ ንጹሕ ይሆን ዘንድ የሚችል የለም፡፡

    ሌላው ስለ ምሥጢረ ንሰሐ ታላቅነት በመጽሐፈ መነኮሳት እንዲህ ብሎ ያመጣዋል ፡-"ንስሐ ግን የበደለን እንዳልበደለ ዘማዊን እንደ ድንግል ታደርገዋለች" የሚለውን ስለ ነፍስ ድንግልና የተነገረውን ሐሳብ ለሥጋ ድንግልና እንደሆነ አስተምረውን በቤተመቅደሱ ሳይቀር ያለ ድንግልና ተክሊል እንድናደርግ ያደፋፈሩን እና እኛም እስከ አሁን ድረስ "ማን በድንግልና አገባ?" በሚለው ፈሊጥ ቤተመቅደሱን ባለመፍራት በተክሊል አግብተን ክብራችንን በነውራችን የለወጥን ብዙዎች አለን እግዚአብሔር ይቅር ይበለን፤ ስንዱዋ እመቤት ቤተክርስቲያን በልዩ ልዩ ምክንያት በፍቃዳችን ድንግልናችንን ላጣን በአማራጭነት የቁርባን ሥርዓትን እንድንፈጽም አዘጋጅታልናለች ግን ማን ፈርቶ ይህን ይፈጽም?

    አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ የሕይወት ታሪኩን እዚህ ላይ ባነሳው ሳንማርበት የምንቀር አይመስለኝም! "ሳሚ እኔ እኮ ክርስቶስን የማላውቅ በቤተክርስቲያን የልምድ ተመላላሽ ፤ኃጢአቴ ብዙ የሆነብኝ ሰው ነኝ፤ለንሰሐ አባቴ ድንግል አለመሆኔን ገለጽኩላቸው ነገር ግን እሳቸው ምንም ችግር የለውም፤ ዋናው ንሰሐ ነው፤ብለው የተክሊል ፕሮግራሙን እንድፈጽም አደረጉኝ እኔም ጥፋት እንደሆነ እያወቅሁ ፈጸምኩ አሁን በትዳሬ ሰላም የለኝም፤ ልጅ ደስታን አላመጣልኝም፡፡..." ተመልከቱ የዚህ ወዳጄ ጥፋቱ ምንድን ነው? ካህኑስ እንዳሉት ንሰሐ የሥጋ ድንግልናን ወይስ የነፍስ ድንግልናን ነው የምትመልሰው? ይህ ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው፡፡ ይሁንና ለጊዜው የመለስኩለት "የማን ጥፋት እንደሆነ እግዚአብሔር ያውቃል!!!" ብዬ ነበር፡፡

    ዛሬ በቤተክርስቲያናችን የምንሰማውም ሆነ የምናየው፤የሚደረገውም ሆነ የምናደርገው ውስጣችንን የሚያደማ እጅግ የሚያስከፋ እና አንገት የሚያስደፋ ነገር ነው፡፡ ይገርመኛል ድንግልና ለሴት ብቻ እንደ ግዴታ የተወሰነ ሕግ ይመስል የሴቷ ድንግልና እንጂ የወንዱ የድንግልና ሕይወት ከግምት ውስጥ የማይገባበት ... ይልቁንም ሳያፍሩ አርግዘው በተክሊል እንደ ደናግላን ሲያገቡ እንደ ማየት የሚያስለቅስ ... ሁለት ልጅ ወልደው በድንግልና የሚሰጠውን ክብር በገንዘብ ብዛት መንፈስ ቅዱስን ሲያታልሉ አንዳች የማይሰማቸው ልበ ደንዳኖችን እንደማወቅ የሚያቆስል ... ድንግልናቸው የተወሰደባቸው ሴቶች ሕይወታቸው ጨልሞ እግዚአብሔርንም ቤቱንም እምነታቸውንም በመጥላት እየረገሙ ሲጮሁ ደፋሪዎቹ ግን ምንም እንዳላደረጉ በተክሊል ሲጋቡ ማየት አይደለም መስማት እንኳን ምን ያህል ህሊናን ያደማል? በተሐድሶ እምነት ውስጥ ቀንደኛ መሪ መሆናቸው እየታወቀ በሰጡት ጉቦ የተክሊል ስርዓት ሲፈጽሙ እንደማየት የሚያሳብድ...የደካሞችን ስህተት ማመሳከሪያ በማድረግ ንሰሐ አባት እንኳን ሳይዙ መስካሪ ሳይኖራቸው ለጊዜያዊ የውጭ ዕድል በድፍረት በከበረው በምሥጢረ ተክሊል ሲያገቡ እንደማየት ምን የሚያስጨንቅ ጊዜ አለ?...ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል ነገር ግን እኔ ደካማ ነኝና አዎን!!! አቡቀለምሲስ የተባለው ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእይው፡- "ዓመፀኛው ወደፊት ያምጽ ርኩሱም ወደ ፊት ይርከስ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ ፤ቅዱሱም ወደ ፊት ቀደስ አለ፡፡ እኔ በቶሎ እመጣለሁ፤ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር ነው፡፡ አልፋና ዖሜጋ ፊተኛውና ኋለኛው መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ፡፡"ራእ22፡12-13 እንዳለ እርሱ የወደደውን ያድርግ፡፡

    ቅዱሱን ጋብቻ በሥርዓተ ተክሊል ሌሎች ወገኖች የማያደርጉበት ብዙ ምክንያት ቢኖርም በተለይ ከእኛ ሐይማኖት ውጪ የሆኑት ግን በዋናነት ጋብቻ ለእነርሱ በተጋቢዎች መካከል እንደሚፈጸም ኮንትራት እንጂ የአንድነት ምሥጢሩን ብዙም ቦታ አይሰጡትም፡፡ ይሁንና እኛ ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደነገረረን ሁለቱም አንድ ሥጋ የሚሆኑበት፤ አንድ ሐሳብ የሚያስቡበት፤እንደ አንድ ልብ አሳቢ የሚናገሩበት፤ባል ለሚስቱ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥበት፤በእግዚአብሔር መንፈስ አንድ የሚሆኑበትና እንደ እርሱ ፍቃድ የሚመላለሱበት፤ መኝታው ከዝሙት ንጹህ ይሆን ዘንድ በቃሉ መመሪያነት የብርሐኑን ሕይወት የምንኖርበት፤ እርሱ ሲፈቅድ ደግሞ የእርሱን ሥጦታ ልጆችን የምንቀበልበት የበረከት በር፤እግዚአብሔርን በፍቅር ሆነን የምናመልከበት፤ እርስ በእርሳችን የምንረዳዳበት፤በጸሎታችን ዲያብሎስን ድል ሕይወት ነው፡፡

    ከድንግልና ጋር በተያያዘ በተክሊል ለማግባት ከሁኔታዎች አንጻር እንደ ደናግላን በቤተክርስቲያን ምሥጢረ ተክሊል የምትፈጽምላቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ በሕክምና ምክንያት ድንግልናቸውን ለሚያጡ፤ በተፈጥሮም ሲወለዱ ድንግልና ለሌላቸው፤ለአቅመ ሔዋን ሳይደርሱ በመደፈር ድንግልናቸውን ላጡ እና በከባድ ስራ ምክንያት የተነሳ ድንግልናቸውን ያጡ እነዚህ ያለፈቃዳቸው በመሆኑ እንደ ደናግላን በተክሊል ማግባት ይችላሉ፡፡ ፍትሐ ነገስት አንቀጽ 24 በስፋት ይዘረዝረዋል... ይቆየን

                                             
                     ክፍል ስድት (6)

    እርሱ እየረዳን፤ እርሱ ድካማችንን እያገዘን፤ እርሱ ጎዶሏችንን እየሞላ፤ እርሱ ጥያቄዎቻችንን እመለሰ፤ እርሱ በጉዟችን ሁሉ ከፊት እየቀደመ ከኋላም እየተከተለ፤ከጎንም እየደገፈን፤ኃይላችን እያደሰ፤በየምዕራፉ እያሳረፈን ከስድተኛው ክፍል አድርሶናል፡፡ በእውነት ይህም በእርሱ ነውና ክብር ብቻውን አምላክ ለሆነው ለእርሱ ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

    ወዳጆቼ በተከታታይ ክፍሎች የተማርናቸውን እናስታውሳቸው ዘንድ እዚህች ግድም ላንሳላችሁ በክፍል አንድ የምሥጢረ ተክሊል ምንነትን፤ በክፍል ሁለት የጋብቻ ዓላማን? በክፍል ሦስት ቅድመ ጋብቻን፤በክፍል አራት የቅድመ ጋብቻን የመጨረሻ ክፍል፤በክፍል አምስት ትምህርታችን ድንግልናና ተክሊል በሚል ርዕስ ተማማርን እርሱ እንደፈቀደ ዛሬ ደግሞ በክፍል ስድስት ትምህርታችን የሥርዓተ ተክሊል መስፈርቶች ምንድን ናቸው? የሚል ይሆናል፡፡ 

    የጋብቻ ዓላማ ዘር ለመተካት፤ለመረዳዳት እና ከዝሙት ለመራቅ ብቻ ሳይሆን ከዚህም በላይ በምድር ላይ መልካሙን ተጋድሎ ፈጽሞ ርስት መንግስተ ሰማያትን መውረስ ነው፡፡ ለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ አንድ ክርስቲያን በየትኛውም የሕይወት ምዕራፍ ውስጥ ቢኖር ተጋድሎ የሚጠበቅበት መሆኑን ከራሱ ሕይወት ያስተምረናል፡- "መልካሙን ገድል ተጋድያለው ሩጫውን ጨርሻለው፤ሐይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፤ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም፡፡" 2 ጢሞ4፡7-8 

    ይህ በተጋድሎ ተጀምሮ በድል የሚጠናቀቀው የጋብቻ ሕይወታችን ከጅማሬው ካልተስተካከለ መቼም ሊስተካከል አይችልም፡፡ ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ በሥርዓትና በአገባብ ይሆን ዘንድ በብዙ ስፍራ ሥርዓታዊ የሆኑ መመሪያዎችን የሚነግረን ለምሳሌ እግዚአብሔር በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የፋሲካን በዓል እንዲያከብሩ የዘላለም ሥርዓት ሰርቶላቸዋል፡፡ ዘጸ12፡17 ፤ ስለ ሰንበትም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ጠብቁ በማለት አስጠንቅቋቸዋል፡፡ ዘሌ8፡35 ፤እነያሱ ከማይቱን ሰባት ጊዜ የዞሩት ሥርዓቱ ስለሚያዛቸው ነው፡፡ ኢያ6፡15 ፤ሰሎሞን እግዚአብሔርን በመውደዱ በኮረብታው የመስገድን፤ የመሰዋትን እና የማጠንን ሥርዓት ከአባቱ ተምሮ በሥርዓት ይፈጽም ነበር፡፡1ነገ3፡3 ብዙ ብዙ መጥቀስ ይቻላል፡፡ 
    የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን መሆኑን የነገረን ይፈጽመው የነበረው ዳዊት ነው፡-"የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፤ልብንም ደስ ያሰኛል፤የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤ዓይንንም ያበራል፡፡"መዝ18(19)፤8 ይህ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር "የእስራኤል ልጆች ከእኔ ዘንድ በሳቱ ጊዜ የመቅደሴን ሥርዓት የጠበቁ የሳዶቅ ልጆች ሌዋውያን ካህናት ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ይቀርባሉ..." ወደ እግዚአብሔር የሚያቀርበን ልዩ መንገድ ሥርዓት መጠበቅ መሆኑን ገልጦልናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያጠቃልልልን ፡-"ነገር ግን ሁሉ በአግባብና በሥርዓት ይሁን፡፡"ብሏል፡፡ 1ቆሮ14፡40 
    መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ልዩ ልዩ መጽሐፈ ሊቃውንት እንደሚመክሩን አንድ ሰው በሥርዓተ ተክሊል ጋብቻውን ለመቀደስ ቢፈልግ ሊያሟላው የሚገባው መስፈርቶች አሉ፡፡ እነዚህን ስናይ መሰረታችን መጽሐፍ ቅዱስ፤ፍትሐ ነገስት አንቀጽ 24 (የጋብቻ አንቀጽ) እና መጽሐፈ ተክሊል ይሆናል፡፡ ምሥጢሩን የሚገልጥልንየአባቶቻችን አምላክ ቅዱስ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን
    5. የሥርዓተ ተክሊል መስፈርቶች ምንድን ናቸው?
    ወዳጆቼ የመጀመሪያው ጋብቻ በእግዚአብሔር ፈቃድ በኤደን ገነት እንደተመሰረተ ሁሉ ዛሬም ሥርዓተ ተክሊል የሚፈጸመው በቅድስት ቤተክርስቲያን ብቻ ነው፡፡ ይህም በዓለም ከሚደረገው ጋብቻ ስለሚለይ ቅዱስ ጋብቻ ይባላል፡፡ በዚህ ደግሞ ይህንን የከበረ እና የተቀደሰ የምሥጢረ ተክሊል ሰማያዊ ምስጢር ለመፈጸም ቤተክርስቲያን ለልጆቿ የራስዋ የሆነ ሥርዓት አዘጋጅታለች፡፡ ይህሚጠበቅብን መስፈርት እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን ቀላል ነው፡፡ "ይህም በእግዚአብሔር ዓይን ቀላል ነው" እንዲል " ለሚያምን ሁሉ ይቻላል" ፡፡
    1. በሐይማኖት አንድ መሆን ይገባል፡፡ 
    ከሁሉም ማመን ይቀድማል፤ከሁሉ መቀበል ይቀድማል፤ከሁሉ የምናምነውን ማወቅ ይቀድማል፤ከሁሉም የምናየውን ማመን ይቀድማል፤ከሁሉም መንፈሳዊ መሆን ይቀድማል፤ከሁሉም መታመን ይቀድማል፤በሐይማኖት አንድ መሆን ብቻም ሳይሆን እስከሞት ድረስ ለመጋደል ራሳቸውን ያዘጋጁ ጥንዶች ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ያላመነ ልብ ያለው ለጊዜው እንኳን አመንኩ ቢል ከጋብቻው በኋላ አሻፈረኝ ብሎ ያለማመኑን እንደማመን ተቀብሎ እግዚአብሔር የሌለበትን ኑሮ እንዲመራ ይገደዳልና ከሁሉም በፊት ማመን የተገባ ነው፡፡
    ቅዱስ ጳውሎስ አብዝቶ ስለ ትዳር ጽፎልናል ለምሳሌ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ከማያውቅ ጋር እንኳን ቅዱሱን ጋብቻ ይቅርና የባልንጀርነት ግንኙት እንዳያደርግ አስጠንቅቆ እንዲህ ሲል ይመክራል፡-"አትሳቱ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል፡፡ በጽድቅ ንቁ ኃጢአትንም አትስሩ እግዚአብሔርን የማያውቁ አሉና..."1ቆሮ15፡33 ተመልከቱ አንድ ሰው እግዚአብሔርን ካላወቀ እንዴት ሆኖ እኛ የምንኖረውን ሕይወት ሊኖር ይችላል? ፤ እንዴት ሆኖ እግዚአብሔርን ስለ ማምለክ ይገባዋል? እንዴትስ ከኃጢአት ርቀህ ከእኛ ጋር ኑር ስንለው እሺ ብሎ ለመኖር ይችላል?
    ወዳጆቼ አንሳት የየትኛውም ጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ልዑልንም ማወቅ ማስተዋል ነው፡፡ በዘመናችን የትዳር አንዱ አለመጽናት የሐይማኖት ልዩነት መሆኑ ጸሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ የፍቺውን ቁጥር ለመገመት መዘጋጃ መሄድም አይጠበቅብንም፡፡ ሳንርቅ በየቤታችን ያለ ጉድ ነው፡፡ አንዳንዴ ሁለቱም ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነን እያሉ እርሱ ክርስቶስ አምላክ ነው ይላል፤ እርሷ ደግሞ ፍጡር ነው እንደውም ስለ እኛ እያማለደ ነው ትላለች፤ሁለቱም ለየራሳቸው ትክክል መሆናቸውን አምነው ተቀብለዋል፡፡ ግን የተለያየ በፍጹም ሊገናኝ የማይችል እምነትና አመለካከት ነው፡፡ ታድያ ያለባቸውን ልዩነት ወደ ትክክለኛው ማምጣት ሲገባቸው እምነት የግል ነው ብለው ከአንድነት ወደ ሁለትነት ይሸጋገራሉ፡፡ እንዲህ ከመሆን ግን...

    ይቀጥላል ይቆየን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ምሥጢረ ተክሊል ምዕራፍ ፪ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top