• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    ቤዛ ኩሉ

    "ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ፡- የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ"
    በመምህር ሙሴ ኃይሉ (B.TH, MA in philo)

    ፍጥረታቱን ከመፍጠሩ አስቀድሞ በዘላለማዊ ፍቅር በምልዓት የሚኖር እግዚአብሔር ይህንኑ ተቀድቶ የማይደርቅ፣ ተሰጥቶ የማያልቅ አምላካዊ ፍቅር ተጋርተው፣ በእርሱ ፍቅር ፀንተው የሚኖሩ ፍጥረታትን ለመፍጠር ወሰነ፡፡ ፍጥረታት የእግዚአብሔር ፍቃድ መገለጫዎች ናቸውና፡፡ በመሆኑም ከብዝሐ ፍቅሩ፣ ከምዕዓተ ፍቅሩ የተነሳ የምናያቸውም ሆነ የማናያቸው ፍጥረታትን ፈጠረ፡፡

    ከእነዚህ ፍጥረታት ይልቅ ደግሞ እጅግ በረቀቀ አምላካዊ ጥበብ ተከውኖ አጋእዝተ ዓለም ሥላሴ "ንፍጠር ሰብአ በአርአያነ ወበአምሳሊነ፡-ሰውን በመልካችንና በምሳሌአችን እንፍጠር" በማለት የተፈጠረና የሕይወት እስትንፋስም ከፈጣሪ እፍታ /እፍ በማለት/ የተቀበለ የሰው ልጅ ብቻ ነው፡፡

    ሰማይና ምድር፣ ፀሐይና ጨረቃ፣ መላእክትና ሊቃነ መላእክት፣ ረቂቃንና ግዙፉን... ሁሉ በአጠቃላይ የተፈጠሩት በእግዚአብሔርትእዛዝ ነው፡፡ "ዘቦቱ ኩሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ፡- ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች እንኳ ያለ እርሱ የሆነ የለም" /ዮሐ. 1/ እንዲል፡፡ ይህም ማለት ለይኩን ብርሃን፣ ብርሃን ይሁን፣ ለታብቁል ምድር፣ ምድርም ታብቅል... /ዘፍ.1፡1-25/ በማለት መፍጠሩንና ፍጥረታት በፈጣሪ ትእዛዝ ፀንተውና ታንፀው የሚኖሩ መልካሞች እንደሆኑ ለማመስጠር ነው፡፡ ሁሉም ይሁኑ፣ ይገኙ ብሎ ባዘዘ ጊዜ ከመ ቅጽበት ዓይን በፍጹም ታዛዥነት አቤት ብለው ተገኝተዋልና ነው፡፡አንጻራዊ በሆነ መልኩ የሰው ልጅ ግን በከፍተኛ ክብርና አምላካዊ ጥበብ የተፈጠረ መሆኑን እንመለከታለን፡፡ ይኸውም ይታወቅ ዘንድ ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ "ንፍጠር ሰብአ" እያለ መናገሩ ከሰማያውያንም ሆነ ከምድራውያን ፍጥረታት ይልቅ በከበረ ሁኔታ መፈጠሩ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

    በዚሁ ሁኔታ የተፈጠረ የሰው ልጅ ከሌሎቹ ፍጥረታት ይልቅ የከበረ አዋቂ አእምሮ የተሰጠው እንደመሆኑም መጠን የተፈጠረባት ገነትን እንዲንከባከባትና ሌሎችን ፍጥረታት የበላይ ንጉሥ ሆኖ እንዲያስተዳድር አምላካዊ ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጠው፡፡ ይኸው ሰማያዊ ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችል ደግሞ ሌሎችን የሚመራበትም ይሁን ራሱን የሚመራበት ሕግ መኖር ስለነበረበት እግዚአብሔር ከሌሎቹ ይልቅ ለአዳም ሕግ ሰጠው፡፡ ይህንን ሕግ የፈጣሪን አዛዥነትና የፍጡርን ታዛዥነት፣ የአምላክን አስገኚነት የፍጡርን ተገኚነት ... ወዘተ የሚገለጽበት በመሆኑ በፍጹም ኃይሉ፣ በፍጹም ነፍሱ፣ በፍጹም ልቡ አክብሮ እንዲጠብቅ አደራ ጭምር ታዟል፡፡ ይህንን ባይጠብቅ የሞት ሞት እንደሚሞት ጭምር በማስጠንቀቅ /ዘፍ.2፡16-17/፡፡ ይሁን እንጂ አዳም የተሰጠውን ጸጋ አልበቃ ብሎት ያልተሰጠውን፣ ያልተፈቀደለትንና የማይቻለውን አምላካዊ ባሕርይ ፈልጎ አታድርግ የተባለውን አድርጎ፣ ጠብቅ የተባለውን ሽሮ... በመገኘቱ በአዳም ልቡና የተፈለገውንና የታሰበውን /አምላክ መሆኑን/ ሳይሆን ቀርቶ በፈጣሪ የተነገረውን ቃል ሊፈጸም ግድ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት የሞት ሞት ተፈርዶበት ከገነት ተባረረ፣ የተሰጠው ሰማያውያን ጸጋዎች ተገፈፈ /ተነጠቀ/፣ ዕርቃኑም እንደሆነ አወቀ፡፡ /ዘፍ.3፡7-8/

    ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር በዚህ መልክ አዳም ቢያጠፉም እንዲሁ ሊተወው ስላልፈለገና በርህራሄ ዓይኑ ስለተመለከተው ሕያው የምታደርግ ዛፍ /የሕይወት ዛፍ/ እንዳይበላና ዘላለማዊ ኃጢአተኛ እንዳይሆን ከእርሷ አራቀው፡፡ በሱራፊም አስወጣው፡፡ አዳም በዚህ ኃጢአት እጅግ ተጸጽቶ ወደ እግዚአብሔር አለቀሰ፣ መሪር በሆነ ሐዘንም ምሕረት ለመነ፡፡ ፍጥረታቱን የሚወድና የሚቀበል እግዚአብሔር ፍጠረኝ ሳይለው የፈጠረው አዳም አድነኝ ብሎ ሲለምነው በምሕረት ክንዱ ተቀብሎ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጠው፡፡ ይህንን የተስፋ ቃል ተቀብሎ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል ቆየ፡፡

    በዚህ ዘመን ውስጥ የነበሩ ሰዎች በሞት ሥጋ በሞት ነፍስ ተይዘው፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት ተለይተው የነበሩበት የመርገመ ሥጋ የመርገመ ነፍስ ዘመን ስለነበረ ዘመነ ፍዳተብሎ ይጠራል፡፡ ብስራተ ቅዱስ ገብርኤል መልአክመሐሪ ወመስተሳህል አምላካችን እግዚአብሔር መርገመ ፍዳ መርገመ ደይን አብቅቶ በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ በዓለም የሚያብብበት ዘመን በደረሰ ጊዜ ዓለምን የቤዛነት ዋጋ ከፍሎ ያድን ዘንድ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድያ ልጁን ላከ፡፡ /ዮሐ.3፡16/

    ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ እንደልጆች እንሆን ዘንድ ከሕግ በታች ያሉትን ይዋጅ ዘንድ /ገላ.4፡4/ እንዲል፡፡ ቤዛ የሚለው ቃል ቤዘወ ከሚል የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ቤዛ በቁሙ ዋጋ፣ ካሳ፣ ለውጥ፣ ምትክ፣ ኃላፊ፣ ዋቢ፣ ዋስ፣ መድን፣ ተያዥ፣ ጫማ፣ ጥላ፣ ጋሻ፣ ... ማለት ነው፡፡

    ቤዛ በደቂቅ አገባብ ሲፈታ ደግሞ ስለ፣ ፈንታ፣ ምክንያት ተብሎ ይፈታል፡፡ /አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡ 1948፡ ገጽ፡ 266/ በሌላ መልኩም ከሳቴ ብርሃን ተሰማ በመጽሐፋቸው ቤዛን ሲተረጉሙ ለውጥ፣ ካሣ፣ በአንድ ሰው መከራና ሞት ተላልፎ መሞት፣ ታዳጊን፣ ምትክን መሆን፣ ለሞት ለመከራ መለወጥ፣ መሥዋዕት፣ መገረፍ መሰቀል ማለት ነው ብለውታል፡፡ ቤዛ ዓለም ለሚለው ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዓለም ብሎ የአምላክነቱን ባሕርይ ከሥጋ ጋራ አዋሕዶ ለኃጢአታችን ተለውጦ ቤዛን መሆን ካሉ በኋላበቁሙ ሲተረጉሙም ቤዛ ማለት ካሣ፣ የደም ቤዛ፣ ዋጋ፣ አንዱ ሰው የሰውን ደም ስለአፈሰሰ ለውጥ ዋጋን፣ ገንዘብን፣ ካሣን፣ መስጠት መዋጀት ማለት ብለው አብራርተውታል፡፡ /ከሣቴ ብርሃን ተሰማ፡ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፡ 1951ዓ.ም፡ ገጽ 532/

    መድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነቱ ምስጢር የፈጸመው በአንድ ጊዜ አይደለም፡፡ ከብሥራቱ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያለው አምላካዊ ጉዞ ሁሉ የድኅነት ሥራ ደረጃ በደረጃ የተፈጸመበት ሰይጣን የሸሸበት የሕይወት መንገድ ነው፡፡

    በመሆኑም ለአዳም የገባለትን ቃል ኪዳን ይፈጸም ዘንድ ዘመነ ሐዲስ በደረሰ ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በንጽሕና ቤተ እግዚአብሔር ታገለግል ለነበረችው ለድንግል ማርያም ፈጣሪዋን እንደምትወልድ ካበሰራት በኋላ ከብዙ ምክክርና ክርክር በኋላ እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገረ የለም /ሉቃ.1፡36/ ብሎ መልአኩ አስረግጦ ሲነግራት እመቤታችን በእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት አጥብቃ ታምን ስለነበረ "ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ" እንዳልከኝ ይሁንልኝ ብላ ቃለ መልአኩን በፍጹም ትሕትና በተቀበለች ጊዜ "ይኩነኒ" ማለቷን ተከትሎ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርሰቶስ ማኅተም ድንግልናዋ ሳይለወጥ በፍጹም ተዋሕዶ ምስጢር ማኅፀንዋን ዓለም አድርጐ መጋቢት 29 ቀን በማኅፀንዋ አደረ፡፡ ሰው አምላክ፣ አምላክምሰው ሆነ፡፡ በዚህም ለዘመናት ተራርቀው የነበሩ ሰውና እግዚአብሔር አንድ ሆኑ፡፡

    በዚህ ሁኔታ የተጀመረውን ቃለ ብሥራት መላእክትና ሊቃነ መላእክት በመንበረ ጸባዖት ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ... እያሉ የሚያመሰግኑት አምላክ በማኅፀነ ድንግልም ተደገመ፡፡ ድንግልም ይህንን ምስጋና ጀሮዋን ወደ ማኅፀንዋ ጠጋ በማድረግ ታደምጥናበነገሩ ሁሉ እየተደነቀች የምታየውንና የምትሰማውን አስደናቂ የአምላክ ሥራ በልብዋ ትጠብቀው እንደነበር የቤተክርስቲያናችን መጻሕፍትና ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡

    ልደት አውግስጦስ ቄሳር የግዛቱ ሰዎች ሁሉ እንዲመዘገቡ ትእዛዝ አውጥቶ ስለነበረ ማርያምና ዮሴፍም ይህንኑ የንጉሥ ትእዛዝ ለመፈጸም ከናዝሬት ገሊላ ወደ ቤተልሔም ሄዱ፡፡ በዚያም እያሉ የእመቤታችን የመውለጃዋ ወራት ስለደረሰ በአካባቢው የሚገኙ ወገኖች እንዲያስጠጓቸው አብዝተው ቢጠይቋቸውና ቢለምኗቸውም የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር ፈቃደኛ ሊሆኑ ባለመቻላቸው ምክንያት ወደ በረት ተጠግታ ወለደችና በግርግም አስተኛችው፡፡ በቦታው የነበሩ እንስሳትም ፈጣሪያቸው መሆኑን አውቀው ትንፋሻቸውን ገበሩለት ማለትም አገለገሉት፡፡

    የነቢዩ የኢሳይያስን ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ሊያድናቸው የመጣላቸው እስራኤላውያን ሳያውቁትና ሳያከብሩት እንስሳቱ ግን ከእነርሱ ተሽለው አምላካቸውን አወቁ፣ ፈጣሪያቸውን አገለገሉ፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮአልና ሰማያት ስሙ ምድርም አድምጪ ልጆችን ወለድሁ አሳደግሁም እነርሱም ዐመፁብኝ በሬ የገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ አወቀ እስራኤል ግን አላወቀም፡፡ ሕዝቤም አላስተዋለም /ኢሳ. 1፡3/ እንዲል፡፡

    በሥጋዊ በደማዊ ሥርዓት የሚመሩ እንስሳት ፈጣሪያቸው መሆኑን አውቀው ለፈጣሪ የሚገባ ክብር ሲሰጡ በፈጣሪ መልክ የተፈጠሩትና አዋቂ አእምሮ የተሰጣቸው እስራኤላውያን ግን የእንግዳ ማረፊያ ይኖራቸው እንደሆነና መንፈሳዊነቱ ይቅርና በሰብአዊነት እንኳ ሁሉም /ሃይማኖት ያለውም ሆነ የሌለው/ የሚራራበትን የውልደት ሥርዓት ለማከናወን በልመና መልክ ቢጠየቁም ቤታቸው በተለያዩእንግዶች መሞላቱን ገልጸው እነርሱ በቤት ውስጥ ሆነው ፈጣሪያቸውን ውጭ አሳደሩ፡፡ ወደቤታቸው መጥቶ ልግባ ፈቀዱልኝ ብሎ ሲጠይቃቸው አንፈልግህም ብለው አርቀው አባረሩት፡፡ "እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድንጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል"፡፡ ራዕ. 3፡20 እንዲል፡፡

    የአከባቢው ሰዎች ከቤታቸው ቢያባርሩትም እንስሳቱ ግን እጅ ነስተው በረታቸውን ሰጡትና በዚያው ተወለደ፡፡ የብርድና የውርጭ ወራትም ስለነበረና እናቱም ልጇን የምታለብስበት በቂ ልብስ ስላልነበራት በዙርያው ከነበሩት ቅጠሎች ቆርጣ ካለበሰችው በኋላ ያም በቂ ስላልነበረ እግዚአብሔር አድሏቸው በቦታው የተገኙ እንስሳትም ግራ ቀኝ ተሰልፈው ትንፋሻቸውን በመስጠት ሕፃኑን እንዳይበርደው አድርጓል፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ነገሥታተ ተርሴስ ሲመራ የነበረውም ኮከብም በላያቸው ላይ መጥቶ አብርቷል፡፡ በአከባቢ ከብቶቻቸው በመጠበቅ ላይ የነበሩ እረኞችም በምሥጢረ ነገሩ ተገርመው እያለ አከባቢያቸው በፍፁም ብርሃን ተሞላ፡፡ ከዚህ ቀጥሎ መልአከ እግዚአብሔር ተገልፆ "እነሆ ለህዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ እነግራችኋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱ ክርስቶስ ተወልዶላችኋል" ብሎ ሲነግራቸው የተወለደውን ሕፃን ለማየት ወደ ከብቶቻቸው በረት ሲሄዱ እልፍ አእላፍ መላእክትና ሊቃነ መላእክት በሕብረት ሲያመሰግኑ ስላገኟቸው እረኞችም ከመላእክት ጋራ ሆነው " ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብእ፡- ምስጋና ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር ለሰው ልጆች ሁሉይሁን " እያሉ አብረው አመሰገኑ፡፡

    በዚህም ለዘመናት ተጣልተው /ተራርቀው/ የነበሩ ሰማያውያን መላእክትና ምድራውያን ሰዎች አንድ ሆነው ለእግዚአብሔር ክብር በመስጠት በመወለዱ ምክንያት የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ አብረው ዘመሩ፣ አብረው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፡፡ /ሉቃ. 2፡10-14/ይህንን አምላካዊ ወመጽሐፋዊ ትውፊት መሠረት በማድረግ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በታላቅ ዝማሬ፣ በማኅሌት፣ በቅዳሴ ... "ቤዛ ኩሉ ዓለም ዮም ተወልደ፡- የዓለም ሁሉ ቤዛ ዛሬ ተወለደ" እያለች የቤዛነቱን ምስጢር እየመሰከረች፣ እያተማረችና እያራቀቀች በታላቅ መንፈሳዊ ትሩፋትና ኢትዮጵያዊ ዜይቤ በየዓመቱ በዓለ ልደትን በደመቀ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በማክበር ላይ ትገኛለች፡፡ በዓሉ የምስጋናና የዝማሬ በዓል ነውና፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቤዛ ኩሉ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top