• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    በዓለ መስቀል


                 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀልን በዓል የምታከብረው መስከረም ፲፯ እና መጋቢት ፲ ነው። እነኚህም አይሁድ በክፋት ቀብረው ሰውረውት የነበረውን መስቀል ለማግኘት ቁፋሮ የተጀመረበት እና መስቀሉ የተገኘበት ዕለታት ናቸው። ክቡር መስቀሉ ከክርስቲያኖች ተሰውሮ የኖረው ለሦስት መቶ ዓመታት ነው።

    ፩፥፩ ክቡር መስቀሉ እንዴት ሊጠፋ ቻለ?

                 መስከረም ፲፮ እና ፲፯ የሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር፦ በክፋት የተመሉ አይሁድ፥ በጌታ መስቀል እና መቃብር ምክንያት ይፈጽሙ የነበሩትን አያሌ ተአምራት አይተው በምቀኝነት መነሣሣታቸውን ይተርካል። አይሁድ በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ እስከ ፷፬ ዓ.ም. ድረስ ምንም ኃይል አልነበራቸውም። ከ፷፬ ዓ.ም. በኋላ ግን ራሳቸውን ከሮማውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት በጀመሩት ዓመጽ ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠሩ። በዚህን ጊዜ ክርስቲያኖቹን ወደ ጌታ መስቀል እና መቃብር እንዳይቀርቡ ከልክለው ቦታውን የቆሻሻ መድፊያ አደረጉት። ከብዙ ጊዜ በኋላ ሥፍራው ትልቅ ጉብታ ሆኖ ከቦታው ጋር ተመሳሳለ። ከዚህም ጋር እሥራኤል በየጊዜው ይማርኩ ስለነበር፥ ከምርኮ ሲመለሱም የከተማይቱ መልክ ስለሚለዋወጥባቸው መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ጉብታ መለየት አልተቻለም። በተለይም ከ፩፻፴፪ - ፩፻፴፭ ዓ.ም. በተደረገው ጦርነት ኢየሩሳሌም ፈጽማ ጠፍታ ነበር። ዳግመኛም ንጉሥ ሐድርያን በ፩፻፴፭ ዓ.ም. ኢየሩሳሌምን በአዲስ ፕላን በመሥራቱና በጎልጎታ የቬነስን መቅደስ በመገንባቱ ክርስቲያኖቹ ምንም ማድረግ አልተቻላቸውም ነበር። ያን ጊዜ ጎልጎታ ከከተማዋ ውጪ ነበር፥ ዛሬ ግን በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም ክልል ይገኛል።

    ፩፥፪፦ መስቀሉ እንዴት ሊገኝ ቻለ?

               ክቡር መስቀሉን ፈለጋ ያገኘችው የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ኅሌኒ ናት። ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች ሙሉ ነፃነት የሰጠ የሮም ንጉሥ ነበር። ከዚያ በፊት ምንም ነፃነት አልነበራቸውም። ቆስጠንጢኖስ ለክርስቲያኖች የሰጣቸው መብት፦ ፩ኛ ቤተ ክርስቲያንን ከግብር ነፃ አደረጋት። ፪ኛ፦ ከመንግሥት ገቢ ለቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ድርሻ ሰጣት። ፫ኛ፦ ዕለተ እሑድ የክርስቲያኖች የበዓል ቀን በመሆኗ በግዛቱ ሥራ እንዳይሠራ በ፫፻፳፩ ዓ.ም. አወጀ። ፬ኛ፦ ለቤተ ክርስቲያን ኑዛዜ የመቀበልና ውርስ የመውረስ መብት ሰጣት። ፭ኛ በክርስቲያኖች መካከል ለሚፈጠሩ አንዳንድ አለመግባባት፥ ወንጀል ነክ ላልሆነ ጉዳይ ለኤጲስ ቆጳሳት የዳኝነት ሥልጣን ሰጣቸው። ፮ኛ፦ ክርስትና የአገሩ ብሔራዊ ሃይማኖት እንዲሆን አደረገ። በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያን የወንጌልን የመዳን መልእክት እያወጀች ሐዋርያዊ ጉዞዋን እንድትቀጥል ያደረገ ንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ነው። ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በመስቀል ምልክት የተደረገለት ተአምር ነበር። ይኸውም የሮምን የምዕራቡን ክፍል ይገዛ የነበረው ማክሴንዲዮስ የጦር ኃይሉን ባዘመተበተት ጊዜ፥ እርሱም በበኲሉ «ምታ ነጋሪት፥ ክተት ሠራዊት፤» ብሎ ለጦርነት ተዘጋጀ። ገና በጉዞ ላይ እንዳለም፦ «በዚህ ድል ታደርጋለህ፤» የሚል በመስቀል ቅርጽ የተጻፈ ጽሑፍ በጠፈረ ሰማይ አየ። በዚህም እየተመራ ሄዶ ድል አደረገ። በዚህን ጊዜ፦ ሠራዊቱ በፈረሱ አንገት፥ በጋሻው እምብርት መስቀላዊ ቅርጽ እንዲያደርግ አወጀ። ሮምን ሙሉ በሙሉ ጠቅልሎ መግዛት የጀመረው ከዚህ በኋላ ነው። ከዚያ በፊት ለአርባ ዓመታት ለአራት ተከፍላ በኋላም ለሁለት ተከፍላ ትተዳደር ነበር።

                እናቱ ንግሥት ኅሌኒ በልጇ ዘመን የተገኘውን የክርስትና ነፃነት ተጠቅማ በ፫፻፳፯ ዓ.ም. ክቡር መስቀሉን ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘች። በዚያም ጉብታ የሆነውን ሥፍራ ሁሉ በማስቆፈር ብዙ ብትደክምም መስቀሉን ለማግኘት አልቻለችም። በዚህን ጊዜ ኪራኮስ የተባለው አረጋዊ፦ «ደመራ አሰደምረሽ፥ ዕጣን አፍስሰሽበት፥ ብታቀጣጥይው ጢሱ ይመራሻል፤» ባላት መሠረት ሳትጠራጠር አደረገችው። የዕጣኑ ጢስ መስቀሉ ከተቀበረበት ጉብታ ላይ እንደ ቀስተ ደመና ተተክሎ በጣት ጠቅሶ የማሳየት ያህል አመለከታት። ቁፋሮውም መስከረም ፲፯ ተጀምሮ መጋቢት ፲ ተፈጸመ። የተገኙት ሦስት መስቀሎች ስለነበሩ የክርስቶስን መስቀል በተአምራቱ ለዩት። ዕውር አበራ፥ አንካሳ አረታ፥ ለምጽ አነጻ፥ ሙት አስነሣ። ንግሥቲቱም የከበረ ቤተ ክርስቲያን አሠርታ በክብር እንዲያርፍ አድርጋለች።

    ፪፦ መሰቀል፤

               ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ተላልፎ በመሰጠት ቅዱስ ሥጋውን የቆረሰበት፥ ክቡር ደሙንም ያፈሰሰበት መስቀል ሃይማኖታዊ ትርጉም አለው።

    ፪፥፩፦ ድኅነታችን የተፈጸመበት (መዳናችን የተረጋገጠበት) ነው፤

               «ኢየሱስም ሆምጣጣውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ፥ አለ፤» ይላል። ዮሐ ፲፱፥፴። በመስቀል ላይ የተፈጸመው ድኅነታችን (መዳናችን) ነው። ይኸውም የዕለት ፅንስ ሆኖ በማኅፀነ ድንግል ማርያም የጀመረውን የማዳን ሥራ ነው። ሉቃ ፩፥፴፩። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ «በእርሱም እንደ ቸርነቱ ብዛት በደሙ ድኅነትን አገኘን፥ ኃጢአታችንም ተሰረየልን።» ብሏል። መድኃኒት ከድንግል ማርያም መወለዱን ለእረኞች አስቀድመው የሰበኩት ቅዱሳን መላእክት ናቸው። ሉቃ ፪፥፲፩።

    ፪፥፪፦ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የተወገደበት ነው፤

                አዳምና ሔዋን ሕገ እግዚአብሔርን በመተላ ለፋቸው የወደቀባቸው የሥጋና የነፍስ መርገም ለሰው ልጅ በጠቅላላ ተርፎት ነበር። «ነገር ግን በአዳም ኃጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ (እስከ ክርስቶስ) የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው።» ይላል። ሮሜ ፭፥፲፬። ሙሴ ለክርስቶስ ምሳሌ ነው። በኦሪቱ እንደተጻፈው በእንጨት ተሰቅለው የሚሞቱ ርጉማን ነበሩ። ዘዳ ፳፩፥፳፫። ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው፥ ተብሎ ተጽፎአልና፤ ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ (መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን ስላመጣብን ኃጢአት ተላልፎ በመሠዋት) ከሕግ እርግማን ዋጀን።» በማለት ገልጦታል። ገላ ፫፥፲፫። ቅዱስ ጴጥሮስም፦ «እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ።» ብሏል። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፳፬።

    ፪፥፫፦ ዲያቢሎስ የተሸነፈበት ነው፤

                ጥንተ ጠላታችንን (ገነትን ያህል ርስት፥ እግዚአብሔርን ያህል አባት ያሳጣንን ዲያቢሎስን) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድል ያደረገልን በመስቀሉ ነው። «ጥልን በመስቀሉ ገደል፤» ይላል። ኤፌ ፪፥፲፮። ጥል የተባለው ለሰውና ለእግዚአብሔር መጣላት ምክንያት የሆነ ዲያብሎስ ነው። እኛም በኃይለ መስቀሉ ድል እያደረግነው የምንኖር ሆነናል።

    ፪፥፬፦ የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ነው፤

                የጥል ግድግዳ የተባለው ኃጢአት ነው። እርሱም ሰውና እግዚአብሔርን ለያይቷቸው ኖሯል። «በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለያይታለች፥ ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሠውሮታል።» ይላል። ኢሳ ፶፱፥፩። ይህ ከእግዚአብሔር ለያይቶን እግዚአብሔርን ሰውሮብን የኖረ የጥል ግድግዳ (በዲያቢሎስ ምክር የተሠራ ኃጢአት) የፈረሰው በመስቀል ላይ በተፈጸመ የክርስቶስ ቤዛነት ነው። «በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳ በሥጋው አፈረሰ፤» ይላል። ኤፌ ፪፥፲፭።

    ፪፥፭፦ እርቅ የተፈጸመበት ነው፤

               ሰውና እግዚአብሔር የታረቁት በመስቀል ላይ በተፈጸመ የክርስቶስ ቤዛነት ነው። ሰውና እግዚአብሔር በመታረቃቸው ነፍስና ሥጋ፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብም ታርቀዋል። እኛ በበድልን እርሱ ክሶ (የደም ካሣ ከፍሎ) ታርቆናል። «ጠላቶቹ ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን።» ይላል። ሮሜ ፭፥፲፣ ፪ኛ ቆሮ ፭፥፲፰፣ ኤፌ ፪፥፲፮፣ «ሁሉንም በእርሱ ይቅር ይለው ዘንድ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ደም በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ።» የሚልም አለ። ቆላ ፩፥፳።

    ፪፥፮፦ አምላካዊ ይቅርታ የተገኘበት ነው፤

               «አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።» በማለት ገርፈው የሰቀሉትን በቃሉ ይቅር ብሎአቸዋል። ሉቃ ፳፫፥፴፬። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ፦ በሞቱ የሰውን ዘር በጠቅላላው ይቅር እንዳለው ሲናገር፦ «አሁን ግን በፊቱ ለመቆም የተመረጣችሁና ንጹሓን፥ ቅዱሳንም ያደርጋችሁ ዘንድ በሥጋው ሰውነት በሞቱ ይቅር አላችሁ።» ብሏል። ቈላ ፩፥፳፪።

    ፪፥፯፦ አምላካዊ ሰላም የተሰጠበት ነው።

                ነቢዩ ኢሳይያስ፦ «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም (ወልድ) ተሰጥቶናልና፥ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።» በማለት ትንቢት የተናገረለት አምላክ ፍጹም ሰላምን የሰጠን በመስቀሉ ላይ በፈጸመው ቤዛነት ነው። ኢሳ ፱፥፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ «መጥቶም ቀርበን ለነበርነው ሰላምን፥ ርቃችሁ ለነበራችሁት ለእናንተም ሰላምን ሰጠን።» ብሏል። ኤፌ ፩፥፲፯።

    ፪፥፰፦ የእግዚአብሔር ፍቅር የተገለጠበት ነው።

               ጌታችን የማታ ተማሪ የነበረውን ኒቆዲሞስን ሲያስተምረው፦ «እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፤» ብሎታል። ዮሐ ፫፥፲፮። ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ የጻፈውን የጌታን ትምህርት መሠረት አድርጎ፦ «በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅሩ በእኛ ላይ ታወቀ፥ በእርሱ በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና። የእግዚአብሔርም ፍቅሩ ይህ ነው፥ እርሱ ወደደን እንጂ እኛ የወደድነው አይደለንም፥ ኃጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ ልጁን ላከው።» ብሏል። ፩ኛ ዮሐ ፬፥፱-፲፩።

    ፪፥፱፦ የገነት በር የተከፈተበት ነው፤

               ጌታችን ወደዚህ ዓለም የመጣው፥ ድኅነተ ምዕመናንንም በመስቀል ላይ የፈጸመው ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ተዘግታ የነበረችውን ገነትን ለመክፈት ነው። ይህም ይታወቅ ዘንድ፥ በቀኙ ተሰቅሎ፥ «አቤቱ በመንግሥትህ በመጣህ ጊዜ አስበኝ፤» እያለ ሲማጸነው የነበረውን ወንበዴ፦ «እውነት እልሃልሁ፥ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ፤» ብሎታል። ሉቃ ፳፫፥፵፪-፵፫።

    ፪፥፲፦ በመስቀሉ እንመካለን፤

                ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ «ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት (ዓለም በእኔ ዘንድ ሙት የሆነበት)፥ እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት (እኔም በዓለም ዘንድ ሙት የሆንኩበት)፥ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር  ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ፤» ብሏል። ገላ ፮፥፲፬። በመሆኑም ዓለምና ቅዱስ ጳውሎስ በጌታ ደም ላይ በተመሠረተች ቤተ ክርስቲያን እና በደሙ በጸናች ወንጌል ምክንያት ተለያይተዋል። አንዳቸው ለአንዳቸው ሙት ናቸው። ዓለም ሕያው የሆነችልን፥ እኛም ሕያው የሆንላት የሚመስለን የዓለም ፈቃድ ፈጻሚዎች ከቅዱስ ጳውሎስ ልንማር ይገባል። ዓለም ታልፋለች፥ እኛም እናልፋለንና።

    ፪፥፲፩፦ በመስቀሉ ከአጋንንት ጦር እንድናለን፤

               ቅዱስ ዳዊት በትንቢት፦ «ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው፥ ከቀስት ፊት (ከአጋንንት ጦር ) ያመልጡ ዘንድ ወዳጆችህም እንዲድኑ።» ያለው ስለ መስቀል ነው። መዝ ፶፱፥፬። በመሆኑም በመስቀል ምልክት አማትበን፥ ከአጋንንት ፈተና እንድናለን።

    ፪፥፲፪፦ መስቀል ኃይላችን ነው፤

               መስቀልን በእጅ መጨበጥ፥ በአንገት ማንጠልጠል፥ መሳለም በዓለም ዘንድ ሞኝነት ነው፥ ለክርስቲያኖች ግን የእምነት ሥራ ነው። «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።» ፩ኛ ቆሮ ፩፥፲፰። በመሆኑም በቀራንዮ በመስቀል ላይ አንድ ጊዜ የተገለጠ ኃይለ እግዚአብሔር እስከ ዘለዓለሙ አይለየንም።

    ፪፥፲፫፦ ለመስቀሉ እንሰግዳለን።

               ቅዱስ ዳዊት፦ «እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን።» በአለው መሠረት የጌታችን እግሮች በመስቀል ላይ፥ ያውም በቀኖት ላይ ስለቆሙ ለመስቀሉ እንሰግዳለን። መስቀሉን በደሙ ቀድሶታልና፥ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንሰጣለን። እግዚአብሔር በረድኤት በደብረ ሲና ራስ በቆመ ጊዜ፥ «ወደዚህ አትቅረብ፥ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደሰች ናትና፥ ጫማህን ከእግርህ አውጣ፤» በማለት ሙሴን አስተምሮታል። ዘዳ ፫፥፭። እንኳን ፈጣሪ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል እንኳ የቆመበትን መሬቱን፥ አፈሩን በመቅደሱ፦ «አንተ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግር አውልቅ።» በማለት ኢያሱን ሲያዘው እርሱም የታዘዘውን ሲያደርግ እናገኛለን። ኢያ ፭፥፲፭።

              እንግዲህ መሬቱን፥ አፈሩን የቀደሰ አምላክ ፦ ሥጋውን የቆረሰበትን፥ ደሙን ያፈሰሰበትን፥ ነፍሱንም አሳልፎ የሰጠበትን መስቀል አልቀደሰውም ለማለት እንዴት ይቻላል? ፈጽሞ አይቻለም። የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፥ የመስቀሉ በረከት አይለየን፥ አሜን።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በዓለ መስቀል Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top