ተዋዳጆች ሆይ! ዛሬ የምንማማረው በእንተ ፍልሰታ ለማርያም አይደለም፡፡ ስለ ራሳችን ፍልሰታ እንጂ፡፡ ኹላችንም ስለ እመቤታችን ፍልሰታ የመናገር ችግር የለብንም፡፡ ዛሬ እንድንማማርና እንድንወቃቀስ የፈለግኹት በሕይወታችን ከግብርናተ ዲያብሎስ ወደ ክርስቶስ ሳንፈልስ (ሳንሻገር) የእመቤታችንን ፍልሰታ ብቻ ለምናከብር ለየኔ ቢጤዎች ነው፡፡
እስኪ ከኹሉም አስቀድመን ለራሳችን ይኽን ጥያቄ እንጠይቀው፡፡ “በሕይወት ዘመኔ ስንት የፍልሰታ አፅዋማት አለፉ? እኔስ በዚኹ ጉዳይ ስንት ጊዜ ተናገርኩ? ስለዚኹ በዓል ለማወቅ መጓጓቴ ለማያውቁትም የማውቀውን ያኽል መናገሬ ክፋት ባይኖረውም እኔ ራሴስ ምን ለውጥ አመጣኁ? ምን ፍሬ አፈራኁ? ስለ ፍልሰታ እየተናገርኩ እኔ ራሴ ሳልፈልስ ስንት ዘመናት አለፉ? ከአገልግሎቴ ምን ረብሕ አገኛችኁ?”
ተወዳጆች ሆይ! እውነት ነው ምንም ሳንለወጥ ብዙ ዘመናትን አሳልፈናል፡፡ እኛ በሕይወት ሳንሻገር ብዙ የመሻገር (የፋሲካ) በዓላትን አክብረናል፡፡ እኛ ሳንነሣ ብዙ የመነሣት (የትንሣኤ) በዓላትን አክብረናል፡፡ እኛ በሕይወት ሳንፈልስ ብዙ የፍልሰታ በዓላትን አክብረናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለእንደዚኹ ዓይነት ምልልሳችን እንዲኽ ነው የሚለን፡- “ቀንንና ወርን ዘመንንም ዓመትንም በጥንቃቄ ትጠብቃላችኁ፡፡ ምናልባት በከንቱ ለእናንተ ደክሜአለኹ ብዬ እፈራችኋለኹ” /ገላ.፬፡፲-፲፩/፡፡ በዓላትን የምናከብራቸው ቀናትን፣ ወራትን፣ ወይም ዘመናትን ለማክበር አይደለም፡፡ እነዚኽን በዓላት ምክንያት አድርገን ራሳችንን የበለጠ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ ነው፡፡ እነዚኽን በዓላት ምክንያት አድርገን የእግዚአብሔር ቸርነቱን ለእኛም ያለውን ፍቅሩን ተረድተን እንድናመሰግነው ነው፡፡ ፍልሰታ ለማርያምን የምናከብረው በእመቤታችን ላይ የምንጨምረው ነገር ስላለ አይደለም፡፡ ፍልሰታን የምናከብረው እንደ እመቤታችን እንኳን ባይኾን የዓቅማችንን ያኽል በዚኽ ጊዜአዊ መቆያችን እስካለን ድረስ በንጽሕና በቅድስና ከምንም በላይ ደግሞ እግዚአብሔርን በፊደላት ሳይኾን በሕይወታችን ዐውቀነው አጣጥመነው የምንኖር ከኾነ ትንሣኤ፤ ፍልሰት እንዳለን እንድናውቅ ነው፡፡
ይኽን ግምት ውስጥ ባላስገባ መንገድ የምናከብረው ከኾነ ግን የእስከ አኹኑ ምልልሳችን አይሁዳዊ ምልልስ ነበር ማለት ነው፡፡ እንዴት? አይሁዳውያን ሕገ ኦሪትን የተሰጠቻቸው ኃጢአታቸውን በርሷ መስታወትነት ዐይተው ንስሐ እንዲገቡባት ስትሰጣቸው፥ እነርሱ ግን የንስሐ ፍሬ ሳያፈሩባት እንዲኹ ስለተመኩባት ለሕይወት የተሰጠቻቸው ሕግ ሞት ኾና አግኝቷታልና፡፡ እኛም እንዲኽ ለኵነኔ ያይደለ ለጽድቅ የተሰጠችን ወንጌል ፍሬ የማናፈራበት ከኾነ ክርስቶስን ከማያውቁ አይሁዳውያን የባስን ነን፡፡
እስኪ አንድ ምሳሌ አንሥተን እንማማር፡፡ አንድ የእግር ኳስ ክለብ በየጊዜው ተጋጣሚውን እንደምን ማሸነፍ እንዳለበት ልምምድ የሚያደርግ ከኾነ ክኅሎቱ ይዳብራል፡፡ ተጋጣሚውንም በቀላሉ ማሸነፍ ይቻሏል፡፡ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚጫወቱ ክለቦች በየአገሩ እየዞሩ አቋማቸውን እየለኩ ያሉት በቀጣዩ ዓመት ለዋንጫ የሚያበቃቸውን ውጤት ለማምጣት እንጂ ተጨዋቾቹ ዕረፍት ማድረግ ስላልፈለጉ አይደለም፡፡ እኛስ! ፍልሰታን የምናከብረው ለምንድነው? እንደ እመቤታችን መነሣት እንዳለ እንድናውቅ ያንንም ሕይወት ገንዘብ ለማድረግ ወይስ እንዲኹ ልማድ ስለኾነብን? ለምንድነው የምንጦመው? ይኽ ጥያቄአችን ወደ ቀጣዩ መፍትሔ ያመራናል!!!
ክርስትና ጠቅላላ ዕውቀት አይደለም፤ እኛ በክርስቶስ ክርስቶስም በእኛ ኾኖ እግዚአብሔርን ማምለክ ነው እንጂ፡፡
እግዚአብሔርን ማምለክ ሲባልም በንግሥ በዓላት ላይ መሳተፍ፣ መዝሙር ወይም ማኅሌት ወይም ሰዓታት ላይ መሳተፍ፣ መጸለይ፣ መጦም፣ አስራት በኵራትን ማውጣት አይደለም፡፡ እነዚኽ ኹሉ ከእውነተኛ አምልኮአችን በኋላ የሚከተሉ ናቸው፡፡ ስለዚኽ እውነተኛ አምልኮ ከዚኽ የሚያልፍ (ከፍ የሚል) ነው፡፡ እውነተኛ አምልኮ እግዚአብሔር እኛን ምን ያኽል እንደሚያፈቅረን ማወቅ ነው፡፡
አዳም በኤደን ገነት ውስጥ ሳለ እግዚአብሔርን ያውቀው ነበር፤ መፍቀሬ ሰብእ እንደኾነ፡፡ በበደለ ጊዜ ግን ዓይነ ልቡናው ታወረ፡፡ እግዚአብሔር ስለ ፍቅሩ አዳምን ሲፈልገው ሲሸሽ የነበረውም በዚኹ ምክንያት ነው፡፡ ድምጹን እንኳን መስማት የተሳነው የእግዚአብሔርን ፍቅር አልረዳ ብሎ ነው /ዘፍ.፫፡፲/፡፡ እግዚአብሔር ግን በባሕርዩ ፍቅር ነውና ሰዎች ፍቅሩን እንረዳለት ዘንድ ይሻል፡፡ መጽሐፍ ቅዱሳችንን በሙሉ ስናነብ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር ምን ያኽል የሰው ፍቅርን እንደተጠማ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ አብርሃምን ሲፈልግ የነበረው፣ በቤቱ ውስጥ ገብቶ ማዕድን ሲበላ የነበረው፣ ከነ ይሥሐቅ ጋር የተወዳጀው፣ ከእነ ያዕቆብ ጋር ሲታገል ያደረው፣ ከእኔ ሙሴ ጋር በሲና ተራራ ፵ ቀንና ሌሊት ሲጨዋወት የነበረው ፍቅሩን የሚረዳለትና የሚያውቅለትን ሰው ፍለጋ ነው፡፡
እስራኤላውያን ፍቅሩን ይረዱለት ዘንድ ሕጉን በሙሴ በኵል ሰጣቸው፡፡ ሕጉም ገና ሲዠምር፡- “አነ ውእቱ እግዚአብሔር ዘአውፃእኩከ እምድረ ግብጽ እምቤተ ቅንየት - ጽኑ አገዛዝ ከምትገዛበት ከግብጽ አገር ያወጣኹኅ ፈጥሬ የምገዛኅ እግዚአብሔር እኔ ነኝ” ነው የሚለው /ዘጸ.20፡2/፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ የሚሻው ተቀዳሚ ነገር ርሱን እንድናውቀው ነው ማለት ነው፡፡ ስናውቀው ፍቅሩን እንረዳለታለን፤ ደግሞም እንወዷለን፡፡ በነቢዩ ሆሴዕ አድሮ የተናገረውም ቢኾን፡- “ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን ከሚቃጠልም መሥዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወድዳለኹና” ነው የሚለው /ሆሴ.፮፡፮/፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን ከመስገዳችን በፊት፣ ከመጦማችን በፊት፣ ከመጸለያችን በፊት፣ ሰዓታት ከመቆማችን በፊት፣ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት እግዚአብሔር እንድናውቀው ይፈልጋል፡፡
ክብር ይግባውና ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚኽ ምድር የመጣውም ለሌላ ዓላማ አይደለም፤ የሰው ፍቅር ጠምቶት እንጂ /ዮሐ.፬፡፯/፡፡ ጌታችን ከኀጢአት በቀር የእኛን ባሕርይ የተዋሐደው እኛ ከርሱ ጋራ እንድንዋሐድ ነው፡፡ የሰውነቱ ሕዋሳት ሲያደርገንም የአብ ፍቅሩ እንደምን ጥልቅ እንደኾነች እንድንረዳ ነው፡፡ አብ አንድያ ልጁን እስኪሰጠን ድረስ እንደወደደን እንድናውቅ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በበዓለ ኃምሳ የተሰጠን ፍቅሩን ተረድተንለት በፍቅሩ ኖረን በእውነት ወዳጃችን እንደኾነ ዐውቀን በሕይወት እንድንኖርለት ነው፡፡ ልጅነትን አግኝተን በወይን ክርስቶስ ውስጥ ቅርንጫፍ የኾንነው የወልድን የባሕርይ ልጅነት በጸጋ ተካፋይ እንድንኾን ነው፡፡ አባ አባት ብለን እንጠራው ዘንድ የልጅነትን ሥልጣን የሰጠን ስለዚኹ ነው፡፡ በዚኽም ማንም ፍጥረት ሊደርስበት የማይችል የአባትነት ፍቅሩን እንድንረዳ ነው፡፡
በቅዱስ ቁርባን ክርስቶስ በእኛ እኛም በክርስቶስ ነው የምንኾነው፡፡ ከዚኽም የተነሣ አብን እናውቋለን፡፡ ምክንያቱም ከወልድ በቀር አብን የሚያውቀው ስለሌለ /ማቴ.፲፩፡፳፮/ ወልድ ደግሞ በለበሰው ሥጋ ከእኛ ጋራ ስለተዛመደና እኛም ከርሱ ጋራ ስለተዛመድን በርሱ በኩል እግዚአብሔር አብን እናውቋለን፡፡ ገና ስንዠምር እውነተኛ አምልኮ ያለውነውም በዚኹ ተፈጻሚነቱን ያገኛል፡፡
የሰው ልጆች አጥተነው የነበረው እውነተኛ ሥርዓተ አምልኮታችን በክርስቶስ (በቅዱስ ቁርባን) በኵል ተመልሶልናል፡፡ አስቀድመን እንደተናገርን ቀዳማዊ አዳም እግዚአብሔርን ከማወቅ ርቆ መታዘዝን እምቢ ብሎ ነበር፡፡ ክርስቶስ ግን ለአባቱ በመታዘዝ እውነተኛ አምልኮአችንን መልሶልናል፡፡
ርግጥ ነው በቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔርን እናውቋለን፡፡ በቅዱስ ቁርባን ግን በልጁ ደም ከርሱ ጋር እንታረቃለን፤ ርሱ በእኛ እኛም በርሱ እንኾናለንና ከየትኛውም መንገድ በላይ እናውቋለን፡፡ የኤማሁስ መንገደኞችን እናስታውሳቸው! የኤማሁስ መንገደኞች ጌታችን ከሙሴ እስከ ነቢያት ያሉ መጻሕፍትን ሲነግራቸው ልባቸው ይቃጠልባቸው ነበር፡፡ ከነርሱ ጋር እራት በበላ ጊዜ ግን ዓይኖቻቸው ተከፈተ፤ ክርስቶስንም ዐወቁት /ሉቃ.፳፬፡፴፪/፡፡
ታድያ እኛ እግዚአብሔርን በእውነት እያመለክነው ነው ወይ? በሌላ አገላለጥ ክርስቶስ በእኛ እኛም በክርስቶስ ውስጥ አለን ወይ? አብን ማወቅ የምንችለው የክርስቶስ ሕዋሳት የኾንን እንደኾነ ብቻ ነው፤ ወልድን የምናውቀው ብልቶቹ እንደኾንን ብቻ ነው፤ መንፈስ ቅዱስንም እንደዚኹ፡፡ ታድያ እግዚአብሔርን የምናወቀው በፊደላት ነው፥ ወይስ በእውነት በክርስቶስ ውስጥ ኾነን ማለትም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል? በዚኽ ፍልሰታ ምን አስበናል አኹንም እንደ አምና እንዲኹ በዘልማድ ለማክበር? እንዲኽስ ከቶ አይኹን!!! እስኪ ከንስሐ አባቶቻችን ጋር እንማከርና ፍልሰታን በእውነት ፍልሰታ ለማርያም ብቻ ሳይኾን ለእኛም እናድርገው፡፡ ይኽን እንድናደርግ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን መላዕክት ተራዳኢነት ይርዳን አሜን!!!
0 comments:
Post a Comment