• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday, 14 November 2015

    ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ


    እጅግ አስተማሪ ሕይወት ያላቸው እውነተኛ እረኛ ናቸው፡፡ በትምህርታቸው የማይማረክ ጽሑፋቸውንም አንብቦ የማይመሰጥ የለም እኝህ አባት ስማቸው ከግብጽ አልፎ በዓለም የገነነ ነው ፡፡ ሕይወታቸው እጅግ ስለሚማርክና ከቤተ ክርስቲያን አልፈው ለግብጽ ባበረከቱት አስተዋጽዖ ባረፉበት ወቅት መላው ግብጽ አዝኖ ነበር፡፡ እኝህ አባት የግብጽ ፓትሪያሪክ አባታችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ናቸው፡፡ እኛም ለአገልጋዮች መልካም የሆነ ገድላቸውን ቢሰማ መልካም ነውና ታሪካቸውን ይዘን ቀርበናል መልካም ንባብ ።

    አረብ አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ድል በነሳበት በመስቀሉ ፍቅር በገዛን ዕለት በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በዕለተ ዐርብ ሐምለ 27 ቀን 1915 ዓመተ ምህረት በኮፕቲክ አቆጣጠር በዕለተ አርብ አቢብ 27 ቀን 1639 ዓመተ ሰማዕታት እኤአ ኦገስት 3 1923 ዓም በላዕላይ ግብጽ አስዩት አብኑብ በተባለ ቦታ የኮፕቲክ ብርሀን የ ሊቀ ዲያቆናት ሐቢብ ጊዮርጊስ ፍሬ ለቤተሰቦቻቸው የመጨረሻ ልጅ ሆነው የተወለዱት ወላጆቻቸው የሰጧቸው ስም ናዚር ጋዪድ የሚል ነበር፡፡ ገና በተወለዱ በጥቂት ቀናት ውስጥ እናታቸውን ያጡት ሺኖዳ ከአምስት እኅቶቻቸው እና ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር ብቻቸውን ቀሩ፡፡ በ ልጅነታቸው በጣም የተረጋጉ ና አስተዋይ ነበሩ።የመጀመርያውን ትምህርት በዳማንሁር ባንሐ ካይሮ የተከታተሉ ሲሆን ከካይሮ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በታሪክ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ ወሰዱ፡፡ ከዚያም ከኮፕቲክ ሴሚናሪ በነገረ መለኮት የመጀመረያ ዲግሪ አግኝተው በዚያው ሴሚናሪ የብሉይ እና የሐዲስ ኪዳን መምህር ሆኑ፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያንን ከድካም ያበረታት ሐቢብ ጊዮርጊስ የሰንበት ት/ቤቶችን እንቅስቃሴ ሲጀምር ዋናው የተልዕኮው አንቀሳቃሽ ሺኖዳ ነበሩ፡፡ እርሳቸው በዚያ ወቅት የኮፕቲክ ወጣቶች ኅብረትን መሠረቱ፡፡ ለሰንበት ት/ቤቶች መጽሔቶች የተለያዩ ጽሑፎችን በማበርከት ወጣቱን ያበረቱት ነበር፡፡ በኋላ ዘመን የመንፈስ አርነት ተብሎ የታተመው መጽሐፋቸው የእነዚህ መጣጥፎች ስብስብ ነው፡፡
    በሐምሌ 18 ቀን 1954 ዓም እኤአ በዋዲ ኤል ናትሩን ወደሚገኘው የሶርያውያን ገዳም ገብተው ምንኩስናን ተቀበሉ፡፡ የገዳሙ አበ ምኔት እንጦንስ የሚል ስም ሰጧቸው፡፡ በዚያ ገዳም ሺኖዳ አያሌ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ማንበባቸው ይነገራል፡፡ በመነኮሱ በዓመታቸው ክህነት ተቀብለው ቄስ ሆኑ፡፡ ሺኖዳ ከምንም በላይ ለምንኩስና እና ለምናኔ ሕይወት ልዩ ትኩረት አላቸው፡፡ በእርሳቸው ዘመን በግብጽ የነበሩት እና ለግብጻውያን ገዳማዊ ሕይወት እንደገና ማንሠራራት ታላቅ አስተዋጽዖ ያደረጉት የኢትዮጵያዊው አብዱል መሲሕ (ገብረ ክርስቶስ) ደቀ መዝሙር ነበሩ፡፡ የገብረ ክርስቶስን ፍጹማዊ መንገድም ለመከተል ይጥሩ ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ለብዙ ዓመታት የኖሩትም በተባሕትዎ ነበር፡፡ መጀመርያ ከገዳሙ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አንድ ዋሻ ውስጥ ተቀመጡ፤

    በመቀጠልም ከገዳሙ ዐሥር ኪሎ ሜትር ወደ ሚርቅ እና በባሕር አል ፋሪግ ወደሚገኝ ዋሻ ገብተው ተጋድሎዋቸውን ቀጠሉ፡፡
    ባሕታዊው የተሰኘውንና በኋላ እኤአ በ1954 የታተመውን ቅኔያቸውን የጻፉት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ በ1959 እኤአ ቄርሎስ ስድስተኛ ልዩ ጸሐፊያቸው አድርገው ሾሟቸው፡፡ ሺኖዳ ግን ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ከገዳማቸው መውጣት እና በኣታቸውን መልቀቅ አያስደስታቸውም ነበር፡፡ ብዙ ጊዜያቸውንም የሚያሳልፉት በዋሻቸው ውስጥ በጸሎት እና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነበር፡፡ ለብዙ ጊዜያትም ወደ ኤጲስ ቆጶስነት እንዳይጠሩ ሲከላከሉ ኖረዋል፡፡ በ1962 እኤአ ሺኖዳ በነበሩበት ገዳም ውስጥ አንድ አስተዳደራዊ ችግር ተፈጠረ፡፡ ጉዳዩም ወደ ፓትርያርክ ቄርሎስ ስድስተኛ ዘንድ ቀረበ፡፡ በዚያ ጊዜ ሺኖዳ በገዳሙ አስተዳደር ውስጥ ነበሩበት፡፡ ገዳማውያኑ እንደ ጥንቱ አበው ሆነው እንዲኖሩ፣ ገዳማት የችግር ቦታዎች ሳይሆኑ የጸሎት ቦታዎች እንዲሆኑ፤ የግብጽ ገዳማት አዲሱን ትውልድ ለመቀበል በሚችሉበት መንገድ እንዲደራጁ፤ ገዳማውያኑ ሥራ፣ ጸሎት እና ትምህርትን አጣምረው እንዲይዙ ይታገሉ ነበር፡፡ ይህ የሺኖዳ ሃሳብ
    ያልተስማማቸው አንዳንድ ገዳማውያንም ሺኖዳን ከስሰው ወደ ቄርሎስ ዘንድ አቀረቧቸው፡፡ አቡነ ቄርሎስ ስድስተኛ ሺኖዳን አስጠሯቸው፡፡ ሺኖዳ በቄርሎስ እግር ሥር ተደፍተው «አጥፍቻለሁ፣ ድሮም ኃላፊነቱን የተቀበልኩት ያለ ዐቅሜ ነው፡፡ እባክዎ ከኃላፊነት ያንሱኝና በዋሻዬ ብቻ ተወስኜ ልኑር፡፡ እኔ ደካማ ሰው ነኝ» ሲሉ ለመኗቸው፡፡ ቄርሎስም «ዛሬ እንደርና ነገ ውሳኔዬን አሳውቃለሁ» አሉ፡፡

    በማግሥቱ መስከረም 30 ቀን 1962 ዓም እኤአ ፓትርያርክ ቄርሎስ እና ሌሎች ጳጳሳት የሺኖዳን ጉዳይ ለማየት በመንበረ ፓትርያርኩ ተሰባሰቡ፡፡ ሺኖዳ ውሳኔውን በጉጉት ነበር የጠበቁት፡፡ ኃላፊነት ከሚባለው ነገር ተገላግለው የምናኔ ሕይወታቸውን ብቻ ለመያዝ ፈልገዋል፡፡ ሺኖዳ ተጠሩ፡፡ ጳጳሳቱ ቆሙ፡፡ ሁሉም ቄርሎስን ያይ ነበር፡፡ ሺኖዳ እንዲንበረከኩ ተነገራቸው፡፡ ተንበረከኩ፡፡ ቄርሎስ እጃቸውን በሺኖዳ ላይ ጫኑ፡፡ ሌሎች ጳጳሳትም ወደ እርሳቸው መጡ፡፡ ሳይታሰብ አቡነ ሺኖዳ ተብለው የግብጽ የመንፈሳውያን ኮሌጆች እና የትምህርት ተቋማት ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ ሺኖዳ ደነገጡ፡፡ አለቀሱም፡፡ በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥናት በማድረግ የታወቀው የካይሮ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ጀርመናዊው ኦቶአ ሜናድረስ የአቡነ ሺኖዳን መሾም ሲሰማ እንኳን ደስ ያለዎት የሚል ደብዳቤ ላከላቸው፡፡ ሺኖዳ ግን የመለሱለት የሚከተለውን ነበር « የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እና ሰላም ካንተ ጋር ይሁን፡፡ እንኳን ደስ ያለዎት ብለህ በቅንነት ስለላክህልኝ መልእክት አመሰግንሃለሁ፡፡ ያንተን ወዳጅነት እና ፍቅር መቼም አልዘነጋውም፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን ለእኔ መላክ ያለበት የኀዘን ደብዳቤ እንጂ የደስታ ደብዳቤ አይደለም፡፡ አንድ መነኩሴ ጸጥታ የተሞላበትን የጸሎት በረሃ ለቅቆ ጫጫታ እና ሁካታ በተሞላበት ከተማ እንዲኖር ሲደረግ እንዴት እንኳድ ደስ ያለህ ይባላል? ማርያምን ከክርስቶስ እግር ሥር ተነሥታ ማርታን ልታግዝ ወደ ጓዳ ስትገባ ማነው እንኳን ደስ ያለሽ የሚላት? ለእኔ ይህ ደስታ ሳይሆን ሀፍረት ነው፡፡ እኔ ኤጲስ ቆጶስ ሆኜ የተሾምኩበትን ቀን በደስታ ሳይሆን በኀዘን እና በለቅሶ ነው የማስታውሰው፡፡ ብሕትውና እና የተጋድሎ ጸሎት ከምንም በላይ የሚበልጥ ነገር ነው፡፡ ብሕትውና እና ምናኔ ከኤጲስ ቆጶስነት ቀርቶ ከፓትርያርክነት ጋር እንኳን የሚወዳደር አይደለም፡፡ «ወዳጄ ሆይ እውነተኛው ቅድስና ሲመት ሳይሆን ልብን ቤተ መቅደስ አድርጎ ለክርስቶስ መቀደስ ነው፡፡ ክርስቶስ በመጨረሻው ቀን የልባችንን ንጽሕና እንጂ የክህነታችንን መዓርግ አይጠይቀንም፡፡ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልህ በምወድዳት ዋሻዬ፣ በባሕር አል ፋሬግ፣ በዋዲ ኤል ናትሩን ውስጥ ሆኜ ነው፡፡ እዚህም እስከ ጥምቀት ድረስ ለመቆየት አስባለሁ፡፡ ከዚያም ወደ ካይሮ እመለሳለሁ፡፡» አቡነ ሺኖዳ እያለቀሱ ያቺን የዋዲ ኤል ናትሩን ዋሻ ትተው ካይሮ ቢመጡም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወደ ዋሻቸው መሄድ ያዘወትሩ እንደ ነበር ታሪካቸውን የጻፈላቸው የቅርብ ወዳጃቸው እና
    በእምነቱ ፕሮቴስታንት የነበረው ኦቶአ ሜናድረስ ይናገራል፡፡ እስከ 1969 እኤአ ድረስ የቤተ ክርስቲያኒቱን የትምህርት ተቋማት በዘመናዊ መልኩ አደራጇቸው፡፡
    በዚህ የተነሣም በሙሉ ጊዜያቸው የሚማሩ ተማሪዎች ቁጥር ከአንድ መቶ ወደ 207 አደገ፡፡ ሺኖዳም በየሳምንቱ ዓርብ ዓርብ ሕዝቡን የሚያስተምሩበት እና የሕዝቡን ጥያቄዎች የሚመልሱበት የትምህርት መርሐ ግብር ከፈቱ፡፡ እስከ አሥር ሺ የሚጠጋ ሕዝብም መርሐ ግብሩን ይከታተለው ነበር፡፡ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች የሚሆኑ መጻሕፍትን፣ መዝሙሮችን እና ትምህርቶችን ያዘጋጁ
    ነበር፡፡ የሰንበት ትምህርት ቤት መምህራንንም ያሠለጥኑ ነበር፡፡ በዚህ የሥራ ብዛት ውስጥ እያሉ እንኳን የሳምንቱን ግማሽ በካይሮ ቀሪውን ደግሞ በገዳማቸው ዋሻ ውስጥ ያሳልፉ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመት ሺኖዳ የመካከለኛው ምሥራቅ የነገረ መለኮት ተቋማት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ፡፡ቤተ ክርስቲያኒቱን ከሌሎቹ ጋር የማቀራረቡን ሥራ የጀመሩት ገና በጳጳስነታቸው ዘመን ነው፡፡ በእርሳቸው መሪነት ቤተ ክርስቲያኒቱ በአያሌ የነገረ መለኮት ውይይቶች ላይ ተሳትፋለች፡፡ ፓርትያርክ ቄርሎስ በመጋቢት 9 ቀን 1971 ዓም ዐረፉ፡፡ በመጋቢት 22 የተሰበሰበው የግብጽ ሲኖዶስም ተተኪውን ለመምረጥ ዝግጅት ጀመረ፡፡ አምስት እጩዎችንም መረጠ፡፡ ነገር ግን በመካከሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ አያሌ ፈተናዎች ገጠሟት፡፡ በዚህም ምክንያት ፓትርያርክ ሳይመረጠ ረዥም ጊዜ ቆየ፡፡ በጥቅምት 29 ቀን የተሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ የእጩዎችን ቁጥር ወደ ሦስት ዝቅ አደረገው፡፡ የሦስቱም እጩዎች ስም በመንበረ ማርቆስ ካቴድራል መንበር ላይ ተቀመጠ፡፡ ሕዝቡ እና ገዳማውያኑም ለሦስት ቀን ሱባኤ ያዙ፡፡

    ጥቅምት 31 ቀን 1971 እኤአ በሰንበት ዕለት ሕዝቡ፣ ካህናቱ፣ ገዳማውያኑ እና ጳጳሳቱ በተገኙበት ጸሎት ከተደረሰ በኋላ አንድ ዓይኑን በሻሽ ለተሸፈነ አይማን ሙኒር ካሊል የተባለ ሕፃን በመንበሩ ላይ የተጸለየባቸው ስሞች ቀረቡለት፡፡ እጁን ዘርግቶ አንዱን ዕጣ አወጣው፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኒቱን በጊዜያዊነት ይመራ የነበረው ኮሚቴ ሊቀ መንበር ለሆኑት ለሜትሮጶሊጣን አንቶኒዮስም ሰጣቸው፡፡
    ወረቀቱን ዘረጉት፡፡ «እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያናችን አባት ይሆኑ ዘንድ አቡነ ሺኖዳን መርጧል» ሲሉ አካባቢው በጭብጨባ እና በእልልታ ተናጋ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ የዛሬ ዐርባ ዓመት ኅዳር 14 ቀን 1971 እኤአ በቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል፣ ሺኖዳ 3ኛ 117ኛው የግብጽ ፓትርያርክ ተብለው ተሾሙ፡፡
    በእራሳቸው ዘመን ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደገና ኃይል አገኘች፡፡ አሁንም በነገረ መለኮት ኮሌጅ ያስተምራሉ፡፡ የኮሌጁ ዲንም ነበሩ፡፡ የኤልኬራዛ መጽሔት አዘጋጅ ናቸው፡፡ ዓርብ ዓርብ ያስተምራሉ፡፡ ገዳማትን እና ትምህርት ቤቶችን አስፋፉ፡፡ ወጣቱን ወደ አገልግሎት ጠሩ፡፡ አሁንም በፓትርያርክነታቸው ዘመን በአባ ቢሾይ ገዳም የሳምንቱን ግማሽ በገዳማዊ ሕይወት ማሳለፋቸውን አልተውም፡፡ መጻሕፍትን ይጽፋሉ፡፡ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ያለውን ሕዝብ ይጎበኛሉ፡፡ እርሳቸው ሲሾሙ በውጭ ያሉት አጥቢያዎች ሰባት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን በአሜሪካ እና ካናዳ የሚገኙትን አብያተ ክርስቲያናት እንኳ ከሰማንያ በላይ አድርሰዋቸዋል፡፡ በአውስትራልያ 26፣ በአውሮፓ 30 አጥቢያዎች ይገኛሉ፡፡ ሺኖዳ ለአቋማቸው እና ለእምነታቸው ሲሉ ስደትን የቀመሱ ፓትርያርክ ነበሩ፡፡ አንዋር ሳዳት የግብጽ መሪ በነበረ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቱ እና በምእመናኗ ላይ የሚደርሰውን መከራ በመቃወም ሺኖዳ ደጋግመው ይናገሩ ነበር፡፡ በዚህ ያልተደሰተው ሳዳት መስከረም 3 ቀን 1981 እኤአ ባወጣው ዐዋጅ ሲኖዳን ከመንበራቸው አሳደዳቸው፡፡ በግዞትም ወደ አባ ብሶይ ገዳም ተላኩ፡፡ ሕዝቡ ሌላ አባት አንመርጥም ብሎ ተከትሏቸው አባ ብሶይ ገዳም ገባ፡፡ እዚያም በሚወዱት ገዳም ተጋድሏቸውን እና ትምህርታቸውን ቀጠሉ፡፡ በገዳሙ በግዞት ለአራት ዓመት ተኩል ከቆዩ በኋላ ሳዳት ሞቶ ሙባረክ ሲተካ በጥር 2 ቀን 1985 እኤአ ወደ መንበራቸው ተመለሱ፡፡ ሺኖዳ ቀልድ ዐዋቂ ናቸው፡፡ በተለይ ሕፃናትን ማስተማር ይችሉበታል፡፡ ሕዝቡን ሲያስተምሩም ቀልድ እና ታሪክ ጣል ማድረግ ይወዳሉ፡፡ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን የነበራቸውን የአገልግሎት ተሳትፎ በማሳደግም ሺኖዳ ከፍተኛ ለውጥ አምጥተዋል፡፡ ሺኖዳ ለሀገራቸው ያላቸው ፍቅር ልክ የለውም፡፡ «በልባችን ውስጥ ያለችው ግብጽ ከምናያት ግብጽ ትበልጣለች» የሚለው አባባላቸው በግብጻውያን ልብ ለዘለዓለም ታትሞ ቀርቷል፡፡ ክርስቲያን እና ሙስሊሙ ሕዝብ ተከባብሮ እና ተባብሮ እንዲኖር በብርቱ ጥረዋል፡፡ በዐርባ ዓመት አገልግሎታቸው ከአንድ መቶ በላይ መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡ ንግግር ዐዋቂ፣ ባለ ቅኔ፣ ሰባኪ እና ደራሲ ናቸው ሺኖዳ፡፡ እንደዚህ ያለ ታላቅ ሰው በሀገራችን ሲሞት “አራት ሰው ሞተ” ይባላል።አባታችን በሙስሊሞች፣ በፕሮቴስታንቶች እና በካቶሊኮች ዘንድ የሚወደዱ እና የሚከበሩ አባት ሆነዋል፡፡ የታላቁ የአልአዝሐር መስጊድ ኢማም የፖፕ ሺኖዳን ሞት ተከትሎ «ግብጽ እኒህን ጥበበኛ ሰው በምትፈልግበት ወሳኝ ጊዜ እርሳቸውን ማጣታችን የሚያንገበግብ ነው» ነበር ያሉት፡፡ ሞታቸው ለግብጽ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የጎዳ ነው፡፡ ተወዶ የሚኖርና ተለቅሶለት የሚቀበር የሃይማኖት መሪ በዓለም ላይ እየጠፋ ባለበት በዚህ ጊዜ ሺኖዳ በሕይወታቸውም በሞታቸውም ያስተማሩ አባት ሆነዋል፡፡ በህክምና ሲረዱ ቆይተውም መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓም ዐረፉ፡፡ በሚወዱት በአባ ብሾይ ገዳምም ተቀበሩ፡፡
    ውድ አንባብያን ከብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሳልሳዊ ታሪክ ብዙ እንደተማራችሁ እንገምታለን የብጹዕነታቸው በረከት አይለየን

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top