• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    በጎ ሕሊና ይኑርህ

    በጎ ሕሊና ይኑርህ 1ጢሞ 1፡19

    በዲያቆን ተሾመ አበራ የአምስተኛ አመት የቲዖሎጂ ደቀመዝሙር
    በጎ ሕሊና ይኑርህ 1ጢሞ 1፡19
    የዚህች አናሳ ጽሁፍ አላማ ሁሉም ክርስቲያን በጎ የሆነ ሕሊና ሊኖረዉ እንደሚገባ ለማስጨበጥ ነዉ ፡፡
    ቃሉን የተናገረዉ ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳዉሎስ ሲሆን ቃሉን የጻፈለትም ለግዜዉ ለመንፍስ ልጁ ለጢሞቲዎስ ነዉ፡፡ በመጨረሻም ለኛ ለክርስቲያኖች ተጽፎልናል፡፡
    በመጀመርያ ሕሊና ምንድነዉ ?ሕሊና በመልካም እና በክፉ መካከል የሚለይ በጥፋቱ ሰዉን የሚከስ ነዉ፡፡ ሕሊና ማለት ስለ ክፉም ሆነ ስለ መልካም ሥራዉ ሰዉን እንዲያመዛዝን የሚያሳስብ ነዉ፡፡ሕሊና የእግዚአብሔር ድንቅ ስጦታ ነዉ፡፡ሕሊና እግዚአብሔር በስዉ ልጅ ዉስጥ የተከለለት የግብረ ገብነት(ሞራል) ምስክር ነዉ፡፡አንድ ክርስቲያን በጎሕሊና አለዉ የሚባለዉ መልካምን ሁሉ ሲያደርግ እና መጥፎ የተባሉትን ነገሮች ማስወገድ ሲችል ነዉ(ዮሐ23፡1)፡፡ ውድ ክርስቲያኖች ሕሊና የእግዚአብሔር ድንቅ ስጦታ ስለሆነ በአግባቡ ብንጠቀምበት በሕይወታችን ዉስጥ የሚገኘዉን ማንኛዉንም ጥቁር ነጥብ ነጥሎ እንዲያወጣልን ግዜ ሳያልፍ እና ለክፉ ተላልፈን ሳንሰጥ እንድንጠነቀቅ ይረዳናል፡፡ውድ ዘመዶቼ የእግዚአብሔርን መንፍስ የሕሊናችን አጋር እንዲሆን ከመፍቀድ የመሰለ አስተማማኝ ሁኔታ የለም ፡፡ይህ እንዲሆን ግን ራስን ማዘጋጀት እና ከእዉነት ጋር ለመተባበር የወሰነ ማንነት ሊኖረን ይገባል፡፡ሕሊናችንን ብናሰለጥነዉ እና ለሚሰጠም ምልክት ትኩረት ብንሰጠዉ ከብዙ ጸጸት ፣እረፍት ማጣት፤ሰላም ማጣት እና ስቃይ እንድናለን፡፡ እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች በጎ ሕሊና ይኑርህ በማለት ሐዋርያዉ ለመንፍስ ልጁ ለጢሞቲዎስ ይምክረዋል ለእኛም እንደዚሁ ያስተምረናል፡፡ ምክንቱም በጎ ሕሊና ለክርስቲያኖች ወሳኝ ስለሆነ ነዉ፡፡ በጎ ሕሊና ያለዉ ክርስቲያን የሰዉን ስሜት አይጎዳም፤ ከበጎ ምግባር ጋር ሁሉ ይተባበራል፤ በጎ ነገርን እንደ ዉሃ ይጠማል፤ ሕይወቱ በአጠቃላይ በበጎ ምግባር ያሸበረቀ ይሆናል፤ ነገሮችን በትክክል ያመዛዝናል ፤ለሰዉ ልጆች ሁሉ ተገቢዉን ክብር አይነፍግም፤ ምንም እንኩዋን ከማይጠፋ ዘር ቢወለድም በስጋዉ እንደ ጤዛ ረጋፊ መሆኑን ያስተዉላል፡፡እንደ መጽሓፍ ቅዱስ ሀሳብ ሶስት ዐይነት ሕሊና አሉ፡፡
     
     1. በጎሕሊና ፤ከፉዉን ከደጉ የለየና ኃጥያት ሲሰራ የሚወቅስ ነዉ፡፡በጎ ሕሊና ያለዉ ሰዉ ስህተት ሰርቶ እንዳልሰራ ማለፍ አይችልም የልቁንም ይወቅሳል ፤ይመክራል እንጂ፡፡ እንዲህ አይነት ህሊና ያለዉ ክርስቲያን ከእግዚአብሔርም ሆነ ከሰዉ ጋር የሰመረ ግንኙነት አለዉ(1ጢሞ 1፡5)፡፡
    2. ደካማ ሕሊና፤ ደካማ ሕሊና ያለዉ ሰዉ በየምክንያቱ እራሱን የሚወቅስ ሰዉ ነዉ፡፡ ባጠፋዉም ሆነ ባላጠፋዉ ነገር የሚጸጸት እና የጥፋኝነት ስሜት የሚያጠቃዉ ሰዉ ነዉ፡፡እንዲህ አይነቱ ክርስቲያን በእግዚአብሔር ቃል በመሞላት እና በመብሰል ማደግ ይኖርበታል (1ቆሮ8፡7)፡፡
    3. ክፉ ሕሊና ፡የተበላሸ እና ሐጥያት ሆነ ክፋት ሲሰራ ከመወቀስ ዉጭ የሆነ ሕሊና ነዉ፡፡ይህ አይነት ሕሊና ያለዉ ሰዉ ምንም ነገር ለማድረግ የማይከለከል ነዉ፡፡ሕሊናዉን ሕይወት አልባ እንዲሆን ስላደረገዉ አይወቅሰዉም (ዕበ 10፡22)፡፡
    ታድያ ውድ የእግዚአብሔር ልጆች የእኛ ሕሊና ከየትኛዉ ወገን ይሆን ? ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳዉሎስ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ በማለት ያስተምረናል ስለዚህ በጎ ሕሊና ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡በጎንም ነገር ለመስራት ልንትጋ ይገባል፤ለዚህ ነዉ ቅዱስ ጴጥሮስ በጎንምለማድረግ ብትቀኑ የሚያስጨንቃችሁ ማነዉ ? በማለት ያስተማረን (1ጴጥ 3፡13)፡፡ስለዚህ እግዚአብሔር በጎ የሆነውን እንድናስብ፤በጎ የሆነውንም ተግባር እንድንሰራ በቸርነቱ ያግዘን፡፡

    ወስብሓት ለእግዚአብሔር
    አዘጋጅ:- ዲያቆን ተሾመ አበራ የአምስተኛ አመት ቲዖሎጂ ደቀመዝሙር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በጎ ሕሊና ይኑርህ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top