ሰኔ ዐስራ ሁለት በዚህ ዕለት ሚካኤል በኬልቅያ አፎሚያን የምትባል ደግ ሴት ባሏ አስተራኒቆስ ይባላል። ከሀብቷ ከንብረቷ እየመጸወተች በጾም በጸሎት ተወስና ትኖር ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ደግ መነኩሴ መስሎ አጋንንትን መነኮሳይት አስመስሎ መጥቶ ከደጅ ሆኖ አስጠራት ከቤት ገብታችሁ በቅዱስ ሚካኤል ስዕል ፊት ጸልዩልኝ አለቻቸው እኛማ በነግህ ጸልየናል እንደው አንቺ ይህ ሁሉ ጾም ጸሎት ምን ያደርግልሻል? ሲበዛ ያለጊዜ አንደ ሚጐዳ አታውቂምን ; ሀብትሽን ሰጥተሸ መጨረሻሽ ምንድ ነው ስትደክሚ የሚረዳሽ የሚጦርሽን ልጅ የለሽ ሁለተኛ ማግባት ኃጢኣት መስሎሻልን እነ አብርሃም እነ ዳዊት ከብዙ ሴቶች ብዙ ልጆች ወልደዋል አሁን ባል አግቢ እኔ የምልሽን እሽ በይኝ አለ “ ኦ አባ አስኬማከ ሠናይ ወቃልከሰ አኩይ” አባ ቃልህ መልካም ነበረ ንግግርህ ግን ክፉ ነው፡፡ አለችውና በሏ በሕይወት እያለ ያሠራላትን የቅዱስ ሚካኤል ስዕል ካስቀመጠችበት አውጥታ ብታሳየው ሰኔ 12 ቀን መጥቼ ከተመካሽበት ከዚያ ሰዕል ጋር አጠፋሻለሁ ብሏት እንደ ትቢያ በኖ ጠፍቷል፡፡ ሰኔ 12 ቀን የብርሃን መልአክ መስሎ መጥቶ ጾም ሸሎትሽ ስግደትሽ፤ ምፅዋዕትሽ፤ አርጎል፡፡ ላድንሽ መጥቻለሁና ስገጅልኝ አላት አንተ ማንህ? አለችው የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ነኝ አላት የንጉሥ መልእክተኛ ያለማኀተም ይሄዳልን በተረ መስቀልህ ወዴት አለ አለችው እርሱም መልሶ መስቀል አሲዞ መሳል ልማድ ነው እንጅ እኛ መላእክት አንይዝም አላት ቆየኝ/ጠብቀኝ/ ስዕሉን ላምጣልህ ብላ ወደ ቤቷ ዘወር ስትል መልኩን ለውጦ ጨለማ መስሎ ታያት ቅዱስ ሚካኤል እንደ ዐይን ጥቅሻ መጣ አፎምያን እረድቶ ጾምሽ፤ጸሎትሽ ስግደት፤ ምጽዋትሽ ቅድመ እግዚአብሔር ደርሷል ዕረፍትሽ ዛሬ ነው፡፡ ብሏት ከሷ ተሰወረ ወደ ቤተክርስቲያን ሄዳ ሥጋውንና ደሙን ተቀብላ ገንዘቧን ሁሉ መጽውታ በዚህ ዕለት በክብር አርፋለች፡፡
ሁለተኛው በዚህ ዕለት የሚከበረው ባሕራን ነው
ሀገሩ እስክንድሪያ ነው ወላጆቹ የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እያከበሩ ይኖሩ ነበር፡፡ ባሕራን ተጸንሶ ሳለ አባቱ ሞተ ባሕራን በተወለደ ጊዜ ሕፃኑን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ባረከው የዚህ የጎረቤትሽን የባለ ጸጋ ሐብት ይወርሳል ሲላት ባለ ፀጋው ጎረቤቷ ሰማ ነገሩን ከልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ቆይቶ ባሕራንን ዐሥር አመት ሲሆነው እናቱ የምታብሰው ቆርሳ የምትሰጠው አጥታ በጣም ተቸገረች ባለፀጋውም እኔ ወስጄ ለምን አላሳድገውም አላትና ለርሷ ሃያ ወቄት ወርቅ ሰጥቶ ወሰደው ወድያውም ሳጥን አሰርቶ በአሰራው ሳጥን ከቶ ከባህር ጣለው ማዕበል እየገፋ ወስዶ ከወደቡ አደረሰው አንድ በጎቹን የሚጠብቅ እረኛ አገኘው ከነጋዴ የወደቀ እቃ አገኘሁ ብሎ ከቤቱ ወስዶ ቢከፍተው መልከ መልካም ልጅ ይፈልግ ነበርና በጣም ደስ አለው ስሙንም ባሕራን ብሎ ጠራው ከባሕር የተገኘ ሲል ነው፡፡ ከበላው እየበላ ከጠጣው እያጠጣ አሳደገው ከብዙ ዓመታት በኋላ ባሕር ላይ የጣለው ባለፀጋ ለንግድ ሲሔድ መሽቶበት ባሕራንን ባሳደገው ቤት አደረ ባሕራን ባሕራን እያለ ሲጠራው ባሕራን ማለት ምን ማለት ነው አለው፡፡ ከባሕር የተገኘ ማለት ነው መቼ አገኘኸው አለው ጊዜውን ጠቅሶ ሲነግረው በልቡ ለካ አልሞተም አለ ሲነጋ ከቤቴ የረሳሁት እቃ አለና እባክህ ፍቀድልኝ ልጅህን ባሕራንን ልላከው፡፡ የድካሙን ዋጋ ለአንተ እከፍላለሁ አለው፤እሽ አለ እንደ ደረሰ ግደሉት ብሎ ደብዳቤ ጽፎ አትሞ ምልክት ነግሮ ስንቁን አስይዞ ላከው ዘጠኝ ቀን በእግሩ ተጉዞ የአንድ ቀን ጎዳና ሲቀረው ቅዱስ ሚካኤል በአምሳለ ሐራ በፈረስ ተቀምጦ መላእክት እንደ ሠራዊት አስከትሎ ከመንገድ ላይ ተገናኘው አንተ ጎበዝ ወዴት ትሔዳለህ? መላእክት ተልኬ ለደርስ እየሄድኩ ነው፡፡ ብሎ መለሰለት እስኪ መልእክቱን አሳየኝ አለው ባሕራንም ደብዳቤውን አሳየው፡፡ እፍ ቢልበት የሞቱን ትዕዛዝ አጥፍቶ የሕይወት ትዕዛዝ ጽፎበታል፡፡ ደብደቤውን ለቤቱ ሹም ሰጠው ቢገልጠው ልጄን ለላኩት ሰው ዳሩለት ሐብት ንብረቱን አውርሱት ባሮቼ ይገዙለት የሚል አነበበ ባሕራንም የባለጸጋውን ልጅ አገባ ባለ ጸጋውም ከንግድ ሲመለስ የዘፈን ጨዋታ ድምፅ ሰምቶ የምሰማው ድምፅ ዘፈን ጨዋታ ምን ተገኝቷል?፡፡የላከው ሰው ልጅህን አግብቶ ሐብትህን ወርሶ ይኸው አርባ ቀን ሙሉ ይዘፈናል አለው ወዲያው ደንግጦ ከፈረሱ ወድቆ ሞቶአል ባሕራንም የባለፀጋውን ሐብት ወርሶ አግዚአብሔርን አያመሰገነ ቅዱስ ሚካኤልንም እያከበረ ኖረ፡፡
ትምህርት
እግዚአብሔር መልእክትን በመንገዳችን እንደሚልክልን (ዘጸ23፡-20) መልካም ሥራችን አንደማንወድቅ(መዝ.40፡-1) የጾምና የጸሎት የምጽዋት ጠቀሜታን(የሐዋ.9፡-31) የሞት ደብዳቤ ወደ ሕይወት እንደሚቀየር ማመን(መ.አስቴር 7፡-9)፡፡
መልእክት
በደግነትና በመልካምነት የታወቀችው አፎምያና በባሕር ውስጥ ተጥሎ የተገኘው ባሕራን በዚህ ዕለት አምላካችን አግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልን ልኮ ከጠላት ታድጎቸዋል፡፡
እኛም በሕይወታችን እግዚአብሔር ካከበርነው በክፉዎች የምንወድቅና የምንሞት ብንመስልም የማይጥለን አምላክ የሞታችንን ደብዳቤ ወደ ሕይወት እንደ ሚቀይርልን አምነን እኑንር ፡፡ የባሕራንንና የአፎምያ ወዳጂ ቅዱስ ሚካኤል በምልጃው ዘወትር ከኛ ጋር ይሁን፡፡አሜን !!!
0 comments:
Post a Comment