ሐራ ዘተዋሕዶ እንደዘገበው
የመግለጫው ዐበይት ነጥቦች፡-
ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተደረገውን የመክፈቻ ንግግር፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ እየተሠሩ ያሉትን የሥራ ሒደቶች የዳሰሰና በኹሉም አቅጣጫ ቤተ ክርስቲያኗ የደረሰችበትን ዕድገትና ሊሠራ የሚገባውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የሚያስገነዝብ በመኾኑ፤ እንዲኹም በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተፈጠረው የዝናም እጥረት ምክንያት በተከሠተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ሊደረግ ስለሚገባው መንፈሳዊ አገልግሎት ርዳታንና ትምህርትን ለመስጠት የሚያስችል አባታዊ መመሪያ በመኾኑ ተግባራዊ እንዲኾን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤በተለያየ ጊዜና ምክንያት ኢትዮጵያ ሀገራችንን ድርቅ እያጠቃት ጥቂት የማይባሉ የሀገሪቱ ዜጎች ለረኀብ ሲጋለጡ፤ እኛ ኢትዮጵያውያንበተለመደው የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህላችንን በተግባር በማሳየት ፈታኝ ችግሮችን ማሳለፋችን ይታወቃል፡፡
በአኹኑ ጊዜም በዝናም ዕጦት ምክንያት በሀገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተከሠተው ድርቅ ምክንያት ለረኀብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመታደግ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በማድነቅ ቤተ ክርስቲያናችንም የተለመደውን አስፈላጊ እገዛና ድጋፍ ማድረግ ስላለባት፣ በአንድ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ድጋፍ ሰጭ በጎ አድራጊዎች ጋር በመቀናጀት የርዳታ ሥራውን እንዲያፋጥን ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
የመልካም አስተዳደር ዕጦትንና የሙስና መስፋፋትን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ሰፊ ውይይት በማድረግ፣ እንዲህ ዓይነቱ ሀገርንና በአጠቃላይም የሰውን ልጅ ኹሉ የሚያጎድፍ ክፉ ተግባር ሀገርንና ወገንን እንዳይጎዳ አጥብቆ መከላከል አስፈላጊ በመኾኑ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ በዚኽ ጉዳይ ላይ አጥብቃ እንድታስተምር፤ ይህ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሙስና መስፋፋት የችግሩ መነሻና መፍትሔ መታወቅ ስላለበት፤ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗን ኹለንተናዊ ችግር የሚያጠና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ያካተተ ዘጠኝ አባላት ያሉበት ዐቢይ ኮሚቴ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተቋቁሟል፤የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአገር ባለውለታ እንደመኾኗ ለዘመናት ሕዝቡን ስለ ሰላም፣ ስለ ልማት፣ ስለ አገር ፍቅር እና ስለ አብሮነት ጊዜው በፈቀደው መንገድ ኹሉ ስታስተምር ቆይታለች፡፡
አኹንም ዘመኑ ባፈራው ብዙኃን መገናኛ አብዛኛውን ኅብረተሰብ በትምህርት ለመድረስ እንዲያስችላት የብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ስርጭት ለመጠቀም እንድትችል በባለሞያዎች ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት እና ብር 12 ሚሊዮን የአንድ ዓመት በጀት ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቋል፤የዕድሜ ባለጸጋ የኾኑ አረጋውያን የሚጦሩበትን፤ በተለያየ ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ዕጓለማውታ ሕፃናት የሚያድጉበትን የምግባረ ሠናይ ተቋማትን ያላቋቋሙ አህጉረ ስብከት እንዲያቋቁሙ፤ አቋቁመው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት አህጉረ ስብከትም አጠናክረው እንዲቀጥሉ መመሪያ ተሰጥቷል፤የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመማር ማስተማር ሥርዐትን በመዘርጋት በአገር ደረጃ የትምህርት መሠረት መኾኗ ይታወቃል፡፡ በአኹኑ ጊዜም በቤተ ክርስቲያኒቱ የተከፈቱና የመማር ማስተማር ሥራውን እያከናወኑ ያሉ ሦስቱ ኮሌጆችን፣ ተማሪዎችን አስተምሮ ለቁም ነገር በማብቃት ቤተ ክርስቲያንና አገርን እንዲጠቅሙ፤ ለኅብረተሰቡ የምሥራች ተናጋሪና ሰላምን የሚሰብኩ ኹነው እንዲያድጉ ለማድረግና ኮሌጆቹን ለበለጠ ዕድገት ማብቃት በሚያስችልበት ኹኔታ የውስጥ ይዘታቸውን እንዲያጠኑ ሦስት ብፁዓን አባቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ ሠይሟል፤ቤተ ክርስቲያኒቱ በማታውቀው ኹኔታ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፈቃድ ሳያገኙ በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ትምህርታዊ ስብከት የሚያስተላልፉ፣ ዝማሬ የሚያሰሙ፤ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጦች፣ ልዩ ልዩ በራሪ ወረቆቶችን የሚያሳትሙ ኹሉ በአገሪቱ ሕግ መሠረት በሕግ እንዲጠየቁ፤ ለሚመለከታቸውም የሚዲያ አካላጽ ማሳሰቢያ እንዲደርስ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
አንዳንድ የእምነት ተቋማት÷ ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት የኾነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መገልገያ የኾኑትን ንዋያተ ቅድሳት፣ አልባሳት፣ መስቀሎች፣ መቋሚያ፣ ከበሮ፣ ጸናጽል እና የመሳሰሉትን ኹሉ፤ በእምነቱ የሌሉበት ጭምር፤ በዓል እናነግሣለን፤ የደመራና የጥምቀት በዓላት እናከብራለን በሚል የራሳቸው የኾነውን የራሳቸው በማስመሰል እየተጠቀሙ መኾኑን ጉባኤው ተገንዝቦበጉዳዩ ሰፊ ጥናት ቀርቦ ውሳኔ እንዲያገኝ ለማድረግ ለጥናቱ ብፁዓን አባቶችን ቅዱስ ሲኖዶስ ሠይሟል፤
በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በአየህጉረ ስብከቱ ተቋቁሞ፣ ለበርካታ ዓመታት ለአገርና ለወገን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት በተለይ በአኹኑ ጊዜ በአገራችን በአንዳንድ ቦታዎች የተከሠተውን ድርቅ ታሳቢ በማድረግ አሳዳጊ ላጡና በድርቁ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ሕፃናት የተለመደውን ሰብአዊ አገልግሎት አጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤በየመንፈሳዊ ኮሌጆች መስፋፋትና ዕድገት ላይ የተነጋገረው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ በኦሮሚያ፣ በጅማ ሀገረ ስብከትና በአማራ ክልል በባሕር ዳር ከተማ ቤተ ክርስቲያኒቱ አዲስ የከፈተቻቸው መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ ቤተ ክርስቲያናችን የዘወትር ተግባሯ አድርጋ የያዘችውን የትምህርት ሥራ ለማጠናከር እንዲያስችላት በመኾኑ የመምህራን ማሠልጠኛዎቹ የመማር ማስተማር ሥራቸውን ለኅብረተሰቡ በሚጠቅም መልኩ እንዲያስቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፤
ቤተ ክርስቲያን ቀጣይ ሥራዎቿን ኹሉ ካለፈው በበለጠ በመሪ ዕቅድ የተደገፈ በማድረግ ማከናወን እንዲያስችላት ለ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድና የዕቅዱ ማስፈጸሚያ በጀት ቅዱስ ሲኖዶስ አጽድቋል፤
የቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረታዊ ተግባርና ተልእኮስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት መኾኑ ይታወቃል፤ ጉባኤው በዚኽ ጉዳይ ላይ በስፋት ተነጋግሮ ሰባክያነ ወንጌል በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው እንዲጎለምሱ፤ ተፈላጊው ሥልጠና እየተደረገላቸው እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ አስፈላጊው ድጋፍ ኹሉ እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፤
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የቆየው ስምምነትና አንድነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥልቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፤የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት አድማስን በማስፋፋት ኢትዮጵያውያን ባሉበት በተለያዩ የውጭ አገሮች ቤተ ክርስቲያን እያቋቋመች ዜጎቿን እንደምታስተምርና እንደምታጽናና የሚታወቅ ነው፡፡ አኹንም ይህንኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮዋን ማስፋት እንዲቻል ቤተ ክርስቲያን እንዲቋቋም በሚል ጥያቄ ላቀረቡ ኢትዮጵያውያን አማንያን፣ በጃፓንና በኮርያ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲቋቋሙ፣ መምህራንም እንዲላኩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤በውጭ አገር ከሚኖሩ አባቶች ጋር ተይዞ የነበረው የሰላም ንግግር ቤተ ክርስቲያናችን ምንጊዜም ቢኾን የምትፈልገውና በዚኹ ላይ አጥብቃ ስትሠራ የቆየችበት ጉዳይ መኾኑን ጉባኤው አውስቶ በቀጣይም በውጭ አገር ከሚገኙ አባቶች በተገኘው አጋጣሚ ኹሉ የሰላሙ ሒደት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤
ከጥቅምት 8 – 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሔደው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ 34ኛ መደበኛ ስብሰባበተላለፈው የጋራ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተነጋግሮ፣ የውሳኔ ሐሳቡ የ2008 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ ዕቅድ ኾኖ በኹሉም አህጉረ ስብከት ተላልፎ በየደረጃው በሥራ እንዲተረጎም ተወስኗል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ከዚኽ በላይ በተገለጹትና በሌሎች መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን ከሰጠ በኋላ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
0 comments:
Post a Comment