• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 12 November 2015

    ቅዱስ መልአክ ይባርክህ


    እኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን ስለምናምን “መልአክ ይባርክህ”ብለን የመናገር ድፍረት አለን፣ መናፍቃን ግን “ቅዱስ ገብርኤል ይባርክህ” ማለትን ይፈራሉ፡፡

    መናፍቅ ማለት ተጠራጣሪ፣ ከፍሎ አማኝ ማለት ነው፡፡ እኛ ከእኛ እምነት ውጪ ያሉትን በዚህ ስያሜ የምንጠራበት ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስ አዋልድ ጽሑፎችን ስለማይቀበሉ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጽፎ ያለውንም ጭምር ከፍለው፣ የሚፈልጉትን ብቻ መርጠው ስለሚቀበሉና ያልተቀበሉትን ቃል “በሉት” “እመኑት” ሲባሉ ስለማያምኑ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-

    ከመናፍቃን አንደበት የማትሰሙአቸው አምስት ነገሮች፤ ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅዱሳት ጽሑፎችን የሚሉአቸውን በመጠኑ ላስጎብኛችሁ፡-

    1. መናፍቃን “የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ይባርክህ” ብለው መናገር ኑፋቄ ስለሚመስላቸው አይሉም፣

    መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉት ቅዱሳን ሰዎች ያውም ጌታችን የሚኮራበትና እንደውም የማን አምላክ እንደሆነ ሲናገር “የያዕቆብም አምላክ ነኝ” የሚልለት ታላቁ እስራኤል የተባለ ያዕቆብ “ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” (ዘፍ 48፡16) ብሎ መልአክ ልጆችን እንዲባርክ ተናግሮአል፡፡ አንድ መናፍቅ የእኛ ካህን “ቅዱስ ገብርኤል ይባርካችሁ” ሲል ቢሰሙ፤ ወይም ከድርሳናት ውስጥ ይህን ቃል ቢያገኙ፤ እንደ ኑፋቄ ቆጥረው፣ እኛን “መናፍቅ” ሲሉን ይገኛሉ፤ የአብዬን ወደ እምዬ ልጥፍ ማድረግ ልማዳቸው ነውና፣ የእነርሱን ኑፋቄ መሸፈኛ እኛን መናፍቅ ናችሁ በማለት ይደመድማሉ፡፡ ቀድመን እኛ መናፍቅ እንዳንላቸው የሚጥሩበት መንገድ ነው፡፡

    2. መናፍቃን “የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቅህ” ብለው መባረክ ይፈራሉ፡፡

    በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ይህ እውነት ጽፎአል፡፡ ያውም የእውነት ምንጭ እግዚአብሔር ራሱ ለሕዝበ እስራኤል ሲነግራቸው “በመንገድ ይጠብቅህ ዘንድ ወዳዘጋጀሁትም ስፍራ ያገባህ ዘንድ፥ እነሆ፥ እኔ መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ” (ዘጸ 23፥20) እያለ፤ እነርሱ ግን የሐሰት ምንጭ የዲያብሎስ መልእክተኞች ስለሆኑ፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቅህ ስንል ከሰሙ፤ “ከእግዚአብሔር ሌላ ጠባቂ የለም እንዴት እንዲህ ትላላችሁ?” በማለት የእነርሱን ኑፋቄ በእኛ ላይ ለማላከክ እኛኑ መናፍቃን ለማለት ይሽቀዳደማሉ፡፡ አሁን የእኛ ካህን ወይም ድርሳነ ገብርኤል ብሎት ቢሆን ይህ መጽሐፈ ኑፋቄ “መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቅሃል ይላል” በማለት ያጣጥሉት ነበር፤ ድርሳነ ገብርኤል ግን የመጽሐፍ ቅዱስ አንዱ ልጅ በመሆኑ ተመሳሳይ አሳብ ያስቀምጣል፤ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና” (መዝ 90፥11) የሚለውን ገልብጦ የያዘ የኑፋቄ መጽሐፍ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ልጅ ነው፡፡

    3. መናፍቃን “የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከክፉ ያድንህ” ብለው መናገር ያንቀጠቅጣቸዋል፡፡

    በእነርሱ ሕሊና “መዳን በማንም የለም” የሚለው ቃል የምንሽር ስለሚመስላቸው፤ አንዱን ጥለው ሌላውን አንጠልጥለው በግማሽ ልብ መጽሐፍ ቅዱስን አቅፈው ይሄዳሉ፣ ግማሽ ልብ ማለት መናፍቅ ማለት ነው፡፡ ሰው በምድር ሳለ ክፉ ነገር ያጋጥመዋል፤ መናፍቃን ደግሞ መላእክት ከክፉ ሊያድኑን እንደተሰጡን አይቀበሉም፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ” (ዘፍ 48፥16) ብሎ በተግባር እንዳዳነው ሲናገር፤ እንዲሁም እኛ የእግዚአብሔር አዳኝነትን የምናምን ምእመናን “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል” (መዝ 33፥7) ተብሎልናል፡፡ መናፍቃን ግን ከፍሎ አማኝ ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን እየቆራረጡ ስለሚቀበሉ፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከክፉ ያድንህ የሚለውን ያጣጥላሉ፡፡

    4. መናፍቃን “ጸሎትህ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል እጅ ወደ እግዚአብሔር ይውጣልህ” ማለትን አጥብቀው ይጸየፋሉ፡፡

    ትዕቢት ውጥር አድርጎ ስለያዛቸው፤ እኔው ራሴ እግዚአብሔርን አነጋግረዋለሁ እንጂ መልአኩ ምን አገባውና ነው እርሱ የእኔን ጸሎት ይዞ የሚወጣው በማለት እርዳታቸውን አይሹም፤ እርዳታቸውን የሚፈልግ ሰውም ካለ፣ እንደ መናፍቅ ይቆጥሩታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ሰዎች ሲጸልዩ ግን ከእግዚአብሔር ጋር እንኳ ሲነጋገሩ በትሕትና እንጂ፣ “እኔ በፊቱ ልቀርብ ይገባኛል” አይሉም፡፡ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” (ያዕቆብ 4፡6)፡፡

    በፊቱ ስንጸልይ እንደ ጻድቁ አብርሃም በትሕትና “እኔ አፈርና አመድ ስሆን ከጌታዬ ጋር እናገር ዘንድ እነሆ አንድ ጊዜ ጀመርሁ” (ዘፍ 18፡27) እያልን ክርስቶስን ማረን እያልን በጸሎት ስንጠይቅ፣ እንደ ሙሴ “በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ” በማለት እነዚያ ጻድቃንን እንደጠሩት እንጠራለን፡፡ በዚህን ጊዜ “እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ” (ዘጸ 32፡13-14) እንዳለው በእነርሱ ቃል ኪዳን ይራራልናልና፡፡

    መናፍቃኑ የመላእክቱ ጸሎት ማሳረግን በድርሳናት እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ያለ ስለማይመስላቸው፣ አንግበው የሚሄዱት መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ “የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ” (ራእይ 8፡3-4) ይላል፡፡ እኛም ጸሎታችንን ይዘው ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ይረዱናል ስንል መጽሐፍ ቅዱስን ተመልክተን ነው፤ እኛ የመላእክት ጸሎታችንን ይዘው መውጣትና ማሳረጋቸውን መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰን ያመንነውን “መናፍቅ” ካሉን፤ እነርሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው ያላመኑት፣ ምን ሊባሉ ነው? እየተጠራጠሩ የሚያጠራጥሩት መናፍቃን ሳይባሉ፤ መናፍቅነትን ወደ እኛ የሚወረውሩት መናፍቅ አይባሉም ይሆን?፣ ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ ከፉ ማለት ይህ ነው፡፡

    5. መናፍቃን “መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ ማራቸው ብሎ እግዚአብሔርን ይጠይቅልህ” ማለት አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ ሲባል ከሰሙ ደም ስራቸው ይገታተራል፡፡

    እነርሱ ፈጣሪ ነው በእግዚአብሔር ፊት ቆሞ እንዲጸልይላቸው የሚፈልጉት፡፡ ፈጣሪ ፈጣሪን እንዲማልደው፣ በተጠመዘዘና በተጣመመ ቃል “የሚማልደው” ብለው አንዴ ስለደመደሙ፣ ፍጡር የሆነው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸሎት ሳይሆን ፈጣሪ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲለምንላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ወይ ጉድ በዙፋን ተቀምጦ የሚለምን ፈጣሪ አለ ብለው ማሰባቸው???

    መልአኩ ገብርኤል ፍጡር ስለሆነ የእኛ መጥፋት ስለሚያሳስበው፣ ወደ ጌታ ፊት ቀርቦ “የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” እያለ ጸሎት ሲያደርግልን በዙፋኑ የተቀመጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ “በምሕረት ተመልሻለሁ” ብሎ መልስ እንደሚሰጠው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የመላእክት የጸሎት እርዳታቸው ወደ ምሕረት እንደሚያደርሰን ተጽፎ ሳለ መናፍቃኑ አይቀበሉትም (ዘካ 1፡12-16)፡፡

    እኛ ኃጢአተኞች ስለሆንን ዕድሜ ለንስሐ እንድናገኝ፣ መልካምነት ሲጠፋብን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈራጅነቱ “ይቆረጥ” ብሎ ሲፈርድ፣ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ቀርቦ “ይህችን ዓመት ደግሞ ተዋት” እያለ ይማልድልናል ስለዚህ የመልአኩ የቅዱስ ገብርኤል ጸሎት ያስፈልገናል (ሉቃ 13፡6-9)፡፡ የጸለየውም ጸሎት ምላሽ አግኝቶ ንስሐ ስንገባ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እና ሌሎቹ መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ስለ እኛ ደስ ይላቸዋል (ሉቃ 15፡10)፡፡

    ቅዱሳን መላእክት፣ እናንተን የሰጠን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነውና ክብር ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡ እናንተን መናቅ አታስፈልጉንም ማለት እግዚአብሔርን መናቅ ነውና፣ ይህንን የእናንተን እርዳታ መቀበል ኑፋቄ አድርገው ከሚሰብኩን ወገኖቻችን ልብ ሰጥታችሁ እነርሱንም ለንስሐ እንዲበቁ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እንድትጸልዩላቸው ለእኛም የእናንተ ቃል ኪዳንና ጸሎት እንዲሁም እርዳታ ስለሚያስፈልገን ጸሎታችንና ጥበቃችሁ እርዳታችሁ አይለየን፡፡

    መናፍቃን ይህን ብቻ ሳይሆን የሚሉት እኛ መላእክት ያማልዳሉ ስንል ለማምለክ ያሰብን አድርገው ይተቹናል፡፡ ያማልዳሉ ማለት ይጸልያሉ ማለት ሲሆን ይህም ፍጡራን ስለሆኑ ለሰው ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ይቆማሉ ማለት ነው፡፡ “በዚያም ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ አለቃ ሚካኤል ይነሣል” (ዳን 12፡1) በተባለው መሠረት ስለእኛ ጉዳይ እንዲምረን ይቆሙልናል፡፡ ይህ የሚያሳየው ፍጡርነታቸው መናገር እንጂ አምላክ ናቸው ከሚል ጋር አይገናኝም፡፡

    ባጠቃላይ አባታችን ያዕቆብም መልአክ ከክፉ እንዳዳነው ሲናገር ፕሮቴስታንት በሕይወታችሁ እንደዚህ እንደ ያዕቆብ “መልአክ ይባርክህ ብላችሁ ታውቃላችሁ?” ወይስ “መልአክ ከክፉ አዳነኝ” ብላችሁስ መስክራችሁ ታውቃላችሁ? ካላወቃችሁ፣ እንደ ያዕቆብና እንደ ዳዊት እኛ ጠብቀን፣ ከክፉ አድነን ስላልን ለምን ትወቅሱናላችሁ? እኛ እንዲህ በማለታችን ኑፋቄ ከሆነ፣ ከላይ ያሉት እነ ንጉሥ ዳዊትና አባታችን ያዕቆብም መናፍቃን ናቸው ልትሉን ነው? እነርሱ ትክክል ካልሆኑ ጥቅሱ ለምን ተጻፈልን? ለምንስ ይዛችሁት ትዞራላችሁ? ካላመናችሁበት ለእኛው ለቀቅ አድርጋችሁ ዞር ለምን አትሉም?

    መናፍቃን ልብ ይስጣችሁ፣ አሜን!

    የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ወዳጆች፣

    ቅዱስ ገብርኤል ይባርካችሁ፣
    ቅዱስ ገብርኤል ይጠብቃችሁ፣
    ቅዱስ ገብርኤል ከክፉ ያድናችሁ፣
    ቅዱስ ገብርኤል ጸሎታችንና ምጽዋታችሁን ያሳርግላችሁ፣
    ቅዱስ ገብርኤል በጌታ ፊት ቀርቦ ማራቸው ብሎ ይጸልይላችሁ፤ ምልጃውም ትድረስላችሁ፡፡ አሜን! አሜን! አሜን!

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱስ መልአክ ይባርክህ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top