• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 13 November 2015

    ከጽንሰታ እስከ ፍልሰታ


    እመቤታችን የቅድስት ድንግል ማሪያም ቅድመ አያቶቿ ቴክታና በጥርቃ ይባላሉ፡፡ይህ ቀራቸው የማይባል ባለጠጎች ነበሩ ምንም  ሀብታቸው ቢበዛም የሚያወርሱት ልጅ ስለሌላቸው ያዝኑ ይተክዙ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ያምኑ ስለነበሩ በራዕይ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስትወጣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስትደርስ ስድስተኛይቱ ጨረቃን ጨረቃይቱ ፀሐይን ስትወልድ አይተዋል፡፡ ሕልም ፈቺ ነበርና ነግረው ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ ጨረቃይቱ ከፍጡራን  ሁሉ የምትሆን ናት የፀሐይ ነገር ግን ንጉስ ይሁን ነቢይ እንጃ አልተገለጸልኝም ብሏቸዋል፡፡

    ከዚህ በኋላ ቴክታ ጸነሰች ሴት ልጅም ወለደች ስሟንም ሂኤሜን አለቻት፡፡ ሄኤሜን ማለት ልመናዬን አገኘሁ ምኞቴን አገኘሁ ማለት ነው፡፡ሄኤሜን ዴርዴንን፡ዴርዴን ቶናን ፡ቶና ሲካርን ፡ ሲካር ሄርሜላን ፡ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና ማለት በሃይማኖት በምግባር የጸናች በንጽህና በቅድስና የተሸለመች ደግ ፍጥረት ማለት ነው፡፡

    ሃና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፡፡ በበጎ ሥራ የተራበ እያበሉ የተጠማ እያጠጡ ካላቸው ንብረት ለነዳያን እየመጸወቱ እግዚአብሄርን ዘወትር በጾም በጸሎት በንጽሕናና በቅድስና እያገለገሉ ይኖሩ ነበር ነገር ግን ልጅ ስላልነበራቸው ያዝኑ ይተክዙ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ከዛፍ ስር ተቀምጠው ሳለ ርግብ ከልጆቻቸው ጋር ሲጫወቱ ዕጽዋቱ አብበው አፍርተው አዩ እነርሱ ግን ልጅ ማጣታቸው የዘወትር ሃዘናቸው ነበርና እግዚአብሔርን  ልጅ  ይሰጣቸው ዘንድ ወንድ ቢሆን ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ሴት ብትሆን ለቤተ እግዚአብሔር መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ሰፍታ ትኑር ፡፡ እንጨት ሰብራ ውሃ ቀድታ ትርዳን አንልም ብለው ብጽአት ገብተዋል፡፡

    ሐምሌ 30 ቀን ሐና ለኢያቄም ግምጃ ሲያስታጥቁህ መቋሚያህ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ አለችው፡፡ ኢያቄምም ለሐና ፀአዳ ርግብ ሰበባቱን ሰማያት ሠንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ ብለው ያዩትን ራዕይ ተጨዋውተዋል፡፡ እንዲህ ያለ ራዕይ ካየን ብለው ዕለቱን በግብር አልተዋወቁም ፈቃደ እግዚአብሔር ቢሆንልን ብለው ለደጅ ጥናት ሰባት ቀን ሰንብተዋል ነሐሴ በገባ ሰባተኛው ቀን በፈቃደ እግዚአብሔር በብስራተ መልአክ በሩካቤ ዘበሕግ እመቤታችን ተፀነሰች፡፡

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ነሐሴ 7 ቀን ከተጸነሰች ጀምሮ በሐና ማሕፀን ሳለች ብዙ ተአምራትን ማለትም ድውይ ተፈውስ ዕውር ታበራ ሙት ታስነሳ ነበር፡፡ ከዚያውም ውስጥ ሳምናስ የሚባል የአጎቷ ልጅ ሙቶ ሊቀብሩት ሲሄዱ ሐና ትወደው ነበረና አልጋውን ይዛ ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት ተነስቶ በማሕፀን እያለች ያስነሳችው እመቤታችንን ሰማይና ምድርን ለፈጠረ እናቱ የምትሆኝ ሆይ ሰላምታ ይገባሻል ብሎ ሰግዶላታል፡፡ከቅድስት       ሐና  የምትወለደው የአምላክ እናት እንደሆነች መስክሯል ይህንና ይህንን የመሰለውን በማድረጓ በተአምራቷ ቀንተው አይሁድ በምቀኝት ሊገድሏቸው ተነሱ፡፡

    መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ቅዱስ ሊባኖስ ወደተባለ ተራራ ይዘሀት ሂድ ብሎት ‹‹እምሊባኖስ ትወጽእ መርዓት ከሊባኖስ ሙሽራ ትወጣለች›› እንዲል ‹‹ንኢ እምሊባኖስ ነይ ከሊባኖስ ነይ›› መኃ.መኃ ዘሰሎ 4፤8 እንዲል፡፡ እመቤታችን ግንቦት አንድ ቀን በ16 ዓ.ዓ በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡ በልደቷም ሁሉም ተደስተው ስሟንም ማርያም አሏት ፡ ማርያም ማለት ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ለጊዜውመ ለእናት ለአባትዋ ጸጋ ወሀብት ሆና ተሰጠታለችና ፍጻሜው ግን ለስው ሁሉ ጸጋ ሀብት ናትና ማርያም አሏት፡፡

    ቅድስት ሐና እንደወለደች በሰሙ ጊዜ ዘመዶቿና ጎረበቤቶቿ ዳቦ እየጋገሩ ንፍሮ እያነፈሩ ሌላም ልዩ ልዩ መባልዕትን እያዘጋጁ ይዘውላት መጡ፡፡ ዛሬም የእመቤታችን በዓል ሲከበር ይህ መንፈሳዊ ልማድ ሲወርድ ሲዋረድ ደርሷልና ይህም ሲፈጸም ይታያል፡፡ በዚህ እለት ዳቦ ጋግሮ ንፍሮ አነፍሮ ጠላ ጠምቆ ጎረቤት ተሰብስቦ ችግረኛን ማብላት ማጠጣት በአንድ ላይ ማዕድን መካፈል የቅድስት ሐናን በሊባኖስ ተራራ እመቤታችንን መውለድ ማሰብ የሚገባን የሚያበረታታ መንፈሳዊ  ልማድ እና ልዩ ልዩ ምግቦችን አዘጋጅቶ ችግረኞችን ማብላትና ማጠጣት በአንድነት ማዕድን መካፈል የሚደገፍ በረከትን የሚያስገኝ ነው፡፡

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም የብጽአት ልጅ ናትና 3 ዓመት ሲሆናት ይህቺ ልጅ አንድ ነገር በብትሆን ከእግዚአብሔርም ከልጃችንም ሳንሆን እንዳንቀር ሆዷዘመድ ሳይወድ አፏ እህል ሳይለምድ ወስደን እንስጥ ብለው መባዕ ጨምረው ወደ ቤተ መቅደስ ይዘዋት ሄዱ፡፡

    ሊቀ ካህናቱ ሕዝቡን ሰብስቦ የምግቧን ነገር ይያዝልኝ አለ ወዲያውም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ኃብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ ይዞ ረቦ ታየ፡፡ዘካርያስም ለእርሱ ይዞት የመጣ መስሎት ዛሬስ ክብሬን በሰው ፊት ሊገልጠው ነው ብሎ ሊቀበል ተነሳ መልአኩም ወደ ላይ ራቀበት ፡፡ የእርሱ ምክትል የሆነው ስምዖንም እንኪያስ ለእኔ የመጣ ይሆናል ብሎ ቀረበ መልአኩም ራቀበት፡፡ ካህናቱም ህዝቡም በተራ ቢቀርቡም ራቀባቸው ምናልባት ጥበበ እግዚአብሔር አይመረመርም ለዚች ብላቴና የመጣ ይሆናል ብለው ሐናን ትተሻት እልፍ በይ አሏት ፡፡ እልፍ ስትል ድክ ድክ እያለች እናቷን ስትከተል መልአኩ ፈጥኖ ወርዶ አንድ ክንፍ አንጽፎ አንድ ክንፍን ጋርዶ በሰው ቁመት ልክ ወደላይ ከፍ አድርጎ መግቧት ዐረገ፡፡ የምግቧ ነገር ከተያዘልንማ ትግባ እንጂ ብለው ከመካነ ደናግል አስገቧት ፡፡ ኅብስት ሰማያዊን እየተመገበች መላእክት እየጎበኟት  12 በቤተመቅደስ ኖራለች፡፡

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያም ስልሳ አራት አመት (64) ዓመት በዚህ ዓለም ኖራ ጥር 21 እሑድ ቀን ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ እናቴ ሆይ ከዚህ አለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ አላት ፡፡ ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህን ዘጠኝ ወር በማህፀኔ ተሸክሜህ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን  አለችው፡፡ በሲኦል የሚሰቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ ሞትሽ ለእነዚህ ቤዛ ይሆናቸዋል አልት፡፡ እኒህን ከማርክልኝ ይሁን አለችው፡፡ ቅድስት ነፍሷን ከክብርት ስጋዋ ለይቶ በዝማሬ መላእክት አሳረጋት፡፡ ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ እመቤታችንን ቅበሩ አላቸው፡፡ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ አይተው ልጇ ተነስቷል ብለው አይሁድን ሲያውኩ አሁን ደግሞ እናቱ አረገች  ብለው ሊያውኩን ነው ኑ እናቃጥላት ብለው ተነሱ፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ታውፍንያ ዘሎ ያልጋውን ሸንኮር ያዘ ፡፡ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ሁለት እጁን በሰይፍ ቀጣዉ፡፡ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት ራሷን ዘንበል አድርጋ ቅዱስ ጴጥሮስን እንደነበር አድርግለት አለችው፡፡


    ፍልሰታ ለእግዝትነ ማሪያም

       ፍልሰታ መሠረተ ቃሉ ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ አቤቱ ወደ እረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት››መዝ 131፡8‹‹ ተንስኢ ወንኢ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኬክሕ ቅሩበ ጥቅም አቅራቢያዬ መልካሟ ርግብ ተነሽ ነዬ በግንብ አጠገብ ወዳለው ዋሻ ጥላ››መኃ.መኃ 2፡10-14 የሚለው ነው፡፡

    ፍልሰታ የሚለው የእመቤታችን ሥጋ ከጌቴሰማኔ ወደ ገነት መፍለሱን ኃላም በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረበት መነሳቱን ለማመልከት የሚነገር ቃል ነው፡፡ ሐዋርያት እመቤታችን ካረፈች በኃላ በሀዘን ላይ እያሉ ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ መላእክት የእመቤታችንን ሥጋዋን ወደ ገነት ሲያፈልሱ አገኛቸው፡፡ ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሳኤ ሳላይ ቀረሁን ብሎ ከልቡ አዘነ እመቤታችን ግን ሐዋርያት ትንሣኤዬን እርገቴን አላዩም አንተ ግን አይተሃል አሁንም ሄደህ ተነሣች ዐረገች በላቸው ባላ ሰበኗን ሰጠችው፡፡

    ሄዶ የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ አላቸው፡፡ አግኝተን ቀበርናት አሉት፡፡ ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ለሰሚም አያምር ተው ይህ ነገር አይመስለኝም አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠርጠር ልማድህ ነው አለው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ተቆጥቶ ፊት ፊት እየሮጠ እነርሱ እየተከተሉት ጌቴሴማኒ ከመቃብሯ ደረሱ፡፡ ቢከፍተው አጣት ደንግጦ ቆመ፡፡ አታምኒኝም ብዬ እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች አላቸው፡፡ ለዚህ ቃልህ ምስክር የሚሆን ምን ይዘሀል አሉት፡፡ በዚህ ሰበን አልገነዛችሁምን አላቸው፡፡ ትንሣኤ ዕርገቷን  አምነው ሰበኑን ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ዛሬም ሠራዒ ዲያቆኑ በቅዳሴ ጊዜ በሚይዘው መስቀል ላይ የሚደረገው ጨርቅ የእመቤታችን ሰበን ምሳሌ ነው፡፡

    ነገር ግን ሐዋርያት የእመቤታችንን የዕርገቷን ምሥጢር ለማወቅ ይጓጉ ነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ‹‹እናቴን አሳያችኋለው›› የሚል ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ እርገቷን አይቶ እነርሱ ሳያዩ በመቅረታቸው እያዘኑ የጌታን ተስፋ ሲጠባበቁ ሳለ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ እመቤታችንን እንዲያሳየን ከነሐሴ 1 ቀን ጀምረን በጾም ፈጣሪያችንን እንጠይቀው አላቸው እነርሱም ሐሳቡን ተቀብለው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ ሁለት ሱባኤ ከጾሙ በኋላ ነሐሴ 16 ቀን ጌታ መላው ሐዋርያትን ወደ ገነት አውጥቶ በገነት ዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረው መቃብር አመቤታችንን ነፍስዋን ከሥጋዋ አዋህዶ አንስቶ ትንሳኤወንና ዕርገቷን አሳይቶ ለዓለም ይህንኑ እንዲያስተምሩ አዘዛቸው፡፡

    እኛም እንደ ሐዋርያት የእርሷን በረከት ለመቀበል ከነሐሴ 1 እስከ 16 ቀን ድረስ ሕጻን ፡ጎልማሳ፡ሽማግሌውም ሁሉ በመጾም እናሳልፈዋለን ፡፡ የአዟኝቷን ምስጋናዋን ከአንደበታችን ፍቅሯን ከልቡናችን አይለይብን ፡፡ እናትነቷ ከሁላችንም ጋር ይሁን 

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ከጽንሰታ እስከ ፍልሰታ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top