ሢመት፦ ሹመት፥ ሥልጣን፥ ማዕርግ ማለት ነው። የሚሾም፥ የሚሸልም፥ የሚያሠለጥን፥ የሚቀድስ፥ የሚያከብር ደግሞ እግዚአብሔር ነው። የይሁዳ ገዢ ጲላጦስ፦ ጌታችንን፦ “ልሰቅልህ ሥልጣን እንደ አለኝ፥ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንደ አለኝ አታውቅምን?” ባለው ጊዜ፥ “ከሰማይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ አንዳች ሥልጣን የለህም፤” ያለው ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፱፥፲-፲፩።
ሢመት ሁለት ወገን አለው፥ ይኸውም፦ ሢመት ዘሥጋዊና ሢመት ዘመንፈሣዊ ነው። የመጀመሪያው ለሥጋዊው አስተዳደር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለመንፈሳዊው አስተዳደር ነው። ሊቀ ካህናቱ ዓዛርያስ፦ “እምነ መንግሥት የዓቢ ክህነት፤ ከሥልጣነ መንግሥት ሥልጣነ ክህነት ይበልጣል፤ (ከሥጋዊው መንፈሣዊው፥ ከምድራዊው ሰማያዊው ይልቃል)፤” ብሎ ለንጉሡ ለዖዝያን እንደነገረው፥ ሢመት ዘመንፈሣዊ የበላይ ነው። በመሆኑም፦ ሥጋውያኑ በመንፈሳውያኑ እጅ ተቀብተው ይሾማሉ እንጂ መንፈሳውያኑ በሥጋውያኑ አይሾሙም። ሠያሜ ካህናት፥ ሠያሜ ሕግ እግዚአብሔር ነውና። ቅዱስ ወንጌል፦ ጌታ፥ ለደቀ መዛሙርቱ፦ “ሥልጣንን ሰጣቸው፤” ይላል። ማቴ ፲፥፩፣ ማር ፫፥፲፭፣ ሉቃ ፲፥፲፱። ይኽንንም ሥልጣን፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ በምድር የምታስሩት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈቱት በሰማይ የተፈታ ይሆናል።” በማለት አጽንቶላቸዋል። ማቴ ፲፮፥፲፱፤ ፲፰፥፲፰። ዐረፍተ ዘመን የማይገታው፥ ባለጊዜ የማያስቀረው መሆኑን ሲነግራቸውም፦ “እኔም እስከ ዓለም ፍጸሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ፤” ብሏቸዋል። ማቴ ፳፰፥፳። ከዚህም የተነሣ ካህናት “አማልክት ዘበጸጋ” ናቸው። ይህም በጸጋ እግዚአብሔር ዓለሙን እንዲገዙ ሥልጣን እንደተሰጣቸው ያመለክታል። በጸሎተ ኪዳን ላይ፦ “የሞት ማሠሪያ ክህደትን በሃይማኖት ድል እንድንነሣው ያደረግህልን፥ ለሚያምኑብህ ቅን ልቡናን የፈጠርህ፥ ከሰው ወገን አማልክት ይባሉ ዘንድ (እንባል ዘንድ)፥ በመንፈስ የጠላትን ኃይል ሁሉ እንረግጥ ዘንድ የሰጠኸን፥ የማይፈታውን እንፈታ ዘንድ (ምድራውያን ነገሥታት ሊፈቱት የማይቻላቸውን እንፈታ ዘንድ፥ ሌዋውያን ካህናት ሊያስተሠርዩት ያልተቻላቸውን የውስጥ ኃጢአት እናስተሠርይ ዘንድ) ከአባትህ ዘንድ ፍቅርን አደረግህልን፥ አቤቱ በመካከል ሆነህ አስታረቅኸን።” የሚል አለ። ጥንት አዳም ሲፈጠር ነቢይ፥ ካህን፥ ንጉሥ፥ የጸጋ አምላክ (ገዥ) ሆኖ ነበር። ዘፍ ፩፥፳፮-፳፯። እግዚአብሔር ሙሴን፦ “እነሆ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፥ ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል።” ብሎታል። ዘጸ ፯፥፩። ጌታችንም በወንጌል፦ “እኔ አማልክት ናችሁ አልሁ፥ ተብሎ በኦሪታችሁ ተጽፎ የለምን? የእግዚአብሔር ቃል የመጣላቸውን እነዚያን አማልክት ካላቸው የመጽሐፉ ቃል ይታበል ዘንድ አይቻልም።” በማለት ከመዝሙረ ዳዊት ጠቅሶ አስተምሯል። ዮሐ ፲፥፴፩፣ መዝ ፹፩፥፮። በመሆኑም መንፈሳውያን ባለሥልጣኖች የሆንን ሁሉ ክብራችንን ማዕርጋችንን ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል። የከበርንበትን ጸጋ ማክበር መንፈሳዊ ግዴታችን ነውና። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በምድራውያን ነገሥታት ፈርዖኖች ላይ አማልክት ዘበጸጋ (የጸጋ ገዢዎች) ሆነን የተሾምነውን መንፈሳዊ ሹመት አምዘግዝገን በመጣል በዓለማውያኑ ፊት የምናዋርደው ከሆነ እግዚአብሔርም ሰውም ይፈርድብናል።
እግዚአብሔር የሚመርጠውን ያውቃል። “ሁሉን እያንዳንዱን ያውቀዋልና። የሰውንም ግብሩን ሊነግሩት አይሻም፥ እርሱ በሰው ያለውን ያውቅ ነበርና።” ይላል። ዮሐ ፪፥፳፬-፳፭። ቅዱስ ዳዊት፦ እግዚአብሔር ለእርሱ የሚሆኑትን እንደሚመርጥ ሲናገር፦ “ሕዝብ ዘኀረየ ሎቱ ለርስቱ፤ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ፤” ብሏል። መዝ ፴፪፥፲፪። ጌታችን በወንጌል ደቀመዛሙርቱን፦ “አኮ አንትሙ ዘኀረይክሙኒ፥ አላ አነ ኀረይኩክሙ ወሤምኩክሙ። እኔ መርጥኋችሁ፥ ሾምኋችሁም እንጂ እናንተ የመረጣችሁኝ አይደለም።” ያላቸው ለዚህ ነው። ዮሐ ፲፭፥፲፮። ይኽንን በቃልም በተግባርም የተማሩ ደቀመዛሙርት፥ እነርሱ በጾምና በጸሎት የሚገባውን አገልግሎት እየፈጸሙ፥ ምርጫውን ለእግዚአብሔር አሳልፈው ይሰጡ ነበር። “አቤቱ ልብን ሁሉ የምታውቅ አንተ፥ ከእነዚህ ከሁለቱ የመረጥኸውን አንዱን ግለጥ። ይሁዳ ወደ ሀገሩ ይሄድ ዘንድ የተዋትን ይህቺን የአገልግሎትና የሐዋርያነትን ቦታ የሚቀበላትን ግለጥ።” ብለው ዕጣ አጣጣሏቸው። የሐዋ ፩፥፳፬-፳፮። “የእግዚአብሔርን ሥራ ሲሠሩ፥ ሲጾሙም መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን እኔ ለፈለግኋቸው ሥራ ለዩልኝ አላቸው። ያንጊዜም ከጾሙ ከጸለዩ፥ እጃቸውንም በራሳቸው ላይ ከጫኑባቸው በኋላ ላኩአቸው።” ይላል። የሐዋ ፲፫፥፩-፫። ለዲቁና እንኳ የሚመረጡት በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የከበሩ ብቻ ነበሩ። አሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሕዝቡን ሁሉ ጠርተው፦ “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም። ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፤ እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር እንተጋለን።” አሉአቸው። ይህም ነገር በእነርሱ ዘንድ የተወደደ ሆነ፤ ሃይማኖቱ የቀና እና መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን እስጢፋኖስን፥ ፊልጶስን፥ ጵሮኮሮስን፥ ኒቃሮናን፥ ጢሞናን፥ ጳርሜናን፥ ወደ ይሁዲነት የተመለሰውን የአንጾኪያውን ኒቆላስንም መረጡ። በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፥ ጸልየውም እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጫኑ። ዮሐ ፮፥፪-፮።
“ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤” ሉቃ ፯፥፮።
ሮማዊው መቶ አለቃ አገልጋዩ ቢታመምበት የአይሁድን ሽማግሌዎች አማላጅ አድርጎ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ላካቸው። እነርሱም፦ “ፈጥነህ ውረድ፥ ይህን ልታደርግለት ይገባዋልና። እርሱ ወገናችንን ይወዳልና፥ ምኵራባችንንም ሠርቶልናልና።” ብለው አጥብቀው ለመኑት። ጌታም ከእነርሱ ጋር ሄደ፤ ወደ ቤቱም በቀረበ ጊዜ፥ የመቶ አለቃው ወዳጆቹን፦ “አቤቱ፥ አትድከም፤ ከቤቴ ጣራ በታች ትገባ ዘንድ አይገባኝምና። እኔም ወደ አንተ ልመጣ አይገባኝም ብሏል፥ ብላችሁ ንገሩልኝ፤” አላቸው። ጌታም በሰማው ነገር አደነቀ፥ “ይገባናል፤” ብለው የተከተሉትንም፦ “እላችኋለሁ፥ በእስራኤልስ እንኳ እንዲህ ያለ እምነት አላገኘሁም፤” አላቸው። ሉቃ ፯፥፩-፲። ይህ የመቶ አለቃው እምነት ትህትና እና መንፈሳዊ ጥበብ አብነት ሆኖ ከምዕመኑ ጀምሮ እስከ ፓትርያርክ ድረስ ከመቍረባቸው በፊት ይጸልዩታል።
የነቢያት አለቃ ሙሴ እግዚአብሔር በመረጠው ጊዜ፦ “ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ ትናንት፥ ከትናንት ወዲያ ባሪያህን ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁም። እኔ አፌ ኰልታፋ፥ ምላሴም ተብታባ የሆነ ሰው ነኝ። . . . ጌታ ሆይ፥ እማልድሃለሁ፤ መናገር የሚችል የምትልከው ሌላ ሰው ፈልግ፤” ብሏል። ዘጸ ፬፥፲-፲፫። ጌዴዎን፦ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ በተናገረው ጊዜ፥ “ጌታ ሆይ! እሺ! እስራኤልን በምን አድናለሁ? ወገኔ በምናሴ ነገድ ዘንድ ጥቂቶች ናቸው፤ እኔም በአባቴ ቤት የሁሉ ታናሽ ነኝ። . . . አቤቱ! አምላኬ ሆይ! ወዮልኝ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁ።” ብሏል። መሳ ፮፥፲፭፣፳፪። እግዚአብሔር ነቢዩ ኤርምያስን፦ “በእናትህ ሆድ ሳልሠራህ አውቄሃለሁ፤ ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፥ ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ።” ቢለው፥ “ወዮልኝ ጌታ እግዚአብሔር፥ እነሆ ሕፃን ነኝና እናገር ዘንድ አልችልም፤” ሲል መልሷል። ኤር ፩፥፬-፯። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፦ “ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ የማይመረመረውን የክርስቶስን ባለጠግነት ለአሕዛብ አስተምር ዘንድ ይህን ጸጋ ሰጠኝ።” ብሏል። ኤፌ ፫፥፰። ይህ ሐዋርያ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ባስተማረበትም ጊዜ፥ “ለጴጥሮስ ታየው፥ ከዚያም በኋላ ለአሥራ አንዱ ደቀመዛሙርት ታያቸው። ከዚህም በኋላ ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታያቸው፤ ከእነርሱ ብዙዎቹ እስከ ዛሬ አሉ፤ አንዳንዶቹ ግን አንቀላፍተዋል። ከዚህ በኋላ ለያዕቆብ ታየው፥ ኋላም ለሐዋርያት ሁሉ፤ ከሁሉም በኋላ ጭንጋፍ ለምመስል ለእኔ ታየኝ። ከሐዋርያት ሁሉ እኔ አንሣለሁና።” ሲል እናገኘዋለን። ፩ኛ ቆሮ ፲፭፥፭-፱።
በቤተ ክርስቲያንም፦ በየገዳማቱ እና በየአድባራቱ ለአበ ምኔትነት እና ለእልቅና ሲመረጡ “አይገባንም፤” እያሉ የሚጠፉ፥ እንዳይጠፉም ከግንድ ጋር የሚታሰሩ እንደነበሩ ታሪክ ሰምተናል። በእኛም ዘመን ለጵጵስና ታጭተው “አይገባንም፤” ብለው የቀሩ በጣት የሚቆጠሩ አባቶች አይተናል። ብዙ ሰው በተለያየ መንገድ ደጅ የሚጠናውን እና ገንዘብ የሚያደርገውን ሥልጣን “አይገባኝም፤” ብሎ መግፋት ሰማዕትነት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በብዙ ፍለጋ (ባሕሩን በታንኳ፥ የብሱን በእግር ተጉዘው) ያገኙት ሰዎች፥ “መምህር ሆይ፥ ወደዚህ መቼ መጣህ?” አሉት። እነዚህ ሰዎች ያን ያህል የደከሙት ሕይወትን ፈልገው አልነበረም። “እንዳንራብ ኅብስት አበርክቶ ያበላናል፤” ብለው ነው። ይኽንንም ስለሚያውቅ ነው፥ ከፊታቸው ዘወር ያለው። ፈልገው ባገኙት ጊዜ ግን፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ እናንተ የምትፈልጉኝ እንጀራ ስለበላችሁና ስለጠገባችሁ ነው እንጂ ተአምራት ስለ አያችሁ አይደለም። የሰው ልጅ (በተዋሕዶ ሰው የሆነ ክርስቶስ) ለሚሰጣችሁ ለዘለዓለም ሕይወት ለሚኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚጠፋው መብል አይደለም፤” ብሎአቸዋል። ዮሐ ፮፥፳፭-፳፯። ጌታችን አስቀድሞ ከፊታቸው ዘወር ያለው ስለ ሁለት ነገር ነው። አንደኛው፦ “ማንም የማይሾመኝ፥ ሹመት የባሕርይ ገንዘቤ የሆነ አምላክ ነኝ፤” ሲላቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ፦ “ሥልጣን አያጓጓችሁ፥ ለሹመት ቢፈልጓችሁ እንኳ ዘወር በሉ፥ ጥፉ፤” ለማለት ለአብነት ነው። “ጌታችን ኢየሱስም መጥተው ነጥቀው ሊያነግሡት እንደሚሹ ዐወቀባቸውና ብቻውን ወደ ተራራ ሄደ።” ይላል። ዮሐ ፮፥፲፭። ከላይ ለመግለጥ እንደሞከርነው የቀድሞዎቹ እርሱን አብነት አድርገው ተጠቅመዋል። እኛ ግን አገልግሎቱን ለጽድቅ ሳይሆን ለእንጀራ አደረግነው። እንጀራን ስናስቀድም ደግሞ ጽድቅን እናጣለን፥ እንጀራውም ደዌ ይሆንብናል፥ በረከት አይኖረውም። ጽድቅን ብናስቀድም ግን ሁሉንም አናጣውም፥ የበረከት እንጀራ ይሰጠናል። ምክንያቱም የነፍስ ቅድስና ለሥጋ ይተርፋልና።
ፍቅረ ሢመት፤
ፍቅረ ሢመት ያደረበት ሰው ለሥልጣን ብሎ የማይሠራው ኃጢአት፥ የማይፈጽመው በደል የለም። ቃየል ወንድሙን አቤልን ከገደለበት ሦስት ምክንያቶች አንዱ ሥልጣን ነው። ይኸውም አባታቸው አዳም “ይህ ብሩኅ ገጽ ያለው ልጄ አልጋ ወራሼ ነው፤” ይል ስለነበር፥ በዚህ ቀንቶ ነው። “እኔ ታላቅየው እያለሁ እንዴት እርሱ ይሆናል?” ብሎ ነው። አቤሴሎም ራሱን ለማንገሥ ሲል በአባቱ ላይ በማመፅ ንጉሡን ዳዊትን አሳድዶታል፥ በጦርነትም ገጥሞታል። ፪ኛ ሳሙ ፲፭፥፩-፴፯። ንጉሥ ሄሮድስን ያስደነገጠው፥ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሕፃናትን ያለ ርኅራኄ እንዲፈጅ ያደረገው፥ “ኮከቡን በምሥራቅ አይተን እንሰግድለት ዘንድ መጥተናልና፥ የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?” የሚለው የሰብአ ሰገል ጥያቄ ነው። ማቴ ፪፥፩-፲፰። የሚገርመው ነገር ሊገድለው ካሳደደው ከኢየሱስ ክርስቶስ በፊት አሳዳጁ ሄሮድስ ቀድሞ ሞተ። በእናቱ እቅፍ ሆኖ ወደ ግብፅ የተሰደደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጽድቅ ስለ ጽድቅ ለሚሰደዱ ሁሉ አብነታቸው ነው።
በከበሬታ ወንበር ይቀመጡ የነበሩ ፈሪሳውያን ከሰዱቃውያን ጋር ሆነው እስከመጨረሻው ኢየሱስ ክርስቶስን የተቃወሙት፥ ለመስቀል ሞትም አሳልፈው የሰጡት የሥልጣናቸው ነገር አሳስቧቸው ነበር። እርስ በርሳቸውም፦ “የምታገኙት ምንም ጥቅም እንደሌለ ታያላችሁን? እነሆ፥ ዓለም ሁሉ ተከትሎታል፤” ይባባሉ ነበር። ዮሐ ፲፪፥፲፱። ይኸውም፦ “ሕዝቡ በጠቅላላ በትምህርቱ ተማርኮ፥ በተአምራቱ ተደንቆ ለኢየሱስ ክርስቶስ ከተገዛ እኛ ማንን እንገዛለን?” ብለው ነው። አሕዛብ እንዲህ ዓይነት ጠባይ አላቸው። ኢየሩሳሌምን የከበበ የአሶር ንጉሥ ሰናክሬም፥ አንድ መቶ ሰማኒያ አምስት ሺህ ሠራዊቱን እርሱ ባላወቀው መንገድ የእግዚአብሔር መልአክ በቀሠፈበት ጊዜ ሸሽቶ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ነበር። በዚያም በሚያመልከው ጣዖት በናሳራክ ፊት ሰግዶ ሳለ፥ ልጆቹ አድራሜሌክና ሳራሳር በሰይፍ ገድለውታል። ይኽንንም ያደረጉት፦ “አባታችን ሕዝቡን አስጨርሶ የመጣው እኛ በማን ላይ ልንነግሥ ነው?” ብለው ነው። ፍቅረ ሢመት እንዲህ በወላጅም ላይ ያስጨክናል። ኢሳ ፴፯፥፴፮-፴፰።
በሥልጣን ታሪክ፦ ያልተሾመው የተሾመውን፥ የተሾመው ደግሞ ይቀናቀነኛል ብሎ የሚያስበውን የመገፋፋት ነገር አለ። መገፋፋት ብቻ ሳይሆን በመድኃኒትም ይሁን በሌላ መንገድ በሕይወትም ጭምር እስከመፈላለግ ይደርሳሉ። በዚህም በሽተኞች ሆነው የቀሩ፥ በሞትም የተወሰዱ አሉ። እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ግብረ አሕዛብ ነው። “አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር በገባህ ጊዜ እነዚያ አሕዛብ የሚያደርጉትን ርኵሰት ታደርግ ዘንድ አትማር። ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚሠዋ፥ ምዋርተኛም ሞራ ገላጭም፥ አስማተኛም፥ መተተኛም፥ በድግምት የሚጠነቍልም፥ መናፍስትንም የሚጠራ፥ ጠንቋይም፥ ሙታን ሳቢም፥ በወፍም የሚያሟርት በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።” ይላል። ዘዳ ፲፰፥፱-፲፫። “ምዋርተኞችና አስማተኞች ሆኑ፥ ያስቆጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ።” የሚልም አለ። ፪ኛ ነገ ፲፯፥፲፯። የእነዚህም መጨረሻቸው ከመንግሥተ ሰማያት በአፍአ መቅረት ነው። ራእ ፳፪፥፲፭።
የሥልጣን ነገር የላዩን ትተን የታቹን ማለትም፦ የዕድሩን፥ የዕቁቡን፥ የማኅበሩን፥ የሰንበት ት/ቤቱን፥ የሰበካ ጉባኤውን እንኳን ብንመለከት፥ ሁላችንም ሞተን ተሟሙተን ቢቻል ሊቀመንበር፥ ካልተቻለ ደግሞ ጸሐፊ መሆንን እንፈልጋለን። ትንሹንም ሆነ ትልቁን ሥልጣን የምንፈልገው ደግሞ ለማገልገል ሳይሆን ለመገልገል ነው። አብነታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ያስተማረንም፥ ያሳየንም እንዲህ አይደለም። በትምህርቱ የነገረን፦ “አሕዛብን አለቆቻቸው እንዲፈርዱባቸው፥ ታላላቆቻቸውም እንዲሠለጥኑባቸው አታውቁምን? ለእናንተስ እንዲህ አይደለም፤ ነገር ግን ከእናንተ አለቃ ሊሆን የሚወድ አገልጋይ ይሁናችሁ። ከእናንተም ታላቅ ሊሆን የሚወድ የሁሉ ታዛዥ ይሁናችሁ። የሰው ልጅ (ወልደ ዕጓለ እመሕያው ክርስቶስ) ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ ሊያገለግሉት አልመጣም።” ብሎ ነው። ማር ፲፥ ፵፪-፵፭። ስለዚህ ዓላማችን ሁሉ አገልግሎት ይሁን። የምናገለግለውም ምድራውያን ገዢዎችን ሳይሆን የሰማዩን ገዢ እግዚአብሔርን ሊሆን ይገባል። እነርሱ መገልገል ከፈለጉ እንደ ምእመን ወንጌል እየተማሩ፥ ንስሐ እየገቡ፥ እያስቀደሱ፥ ሥጋ ወደሙ እየተቀበሉ ሊገለገሉ ይችላሉ። የሚገባቸውንም ክብር አያጡም። “ለእግዚአብሔር ብላችሁ ለሰው ሁሉ ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ ለንጉሥም ቢሆን፥ ክፉ አድራጊዎችን ሊቀጡ፥ በጎ አድራጊዎችንም ሊያመሰግኑ እርሱ ይልካቸዋልና። . . . ሁሉን አክብሩ፥ ባልንጀራችሁንም ውደዱ፥ እግዚአብሔርን ፍሩት፥ ንጉሥንም አክብሩት።” ይላልና። ፩ኛ ጴጥ ፪፥፲፫-፲፯። ችግር የሚፈጠረው እግዚአብሔርን የማይፈሩ፥ ሕዝቡን የሚበድሉ ከሆነ ነው። ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብተው እንዘዝ፥ ሹመት እናደላድል የሚሉበትም ጊዜ አለ። ያን ጊዜ “እግዚአብሔርን የይደለ እናንተን ልንሰማ በእግዚአብሔር ፊት ይገባልን? እሰኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ። እኛስ ያየነውን እና የሰማነውን ከመናገር ዝም እንል ዘንድ አንችልም፤” ልንል ይገባል። የሐዋ ፬፥፲፱።
በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ሰው የሚመለከተው ሥልጣኑን የያዘው የእርሱ ዘር መሆኑን ብቻ ነው። ችግሩን እያወቁት፥ ጉድለቱን እየተረዱት፥ ጥፋቱን እያስተዋሉት በዘረኝነት ይታወራሉ። እንዲህ ዓይነት ሰዎች በሌላው ላይ ለመሠልጠን ይስማማሉ እንጂ ወስደው አንድ ቤት ቢዘጉባቸው እርስ በርስ ተበላልተው የሚያልቁ ናቸው። በአውራጃ፥ በወረዳ እየተከፋፈሉ እርስ በርስ ለመጠፋፋት ትግል የሚገጥሙ ናቸው። ይህ ችግር የተወሰነ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የሁሉንም በር አንኳኩቶ የገባ፥ ዙፋኑንም ዘርግቶ የነገሠ ነው። “ሰው ራሱን አያይም፤” እንደተባለው ሆኖብን ነው እንጂ ሁላችንም ጤነኞች አይደለንም። በክርስትና ሕይወት የሚጠየቀው ሃይማኖቱና ሥነምግባሩ እንጂ ዘር አይደለም። ምክንያቱም “ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ ወንድሞቻችሁን ትወዱ ዘንድ፥ በእውነት በመታዘዝ ሰውነታችሁን አንጹ፤ እርስ በርሳችሁም ተፋቀሩ። ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፤ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ።” ይላልና። ፩ኛ ጴጥ ፩፥ ፳፪- ፳፫። ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም፦ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው። እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከሥጋዊና ከደማዊ ግብር ወይም ከወንድና ከሴት ፈቃድ አልተወለዱም፤” ብሏል። ዮሐ ፩፥፲፪።
የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን አሜን።
0 comments:
Post a Comment