ኢያሱ ማለት የቃሉ ትርጉም መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ኢያሱ መባሉ ስለሁለት ነገር ነው አሜሊቃዊያን ድል አድርጎ እስራኤልን ምድረ ርስት እንዲወርሱ አድርጎልና ሁለተኛው ኢያሱ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ እንዲሆን አስቀድሞ ጌታ ያውቃልና ይህም ኢያሱ አእዛብን ድል አድርጎ ምድረ ርስት እንዳስገባቸው የሁላችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያቢሎስን ድል አድርጎ መንግስቱን አውርሶናልና ኢያሱ በጌታችን ይመሰላል፡፡
ኢያሱ ነቢይ የተወለደው በምድረ ግብጽ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ አውሴ ይባላል:: ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ215 ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ_ነቢያት_ሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ 80 ዓመቱ ኢያሱ ደግሞ 40 ዓመቱ ነበር::ሕዝቡ ልበ ደንዳና አልታዘዝ ባይ ነበርና ለአርባ ቀናት ብቻ የታሠበላቸውን መንገድ አርባ ዓመታት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምህሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም::
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ደብረ_ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን ካህናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: በዚህ ወቅትም እድሜው ሠማንያ ዓመት ነበር፡፡ እግዚአብሔርም በእስራኤል ላይ ሾመው፡፡ ሕዝቡንም በትጋት ያገለግል ነበር፡፡ በድንቅ ተዓምራት ዮርዳኖስን ከፍሎ አሻገረ የኢያሪኮን ቅጥር አፈረሰ ጠላቶቹን ድል ነስቶ ምድረ ርስት ከነአንን በእግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት እንድወርሱ አድርጎል፡፡
ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን በተወለደ በ120 ዓመቱ መስከረም 4 ቀን በእዚች ዕለት በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለሠላሳ ቀናት አለቀሱለት:: በረከቱ ይደርብን እኛንም በቅዱሱ ምልጃ ይማረን፡፡
0 comments:
Post a Comment