• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday, 5 November 2015

    ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፪)

    መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው

                    በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

                                                                                              (ክፍል ፩ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ  http://gundemeskel.blogspot.com/2015/11/blog-post_46.html) 

    ፪፦ በውዳሴ ማርያም ትሰብከዋለች፦

    ውዳሴ ማርያም፦ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ፥ ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ከፈጣሪ በታች ሆና  ለምትከብር ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ያቀረበው ምስጋና ነው። ሊቃውንት የቤተክርስቲያንን ትምህርት ገና በሕፃንነት የሚጀምሩት ከውዳሴ ማርያም ነው። (ንባቡን ቃል በቃል ማጥናት የሚጀምሩት በአምስት እና በስድስት ዓመታቸው ነው)። የዜማውንም ትምህርት እስከ ድጓ ድረስ የሚዘልቁት፦ «ሰላም ለኪ፤» ብለው ከውዳሴ ማርያም ዜማ ጀምረው ነው። የዚህንም ጣዕሙን የሚያውቁት በውስጡ ያለፉ ሰዎችና ሲነገራቸው የሚገባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። አልፎ ሂያጅ መንገደኛ ግን አይገባውም። በውስጡ አልፈውም በዕውቀት ብቻ የቀረባቸው፥ ከሰውነታቸው ያልተዋሐዳላቸው፥ ምሥጢሩ የተሰወረባቸው፥ ማሩ  የመረረባቸው፥ ወተቱ የጠቆረባቸው፥ «ነአኲተከ» እንኳ ካላሉት መናፍቃን፥ ዕድል ፈንታቸው ጽዋ ተርታቸው የሆነባቸውም ጥቂቶች አይደሉም። የጥንቶቹ መናፍቃን ቢያንስ የተማሩ ናቸው፥ ነገር ግን በዕውቀታቸው ሲመጻደቁ አጓጉል ፍልስፍና ውስጥ እየገቡ በትዕቢት ምክንያት፦ ትርጓሜው፥ ምሥጢሩ እየተሰወረባቸው ተስነካክለዋል።

    የውዳሴ ማርያም ድርስት የመንፈስ ቅዱስ ድርሰት ነው፤ በትርጓሜው መቅድም ላይ፥ ስለ ደራሲው ስለ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ ይላል። ቅዱስ ኤፍሬም የያዕቆብ ዘንጽቢን ደቀ መዝሙር ነው። ያዕቆብ ዘንጽቢን ቊጥሩ ከሠለስቱ ምእት (ከሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ) ሊቃውንት ነው። እነዚህም እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው፥ «ወልድ ፍጡር ነው፤» (ሎቱ ስብሐት) ያለ አርዮስን በአ ፍም በመጽሐፍም ረትተው እርሱን እና ትምህርቱን አርዮስን አውግዘው የክርስትናን ሃይማኖት ያጸኑ ናቸው። ወልድ ዋሕድ ኢየሱስ ክርስቶስም ሦስት መቶ አሥራ ዘጠነኛ እየሆነ በመካከላቸው ይገኝ ነበር። ይኸውም  ይታወቅ ዘንድ ጉባኤውን ከመጀመራቸው በፊት ሦስት መቶ አሥራ ስምንት የነበሩት፥ ጉባኤውን በጸሎት ሲከፍቱ ሦስት መቶ አሥራ ዘጠኝ ይሆኑ ነበር። ጉባኤውን በጸሎት ከዘጉ በኋላ ደግሞ ተመልሰው ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ይሆኑ ነበር። «በዚህም፦ ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት፥ እኔ በዚያ በመካከላቸው እኖራለሁና።» ያለውን ቃሉን ፈጽሞላቸዋል። ማቴ ፲፰፥፳። ከዚህም ሌላ፦ «እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ በዘመኑ ሁሉ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ።» በማለት ለአባቶቻቸው ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸውን ቃል ኪዳን አጽንቶላቸዋል። ማቴ ፳፰፥፳። ዘመኑም ፫፻፳፭ ዓ/ም ነው።

    ቅዱስ ያዕቆብ ለአውግዞተ አርዮስ ሲሄድ ቅዱስ ኤፍሬምን አስከትሎት ነበር። አርዮስን አውግዘው፥ ሃይማኖትን አጽንተው ሲመለሱ፥ ካደሩበት ቦታ ዐምደ ብርሃን (የብርሃን ምሰሶ) ተተክሎ ሌሊት በሕልም ራእይ ያያል። እርሱም፦ «ራእ ዩን እንደገለጽክልኝ፥ ምሥጢሩን (ባለቤቱንም) ግለጥልኝ፤» ብሎ ጸለየ። (ወደ እግዚአብሔር አመለከተ)። በዚህን ጊዜ ከእግ ዚአብሔር የታዘዘ መልአክ መጥቶ፦ «ባስልዮስ ዘቂሳርያ ነው፤ ምክንያቱም እርሱ ለቤተ ክርስቲያን ዐምድ (ምሰሶ) ጽንዕ (ጽናት) ነውና፥ በትምህርቱ የሰውን ልቡና ብሩህ ያደርጋልና፥ እንዲህ ባለ አርአያና ምሳሌ አየኸው፤» ብሎታል። ከዚህ በኋላ ቅዱስ ኤፍሬም፥ መምህሩን ከበዓቱ አድርሶ ስለ ሦስት ነገር ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ይሄዳል። ፩ኛ፦ «እንዲህ ካለ ሰው ጋር ቢ ጨዋወቱ መንፈሳዊ ነገር ይገኛል፥» ብሎ ነው፤ ፪ኛ፦ «በጆሮ የሰሙትን በዐይን ቢያዩት ይረዳል፥» ብሎ ነው፤ ፫ኛ፦ «ራዕዩ ከመንፈስ ቅዱስ ነውን?» ብሎ ነው። ቢሄድ፦ በወርቅ ወንበር ተቀምጦ፥ በወርቅ አትሮንስ የወርቅ ወንጌል አዘርግቶ፥ ካባ ላናቃ ለብሶ፥ ኩፋር ጠምጥሞ፥ መያዣው የወርቅ የሆነ የሐር መነሳንስ ይዞ ሲያስተምር አግኝቶታል። በዚህን ጊዜ ቅዱስ ባስ ልዮስን እንደ ሥጋዊ ሰው ቆጥሮት በልቡ ታዘበው። «ምሥጢር የሚገለጠው፥ ጥበብ የምታድረው በትሑታን እንጂ እንዲህ ባለች ሰውነት አይደለም፤» አለ። «ለመንፈስ ቅዱስ ሁለት ግብር አለውን? ወይስ ሰይጣን ተጫውቶብኝ ይሆን?» እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ፥ አራት ነገሮችን አይቶ፥ ስለ ቅዱስ ባስልዮስ መንፈሳዊነት ተረድቷል። ፩ኛ፦ ከአፉ ነጸብራቀ እሳት እየወጣ ሕዝቡን ሲዋሐዳቸው፤ ይህም ትምህርቱ ነው። ፪ኛ፦ ርግብ መጥታ ስታርፍበት፤ ፫ኛ፦ ተሐዋስያን ከልብሱ ላይ እያረፉ እ ንደ ቆሎ ሲረግፉ፤ ይኸውም ለከዊነ እሳት በመድረሱ ነው፤ ፬ኛ፦ ስሙን ሳያውቅ፥ ሀገሩን ሳይጠይቅ፥ «ኤፍሬም ሶርያዊ፥ ኤ ፍሬም ለብሐዊ፤ ብላችሁ ጥሩልኝ፥ ከማዕዘነ ቤተክርስቲያን ባንዱ ቆሞ ይጸልይላችኋል፤» ብሎ አስጠርቶታል።

    በአስተርጓሚ ሲጨዋወቱ፥ ጨዋታው ባይካተትለት፥ «አባቴ ጸልይና ያንተ ቋንቋ ለኔ ይገለጥልኝ፤» አለው። ጸልዮም ጽርዕ የሆነው የቅዱስ ባስልዮስ ቋንቋ ለቅዱስ ኤፍሬም፥ ሱርስት የሆነው የቅዱስ ኤፍሬም ቋንቋ ደግሞ ለቅዱስ ባስልዮስ ተገ ልጦ፥ ሲጨዋወቱ አድረዋል። ሲነጋ አሰናብተኝ ቢለው፦ «መች ልትሄድ አምጥቶሃል፥ ልትኖር ነው እንጂ፤» ብሎ፥ ሕዝባዊ ነው ቢሉ ዲቁና፥ ዲያቆን ነው ቢሉ ቅስና ሹሞ ከሀገረ ስብከቱ ሀገር ከፍሎ፥ «አስተምር፤» ብሎ ሰጥቶታል። ቅዱስ ባስልዮስ በእንደዚያ ዓይነት አርአያ ሆኖ ያስተምር የነበረው ስለ ክብረ ወንጌል ነው። በውስጥ የለበሰው ግን ማቅ፥ የታጠቀውም ሰንሰለት ነበር። ከብረ ሥጋን አይሻውም።

    ከዚህ በኋላ ኃጢአቷን እየጻፈች የምትኖር ከአዋልደ ነገሥት ወገን የምትሆን ሴት ነበረች። ይኽንን የምታደርገውም ለመናገር ብትፈራ አንድም ቢበዛባት ነው። አንድ ቀን መጥታ፥ መዝገበ ኃጢአቷን እንደተጠቀለለ ይዛ፥ «አባቴ በዚህ ያለው ኃጢአትሽ ይፋቅልሽ በለኝ፤» አለችው። «ይፋቅልሽ፤» አላት። ገልጣ ብታየው፥ ሁሉ ተፍቆ አንዲቷ ብቻ ቀርታለች። እርሷንም ዘዕፅብት ለነጊር፥ ለገቢርም ይላታል። «ይህችሳ?» አለችው። «ይህስ ለቅዱስ ኤፍሬም ቢቻለው እንጂ ለእኔ አይቻ ለኝም፤» አላት። እንዲህም ማለቱ ሳይቻለው ቀርቶ አይደለም። ፩ኛ፦ ቅዱሳን የራሳቸው ክብር ከሚገለጥ የወንድማቸው ክብር ቢገለጥ ስለሚወዱ ነው፤ ፪ኛ፥ ስትመጣ ስትሄድ፥ ድካም ያለባት ስለሆነ፥ ቀኖና እንዲሆናት ነው። ሄዳም «በዚህ ወረቀት ላይ የተመዘገበነው ኃጢአትሽ ይፋቅልሽ፥ በለኝ፤» ብትለው፥ እርሱም እየተቻለው፥ የእርሱ ክብር ከሚገለጥ የወንድሙ ክብር እንዲገለጥለት ሲል፥ መመላለሷም ቀኖና እንዲሆንላት ብሎ፥ «ይህስ ለሊቀጳጳሱ ለቅዱስ ባስልዮስ ቢቻለው እንጂ ለእኔ አይቻለኝም፤ ስትሄጂም እንደቀድሞ በሕይወተ ሥጋ አታገኚውም፥ ሙቶ ወደ መቃብር ሲወስዱት ታገኚዋለሽ፥ ሳትጠ ራጠሪ ከአስከሬኑ ላይ ጣዪው፥ ይፋቅልሻል፤» አላት። ብትሄድ ሙቶ ሊቀብሩት ሲሄዱ አገኘችውና ሳትጠራጠር ከአስስከሬኑ ላይ ብትጥለው ተፍቆላታል። ይህም የካህናትን ማዕረግ ደግነት ያሳያል። በሕይወተ ሥጋም ሳሉ፥ ከሞቱም በኋላ ኃጢአትን ያስተሰርያሉ። መንፈሳዊ ጸጋ ሞተ ሥጋ የሚገድበው፥ መቃብር ውጦ የሚያስቀረው አይደለም። ነቢዩ አልሳዕ ከሞተ በኋላ በአጽሙ ሙት አስነሥቷል። ፪ኛ ነገ ፲፫፥፳።

    ስምዖን ዘዓምድ የሚባል መምህር ነበር። እርሱም የያዕቆብ ዘንድቢን ተማሪ ነው። ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር በአንድ ወንበር ተምረዋል። ቅዱስ ኤፍሬምን ሊጠይቀው ቢመጣ፦ «ሰላም ለኪ ኦ እግዝእትየ ቅድስት ድንግል ማርያም፤» እያለ ሲያስተምር ቢያገኘው፦ «ኦ እግዝእትየን ከየት አመጣኸው? መምህራችን እንዲህ አላስተማረንም፤» አለው። ቅዱስ ኤፍሬም ግን፦ «አስተምሮናል፥ እንጂ፤» ብሎ ተከራከረው። ከዚህም የተነሣ፦ «መምህራችን ይመስክር፤» ብለው ወደ መቃብሩ ቢሄዱ፥ ዐሥሩ ጣቶቹ እንደፋና እያበሩ ተነሥቶ፥ «በሕይወትየ እብለኪ፥ ሰላም ለኪ ኦ ቅድስት ድንግል፥ ከመ ስምዖን ዘዓ ምድ፥ ወድኅረ ሞትየሰ ኲሎሙ አዕፅምትየ ይብሉኪ ወይዌድሱኪ፥ ሰላም ለኪ ኦ እግዝእተየ ቅድስት ድንግል ከመ ኤፍሬም ሶርያዊ፤ እመቤቴ ሆይ በአጸደ ሥጋ እያለሁ፥ እንደ ስምዖን ዘዓምድ፥ ቅድስት ድንግል ሆይ፥ ሰላም ለአንቺ ይሁን፥ አልኩሽ፤ ከሞቴ በኋላ ደግሞ በአጸደ ነፍስ ኾኜ፥ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም፥ አጥንቶቼ ሁሉ፥ እመቤቴ ቅድስት ድንግል ሆይ፥ ሰላም ላንቺ ይሁን፥ ይሉሻል፤» ብሎ መስክሮለታል። ይህም የቅዱስ ኤፍሬም ጸጋውና ክብሩ ነው። ምክንያቱም መምህሩ ከሞተ በኋላ በአጸደ ነፍስ የሚናገረውን አውቆ አመስግኗልና ነው።

    ቅዱስ ኤፍሬም በጉልበቱ አየሠራ ከሚያገኘው፥ የዓመት ልብሱን እና የዕለት ምግቡን ብቻ እያስቀረ በእመቤታችን ስም ይመጸውት ነበር። ይኸውም ሌሎችን ንቆ አጥቅቶ ሳይሆን የእመቤታችን ፍቅር ባያደርሰው ነው። እመቤታችንንም ከመ ውደዱ የተነሣ፦ «የእመቤቴ ምሥጋናዋ እንደ ሰማይ ኮከብ፥ እንደ ባሕር አሸዋ በዝቶልኝ፥ እንደ ልብስ ለብሼው፥ እንደ ምግብ ተመግቤ ጠግቤው» እያለ ሲመኝ ይኖር ነበር። በቅን ልቡና፥ በትሑት ሰብእና፥ የፈለጉትን መግለጥ የእግዚአብሔር ልማዱ ስለሆነ፥ «አኀዝ እግዚኦ መዋግደ ጸጋከ፤» እስኪል ድረስ እልፍ ከአራት ሺህ ድርሰት ደርሷል። የሚጸልየውም ከሉቃስ ወንጌል፦ ወበሳድስ ወርኅ ከሚለው እስከ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ድረስ ያለውን አውጥቶ፥ በእመቤታችን ዕድሜ ልክ ስድሣ አራት ጊዜ እየደጋገመ ነበር። ሉቃ ፩፥፳፮።

    ከእለታት በአንድ ቀን፥ ዕለቱ ሰኑይ (ሰኞ)፥ ጊዜው ነግህ ነው። የነግህ ተግባሩን አድርሶ፥ ከመካነ ግብሩ ተቀምጦ ሳለ፥ እመቤታችን ትመጣለች። የብርሃን ምንጣፍ ይነጠፋል፥ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል። ከዚያም ላይ ሁና፦ «ሰላም ለከ ኦ ፍቁርየ ኤፍሬም፤ ወዳጄ ኤፍሬም ሆይ፥ ሰላም ለአንተ ይሁን፤» ትለዋለች። እርሱም ታጥቆ እጅ ነሥቶ ይቆማል፤ «ወድሰኒ (አመስግነኝ)»፥ ትለዋለች፤ እርሱም፦ «እፎ እክል ወድሶተኪ ዘኢይክሉ ሰማያውያን ወምድራውያን፤ ምድራውያን ጻድቃን ሰማዕታት፥ ሰማያውያን መላእክት አንቺን ማመስገን የማይቻላቸው (አመስግነው ምሥጋናሽን መፈጸም መወሰን የማይሆ ንላቸው) ለእኔ እንደምን ይቻለኛል?» አላት። «በከመ አለበወከ መንፈስ ቅዱስ፥ መንፈስ ቅዱስ እንዳሳሰበህ ተናገር፤» አለችው። በተረቱበት መርታት ልማድ ነውና በተረታችበት ረትታዋለች። ምክንያቱም፦ የእግዚአብሔር ባለሟል ቅዱስ ገብር ኤል፥ አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና እንደምትወልድ በነገራት ጊዜ፦ እፎኑ ይከውነኒ፥ እንዴት ይሆንልኛል?» ብላ ነበር፤ መልአኩም፦ «መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላእሌኪ፥ ቅዱሱ የእግዚአብሔር መንፈስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤» ብሏት ነበርና ነው። ከዚህ በኋላ፥ «ባርክኒ፥ ባርኪኝ፤» ይላታል፤ እርሷም፦ «በረከተ ወልደየ፥ ወአቡሁ፥ ወመንፈስ ቅዱስ ይኅድር በላዕሌከ፥ የልጄ የወልድ፥ የባሕርይ አባቱ የአብ፥ የባሕርይ ሕይወቱ የመንፈስ ቅዱስም በረከት በአንተ ላይ ይደር፤» ብላ ትባርከዋለች።

    ተባርኮም ምስጋናዋን ይጀምራል። ሲያመሰግናትም ደቀመዝሙር ቅኔ ቈጥሮ እንዲቀኝ፥ ድርሰት አስቦ እንዲጽፍ አይደለም። ብልህ ደቀመዝሙር ያጠናውን ቀለም (ቃለ እግዚአብሔር) ሰተት አድርጎ እንዲያደርስ እንደዚያ ነው። ስታስደ ርሰውም ከሰባት ከፍላ አስደርሳዋለች። ይኸውም በሰባቱ ዕለታት መመስገን ፈቃዷ በመሆኑ ነው፥ አንድም ሰባቱ ዕለታት ምሳሌዎቿ በመሆናቸው ነው። የቅዱስ ኤፍሬምን ሕይወት በመጠኑ የተረክነው፥ ውዳሴ ማርያምን የደረሱ ሰዎችን የቅድስና ሕይወትና፥ ውዳሴ ማርያምን የሚያጣጥሉ ሰዎችን ሕይወት፥ (ልዩነታቸው የሰማይና የምድርን፥ የብርሃንና የጨለማን ያህል ቢሆንም) እንድታነጻጽሩት ነው።

    ፪፥፩፦ አምላክ ለምን ሰው ሆነ?

    ውዳሴ ማርያምን በሃይማኖት የሚደግም ሰው የሚጸልየው የኢየሱስን ስም ነው። በቤተክርስቲያናችን የኢየሱስ ስም ስብከት ብቻ ሳይሆን ጸሎትም ምስጋናም ነው። የሰኞ ውዳሴ ማርያም፦ «ጌታ ልቡ ያዘነበትንና የተከዘበትን አዳምን ነፃ ያወጣውና ወደ ቀድሞው ቦታው (ከጉስቁልና ኃጢአት፥ ከሲኦል ውድቀት፥ ከዲያቢሎስ ባርነት ነፃ፥ አድርጎት ወደ ጥንተ ርስቱ ወደ ገነት) ይመልሰው ዘንድ ወደደ፤» ይላል። «ወደደ፤» ብሎም አልተወም፤» «ዘር ምክንያት ሳይሆነው (በመንፈስ ቅዱስ ግብር) ከድንግል በሥጋ ተወልዶ አዳነን፤» ብሏል። አዳምን አንሥቶ ሔዋንን አልረሳትም፥ «ከይሲ (ዲያብሎስ) ያሳታ ትን ሔዋንን፥ እግዚአብሔር ምጥሽንና ጣርሽን አበዛዋለሁ ብሎ ከፈረደባት በኋላ፥ ሰውን ወደደና ነፃ አደረጋት፤» ብሏል። ይህም፦ አምላክ ሰው የሆነበት ዓላማ፥ የሰውን ልጅ ለማዳን መሆኑን ይሰብካል። ጌታችን አምላካችን መድኃ ኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል፥ «በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና። ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ ወደዚህ ዓለም አልላከውምና።» ብሏል። ዮሐ ፫፥፲፮። ይኽንንም ይዞ፦ «ሰው ሆይ፥ ፈጽመህ ደስ ይበልህ፥ እግዚአብሔር ዓለሙን ወዶታልና፤ አንድ ልጁንም የሚያምንበት ሁሉ እስከ ዘለዓለም ፈጽሞ ይድን ዘንድ አሳልፎ ሰጥቶአልና፥ ልዑል ክንዱን ሰደ ደልን፤» ብሏል። (የሰኞ  ቁ.፮)። ክንዱ ያለው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።

    በቁጥር ዘጠኝ ላይ ደግሞ፦ «የሰው ሁሉ ሰውነት ደስ ይላታል፥ በሰማይ ለእግዚአብሔር  ምስጋና ይሁን፥ በምድ ርም ሰላም፥ ለሰውም እርሱ በሚፈቅደው እያሉ ከመላእክት ጋር አሰምተው ንጉሥ ክርስቶስን ያመሰግኑታል፥ የቀድሞውን እርግማን (በኃጢአት ምክንያት የመጣውን የሥጋና የነፍስ መርገም) አጥፍቷልና። የጠላትን (የዲያብሎስን) ምክሩን (ሥጋን በመቃብር ነፍስን ደግሞ በሲኦል ተቆራኝቼ እኖራለሁ፥ ያለውን) አፈረሰበት። ለአዳምና ለሔዋን የዕዳ ደብዳቤያቸውን ቀደደ ላቸው። (አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ፥ ሔዋን አመቱ ለዲያብሎስ ተብሎ፥ በሁለት ዕብነ ሩካብ ተጽፎ፥ ወደ ሲኦልና ወደ ዮርዳ ኖስ ተጥሎ የነበረውን፥ ረግጦና አቅልጦ አጠፋላቸው)። በዳዊት ሀገር የተወለደ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ሄዋንን ነፃ አደረጋቸው።» ብሎአል።

    ትንቢተ ነቢያትን በተመለከተም፦ «ርእየ ኢሳይያስ ነቢይ በመንፈሰ ትንቢት፥ ምሥጢሮ ለአማኑኤል፥ ወበእንተዝ ጸርሐ እንዘ ይብል፦ ሕፃን ተወልደ ለነ፥ ወልድ ትውህበ ለነ፤ ነቢዩ አሳይያስ በመንፈስ ቅዱስ የአማኑኤልን ምሥጢር አየ፤ ስለዚህም፦ ሕፃን ተወለደልን፥ ወልድም ተሰጠልን፥ ብሎ አሰምቶ ተናገረ፤» የሚል አለ። (ቊ. ፭) ኢሳ ፯፥፲፬፣ አሳ ፱፥፮። በሐሙሱ ምስጋና ላይም፦ «እግዚአብሔር የባሕርይህን ፍሬ በዙፋንህ ላይ አኖራለሁ ብሎ ለዳዊት ማለለት፥ አይጸጸትም፤ ጻድቅ እርሱ ዳዊት፥ ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ እንዲወለድ ባመነ ጊዜ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ማደሪያ ፈልጎ ያገኝ ዘንድ ወደደ፤ ይህንንም በታላቅ ትጋት ፈጸመ፤ ከዚህም በኋላ እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፥ (በኤፍራታ ምድር በቤተልሔም ከድንግል ማርያም ተወልዶ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው)፥ ብሎ በመንፈስ ቅዱስ አሰምቶ ተናገረ። ይህቺውም አማኑኤል እኛን ለማ ዳን በሥጋ ይወለድባት ዘንድ የመረጣት የያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ናት። ዳግመኛም ከነቢያት አንዱ ሚክያስ፦ «አንቺ የኤፍ ራታ ክፍል የሆንሽ ቤተልሔም ከይሁዳ ነገሥታትና መሳፍንት አገር አታንሺም፥ ወገኖቼ እሥራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ካንቺ ይወጣልና፤» ብሏል። (ቊ. ፮) መዝ ፩፻፴፩፥፩-፲፰፣ ሚክ ፭፥፪።

    ፪፥፪፦ አምላክ ሰው በሆነ ጊዜ አልተለወጠም፦

    ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ፦ በማክሰኞ ምስጋና ላይ፥ እመቤታችን፦ ከነገሥታት ዳዊትን፥ ከመሳፍንት ኢያሱን፥ ከደናግል ኤልያስን አስከትላ መጥታ ስለነበር፥ «የመመኪያችን አክሊል (ዘውድ)፥ የደኅንነታችን መጀመሪያ፥ የንጽሕናችን መሠ ረት፥ እኛን ስለማዳን ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል በወለደችልን በድንግል ማርያም ተገኘልን፤» ብሏል። ይህም፦ ዳዊትን፥ «ምን ንጉሠ ነገሥት ብትባል፥ የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልቻልህም፤» ሲለው ነው። ኢያሱንም፦ «ምን መድኃኒት ብትባል፥ የደኅንነታችን መጀመሪያ መሆን አልቻልህም፤» ሲለው ነው። ኤልያስን ደግሞ፥ «ምን ንጹሕ፥ ድንግል ብትባል የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልቻልህም ሲለው ነው። ከዚህም አያይዞ፦ «እምድኅረ ኮነ ሰብአ፥ ጥዩቀ አምላክ ፍጹም ውእቱ፤ ሰው ከሆነም በኋላ ፍጹም አምላክ ነው፤» ብሏል። (ቊ. ፩) በሐሙሱ ምስጋና ላይም፦ «እምድኅረ ወለደቶ ድንግልናሃ ተረክበ፥ ወመለኮቱ ኢተወለጠ፥ ኮነ ወልደ ዕጓላ እመሕያው፥ አምላክ ዘበአማን መጽአ ወአድኀነነ፤ ከወለደችውም በኋላ ድንግልናዋ አልተለወጠምና፥ እርሱም ሰው ሲሆን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና፥ ሰው ሆኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፤» ይላል። (ቊ. ፩)። በተጨማሪም፦ «ሰውን የሚወድ እግዚአብሔር አንድ ብቻ የሆነ፥ አምላክነቱ ሳይለወጥ፥ ከዓለም በፊት የነበረ የአብ ቃል፥ ከአብ ዘንድ መጥቶ ልዩ ከሆነች እናቱ ሰው ሆነ፤ ከወለደችውም በኋላ ድንግልናዋ አልተለወጠም፤» የሚል አለ። (ቁ. ፫)፤ በሰንበተ ክርስቲያን ምስጋናም ላይ፥ «. . . ያለመለየትና ያለመለወጥ ሰው የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይመስልልናል፥ ይኸውም መለወጥ የሌለበት ንጹሕ መለኮት ነው፥ ከአብ ጋር የተካከለ ነው፤. . . በእግዚአብሔር ሥዕል የተሣሉ ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደስ አንቺ ነሽ፤ ንጽሕት ሆይ፥ ያለመለወጥ ካንቺ ሰው የሆነው ቃል ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልን እና አበሳችንን የሚደመስስልን ሆነ፤» ይላል። (ቊ. ፫ እና ፬)

                          እንደ እግዚአብሔር ፍቃድ፦ ይቀጥላል .....

                    የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት ይጠብቀን፤ አሜን!።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ፦ የቤተክርስቲያን ትምህርት፤ (ክፍል ፪) Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top