• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    መጠራታችሁን ተመልከቱ


    እግዚአብሔር ፍጥረታትን ሲፈጥር ያለ ዓላማ የፈጠረው ፍጥረት እንደ ሌለ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። የፍጥረት ዓይነቱ ልዩ ልዩ እንደሆነው ሁሉ የተፈጠረለት ዓላማውም ልዩ ልዩ ነው። በተለይ የሰው ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ ይለያል። ፍጥረታት በሙሉ የራሳቸውን መልክ ይዘው ሲፈጠሩ ሰው ግን እግዚአብሔርን መስሎ ነው የተፈጠረው። ይህም በመሆኑ ዘላለማዊነትና ገዥነት ተሰጥተውት ነበር። በዚህ ክብርና ልዕልና ጸንቶ የቆየው ግን ለሰባት ዓመታት ብቻ ነበር። በጥንተ ጠላቱ ዲያቢሎስ ተታሎ ከአስተዳዳሪነት ወደ ባርነት ከዘላለማዊነት ወደ ኃላፊነት ከገነት ወደ ምድረ ፋይድ ከተሸጋገረ በኋላ ይገዛቸው ያስተዳድራቸው ዘንድ ሙሉ ስልጣን ሰጥቶት የነበረው እንስሳት እንኳን ሸሹት። ለፈጣሪው ያልታመነ ለኛ የሚራራ ልብ እንዴት ይኖረዋል ያሉ ይመስላል። 

    አስቀድሞ በገነት ወዴት አለህ ብሎ የጠራው አምላኩ በሲኦል በዲያቢሎስ አገዛዝ ስር ሳለም የሰላምና የፍቅር ድምጹን አሰምቶታል። እግዚአብሔር ምንጊዜም ቢሆን ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር አይለወጥም። እኛ ሰዎች ግን አብዝቶ የወደደንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ሳይሆን፥አብዝቶ ውድቀታችንን የሚመኝልንን የዲያቢሎስን ፈቃድ ለመፈጸም እንተጋለን። ለክብር ተጠርተን ውርደትን እንመርጣለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ,,ወንድሞች ሆይ፥ መጠራታችሁን ተመልከቱ፤ እንደ ሰው ጥበብ ጥበበኞች የሆኑ ብዙዎች፥ ኀያላን የሆኑ ብዙዎች፥ ባላባቶች የሆኑ ብዙዎች አልተጠሩም።ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ነገር ግን። የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይሆን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የሆናችሁ ከእርሱ ነው።,, 1ኛ ቆሮ 1፥26  ብሎ እንደተናገረው በተለያየ መንገድ ለአገልግሎት የተጠራን ሁላችን መጠራታችንን ልናስተውለው ይገባል። ማንም ቢሆን ያለው እውቀትና ጥበብ ተመዝኖ ለአገልግሎት የሚመረጥ የለም። እግዚአብሔር በወደደና በፈቀደ ጊዜ ለፈለገው አላማ ይጠራዋል። ኤር 1፥5  የሐ ሥ 9፥3

    ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ከማህጸን ጀምሮ ለአገልግሎት የሚጠራ አለ። በተለያየ እድሜም ሳሉ የሚጠሩ አሉ። አገልግሎት ልዩ ልዩ እንደሆነው ሁሉ ጥሪያችንም ልዩ ልዩ ነው። ክብር የሚያሰጠው ለተጠሩለት ዓላማ ታማኝ ሆኖ መገኘት ብቻ ነው።

    ብዙ ጊዜ ሰዎች የተጠሩለትን ዓላማ በመዘንጋት ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ሰማያዊ በረከት ያጣሉ። በምድር ላይ ሆኖ የእግዚአብሔርን ጥሪ ተቀብሎ እንደ እግዚአብሔር ሃሳብ መመላለስ ከባድ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሁሉን የምናሸንፍበት ከእግዚአብሔር የተሰጠን ልዩ ልዩ ጸጋ አለ። ያንን ፈልጎ ማግኘት ነው።

    አሁን ያለንበት ወቅት ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች በጸጋ የተሰጠ፣ ዓለምን የምናሸንፍበትን ኃይል የምንጎናጸፍበት ትልቅ የጾምና የጸሎት ወቅት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ ወደዚህ ዓለም መጥቶ የሰውን ልጆች ከራሱ ጋር የማስታረቅን አገልግሎት በፈጸመበት ወቅት ዲያቢሎስን ያሳፈረበት ጾም ነው። ማቴ 4፥1

    የጾም ዓላማና ትርጉም ሰፊ ቢሆንም ዋናው ከስጋ ፈቃዳት መከልከል መሆኑ ይታወቃል። ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ  ,, በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ,, ገላ 5፥25 እንዳለው ጾም በመንፈሳዊ ህይወት ጠንክሮ ለመኖር ዋናው መሳሪያ ነው። መከልከል ስንል ከህል ከውሃ ብቻ ሳይሆን ጌታ በውንጌል እንደተናገረው ከእህል ከውሃ መከልከላችን ስጋዊ ፈቃዳችንን ለማድከም እንጅ ብቻውን መንፈሳዊ ኃይል የማግኛ ዘዴ ሊሆን አይችልም። ማቴ 15፥11 እንደሚታወቀው ሰው በተለያየ መንገድ ከምግብ ሊከለከል ይችላል ነገር ግን በህሊናው የስጋ ፈቃዳት የሚመላለሱ ከሆነ ተራበ እንጅ ጾመ ሊባል አይችልም። ነገር ግን ከእግዚአብሔር የመጣልንን ጥሪ አስበን፣ በመንፈሳዊ ኃይል ዲያቢሎስን ድል ማድረግ እንደምንችል አምነን፣ ከእህል ከውሃ ተከልክለን፣ ከቂም ከበቀል እርቀን የአለምን ከንቱነት ተረድተን ከሆነ የምንጾመው ዓለምን እናሸንፍበታለን።

    ሁልጊዜም ቢሆን ሳንጠቁመው የማናልፈው ነገር፥ ያለንበት ዘመን ቤተክርስቲያናችን በተለያዩ ፈተናዎች ተከባ ልጆቿ ሰላም እርቋቸው ለመንፈሳዊ ህይወት በማይመች አካሄድ እንደተጠመዱ አይዘነጋም። ዋናው ምክንያት አገልጋዮችም ሆኑ ምዕመናን የእግዚአብሔርን ጥሪ ካለመስማት በሚያነሱት ክፉ ሃሳብ ነው። የካህናትም ሆነ የምዕመናን ጥያቄ የሰላም ጥያቄ ነው ሊሆን የሚገባው። ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ነች። ክርስቶስ ደግሞ ሰላም ነው። በሰላም የሚኖሩ ደግሞ የሱ ልጆች ይባላሉ። ይህን በረከት ለማሳጣት የሚጥረው ዲያቢሎስ መሳሪያ እንዳያደርገን ልንጠነቀቅ ይገባል። መቸም በጥቂቶች ዘንድ ሰላም አለ ብንልም ነገር ግን ሁላችን በክርስቶስ አንድ አካል ነንና የሌላው ሰላም ማጣት ሁሉንም እንደሚያውክ የታወቀ ነው። ለዚህ ሁሉ ችግር የተዳረግነው ሁላችንም መጠራታችንን መመልከት ባለመቻላችን ነው። እግዚአብሔርን ለማገልገል የተጠሩ ሰውን ወደ ማገልገል ዘወር ሲሉ ነው ሰላም የጠፋው። አባቶቻችን ሐዋርያት ,,ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል,, የሐ ሥ 5፥29 ብለው እንዳስተማሩን እንደሰው ሃሳብ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር አሳብ ብንመላለስ የምንፈልገውን እናገኛለን።

    አገልግሎት ልዩ ልዩ ነው እንደተባለው ሁሉም በተሰጠው ኃላፊነት እግዚአብሔርን በታማኝነት ቢያገለግል ከራሱ አልፎ ሌላውንም ይጠቅም ነበር። የመንፈሳዊ አገልግሎት ስኬት ምንጊዜም ቢሆን የሰውን ደካማ ጎን መመልከት ሳይሆን የራስን ድክመት እየመረመሩ ከስህተት መማር ነው። ብዙ ጊዜ እኛን የሚያታልለን የራሳችንን ጉድፍ ሳናጠራ በሌላው ላይ  የምንፈርድ ስለሆንን ስኬት አልባ እንሆናለን። ስለዚህ በዚህ በሱባኤ ወቅት እራሳችንን ለእግዚአብሔር በመስጠት የተጠራንለት ዓላማ ምን እንደሆነ መርምረን ተረድተን፣  የእግዚአብሔርን ሃሳብ አውቀን የሚጠበቅብንን ለማድረግ የምንተጋበት ነው መሆን ያለበት። 

    ቤተክርስቲያን የክርስቶስ እንደሆነችው ሁሉ እኛም ሁላችን የክርስቶስ ነን። የሱ እንደመሆናችን ከሁላችንም የሚፈልገው ነገር አለ። የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ ተደምሮ ነው ቤተክርስቲያን ሉአላዊት ሆና ልትኖር የምትችለው። የጳጳሱ፣የቄሱ፣ የመነኩሴው፣ የዲያቆኑ የሰባኪው፣የዘማሪው አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ምዕመናን ተሳትፎ ከታከለበት ነው የምንፈልገውን ሰላምና በረከት የምናገኘው። ስለዚህ ወቅቱ የበረከት ፍሬ እንድናፈራበት ለእኛ የተሰጠ ነውና እንጠቀምበት።        

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: መጠራታችሁን ተመልከቱ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top