በዲያቆን ኤርምያስ ነቢዩ (አትሮንስ:- http://www.ermiasnebiyu.org/)
በክርስትና ሕይወት ላይ የሚመጡ ፈተናዎች ፈተና የሰው ልጅ የ እምነት መለኪያ; የ እምነት መገለጫ ወይም መታወቂያ ነው:: የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን የተጠራ ማንም ሰው በጉዞው ወቅት የሚገጥሙት ፈተናዎች አሉ:: እያንዳንዱ ክርስቲያንም በክርስትና ሕይወት ከብዙ የፈተና ሕይወት ጋር ግብግብ ይገጥማል:: ምንጊዜም ክርስትና ባለበት ፈተና አለ:: ፈተና የሌለበት ክርስትና ሕይወት እድገት አያሳይም:: በመሆኑም ባገኘን የፈተና ወጀብ ውስጥ ለማለፍ በዓለማ ጽናት ለመራመድ የምንችለው በገጠመን መከራ ተስፋ ሳንቆርጥ አብዝተን ወደ ጌታ እግዚአብሔር ስንጸልይ ነው::
ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን ሁሉ እኛም የቀረበብን ፈተና እምነታችን የሚለካበት መሆኑን አውቀን በትዕግስት ስንቀበለውና ነጥረን ስንወጣ ክብር እናገኝበታለን:: " በዚህም እጅግ ደስ ይላችኋል፥ ነገር ግን በእሳት ምንም ቢፈተን ከሚጠፋው ወርቅ ይልቅ አብልጦ የሚከብር የተፈተነ እምነታችሁ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲገለጥ፥ ለምስጋናና ለክብር ለውዳሴም ይገኝ ዘንድ አሁን ለጥቂት ጊዜ ቢያስፈልግ በልዩ ልዩ ፈተና አዝናችኋል።እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ
አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል:: እንዳለ 1ኛ ጴጥ 1:6-9 እግዚአብሔር በፈተና ሁሉ መንገድ አለው ቀርቦ ይረዳናል:: ከመከራ ሁሉ ያወጣል:: ሕይወታችን ያከተመ በመሰለን ጊዜ: አስጨናቂያችን ጠላት ከፊት ከኋላ: ከግራ ከቀኝ ከቦን መውጫ ስናጣ: የተስፋ ጭላጭል ባናይ: ብርሃን በጨለማ ቢተካ: የሚያዝ የሚጨበጥ ቢጠፋ በዚህ ሁሉ ጊዜ የተቆረጠውን የሚቀጥል ታላቅ አምላክ እንዳለ አምነን ወደ እርሱ ብንጮህ የከበበንን የጠላት ወጥመድ ሰብሮ: የዋጠንን የጨለማ ፍርሃት በብርሃን ተክቶ: አሮጌው አዲስ ይሆንልንና ሁሉን አልፈን የሀዘን እንጉርጉሮአችንን ወደ አዲስ ደስታ ዝማሬ ይቀይርልናል::
በግፍ መከራ የሚቀበል ሰው እግዚአብሔርን እያሰበ ሃዘንን ቢታገስ ምስጋና ይገባዋል:: እንዳለ 1ኛ ጴጥ 2:19 ስለዚህ በችግርና በፈተና ውስጥ ስናልፍ መጨረሻው ለበጎ ነገር እንደሆነና በእኛ ሕይወት ውስጥ ሊፈጽመው ያሰበው ነገር እንዳለ ከኢዮብ እንማራለን:: እግዚአብሔር አምላካችን የኢዮብን ትዕግስት ያድለን:: ስለዚህ ዋና ዋና የፈተና መንገዶችን ሦስት ናቸው እነዚህም 1) ከሥጋ ምኞት 2) ከዓለም የሚመጣ ፈተና 3) ከሰይጣን የሚመጣ ፈተና ለእነዚህም ለእያንዳንዳቸው ለፈተናው መነሻ የሚሆኑትን ዋና ዋና ነጥቦች ለመዘርዘር እሞክራለሁ: 1) ከሥጋ ምኞት የሥጋ ምኞት:- የዚህ ፈተና ዋናው መነሻው ወይም የሚመጣው ከራስ ውስጣዊ ምኞት(ፍላጎ) ነው::
የሰው ልጅ በራሱ የሥጋ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል:: ምንም እንኳ የሰው ተፈጥሮ ሃጢአት የሚስማማው ደካማ ቢሆንም እንኳ በደካማ ሥጋ ምኞት ባሕርይ የተነሳ ሰው ፈተናን ወደ ራሱ የሚጋብዝበት ጊዜ አለ:: "ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል: እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም :: ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል:: ከዚህ በኋላ ምኞት ጸንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች: ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች:: ያዕ 1:13-15 ሁልጊዜ ክፋትን የሚያመነጭ ልብ የኃጢአት ጎተራ ነው:: ኃጢአትን የሚመኝ ፍጻሜው ሞት ነው::
በአለም የሥጋ ምኞት ተስቦ በቅንአትና ያለ አግባብ የሌላውን ሰው ገንዘብ: ሃብት: ንብረት: ሥልጣን: መመኘት ሲመጣ በሰው ልጆች መካከል ጸብ: ክርክር ቁጣ ምቀኝነት መገዳደል ይነግሳሉ:: ፍቅርን በማጣት ይለያያሉ:: ከትእዛዛት አንዱ "የባልንጀራህን ቤት: ሚስት ሎሌ ገረድ በሬ አህያ ገንዘብን ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ:: ይላል " ዘጸ 20:17 በተጨማሪም የዚህ ዓለም ምኞት ሁሉ በዚህ ዓለም ቀሪና ሃላፊ ነው:: " "ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም: ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል"። 1ኛ ዮሐ 2: 15-17 "ሰባኪው:- ከንቱ: የከንቱ ከንቱ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል:: መክ 1:2 የሥጋ ምኞት ሰውን በቀላሉ በኃጢአት ገመድ ይጠላልፋል::
በጾምና በጸሎት እንዳንተጋ በልባችን ውስጥ ክፋትን በማሳደር መንፈሳዊ ኃይልን እንድናጣ ያደርጋልና የሥጋ ምኞትን ማራቅ ያስፈልጋልን:: "ወዳጆች ሆይ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደመሆናችሁ እለምናችኋለሁ:: 1ኛ ጴጥ 2:11 "በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ::"ሮሜ 6:12
ይቆየን.......
0 comments:
Post a Comment