• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 9 November 2015

    አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ

    መስከረም 6 የዋልድባው የአቡነ ሳሙኤል ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ነው፡፡

    በዚህች ዕለት የአቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ዋሊ ዐፅማቸው ከዋልድባ አብረንታንት ወደ ደብረ ዓባይ የፈለሰበት ነው፡፡ ጻድቁ ገና በ12 ዓመታቸው ማይ ሹም በተባለው ባሕር ገብተው ሲጸልዩ ባሕሩ በብርሃን ተከቦ ይታይ ነበር፡፡ ከባሕሩም ወጥተው ወደ ቤተክርስቲያን ገብተው እያለቀሱና እያዘኑ ሲጸልዩ ካህናቱ ‹‹ይህ ሕፃን የእኛ ኃጢአት እየታየው? ወይስ ምን ኃጢአት ኖሮበት ነው እንዲህ የሚያዝነውና የሚያለቅሰው?›› እያሉ ያደንቁና ይገረሙ ነበር፡፡

    አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ እናቱ አመተ ማርያም ቤተሰቧንና ቤት ንብረቷን ትታ ከመነኮሰች በኋላ እርሱም ካልመነኮስኩ በማለት አባቱ እስጢፋኖስን ቢለምነውም እምቢ ስላለው በራሱ ፈቃድ ከአንድ ሽማግሌ ጋር ወደ አባ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ደብረ በንኰል ገብቶ መነኮሰ፡፡ በዚያም ነፍሱን ‹‹ነፍሴ ሆይ! እነሆ ለክርስቶስ ታጨሽ፣ የቅዱሳንን ቀንበር እንሆ ተሸከምሽ፣ የመላእክትን ንጽሕና ትጠብቂ ዘንድ ዛሬ በእግዚአብሔርና በቅዱሳኑ ሁሉ ፊት ቃልኪዳን ገባሽ፣ ቃልኪዳንሽን ብትጠብቂ መላእክት ይደሰቱብሻል፣ ባትጠብቂ ግን አጋንንት ይዘባበቱብሻል…›› እያለ ብዙ መከራን በራሱ ላይ በማብዛት ሰባት ዓመት በዚያች ገዳም ኖረ፡፡ እህልም አይቀምስም ነበር ይልቁንም የሚሰጡትን እንጀራ ለሕጻናትና ለውሾች እየሰጠ አሠር ይመገብ ነበር፡፡ ዳግመኛም በሌላ ጊዜ ቅጠልን እየቀቀለ እስከ አምስት ቀን ከድኖ ያስቀምጠዋል፣ እስከሚተላም ድረስ ይጠብቀውና ያን ይመገባል፡፡ ኩስይ የምትባል ከሣር ሁሉ የምትመርን ሣር ምግቡ አደረገ፡፡ በኋላም አባቱም ልጁን ሳሙኤልን ተከትሎ ወደ እርሱ መጥቶ በአባ አድኃኒ እጅ መነኮሰ፡፡ ለአባቱም መምህር ሆኖት እያገለገለው ያስተምረው ነበር፡፡ በሌላም ጊዜ 17 ዓመት ከተቀመጠባት ወይና በምትባል ቦታ ሲኖር ከውኃ በቀር ምንም ሳይቀምስ 12 ዓመት ተቀምጧል፡፡ ለ50 ዓመትም ያህል ሣር፣ ቅጠል፣ የዛፍ ሥርና ፍሬን እነዚህንና የመሳሰሉትን እየበላ ኖረ እንጂ እህል የሚባል አልበላም፡፡ ወጥቶም ወደ ዋሻ እየገባ ብዙ ጊዜ 40 ቀንና 40 ሌሊት በጾም በጸሎት እየኖረ እንቅልፍም እንዳያሸንፈው እስከሚነጋ ድረስ ሳይቆም ሳይተኛ እንደቆመ በጽኑ ተጋድሎ ተቀመጠ፡፡ ትልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ በውስጡ እየገባ ሳይቀመጥ ሳይተኛ ሰውነቱ እንደ እንጨት እስኪደርቅ ድረስ በጾም በጸሎት በእጅጉ ይተጋ ነበር፣ በዚህም ወቅት ጌታችን ተገልጦለት ሰውነቱን በሙሉ ምራቁን ስለቀባለትና አውራ ጣቱን ስላጠባው ከዚህ ጊዜ በኋላ ርሀብና ጥሙ ጠፍቶለት ሰውነቱም ታድሶለታል፡፡ ዳግመኛም በአፉም ድንጋይ ጎርሶ፣ እግሩንም ታስሮና ማቅ ለብሶ ወደ ባሕር እየገባ ይጸልይ ነበር፡፡

    አባታችን አባ ሳሙኤል በሕይወተ ሥጋ ሳለ እጅግ ድንቅ ድንቅ የሆኑ ተአምራትን አድርጓል፡፡ እንደሙሴ ባሕርን የከፈለበት ጊዜ አለ፤ በልዑልም ዙፋን ፊት እየቀረበ ከቅዱሳን መላእክት ጋር የሚያመሰግንበት ጊዜ አለ፣ ከሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይም ጋር ሆኖ የሚያጥንበት ጊዜ አለ፤ በሰማያዊት ኢየሩሳሌምም ሆኖ ከእነ ቅዱስ ጴጥሮስና ከሁሉ ቅዱሳን ጻድቃን ሰማዕታት ጋር በአንድ ላይ ማዕድ የሚቀርብበት ጊዜ አለ፤ በእጆቹ የያዛቸው መጻሕፍቶቹ ምንም ሳይርሱ ትልቅ ወንዝን በውስጡ እያቋረጠ የሚሻገርበት ጊዜ አለ፤ እመቤታችንንም ሲያመሰግናት ከምድር ወደ ላይ አንድ ክንድ ያህል ከፍ የሚልበት ጊዜ አለ፤ በቤትም ውስጥ ሆኖ ምስጋናዋን ሲጀምር የቤቱ መሠረት እየተናወጠ ዝናብ እንደያዘ ደመና ቤቱ ከምድር ከፍ ብሎ የሚቆምበት ጊዜ አለ፤ መንፈስ ቅዱስም በብርሃን ክንፍ እየወሰደው ወደተለያዩ ገዳማት ያደርሰውና ሥጋ ወደሙን እንዲቀበል ያደርገው ነበር፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልም የሁልጊዜ ጠባቂው ነውና በሁሉ ነገር ይራዳውና እንደ ጓደኛም ያማክረው ነበር፡፡

    አባ ሳሙኤልን የዱር አራዊትም ሁሉ ይገዙለት ነበር፡፡ ታላቅ የሆነ ዘንዶ፣ ነብር፣ ጅብ፣ ቶራህ፣ ዝሆን፣ አንበሳና ሌሎችም የዱር አራዊት ሁሉ እየመጡ እግሩን እየላሱት ወደ ቦታቸው ይመለሱ ነበር፡፡ አንበሶቹንም እሾህም በወጋቸውና እግራቸው መግል በያዘ ጊዜ በመርፌ እያነቆረ ያድናቸው ነበር፡፡ ስንጥርም ሲወጋቸው ወደ እርሱ እየመጡ ያሳዩትና ያወጣላቸው ነበር፡፡ አንበሳም አጋዘንን ገድሎ ሲበላ ሲያየው ‹‹አንዴ ዞር በልልኝ ቆዳዋን ለልብሴ እፈልገዋለሁ›› ባለው ጊዜ ይለቅለት ነበር፡፡ እንዲሁም አንበሳው ለአባታችን ምግብም ትሆነው ዘንድ ጅግራን እየያዘ በሕይወት ሳለች ያመጣለት ነበር፡፡ አባታችንም ከገዳም ወጥቶ መሄድ በፈለገ ጊዜ አንበሶችን እንደ ፈረስና በቅሎ ይጋልባቸዋል፣ መጻሕፍቶቹንም ይጭንባቸዋል፤ መንታ የወለደች አንበሳም ብትኖር ልጆቿን እየታቀፈ በየተራ ያጠባቸው ነበር፡፡

    ወደ ደብረ ዋሊም በሄደ ጊዜ ጌታችን ተገልጦለት በዕለቱ የእመቤታችን በዓል ስለነበር እንዲቀድስ ነግሮት ከሰማይ ኅብስትና ጽዋ መጥቶለት ቅዱሳን ሐዋርያት በቀኝ በግራ እየተራዱት ሲቀድስ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ ኅብስቱንና ጽዋውን ጋርዶታል፡፡ ጌታችንም ቦታዋንና በዚያ ያሉትን መነኮሳት ሁሉ ልጆቹ ይሆኑ ዘንድ አስራት አድርጎ ሰጠው፡፡ ዋልድባ የተመሠረተው በቀደምት ጥንታዊያን አበው ቢሆንም አባ ሳሙኤል ሲገቡበት ምድረ በዳ ሆኖ ጠፍቶ ቋያ በቅሎበት የወባ ትንኞች መፈልፈያ ሆኖ ነበር፡፡ አባታችን ግን የተበታተኑትን መነኮሳት ሰብስበው ዋልድባን እንደገና አደራጅተውና አድሰው አቀኑት፡፡ የተባሕትዎ ኑሮንም አጠናከሩበትና ገዳሙን የመናንያን አበው መሰብሰቢያ አደረጉት፡፡ አባታችን ዋልድባን እንደ ሞሰብ አንስተው አስባርከዋታል፡፡

    አባ ሳሙኤል ጊዜው ደርሶ ከማረፉ በፊት ቅዱስ ሚካኤል ነሐሴ 16 ቀን ወደ ገነት ነጥቆ ወስዶ ከዕረፍቱ በኋላ ከልጆቹ ጋር የሚኖርበትን ሥፍራ አሳይቶታል፡፡ በገነት ያሉ ቅዱሳንን ሁሉ ካሳየው በኋላ በእግዚአብሔርም ዙፋን ፊት ቀርቦ ምስጋናና ቃልኪዳንን ተቀብሎ ወደ በዓቱ ተመልሶ ታኅሣሥ 12 ቀን በታላቅ ክብር ዐርፎ ነፍሱን ጌታችን በእጆቹ ተቀብሏታል፡፡

    ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እኛንም በአማላጅነታቸው የምንታመን የተዋሕዶ ልጆች የሆንን ሁላችንን ዛሬ መስከረም 6 ቀን በዓመታዊ በዓላቸው አስበናቸው የምንውለውን ረድኤት በረከታቸውን ያሳድርብን፣ በጸሎታቸው ይማረን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top