• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    ቅዱስ ቀሌምንጦስ

    ቅዱስ ቀሌምንጦስ /91-100/

    ይህ ታላቅ አባት በሮም ተወልዶ በዘመነ ሐዋርያት ከቅዱስ ጴጥሮስ ማዕረገ ክህነት የተቀበለና የእርሱ ደቀመዝሙር የነበረ ሲሆን ስጋዊ ትምህርቱን በዚያው በሮም ያጠናቀቀ ምሁር ነበር። በቅዱስ ጴጥሮስ ሲመት የሮም ኤጲስ ቆጶስነት ተሰጥቶት ከሰባ ሁለቱ (72) አርድእት አንዱና የክርስትናን ትምህርት በፈሊጥ ካስተማሩትና የቤተክርስቲያን ቀኖናን በጽሁፍ ካወረሱን ታላላቅ ሊቃውንት አባቶች ከዋነኞቹ አንዱ ነው።

    ቅዱስ ቀሌሜንጦስን ቅዱስን ጳውሎስ በፊሊ 4፡3 ላይ የጠቀሰውና ለእርሱም በማስተማር ጊዜ ረዳቱ የነበረ መሆኑ ይነገርለታል። የቆሮንጦስ ሰዎች (ምዕመናንና ምዕመናት) ሁከትና ረብሻ ስለነበረባቸው 1ኛ ቆሮ 1፤10-17 ሐዋርያው ጳውሎስ ከሰጣቸው ምክርና ተግሳጽ በተጨማሪ ይህ ታላቅ አባት በ96 ዓ.ም ቦታው ላይ በመገኘት ሰላም እንዲሰፍን ምክር ከሰጠ በኃላ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ላይ የተመሰረቱ ሁለት መልእክታትን ጽፎ በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ ለምዕመናን እንዲነበብላቸው አድርጓል።

    የቆሮንቶስ ጳጳስ አቡነ ዲዮናሲዮስ 170 ዓ.ም ለሮም ፓፓ ለስቴር የላከው ደብዳቤ በዚሁ አባት የተጻፈ ነው። የመጀመሪያ መልዕክት በበዓላትና በሰንበት ቀን በቤተክርስቲያን ለሚሰበሰቡ በየጊዜው በመነበብ ላይ ይገኛል።

    የቅዱስ ቀሌሜንጦስ መልዕክታት ስለ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም መቀመጥ ስለቅዱስ ጳውሎስ ማስተማርና ወደ እስፓኝ ስላደረገው ጉዞ እንዲሁም የሁለቱ ሊቃነ ሐዋርያት በኔሮን ቄሳር ዘመን የተቀበሉትን ሰማዕትነት የሚያብራራ ሲሆን ለቤተ ክርስቲያንም ስለ ማዕረገ ክህነት ስለ ምዕመናን ፤ ስለንስሃ ፤ ስለትንሳኤ ሙታን የተመለከቱ ነጥቦችን ከትቦ አቆይቷል።

    ቅዱስ ቀሌሜንጦስ የቅዱስ ጴጥሮስ ደቀመዝሙር የቀዱስ ጳውሎስ የትምህርት ፈሊጥ አድናቂ የነበረ ሲሆን በመጽሐፉም ከቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት የሮሜን የቆሮንቶስንና የኤፌሶንን መልእክት እየጠቀሰ መጽሐፍትን በማብራራትና የስነ-ምግባራትን ህግጋት በማተኮር የፃፈ በመሆኑ በቤተክርስቲያናችን መጽሐፉ ከሐዲስ ኪዳን መጽሐፍት እንደ አንዱ የሚቆጠር ነው።

    ሐዋርያት ፍጻሜያቸው በሰማዕትነት የሚጠናቀቅ፤ ተጋድሏቸው በትሩፋት የተገነባና ክብራቸው የደም ሐውልት የሰራ እንደመሆኑ መጠን እርሱም ተረኛ ሆኖ ማስተማሩ እንደወንጀል ተቆጥሮ በንጉስ ትራጃን ዘሮም ዘመነ መንግስት በ 100 ዓ.ም በስደት ሲንገላታ ከቆየ በኃላ በፅኑ እስር ቆይቶ አንገቱ ላይ በገመድ /በመልሕቅ/ ታስሮ ጥቁር ባህር ውስጥ ተጥሎ አርፏል።የአርድእቱ በረከትን ያሳድርብን።

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ቅዱስ ቀሌምንጦስ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top