• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 13 November 2015

    ክብረ ታቦትና ሥርዓቱ


    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ!

    ክብረ ታቦትና ሥርዓቱ

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በየዓመቱ በጥምቀት በዓል ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው ተነሥተው ወደ ከተራው (ውኃው ወደ አለበት ወንዝ) ቦታ ይሄዳሉ፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ መጠመቁን የሚያዘክር ነው፡፡ በዚህች ቅድስት የጥምቀት ክብረ በዓልም ምዕመናን ታቦታቱን ከየአጥቢያው አጅበው ወደ ባህረ ጥምቀቱ በዋዜማ እንደመጡ ሁሉ በዚያው አድረው ያልቻለ ጠዋት ተሰባስቦ ወደየመንበራቸው በዝማሬና በእልልታ አጅበው ወደ መጡበት ቤተ መቅደስ ይመልሷቸዋል፡፡

    እግዚአብሔር “በመካከላችሁ አድር ዘንድ መቅደስን ሥሩልኝ” ብሎ እስራኤልን አዝዞ ነበር (ዘጸ 25፡8) ይህ መቅደስ የሚያስፈልገውም ለታቦቱ ማደሪያ ቤት መሆኑን “ታቦትን ከግራር እንጨት ሥሩ” ማለቱን (ዘጸ 25፡10) እንዲሁም ታቦቱ ደግሞ የእግዚአብሔር ስምና ቅዱስ ቃሉ ያለበት የጽላቱ ማኖሪያ እንደሆነ እንገነዘባለን (ዘጸ 25፡16)፡፡

    ይህ ክቡር ታቦት በሰማያዊው ታቦት ምሳሌ ዓይነት አድርጎ እንዲሠራው ለሙሴ “በተራራ ላይ እንዳሳየሁህ ምሳሌ እንድትሠራ ተጠንቀቅ” አለው (ዘጸ 25፡ 40) በዚህ ኃይለ ቃል ውስጥ ምሳሌ የሚለውን ቃል ቅዱስ ጳውሎስ በአጽንኦት ጠቅሶታል፤ እንዲህ በማለት “…በተራራው እንደ ተገለጠልህ ምሳሌ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ተጠንቀቅ ብሎት ነበርና” ይላል (ዕብራ 8፡5)፡፡

    በታቦት አድሮ የሚያነጋግራቸውም እግዚአብሔር ለመሆኑ “በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል፥ በስርየት መክደኛውም ላይ ሆኜ እነጋገርሃለሁ” በሚለው አምላካዊ ቅዱስ ቃል ተረጋግጧል (ዘጸ 25፡22፣ ዘኍ 7፡89)፡፡ ስለዚህ በዚህ አድሮ የሚያነጋገራቸው በመሆኑ በብሉይ ኪዳን ያሉት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ታቦቱ በተንቀሳቀሰ ጊዜ ሁሉ ያጅቡት ነበር፡፡ “ሕዝቡን፦ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦትና ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ፥ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት” ተብለዋልና (ኢያሱ 3፡3) ከዚህም ጋር ሆ ብሎ ማጀብም ከዚያው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወረሰ ነው፡፡ “እንዲሁ እስራኤል ሁሉ ሆ እያሉ ቀንደ መለከትና እምቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ” (1ኛ ዜና 15፡28) ለዚህም ነው በአዲስ ኪዳን በንግሥና በጥምቀት በዓላት ወቅት ሕዝቡ ሁሉ ከቤቱ ተነሥቶ ታቦቱን የሚከተሉት፡፡

    ታቦቱን ለምን እናከብረዋለን?

    ለታቦቱ የምንሰጠው ክብርና ስግደት ምክንያቱ የእግዚአብሔር ስም በላዩ ስለተጻፈበት ነው፡፡ “ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ” (ፊልጵ 2፡10) ባለው መሠረት ለታቦት እንሰግዳለን፡፡ ስለሆነም በብሉይ ኪዳን ያሉት በፊት ለፊቱ እንደሚሰግዱት እኛም ለስሙ ክብር እንሰግዳለን፤ ቃሉ “የእስራኤልም ሽማግሌዎች በእግዚአብሔር ታቦት ፊት እስከ ማታ ድረስ በግምባራቸው ተደፉ” ይላልና (ኢያሱ 7፡6)፡፡ እኛም ታቦቱ ሲነግሥ አክብረን እንሰግዳለን፡፡ ከዚህ ጋር ታቦቱ ያለበትን ቤተ መቅደስ ስለ ቅድስናው፤ ቅድስናን በመሻት እንሳለማለን፡፡ ቤተ መቅደስ መሳለም (መሳም) የፈጣሪን ቤት የመውደዳችንና የእግዚአብሔር የጸጋው ማደሪያ መሆኑን በመረዳት፤ ከእግዚአብሔር በረከትን፣ ድኅነትን እናገኛለን በማለት የማመን ፍሬ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “የልብሱንም ጫፍ ብቻ ሊዳስሱ ይለምኑት ነበር፤ የዳሰሱትም ሁሉ ዳኑ” (ማቴ 14፡36) በሚለው ቃል መሠረት፤ ቤተ መቅደሱ እና ንዋያተ ቅድሳት ለእኛ ለምናምን፣ የአምላካችን ልብሱ ዘርፎች ናቸው፡፡ እንኳንስ የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደሱ፣ የቅዱሳን ወዳጆቹ ልብሳቸው ጥላቸው እንኳ ሳይቀር ድውይ መፈወሱ በቅዱሳት መጻሕፍት ተመዝግቦ ይገኛል (ሐዋ 5፡15 ሐዋ 19:11)፤ ክርስቲያኖች ቤተ መቅደስ ሄደን ስንሳለም፣ ስንስም ስንሰግድ፣ በዚያ አድሮ በሚኖረው ረድኤተ እግዚአብሔር እንባረካለን እንቀደሳለን፣ እንፈወሳለን እንጽናናለን ብለን በማመን ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል” ብሏልና (ዘጸ 30፡29)፡፡

    ወደ ቤተ መቅደስ ስንገባም ሆነ፤ ጥምቀተ ባህሩ አካባቢ ታቦተ ክብሩ ባደረበት ድንኳን ውስጥ ስንቀርብ ጫማችንን ከእግራችን የምናወልቀው መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነው” (2ኛ ዜና 8፡11) ስለሚል ነው፡፡ “ለስሙ የሚገባ ክብርን ለእግዚአብሔር አምጡ ቍርባንን ይዛችሁ በፊቱ ግቡ በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ” (1ኛ ዜና 16፡29) በተባለውም መሠረት ቅዱሱ ታቦት ባለበት ስፍራ ዝቅ ብለን እንሰግዳለን፤ ለክብሩም ጫማችንን ከእግራችን ልናወልቅ ይገባል፡፡

    ታቦት እንዲቀረጽ ስለ መፈቀዱ

    አንዳንዶች ታቦትና ጣኦትን አንድ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ይህም ስሕተት ነው፡፡ ልዩነት እንዳላቸው በቅዱሳት መጻሕፍት ከተጻፉት እንመልከት፡፡ ጣኦቱንና ታቦቱን አብረው አንድ ቤት ባስቀመጡ ጊዜ የተከናወነው ድርጊት የትኛው ታቦት የትኛው ጣኦት መሆኑ ተለይቶአል፡፡ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አገቡት፥ በዳጎንም አጠገብ አኖሩት፡፡ በነጋውም የአዛጦን ሰዎች ማለዱ፥ እነሆም፥ ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር ዳጎንንም አንሥተው ወደ ስፍራው መለሱት…ዳጎን በእግዚአብሔር ታቦት ፊት በምድር ላይ በግምባሩ ወድቆ ነበር የዳጎንም ራስ እጆቹም ተቈርጠው በመድረኩ ላይ ወድቀው ነበር የዳጎንም ደረት ብቻውን ቀርቶ ነበር” (1ኛ ሳሙ 5፡1-12)፡፡

    ይህን የመሰለ ማስረጃ ስናቀርብ ደግሞ የብሉይ ኪዳን ታቦት አንድ ነው፤ ይህ ሁሉ ከየት መጣ ብለው ይጠይቁናል፡፡ ይሁን መጠየቅ ባልከፋ፣ ጥያቄአቸውን በጥያቄ እንድንመልስ ያስገድደናል፤ ንጉሥ ሰሎሞን ያነፀው ቤተ መቅደስ አንድ ነበር፣ ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን ሌሎች ቤተ መቅደሶችን ለምን ሠሩ? እስራኤላውያን የነቢያት መጽሐፍ መካከል የኢሳይያስ መጽሐፍ አላቸው እኛም ኢትዮጵያውያን “የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር” (ሐዋ 8፡26-30) የተባለው ይህን መጽሐፍ እንዴት ይዞት ተገኘ? እኛስ መጽሐፍ ቅዱስ በየቤታችን እንዴት ኖረን? ያሰኛል፡፡

    እግዚአብሔር ይመለክበት ዘንድ ነቢዩ ሙሴን ቤተ መቅደስ ሥራ ካለው፤ ከእርሱ በኋላ ያለን ምእመናን ፈጣሪን እያመለክነው ነውና፤ ቤተ መቅደስ መሥራት እንችላለን ማለት ነው፡፡ ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደስ የሠራው ደብተራ ኦሪት ከተሠራ ከብዙ ዘመን በኋላ ነው፤ መቅደስ የተሠጠው ለነቢዩ ሙሴ ነው እንጂ ለአንተ አይደለም በማለት ንጉሥ ሰሎሞንን የነቀፈው ማንም የለም፤ ከሠራውም በኋላ እግዚአብሔር አምላክ “በስሜ የተጠሩት ሕዝቤ ሰውነታቸውን አዋርደው ቢጸልዩ፥ ፊቴንም ቢፈልጉ…አሁንም በዚህ ስፍራ ለሚጸለይ ጸሎት ዓይኖቼ ይገለጣሉ፥ ጆሮቼም ያደምጣሉ አሁንም ስሜ ለዘላለም በዚያ ይኖር ዘንድ ይህን ቤት መርጫለሁ ቀድሻለሁም ዓይኖቼና ልቤም ዘወትር በዚያ ይሆናሉ” ብሎታል (2ኛ ዜና 7፡14-16፣ 1ኛ ነገሥ 9፡3)፡፡ አሁን በዓለም ዙሪያ ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና የመጡ ሁሉ በየቦታው ቤተ መቅደስ አንጸው እንዲጸልዩበት ጌታ “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች” (ማር 11፡17) ባለው መሠረት በሁሉም ቦታ ለስሙ ቤት ይሠራል፡፡

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መሠዊያ ቀጣይነት ሲያስተምር “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፥ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፤ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፥ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፥ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ” (ማቴ 5፡23-24) በማለት በመሠዊያው ለታቦቱ ስእለት ተስለውም ሆነ በበጎ ፈቃደኝነት የሚመጣውን መባ እንደሚቀበል ከተናገረ ሐዋርያት በቀጣይነት የሥጋ ወደሙ መሠዊያ እንዲኖራቸው አስፈልጓል፤ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “መሠዊያ አለን” (ዕብራ13፡10) ያለው፤ ይህም የሥጋ ወደሙ መፈተቻ የሆነው ታቦቱ ነው፡፡

    በእርግጥ ጥንት አምልኮተ እግዚአብሔር በእስራኤል ብቻ ነበር፤ ቤተ መቅደስም እንዲሁ፡፡ በአዲስ ኪዳን ግን በመላው ዓለም ሁሉ እንዲኖር ፈጣሪ መፍቀዱን ነቢዩ ሚልክያስ “ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፥ ንጹሕም ቍርባን ያቀርባሉ ስሜ በአሕዛብ ዘንድ ታላቅ ይሆናል” (ሚልክ 1፡11) ብሏል፡፡ በየስፍራው ሲል በየአጥቢያው ለልዩ ስሙ ልዩ የምስጋና ቤተ መቅደስ ታንጾ እንዲመለክበት መፍቀዱን ያስረዳናል፡፡ ስለሆነም የፈጣሪ አምልኮት በእሥራኤል ብቻ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎች ሊታረሙ ይገባል፡፡

    እንደዚሁም ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር ለሙሴ ሠርቶ የሰጠው ታቦት ሲሰበርበት፣ እንደገና እንዲሠራው ያደረገው ከዚያ በኋላ በሰዎች እንዲሠራ መፈቀዱን ያሳያል፡፡ “እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች እንደ ፊተኞች አድርገህ ጥረብ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላቶች የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ…ሙሴም እንደ ፊተኞቹ አድርጎ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ጠረበ” ይላልና ሌላ ታቦትንና ጽላትን እግዚአብሔር ባሠለጠናቸው ቅዱሳን አበው እንዲሠራ ቅዱስ ፈቃዱ ሆኖአል (ዘጸ 34፡1-4)፡፡ ጌታ በአዲስ ኪዳን ቤተ መቅደሱ ውስጥ ገብቶ ነጋዴዎችን ሲያስወጣ በቤተ መቅደስ የሚገኙ ንዋያተ ቅድሳትን አውጥቶ ጣለ የሚል ቃል አልተጻፈልንም፡፡

    እኛ ክርስቲያኖች ሰማያዊ ዜጎች እንደመሆናችን ታቦት በዚህ ምድር ላይ እንዳለን ሁሉ፤ ወደ ሰማያዊ አገራችንም በምንሄድበት ወቅት የዚሁ አይነት ታቦት እዚያ እናገኛለን፡፡ “እኛ አገራችን በሰማይ ነውና” (ፊልጵ 3፡20) “በሰማይም ያለው የእግዚአብሔር መቅደስ ተከፈተ፥ የኪዳኑም ታቦት በመቅደሱ ታየ” (ራእይ 11፡19) ስለዚህ በዚያም መገኘቱን ልብ እንበል፡፡

    ይህን የተከበረ ታቦታችንን ለማጣጣልና ምእመናንን ለማደነጋገር “የብሉይ ኪዳን ታቦት አራት ካህናት እንዲሸከሙት ሆኖ ነው የተሠራው፤ የአዲስ ኪዳን ታቦት አንድ ካህን እንዲሸከሙት ሆኖ ነው የተሠራው ለምን?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አሁን የአዲስ ኪዳን ታቦት ለአራት ሆነው ካህናት ሲያከብሩት (ሲሸከሙት) ቢያዩ የሚቀበሉ ሆነው አይደለም፡፡ አይሁድ ክርስቶስን በመስቀል ሰቅለው “አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ አሁን ከመስቀል ይውረድ አሉ” (ማር 15፡32) ጌታ ሁሉን ቻይ ነው፤ የሚያምኑበት ቢሆን አድርጎ ያሳያቸው ነበረ፣ ነገር ግን ስለማያምኑበት ዝም እንዳላቸው እኛም አሁን የምንመልስላቸው ለእነርሱ አይደለም፤ ምእመናንን ከግርታ ለመታደግ፤ ደግሞም በመሰል ጥያቄዎች ልባቸው ለተከፈለ የተረጋገጠ መረጃ ለመስጠት እንጂ፡፡

    ታቦት ማለት ማደሪያ ማለት ሲሆን በውስጡ ባለው ጽላት የእግዚአብሔር ቃል ተጽፎበታል፡፡ ሌላው መታወቅ ያለበት ታቦትና ጽላት ተተካኪ አገባብ ይዘው በጽሑፍ ሊገኙ ይችላሉ፤ አዳሪው (ጽላት) በማህደሩ (ታቦት) መጠራት የተለመደ ነው፡፡ የክርስቶስ ሥጋውና የከበረ ደሙ ለመስዋዕትነት ይቀርብበታል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “መሰዊያ አለን” (ዕብራ13፡10) ብሎ የተናገረው ታቦቱን ነው፡፡ ለምን ቅርጹ ለአራት የሚሸከሙት ታቦት አይነት አልሆነም ለሚለው እስራኤላውያን ታቦት የተሰጣቸው ከግብጽ አገር ወደ ከነዓን አገር በሚጓዙበት ወቅት ስለሆነ በመሎጊያ (ቀዳዳ) ሁለት የግራር እንጨቶች በማስገባት ይሸከሙአቸው የነበሩት፡- ታቦት (ዘጸ 25፡15)፣ ገበታቸውም (ዘጸ 25፡28)፣ መሠዊያቸውም የሚሸከሙት በአንድ ሰው አልነበረም (ዘጸ 27፡7) ይህን አይነት ታቦትም ሆነ መንበር ለጉዞ እንዲመች የወጣ ሥርዓት ነበር፡፡

    በአዲስ ኪዳን ግን ቤተ ክርስቲያን ተረጋግታ፣ ከአንዱ አገር ወደ አንዱ አገር የምትጓጓዝ ባለመሆንዋ፣ ሥርዓቱን የማሻሻል ሥልጣን አላት፡፡ ጽላቱ ያለበትን መጠን ብቻ በሚሸፍን መልኩ በአንድ ካህን የሚከብር ታቦት አድርጋዋለች፡፡ የጽላቱ ማደሪያ ታቦት መጠኑ መቀየር የለበትም የሚባል ከሆነ፣ ጥንት መጻሕፍት ሲጻፉ በጥቅልል ብራና እንጂ በወረቀት ጥራዝ አልነበረም፣ “በመጽሐፍ ጥቅልል” (ዕብ 10፡7) እንዲል፤ ቅርጹ ይህን አይመስልም ነበረ “መጽሐፉንም ጠቅልሎ ለአገልጋዩ ሰጠው” (ሉቃ 4፡20) የሚለውንም ይህንን ያመለክታል፡፡ ቃሉ ያለበት ታቦት ለምን መጠኑ ተቀየረ ማለት፤ መጽሐፍ ቅዱስ ከጥቅልል ወደ ወረቀት ጥረዛ መጽሐፍ ሆኖ ለምን ተቀየረ? ብሎ እንደመጠየቅ ይቆጠራል፡፡ ይህ ሥርዓት ነው፡፡ ሃይማኖትን እናድስ ብሎ መነሣት ነው እንጂ የሚከለከለው፤ ሥርዓትን ማሻሻል የተገባና የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥልጣኗ ነው፡፡

    ወስብሐት ለእግዚአብሔር

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ክብረ ታቦትና ሥርዓቱ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top