በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ
ሥርዓተ ቅዳሴቤተ ክርስቲያናችን ሥጋ ወደሙን የምታከብርበት የተለየ ሥርዓተ ጸሎት አላት፡፡ ይህ ልዩ የምስጋና ጸሎት ‹‹ጸሎተ ቅዳሴ›› ይባላል፡፡ ያለ ጸሎተ ቅዳሴ ሥጋ ወደሙ አይዘጋጀም (አይፈተትም)፡፡ ያለ ሥጋ ወደሙም ቅዳሴ አይቀደስም፡፡
በቤተ ክርስቲያን የታወቁና እስከአሁንም በአገልግሎት ላይ ያሉ ቅዳሴያት በዓይነት 14 ሲሆኑ ቀደም ባሉት ዘመናት በተለይ በወርኀ ጽጌ ይቀደስ የነበረ ‹‹መዓዛ ቅዳሴ›› የሚባል 15ኛ ቅዳሴም በቤተ ክርስቲያናችን ይገኛል፡፡
ጸሎተ ቅዳሴ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የዚህ አጭር ገጸ ንባብ /የመግቢያ ንግግር/ ዓይነተኛ ዓላማ ቅዳሴ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑን ግልጽ ማድረግ ነው፡፡
ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ምሥጢረ ቁርባንን በመፈጸም ከሥርዓተ ጸሎቱ ጋር ለሐዋርያት አሳይቷቸዋል፡፡ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ወሎሙ አርአየ ሥርዓተ ምሥጢር ዘቁርባን›› - ‹‹ለእነርሱም የምሥጢረ ቁርባንን ሥርዓት አሳያቸው›› በማለት የዘመረው ስለዚህ ነው፡፡
መቼና የት አሳያቸው ለሚል ሰው ወንጌል ‹‹እንጀራንም አንሥቶ ባረከ ቆርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ›› ትለናለች፡፡ (ማቴ26.26) ይህ የሆነው እንደ ነገ ዐርብ ሊሰቀል ሐሙስ ማታ ነው፡፡ ቦታውም ቤተ አልዓዛር ነው፡፡ በወቅቱ ‹‹እንጀራንም አንሥቶ›› ያለው ተራ ማዕድን አይደለም፡፡ ‹‹ባረከ›› የሚለውም የማዕድ ጸሎት አደረገ ለማለት አይደለም፡፡ ታዲያ ምንድን ነው ለሚል ሰው ‹‹እንጀራ›› ያለው ወደ አማናዊ ሥጋ አምላክነት የሚለወጠውን ‹‹ኅብስት›› ነው፡፡ ‹‹ባረከ›› ያለውም በአንድ ቃል ቢገለጥም ለቁርባን ማክበሪያ የሚደረገውን የምስጋና ጸሎት ማለትም ቅዳሴውን ነው፡፡
ይህ የሚታወቀው በወንጌል ውስጥ ከዚህ አስቀድሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብስት አበርክቶ በተደጋጋሚ ሕዝብን መግቧል፡፡ እንጀራና ዓሣንም በሚያበረክትበት ጊዜም አመስግኗል፡፡ ይሁን እንጂ ምስጋናው ‹‹ጸሎተ ማዕድ›› ምግቡም ‹‹ምግበ ሥጋ›› እንጂ ከዚያ ያለፈ ምሥጢር አልነበረውም፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሆነው ግን እጅግ የተለየ ነበር፡፡
ምክንያቱም በጸሎተ ሐሙስ የምስጋና ጸሎት ኅብስቱ ወደ እውነተኛ ሥጋነት ወይኑም ወደ እውነተኛ ደምነት ተለውጧልና፡፡ ይህም አያይዞ ‹‹እንካችሁ፥ ብሉ ይህ ሥጋዬ ነው።›› በማለቱ ይታወቃል፡፡ (ማቴ26.26)
ይህ ለሥጋ ወደሙ ማክበሪያ የምንጠቀምበት ልዩ የምስጋና ጸሎት ‹‹ጸሎተ አኮቴት›› ወይም ደግሞ ‹‹አኮቴተ ቁርባን›› ይባላል፡፡ ለዚህ ነው ገባሬ ሠናዩ ካህን በቅዳሴ ጊዜ ከሥርዓተ ቅዳሴ ወደ ፍሬ ቅዳሴ ሲገቡ ‹‹አኮቴተ ቁርባን ዘእግዝእትነ ማርያም ዘደረሰ ላቲ፤ አኮቴተ ቁርባን ዘቅዱስ ‹‹እገሌ›› …›› የሚሉት፡፡ እስከዚህ ያለው ስለ ሥጋው የተነገረው ነው፡፡
እንዲሁ ደግሞ ቅድስት ወንጌል ስለ አማናዊ ደሙ ‹‹ጽዋንም አንሥቶ አመስግኖም ሰጣቸው፡፡›› ትለናለች፡፡ (ማቴ26.27) ‹‹አመስግኖ›› የምትለዋን ቃል ልብ በሉ፡፡ ቀደሰ ማለት አመሰገነ ማለት ነውና፡፡ ቅዳሴ ማለት ደግሞ ምስጋና ማለት ነው፡፡ አመስግኖ ሲል ቀድሶ ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
ስለዚህ ምንም እንኳን ምን ብሎ እንደቀደሰ በወንጌሉ ላይ በዝርዝር ባይቀመጥም ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ወደሙን ለሐዋርያት ያቀበላቸው ራሱ ቀድሶ ነው፡፡ ‹‹አመስግኖም ሰጣቸው›› ይላልና፡፡ ጸሎተ ቅዳሴ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ያሰኘውም ይህ ቃል ነው፡፡
ድኅረ ቁርባን ያለው ከ‹‹ነአኩቶ›› እስከ ‹‹እትዉ በሰላም›› ያለው ልዩ ልዩ ክፍሎች ያሉት የጸሎት ክፍልም እንዲሁ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀድሶ (አመስግኖ) ሥጋውና ደሙን ለሐዋርያቱ ካቀበላቸው በኋላ ‹‹መዝሙርንም ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ወጡ›› ይላል፡፡ (ማቴ26.30) እንግዲህ ከቁርባን በኋላ ሐዋርያት የዘመሩት ይህ መዝሙር ዲያቆኑ ከቁርባን በኋላ ‹‹ነአኩቶ›› ብሎ ጀምሮ እትዉ በሰላም እስኪለን ድረስ ያለውን ክፍል የሚወክል ነው፡፡
ይህን በመሰለ ቅዳሴ የሚፈተተው አማናዊ ሥጋ የሚቀዳውም አማናዊ ደም ነው፡፡ ስለ ስጋው አማናዊነት ቀደም ሲል ጠቅሰናል፡፡ ስለ ደሙ አማናዊነት ደግሞ ‹‹ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታየሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።›› ይላል፡፡ (ማቴ26.27) ‹‹ደሜ›› እያለ መስጠቱን ልብ ማለት ነው፡፡
‹‹በረከትን የሚሰጥ የሕግ መምህር›› ኢየሱስ ክርስቶስ የሐዲስ ኪዳንን ሕግ ሲሠራ በዝርዝር ሳይሆን አጠቃላይ መመሪያ እንደሰጠን አስቀድሞ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ዝርዝሩን ማዘጋጀት የእርሱ ተከታዮችና ሥልጣን የሰጣቸው አባቶች ድርሻ ነው፡፡ እነርሱ ሥርዓቱን ሲሠሩ ደግሞ ‹‹እስከ ዓለም ፍጻሜ›› ከእነርሱ እንደማይለይ ቃል ኪዳን ገብቷል፡፡
ይህን ሐሳብ በምሳሌ እንመልከት፡- ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ›› ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንደማይገባ አስረግጦ አስተምሯል፡፡ ነገር ግን መቼና የት መጠመቅ እንዳለብን፣ ማን አጥማቂ መሆን እንዳለበት ወዘተ ዝርዝር መመሪያ አልሰጠንም፡፡
ስለ ሥጋ ወደሙም እንዲሁ ነው፡፡ ሥጋውንና ደሙን ያልበላ የዘለዓለም ሕይወት እንደሌለው ሲናገር ሥጋ ወደሙን እንዴት እንደምናገኝ፣ ማን እንደሚያዘጋጀው፣ እንዴት እንደሚዘጋጅ፣ መቼና በምን ዓይነት ዝግጅት መቀበል እንዳለብን ዝርዝር መመረያ አልሰጠንም፡፡ ከዚህ የተነሣ የሚታወኩ በርካታ የእምነት ድርጅቶች አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ግን ከዚህ ሁከት ነጻ ናት፡፡ ይህን ሁሉ ኃላፊነት የተቀበሉ አባቶች ስላሏት በሚገባ አሰናድተዋታል፡፡
ከዚህ በመነሣት አባቶቻችን ወንጌል ‹‹አመስግኖም ሰጣቸው›› ትላለች እኛም ሥጋ ወደሙን ለምእመናን ከማቀበላችን በፊት የምናቀርበው ወጥ የምስጋና ሥርዓት ያስፈልገናል ብለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል እየተመሩ በርካታ የቅዳሴ መጻሕፍትን አዘጋጁ፡፡ ሐዋርያት ከቁርባን በኋላ መዝሙር እንደዘመሩ ወንጌል ስለምትናገር እንዲሁ ድኅረ ቁርባን የሚገባውንም ጸሎት አዘጋጁ፡፡ ይህ ሐተታ ስለ ቅዳሴ አጠቃላይ ይዘት የሚናገር ነው፡፡ ስለ እያንዳንዱ ቅዳሴ የውስጥ ይዘት፣ ስለ ዜማው፣ ስለ ቅዳሴ ሥርዓት፣ ስለካህናትና ስለተግባራቸው፣ ስለአልባሳታቸው እንዘርዝር ብንል ጊዜ ያጥርብናል እንጂ ስለ ሁሉም እንዲሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ እያመሳጠሩ ማሳየት ይቻላል፡፡
ይህን ከጣዕሙ ብዛት የተነሣ አጥንትን የሚያለመልም ዝማሬ በሥጋዊ ዓለም ሳለን ቀምሰን እንድናጣጥመው ያደረገን አምላክ ክብር ምስጋና ይድረሰው!
0 comments:
Post a Comment