ስእለትና ሥርዓቱ
ስእለት ማለት ሰአለ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ለመነ፣ ተማጸነ፣ ጠየቀ ማለት ነው፡፡ በዚህ ልመና ውስጥ ጠያቂው ወይም ልመና አቅራቢው በራሱ ፈቃድና ተነሣሽነት “ለክብርህ መገለጫ ይህን አመጣለሁ” ብሎ ብፅዓት (ቃል) ይገባል፡፡ ይህ አማኝ እንዲህ አደርጋለሁ ብሎ ቃል እንዲገባ የሚያስገድድ የሃይማኖት ሥርዓት የለም፤ ልቡ የፈቀደውን አደርጋለሁ ካለ ግን ቃሉን መጠበቅ ይገባዋል፡፡ ብዙ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተጻፉት ልመና አቅራቢዎች ቃላቸውን ጠብቀው ያደርጋሉ፡፡ ቃሉ፡- “ለእግዚአብሔርም ስእለት ይሳላሉ ይፈጽሙትማል” (ኢሳ 19፡21) ይላልና፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ በራሱ ፍቃድ ስዕለትን ስለተሳለው ሰው የሚናገረውን ክፍል እስቲ እንመልከት “ያዕቆብም እንዲህ ብሎ ስእለት ተሳለ። እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ቢሆን፥ በምሄድባትም በዚች መንገድ ቢጠብቀኝ፥ የምበላውንም እንጀራ የምለብሰውንም ልብስ ቢሰጠኝ…ለሐውልት የተከልሁት ይህም ድንጋይ የእግዚአብሔር ቤት ይሆናል ከሰጠኸኝም ሁሉ ለአንተ ከአሥር እጅ አንዱን እሰጥሃለሁ” ብሏል (ዘፍ 28፡20-22) እንደለመነው በተደረገለትም ጊዜ ይህንንም ስእለት እንዲፈጽም እግዚአብሔር “ሐውልት የቀባህበት በዚያም ለእኔ ስእለት የተሳልህበት የቤቴል አምላክ እኔ ነኝ” (ዘፍ 31:13) ብሎ ተገልጦለታል፤ ይህ የስእለትን በጎነት እግዚአብሔር እንደፈቀደ ያመለክታል፡፡
እንደ እምነቱና እንደ ልመናው የተደረገለትም፣ “አምና ይሄን ጊዜ ተስዬ ነበር”፤ “ይህንና ይሄንን ካደረግህልኝ ለክብርህ መገለጫ ጥላ ይዤ እመጣለሁ”፤ “የምትመሰገንበትን ዕጣን፣ ጧፍ፣ ንዋየ ቅድሳቱን ወይም ገንዘብን አስገባለሁ” ሲሉ፤ ጥቂት ጉልበት ያላቸው ወጣቶች ደግሞ “ታቦቱ የሚሄድበትን መንገድ እጠርጋለሁ”፣ “ቄጤማ ገዝቼ እጎዘጉዛለሁ”፣ “ምንጣፉን ተሸክሜ አምጥቼ ታቦቱ በሚሄድበት መንገድ ላይ በሆሣዕና ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያዋ ላይ ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ ሲገባ ጨርቅ እንዳነጠፉት ተከታዮቹ፣ እኔም ምንጣፍ ዘርግቼ ታቦቱን አከብራለሁ” ብለው የአምና ስዕለታቸው በተግባር ይፈጽማሉ፡፡ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሕግ ከሆነ፡- “ማናቸውም ሰው ስእለቱን ሁሉ፥ በፈቃዱም የሚያቀርበው” (ዘሌ 22፡18) በማለቱ ፈቃደኝነት ያለበት ነው እንጂ ትእዛዛዊ አይደለም፡፡
በስእለት ሥርዓት ትኩረት የሚያስፈልገው ስእለት ከተሳሉ ቃልን መጠበቅ እንጂ መርሳት እንደማይገባ ነው፡፡ ስለዚህ የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፡-
– “ሰው ለእግዚአብሔር ስእለት ቢሳል፥ ወይም ራሱ በመሐላ ቢያስር፥ ቃሉን አይስበር
ከአፉ እንደ ወጣው ሁሉ ያድርግ” (ዘኁ 30፡2)
– “ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኃጢአትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አታዘገይ” (ዘዳ 23፡21)
– “ወደ እርሱም ትጸልያለህ፥ እርሱም ይሰማሃል ስእለትህንም ትሰጣለህ” (ኢዮ 22፡27)
– “ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ የተሳልኸውን ፈጽመው” (መክ 5፡4)
መልካም የሆነ ስእለት እንዳለ ሁሉ ሃይማኖቱን የሚጻረር “ስእለት” ደግሞ በጥምቀተ ባሕር በታቦቱ ዙሪያ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህም አምላክን ከማሳዘኑም አልፎ ምእመኑን ራሱን በነፍስ በሥጋ ወደሚጎዳ ስህተት የሚመራ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ሊለመን የሚገባውና ስእለት ሆኖ ሊቀርብ የሚገባው አምላክ የሚወደው እንጂ የሚጠላው መሆን አይገባውም፡፡ ፈጣሪያችን “የምትለምኑትን አታውቁም” (ማቴ 20፡22) በማለት ጌታችን በተሳሳተ መንገድ ለቀረቡት ደቀ መዛሙርቱ ገስጾአቸዋል፡፡
በክብረ ታቦቱ ዕለት እያጀቡ ከሚከተሉት ምእመናን መካከል፤ “አምና ይሄን ጊዜ ተስዬ ነበረ” እየተባሉ የሚዘመሩ መዝሙሮች እንዳሉ ይታወቃል፤ እነዚህ መልካም ሲሆኑ በሙዚቃ መሣሪያዎች እየታጀቡ የሚደንሱት ደግሞ እንዲሁ በተመሳሳይ “ለታቦቱ እዘፍናለሁ ብዬ ተስዬ” ነበረ ቢሉ ይህ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና ትምህርት የወጣ የጥፋት መንገድ መሆኑን ሁሉም ሊረዳውና ሊታረም የተገባ ነው፡፡
ስለዚህ ወገኖቼ ስእለት ከመግባታችን በፊት ለቤተ ክርስቲያን ምን ይጠቅማል ማለት ይገባናል፤ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን የማይጠቅም “አይጥ አመጣለሁ” ብሎ ቢሳል በፈጣሪ ላይ ማላገጥ ይሆናል፤ እንደ እምነታችን ቢሆንም በባዶ እግሬ እመጣለሁ፣ በእንብርክኬ እዞራለሁ፣ የመሳሰሉ ጠቃሚ አለመሆናቸውን ሳንጠቁም አናልፍም፡፡ ነገር ግን ካለመረዳት ይህን ቃል ከገባን አምላክ ቃል የመጠበቅ ታማኝነታችንን ስለሚፈልገው ያንኑ ማድረግ ግድ ሊሆንብን ነው (ዕብራ 11፡32-33፤ መሣፍ 11:31-39)፡፡ መልካሙን ሁሉ ለማድረግ ቃላቸውን የጠበቁ ሁሉ ከአምላክ ክብርንና ጸጋን ያገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የነቢዩ ሳሙኤል እናት “ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፥ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ…ብላ ስእለት ተሳለች” (1ኛ ሳሙ 1፡11) እግዚአብሔርም ሰማት እንደ ስእለትዋ ወደ ቤተ መቅደስ እንዳመጣችው፤ እንዲሁም በተመሳሳይ ቅዱስ ኢያቄምና ቅድስት ሐና እመቤታችን ድንግል ማርያምን በስእለት በማግኘታቸው ብጽአታቸውን ለፈጣሪ አስረክበዋል፡፡ እንዲሁ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚሆን የሚሳሉ ሁሉ ፈጣሪ ሲሰማቸው ቃላቸውን ሊጠብቁ ይገባል፡፡ “የተቀደሰውን ነገርህን ስእለትህንም ይዘህ እግዚአብሔር ወደ መረጠው ስፍራ ሂድ” (ዘዳ 12፡26) ይላልና፡፡
ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ስእለት ኃጢአት መሆን እንደሌለበት መጽሐፍ ቅዱስ፡-
– “ነውር የሌለበትን በእግዚአብሔር ፊት ያቅርብ” (ዘሌ 3፡1)፣
– “ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የጋለሞታይቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸው” (ዘዳ 23፡18)
እንዳለው ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
በጥምቀተ ባሕር አካባቢዎች ሰይጣን የዘራቸው እንክርዳዶች ሊነቀሉ ያስፈልጋል፤ የሚያስጸይፉ ናቸውና፡፡ እርግጥ ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰለው ምሳሌ እውነተኛና ትክክለኛ ሃይማኖትና የእግዚአብሔር ቃል በመልካም ስንዴ ሲመሰል፤ በዚህ ውስጥ ሰይጣን እንክርዳድ እንደሚዘራና አመሳስሎ ሕዝብን ለጥፋት እንደሚዳርግ ተቀምጦአል (ማቴ 13፡26-39)፡፡ ይህ ሰይጣን የዘራው እንክርዳድ (የስህተት) ጉዞ እንደዋዛ በቅሎ ልንነቅለው እስከማንችል ስር የሰደደ ይመስላል፡፡ እኒህም ዘፈን፣ ዳንኪራ፣ በዓሉን ሊያከብሩ የሚመጡ ሴቶችን አላሳልፍ ብሎ መጎተት፣ በዝሙት ቃላት መወራረፍ፣ የምንዝር ጌጦችን አድርጎ ታቦቱን ማጀብ፣ መስከርና ታቦቱ በሚያድርበት ዙሪያ ዝሙትን መፈጸም፣ የመሳሰሉ ሥርዓት ያልሆኑ ክብረ ነክ ድርጊቶችን የሚፈጽሙት ሁሉ ናቸው፡፡
ከዚሁ ጋር “ዘፈን ለመዝፈን ስእለት ተስዬ ነበር” አነጋገር ከእኛ ሊቀረፍ ይገባል፡፡ “በቀን እንደምንሆን በአገባብ እንመላለስ፤ በዘፈንና በስካር አይሁን፥ በዝሙትና በመዳራት አይሁን፥ በክርክርና በቅናት አይሁን” (ሮሜ 13፡13) እንዳለው በበዓሉ ቀን ሰክሮ መታየት ርኩሰት ከመሆኑ አልፎ ፈጣሪንና ሃይማኖቱን ማስነቀፍ ይሆናል፤ “በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባልና ተብሎ እንደ ተጻፈ” (ሮሜ 2፡24)፡፡
ልብ በሉ! በታቦቱ ዙሪያ ሲዘፍኑ መገኘት፣ ሃይማኖቱ ዘፈን ይፈቅዳል ብሎ እንደመመስከር ስለሚሆን ሊቆም ይገባል፡፡ “ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር” አለን እንጂ ይዝፈን አላለንምና (ያዕ 5፡13)፣ ከሚዘምሩ መዘምራን ጋር ክብ ሠርተን እንዘምር እንጂ ዘፈንን ከሚዘፍኑ ጋር አንዋል፡፡ ዘፈን የእግዚአብሔር መመስገኛ ሳይሆን የሰይጣን ግብር ነው፡፡ ውጤቱም ገሃነመ እሳት የሚያስገባ ነው (ገላ 5፡15)፡፡ እነዚህ ለታቦት ተስዬ ነው ብለው የሚዘፍኑ ብርሃንን ከጨለማ ጋር ሊያቀላቅሉ የሚሹ ናቸው፡፡ አትዝፈኑ ተብሎ እየተደጋገመ እየተነገረ በአመጽ የሚሰሙ አልሆኑም “የዓመፃቸውን ደመወዝ ይቀበላሉ። በቀን ሲዘፍኑ እንደ ተድላ ይቆጥሩታል፤ ነውረኞችና ርኵሳን ሆነው ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣ ይዘፍናሉ፡፡ ምንዝር የሞላባቸው ኃጢአትንም የማይተዉ ዓይኖች አሉአቸው፤ የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፤ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው፤ የተረገሙ ናቸው” (2ኛ ጴጥ 2፡13-14)፡፡
ከእነዚህም ጋር የሚውል የተረገመ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ እርግማን ለመውጣት ንስሐ በመግባት ታቦቱን ከሚያከብሩ ካህናትና ከሚዘምሩ መዘምራን ጋር ብቻ በመገኘት አብሮ በመዘመር፣ ግጥሙን ባናውቀውም እንኳ በጭብጨባና በእልልታ ማጀብ ይገባናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ” ይላልና (መዝ 1፡1) ከእነዚህ ሰዎች በመለየት እርቃናቸውን ስናስቀራቸው፤ ሰው ለምን ወደ እነርሱ መምጣት እንደተወ ሲገባቸው ወደ እውነትም ይመለሳሉ፤ የምናጅባቸውና የምንመለከታቸው ከሆነ በርቱ ብሎ እንደማበረታታት ይቆጠራልና “ወዳጅ ሆይ፥ በጎ የሆነውን እንጂ ክፉን አትምሰል” ያለውን ሕግ እንከተል (3ኛ ዮሐ 1፡11)፡፡
ባጠቃላይ ፈጣሪ ዘንድ ቀርበን የምንለምነው ልመና እና የምንገባው ብፅዓት ንጹሕ፣ ለሕይወታችን ለውጥን የሚያመጣ፣ የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓትን የሚጠብቅ፤ አገልገሎትዋንም የሚደግፍ ልመና መሆን ይገባዋል፡፡ በዘፈን፣ በስካር፣ በዳንኪራ፣ በዝሙት ጠላት ሰይጣንን ካልሆነ በቀር እግዚአብሔር አምላችንን ማገልገል አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ከጥምቀቱ ረድኤት በረከት ይክፈለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment