• በቅርብ የተጻፉ

    Wednesday 11 November 2015

    ምሥጢረ ተክሊል ምዕራፍ ፫

                                                                      ምሥጢረ ተክሊል ክፍል ሰባት 

    በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን 

    የወደደን የፍቅር መምህራችን እግዚአብሔር ስለማይነገር ስጦታው ሁሉ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤ የአምላክ እናት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም በትውልዱ ሁሉ አንደበት ምስጋና ይድረሳት፤ ለስሙ ለተለዩ ቅዱሳን፤ ለስሙ ለሞት ተላልፈው ለተሰጡ ሰማእታት፤ መናፍቃንን ድል ለነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፤ ስለ ስሙ ለተሰደዱ ጻድቃን ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡

    እርሱ እየረዳን፤እርሱ ድካማችንን እያገዘን፤እርሱ ጎዶሏችንን እየሞላ፤እርሱ ጥያቄዎቻችንን እመለሰ፤እርሱ በጉዟችን ሁሉ ከፊት እየቀደመ ከኋላም እየተከተለ፤ከጎንም እየደገፈን፤ኃይላችን እያደሰ፤በየምዕራፉ እያሳረፈን ከሰባተኛው ክፍል አድርሶናል፡፡ በእውነት ይህም በእርሱ ነውና ክብር ብቻውን አምላክ ለሆነው ለእርሱ ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡ አሜን፡፡

    ወዳጆቼ እንደ ውቂያኖስ የጠለቀ እንደ ባሕር የሰፋውን የእናት ቤተክርስቲያናችንን ምስጢራት በማንኪያ ታህል እንድንቀምስ የረዳን እግዚአብሔር በክፍል አንድ የምሥጢረ ተክሊል ምንነት፤ በክፍል ሁለት የጋብቻ ዓላማ፤ በክፍል ሦስት ቅድመ ጋብቻን፤በክፍል አራት የቅድመ ጋብቻን የመጨረሻ ክፍል፤በክፍል አምስት ድንግልናና ተክሊል ፤ በክፍል ስድስት የሥርዓተ ተክሊል መስፈርቶች ምንድን ናቸው? በሚሉ ንዑሳን ርዕሶች እርሱ ያስተማረንን በጥቂት በጥቂቱ ተምረናል አሁንም እርሱ እንደረዳን በክፍል ሰባት ትምህርታችን ከመስፈርቶቹ ሁለተኛውን በመጽሐፍ ቅዱስ እና በሊቃውንት መጽሐፍ እንመለከታለን፡፡
    የሥርዓተ ተክሊል አንዱ መስፈርት ሐይማኖት እንደሆነ፤ ሐይማኖት የሌለውና ልጓም የሌለው ፈረስ አንድ እንደመሆኑ ሃይማኖት ከሌለው ወይም ሃይማኖቱ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ካልሆነው ሰው ጋር መጋባት እግዚአብሔርን አለመፍራት ሰውንም አለማክበር እንደሆነ ከብዙ በጥቂቱ በክፍል ስድስት ትምህርታችን ተመልክተናል፡፡ ይልቁንም አይደለም አብሮ "መኝታው ንጹሕ ይሁን" በተባለው ቅዱስ ጋብቻ መኖር ቀርቶ ባልንጀርነትን ሁሉ ሃይማኖትም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከለክል ይህንን ግን እንዳልሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንቢ ላለ በሥጋ የዘራውን መበስበስን እንደሚያገኝ በግልጽ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ይነግረናል፡፡ገላ 6፡7 

    2. ድንግልና ተጠብቆ ሊኖር ይገባል

    ወዳጆቼ ድንግልናን በተመለከተ በክፍል አምስት ያየነው ጉዳይ በመሆኑ አልመለስበትም ይሁንና በዚህ ርዕስ ስር እንድናይ የወደድኩት በዘመናችን ድንግልናን እንዳንጠብቅ ፈተና የሆኑብንን እና መፍትሄቸውን ጭምር ነው፡፡ የመጀመሪያው የዕድሜ ጉዳይ ድንግልናችንን እንዳናጸና ፈተና የሆነብን ብዙዎች ነን፡፡ አብዛኞቻችን በልዩ ልዩ ችግሮች ሰላሳዎቹ እና አርባዎች መጀመሪያ ላይ የጋብቻን ሥርዓት እንፈጽማለን ከዚህም የተነሳ ድንግልናችንን ጠብቀን መቆየት ይሳነናል፡፡ ይህ በእርግጥ ድንግልናን ላለማጽናት እንደምክንያት ሆኖብናል ብለን እኛ እንጥቀሰው እንጂ በእውነት ስንመለከተው ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

    ምክንያቱም ድንግልናን በዕድሜ ገድበን እስከዚህ ድረስ መቆየት አለበት የምንለው ተራ ነገር ሳይሆን ክቡር እና እግዚአብሔርን ስለመፍራታችን በስተመጨረሻው ክብር የምናገኝበት የመለየታችን ውጤት ነው፡፡ እዚህ ላይ ላንዘነጋው የሚገባው የምንኩስና እና የብእትውና የደናግላንን ኑሮ ነው፤ እኛ እስክናገባ ድረስ መጠበቅ የተሳነንን ድንግልና የሕይወት ፍጻሜያቸው ድረስ የክርስቶስ ሙሽራ ሆነው ይኖሩ ዘንድ የጨከኑ ከጠላት በሚመጣባቸው ፍላጻ ሳይሸበሩ ከአርያም የምትላክላቸውን የእግዚአብሔርን የማዳን እጅ ተስፋ እያደረጉ የጸኑ ቅዱሳን በዘመናችንም በየገዳማቱ አሉ፡፡ በረከታቸው ይደርብን፡፡ አሜን
    ድንግልናን የምናጣበት ሌላው ምክንያት ዕውቀት የማጣት ችግር ነው፡፡ ከደቂቀ ነብያት አንዱ የሆነው ነብየ እግዚአብሔር ሆሴ እንዲህ ብሏል፡-" ሕዝቤ እውቀትን ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለው፤ የአምላክህን ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ፡፡"ሆሴ4፡6-7 ተመልከቱ ሰው እግዚአብሔርን የሚያውቅበት የእምነት እውቀት ከሌለው እንዲሁ ታስራ እንደ ተፈታች ጥጃ ወደዚያ ወደዚህ እያለ የሚኖር ነው የሚሆነው፡፡ 

    ከቅዱሱ ጋብቻ በፊት የሚደረግ ማንኛውም የግብረ ሥጋ ግንኙነት ዝሙት ይባላል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ተግባርን የፈጸመ ሰው በድንጋይ ተወግሮ ከመገደል እና በእሳት ተቃጥሎ ቅጣት የሚደርስበት ከመሆኑም በላይ እግዚአብሔርንም መንግስቱንም የሚያሳጣ እንደሆነ ያስተምረናል፡፡ ጌታችን ዝሙት ከልብ የሚወጣ እንደሆነ፡- "ከልብ ክፉ አሳብ፤መግደል፤ምንዝርነት፤ዝሙት፤መስረቅ፤በውሸት መመስከር፤ስድብ ይወጣሉና፡፡" ማቴ15፡19 በማለት እጅን ስለመታጠብ ስላለመታጠብ ለጨነቃቸው ፈርሳውያን አስተምሯቸዋል፡፡

    ዝሙት ከጣኦት እና ከእርኩሰት ጋር ከእኛ ሕይወት ሊርቅ የሚገባው ክፉ ግብር ነው፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ከአሕዛብነት ወደ እግዚአብሔር ለዞሩት(ለተመለሱት) ሕዝቦች ሲመክር እንዲህ ብሏል፡- "ነገር ግን ከጣዖት ርኩሰትና ከዝሙት ከታነቀም ከደምም ይርቁ ዘንድ እንድንጽፍላቸው እቆርጣለው፡፡"ሐዋ15፡19 ሚያፈርስ መሆኑን ከዚህም በላይ የከፋና የአግዚአብሔር ቤት የሆነ ሰውነታችንን የሚያፈርስ እንደሆነ እና ከዚህ መራቅ እንዳለብን ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጽ፡-" ከዝሙት ሽሹ ፡፡ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ዝሙትን የሚሰራ ሲገልጽ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሰራል፡፡ ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ፡፡" 1ቆሮ6፡18-19፡20 እርሱን እንድናከብር ይርዳን፡፡

    አንዳንድ ጊዜ ክፉ ወሬ እና በቁልምጫ የሚያታልሉ ምክሮች በዲያብሎስ ተዘጋጅተው በጓደኞቻችን ሊተገበሩ ይችላሉ፤ ድንግል መሆናችንን የሚያውቀው ዲያብሎስ ውሃ አጣጫችን በምናደርገው ወይም በምናደርጋት ክፉ ምክሮችን እንዲህ በማለት ሊያቀርብልን ይችላል፡"ምን ችግር አለው?" ፤ "መጋባታችን አይቀርም አይደል?" ፤ "እንዴ እነ እገሌን አታያቸውም" ፤" ካለፈጸምን እንድንጋባ አልፈልግም" ፤ "ማየት ማመን ነው" ፤ "ተጋብተን በግንኙነት ካልተጣጣምን ከምነፋታ አሁን እንሞክር" ፤ "ድካማችንን እርሱ ያውቃል" ፤ "ወደ ሌላው(ዋ) ከምሄድ አይሻልም?"፤ "የእኔ ቆንጆ ገና ሳይህ(ሽ) ይነሳሳብኛል"... ብዙ የብዙ በዙ የጠላት የሽንገላ እና የማጥመጃ የክፋት መረቦችን ማንሳት ይቻላል፤ ይሁንና እኛ ምን እንደምንባባል ለራሳችን ልተወውና ለዚህ ሁሉ መፍትሄው የእምነት እውቀት ነው ለዚህም እንዲህ ይለናል ሕያው ቃሉ፡-" በቀረውስ በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ፡፡ የዲያብሎስን ሽንገላ ትቃወሙ ዘንድ እንዲቻላችሁ የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ ልበሱ፡፡" ኤፌ6፡11 

    አሁን በዘመናችን የከፋው ችግር የዲያብሎስን የሽንገላ ከንፈር እንሰማ የሚለው ሐሳብን እና የቤተክርስቲያናችንንም ስርዓት እንፈጽም የሚሉ ሁለት ተቃራኒ ሐሳቦችን ለማስታረቅ የመሞከር አባዜ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእውነት ስለ ሕሊናችን ሳይሆን ስለ ሰዎች፤ ስለ ሰማያዊው ክብር ሳይሆን ስለ ምድራዊው ክብር፤ ስለመንፈሳዊው ሳይሆን ስለ ስሜታችን ብቻ የምንኖረው እንሰሳዊ ባህርያችን እጅግ ስለተቆጣጠረን የሚታይብን ችግር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ስለ እግዚአብሔር የምናስብበትን መንፈሳዊ ባህሪያችንን አጥተን ሥጋውያን ብቻ ስለሆንን እንደ አሕዛብ አንዳንዴም አሕዛብ እንኳን የማይደፍሩትን የእግዚአብሔርን ቤት አወቅኩሽ ናቅሁሽ እንደሚባለው ሆኖብን በሚያሳዝን ሕይወት ረዝሙን የትዳር ሕይወት የገነባን መስሎን በማፍረስ እንጀምራለን ትውልዱንም መረን ትውልድ እንዲሆን እናደርጋለን፡፡

    መቼም ዓይን የማያሳየው ምንም ነገር የለም፤ እናንተም ታዝባችሁ ይሆናል ብዬ እገምታለው፤ በዚህ ዘመን አደራ ዘመኑን ሳይሆን ዘመነኞቹን ለመውቀስ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ምክንያቱም ዘመን የባለቤቱ የእግዚአብሔር ነውና ዘመንሁሉ በጎ ነው፡፡ ነገር ግን በጎውን ዘመን ለማየት የሚፈልግ በጎ አድራጊ የጠፋበት ዘመን እየሆነ ስለመጣ ነው "በዚህ ዘመን" ብዬ እንድነሳ የወደድኩት ይሁንና በልዩ ልዩ ምክንያት በራሳቸው ፍቃድ ድንግልናቸውን ያጡ ነገር ግን እንደ ድንግል ሆነው በተክሊል ሲጋቡ አንዳች የማይሰማቸው ደፋሮች፤የሥጋቸውን ስሜት እንጂ የህሊናቸውን ድምጽ መስማት የማይፈልጉ ገንዘብ ያወራቸው አሰናካዮች ፤ ከደብር ደብር እየተሸለከለኩ ቅዱሱን ጋብቻ ያረከሱ፤ የዋሃንን ለማሰናከል ቀን ከሌት የዲያብሎስ አበጋዝ የሆኑ ዲያቆናት ሰባክያን ዘማርያን እንደ አሸን በዝተዋል፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን ወገኖች ወደ ልባቸው ይመልስልን፡፡ 

    ወዳጆቼ ሁለት ሚስት የነበረው በተክሊል አግብቷል፤ ነፍሰጡር ሆና በተክሊል አግብታለች፤ ልጆቹ እያለቀሱበት በተክሊል አግብቷል፤ ከአንድ እና ከሦስት ሴቶች ጋር ኣስፈላጊ ሩካቤ ሥጋ ፈጽሞ እንደ ንጹሕ ዲያቆን ነኝ በሚል ታፔላ በተክሊል አግብቷል፤ ሚስቱ ቤተክርስቲያን ድረስ መጥታ እየጮኸች ዕብድ ናት ብሎ እስመስክሮባት በተክሊል አግብቷል፤ ለዚህ ሁሉ ግን ተጠያቂው እናት ቤተክርስቲያን ሳትሆን አድራጊዎቹ እኛው ነን፤ በዚህም ላይ በድፍረት ሥርዓቱ ይስተካከል ስንል ትንሽ አፈሬታ የሌለን ከንቱዎች መሆናችን ያሳዝናል፡፡ 

    አሁንም በዚህ ጎዳና ተጉዘን ያገባን ምዕመናን በተለይ አገልጋዮች ተፋቱ አልላችሁም ግን በይፋ ሳይገባን ተክሊል አድርገናልና በቁርባን ሥርዓት ጋብቻችንን እናት ቤተክርስቲያን ሆይ እንድንፈጽም አድርጊን ብላችሁ ንሰሐ ግቡ፡፡ በዝግጅት ላይ ያላችሁ ግን ድንግልና ከሌላችሁ እባካችሁ የሚያቃጥለው አክሊል ይቅርባችሁና በክብር የቁርባኑን ሥርዓት በመፈጸም እግዚአብሔርን አክብሩ፡፡ 
    ስለድንግልና የሊቃውንት አባቶቻችን አስተምህሮ እንዲህ ይለናል፡- "ድንግልናውን ከተሳለ በኋላ ማግባት ኀፍረት ነው፡፡ዕንቆራ18 ድንግልናውን ይጠብቅ ዘንድ የተሳለ ሁሉ ፈቃዱን ይፈጽም፡፡ ባይፈጽም ግን ፍርዱ ሁለት(ሚስት) ሴቶች እንዳገባ ይሆናል፡፡ የተናገርነውም ቃል ይህ ነው፡፡ መጀመሪያው ግቢ(ትዳር) በአንዲት ሴት የሚሆነው ነውና፡፡ ከሌላይቱ ጋር የምትሆነው ሁለተኛ ግቢ ግን ከፊተኛይቱ ታንሳለችና ለዚች የማስተስረያ ያድርጉ እንጂ ተክሊል እንዳይደርስላት በሕግ ተጻፈ፡፡" ፍት.ነገ.አን.24፡834 ምን አልባት ግልጽ ላልሆነላችሁ ወዳጆቼ አባቶቻችን ሊሉ የፈለጉት ሁለት ዓይነት የቅዱስ ጋብቻ የአፈጻጸም ሥርዓት እንዳለ ነው፡፡ ይኸውም 1ኛ. ለደናግላን የሚፈጸም የተክሊል ሥርዓት 2ኛ. ድንግልና ለሌላቸው የሚደረግላቸው የቁርባን ሥርዓት እንዳለ ለመግለጽ ሁለቱንም ከእነ ሥርዓት ልዩነተቸው በሚያምርና በተዋበ የነገረ መለኮት እውቀት ገልጸውታል፡፡ ቤቱን በመፍራት እግዚአብሔርን በእውነት በማምለክ ያጸናን ዘንድ ቅዱስ ፍቃዱ ይሁን፡፡

                                                          ምሥጢረ ተክሊል ክፍል ስምንት 

    ወዳጆቼ ነብዩ ዕንባቆም "እግዚአብሔር ግን በተቀደሰ መቅደሱ አለ፤ምድርም ሁሉ በፊቱ ዝም ትበል"ት.ዕን.2፡20 እንዳለ እኛ ዝም ብለን እርሱ እንዲናገረን ልባችንን ሐሳባችንን እንሰበስብ ዘንድ ኃይሉን ቢሰጠን ክፍል ስድስት ላይ የቅድመ ጋብቻ መስፈርቶች ብለን በክፍል ሰባትም ሁለተኛውን መስፈርት አንስተን እዚህ ክፍል ስምንት ላይ ደርሰናል፡፡ ከምንም በላይ በቤተመቅደስ ሰውነታችን ያለውን ጌታ እንድናይ እና ዝም ብለን እርሱ የሚያስተምረንንን እንድንሰማ እና እንድናደርግ ሁላችንን ይርዳን፡፡ አሜን

    3. ከመጠን በላይ የዕድሜ መበላለጥ ሊኖር አይገባም፡፡

    ስንዱዋ እመቤት ቅድስት ቤተክርስቲያን ፤ የሁላችን አሳዳጊና መንግስቱን የምንወርስባት የክርስቶስ አካል እንደመሆኗ መጠን በዚህም ዙሪያ ቢሆን አስቀድማ ሕግን ሰርታልናለች፡፡ መንፈሳዊው ሕጓ እንዲህ ይላል፡-" ከ15 ዓመት በላይ ዕድሜ (ቆንጆ) ከ18 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው ድንግል(ጎበዝ) ተጫጭተው ጋብቻን መፈጸም ይችላሉ፤ በውዴታ የሰጡት ቃላቸው ይጸናል፡፡ ከዚህ ዕድሜ በታች ቢሆኑ ግን አይጸናም፤..." መጽሐፈ ተክሊል ገጽ 75-76 ... ተመልከቱ የሥርዓቷን ማማር በዚህ ሰማያዊ ሥርዓት ሰማያዊውን ምሥጢረ ተክሊል ፈጽመን የጌታችንን ሥጋና ደም በመቀበል አትመን አገራችን በሰማይ እንደሆነ መስክረን፤ መዳናችንን እንፈጽማለን፡፡ ክብር ለአምላካችን ይሁን፡፡

    አንዳንድ ጊዜ በገጠሪቷ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሀብትን ለመቀራመት በማሰብ፤ እገሌ የገሊት ዘርን ነው የሚያገባው፤ እገሊት የገሌን ዘር ነው የምታገባው፤ የሚሉት አላስፈላጊ ነገሮችን በማስቀደም ሊቀድም የሚገባውን እግዚአብሔርን በኑሯቸው ሳያስቀድሙ እንዲኖሩ የተገደዱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ሁለቱ አንድ ሥጋ የማይሆኑበትን ያልተቀደሰ ጋብቻ በግድ ልጆች እንዲፈጽሙ መደረጉ ደግሞ እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ሰውን ደግሞ የሚያሳፍር ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያዝነው በቅዱሳኑ በኩል የሰጠውን ትህዛዝ ባለመፈጸማችን ሲሆን ለሰው ደግሞ የሚያሳፍረው "እንዴት ከአባቷ ጋር ትጋባለች? እርሷ አንድ ፍሬ እርሱ የሽበት ዘውድ የደፋበት!" የሚለውን ድምጽ መስማታችን ነው፡፡

    በከተማችንም አልፎ አልፎ ይታያል ብዙ ጊዜ ወንድ ከሆነ ገንዘቧን በማየት ከ10 ዓመት በላይ ከምትበልጠው ሴት ጋር ቅዱሱን ጋብቻ ይፈጽማል ይህም ሕጉን አለመፈጸም ነው፤ አባቶቻችን ካወጡልን ሕግ የምንማረው የዕድሜውን ጣሪያ ባያስቀምጡትም በመካከላቸው ግን ሊኖር ስለሚገባው የሦስት ዓመት ልዩነት ገልጠውታል፡- "ሴት 15 ወንድ 18" ይህ ደግሞ ከስነ ልቦና ፤ ከጤና እና ከመንፈሳዊው መስተጋብር አንጻር ለሁላችን የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ ሆኖ ሊታይ አይገባም፡፡ ሴቶችም ከዕድሜ አቻዎቻቸው ጋር ይህንን ቅዱስ ጋብቻ ሊፈጽሙ ሲገባ በተቃራኒው በዕድሜ ከማይመጥኗቸው አባቶቻቸው ሊሆኑ ከሚችሉ ወንዶች ጋር ቅዱሱን ጋብቻ ይፈጽማሉ፡፡ 
    ይህ ጉዳት አለው ወይ ?ዋናው ፍቅር አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄ እንደምታነሱ አልጠራጠርም ልክ ነው ዋናው ፍቅር ነው፤ ችግሩ ግን በዕድሜ የመበላለጣችን ጉዳይ የተጋነነ ከሆነ በስነ ልቦናችን ጉዳት ሊያመጣብን ይችላል፡- ለምሳሌ ከባለቤታችን ጋር እየሄድን ባለንበት ወቅት ወይም ደግሞ በገብያ መሀል ባለቤታችንን የተመለከተች እንስት አባትሽ ነው? ብላ ብትጠይቀን? ምን ይሰማናል? በስነ ልቦና ወደድንም ጠላንም መጎዳታችን የማይቀር ነው፡፡ አንዳንዴም እኮ የሰው ምላስ ይሰብራል፤ ምን ባል አጥታ ነው?ሚስት አጥቶ ነው?ሀብታም እና ተዋቂ ስለሆነች ነው፤ሀብታም እና አዋቂ ስለሆነ ነው፤የሚሉት ወሬዎችን በእኛ ዙሪያ ሲወሩ ስንሰማ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ጉዳት ይደርስብናል፡፡ ከዚህ ይልቅ በተወሰነው የዕድሜ ልዩነት የትዳር አጋሮቻችንን መምረጡ ሳይሻል አይቀርም ምክንያቱም አንድም ሕጉን እንፈጽማለን፤አንድም በስሜትም ይሁን በሐሳብ ለመግባባት አንቸገርም፡፡
    ዕድሜን በተመለከተ የቤተክርስቲያናችን የሕግ መጽሐፍ የሆነውን ፍተሐ ነገስትን ስናነብ እንዲህ ይላል ፡- "ስለ ጋብቻ 13ኛው ክፍል ዕድሜዋ ከስድሳ ዘመን ያለፈውን ማግባት እንዳይገባ ይናገራል" ፍት.ነገ.አን.24 ቁጥ.864 ሀገራችንም ሆነች የዓለም ሕዝብ የሚስማማበት ሀሳብ መሆኑን በመፈክር ደረጃም ቢሆን የምንሰማው ሐሳብ አለ ይኸውም "ያለ አቻ ጋብቻ" ይህ እንዴት ዓይነት ሐሳብ እንደሆነ ለእናንተ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆናል፡፡ ይሁንና የዕድሜያችንን ቁጥር እናውቀዋለንና በዕድሜ አቻ እና የተጋነነ ዕድሜ ልዩነት ከሌለን አጋሮቻቸችን ጋር የቅዱሱን ጋብቻ ሕይወት ከምንጭ እንደሚፈስ ኩልል እያለም እንደሚወርድ ፍቅራችንን እየጠጣን እንረካ ዘንድ የፍቅር ባለቤት እግዚአብሔር ትዳራችንን ይባርክ፡፡

    4. በሁለት ጥንዶች መካከል እውነተኛ መፈቃቀድ ሊኖር ይገባል፡፡

    መፈቃቀድ ማለት መዋደድ ማለት አይደልም፤ ምክንያቱም ሰው የሚወደውን ሁሉ አያገባምና፤ ለማግባት ግን መዋደድ ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ ለዚህም ነው አባቶቻችን በሥርዓተ ተክሊሉ ላይ እርስ በእርሳቸው ተፈቃቅደው ቅዱሱን ጋብቻ ለመፈጸም የወደዱትን ጥንዶች ቃል ሲያስገቧቸው "ወድጄ ፈቅጄ እገሌን(እገሊትን) ተቀብዬዋለሁ(ተቀብያታለሁ)" የሚያስብሏቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በይሉኝታ ሴቷ ሳትፈቅድ ወይም ወንዱ ሳይፈቅድ በቤተሰብ ተጽህኖ እሺ ብላ ወይም እሺ ብሎ ይህንን ስርዓት ልትፈጽም ወይም ሊፈጽም ትችላለች(ይችላል) ፤ ጋብቻ ደግሞ ብዙ ትግል ያለበት የሕይወት ጦር ሜዳ ነው፤ ድል ከነሱበት የሚደሰቱበት ድል ከተነሱ ደግሞ የሚያዝኑበት ይህም በመሆኑ ገና የትግሉ ማስጀመሪያ ፊሽካው እንደተነፋ ከጨዋታው ውጪ ይሆናሉ ፍቺውንም ያለፍቃዳቸው ይጠይቃሉ፤ በዚህ ዓይነቱ ያለመፈቃቀድ ግንኙነት የብዙዎች ትዳር መሰረቱ ተናውጽዋል፤ሲቀጥልም ፈርሷል እግዚአብሔር ከዚህ ሁላችንን ይጠብቀን፡፡

    ከላይ ያነሳነው የሕግ መጽሐፍ ስለዚህም ጉዳይ እንዲህ ይለናል፡- "ከእነርሱም ብልህ አባቱ ወይም ሞግዚት ወይም ሌሎች (ዘመዶቹ) ገና ትንሽ ሳለ መልካም ደምግባት ካላት ወይም ስለ ገንዘብዋ ብዛት ወይም ስለ ዘመዶቿ ክብር ወይም ስለ ጌጧ ወይም ስለ ልባምነቷ እንዳታመልጠው ወድዶ ሌላውን ስለ መቅደም የሚያጋባው አለ፡፡" ፍት.ነገ.አን.24.ቁጥ.839  እዚህ ላይ ቤተሰቦቻችን የሚያመጡልን የትዳር አጋር ሁሉ መጥፎ ነው ማለት እንዳልሆነ ሁላችንም እንገነዘባለን ይሁንና ፍቃዳችን ከፍቃድዋ ወይም ከፍቃዱ ጋር አንድ እስካልሆነ ድረስ አንድ ሥጋ ፤አንድ አካል ይሆናሉ የሚለውን ሰማያዊ መመሪያ አናሟላምና ከወዲሁ ፍቃዳችንን መመርመር በፍቃድ አንድ መሆንና የእግዚአብሔርን ፍቃድ ማስቀደም ለትዳራችን መባረክ ከፍተኛ አስተዋጽዎ ያደርጋል፡፡ መክ2፡25

    ወዳጆቼ የእርስ በእርስ ፍቃዳችን አንድ መሆኑ በመጀመሪያ የሚጠቅመው ራሳችንን ነው፤ ምክንያቱም የእኛ ፍቃድ መንፈሳዊነት ሆኖ የእኛ የሆነው አካላችን ግን በዚህ ፍቃዱ የተለየና ዘመናዊ ወይም ዓለማዊ ከሆነ ፍቃዳችን አንድ እስከሚሆን ድረስ እስከመለያየት የሚያደርሱ ብዙ ችግሮች ይገጥሙናል፤ከፍ ካለም ልንለያይ እንችላለን፡፡ ይህም በመሆኑ አስቀድመን ፍቃዳችንን እግዚአብሔር አንድ እንዲያደርገው በጸሎት በመትጋት ልናሳስብ እና ልንተጋ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር በተለይ በሰማያዊው ሕይወታችን ፍቃዳችን አንድ ይሆን ዘንድ ይወዳል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን፡-"አሳቤ እንደ አሳባችሁ መንገዳችሁም እንደ መንገዴ አይደለምና ይላል እግዚአብሔር ፡፡" የተባለው ትንቢት በእኛ ሕይወት ይፈጸማል፡፡
    5. የአእምሮም ሆነ የአካላዊ ብቃት ሊኖረን ይገባል

    አእምሮአዊው ብቃት ሲባል በተለይ በትዳር ዙሪያ ባሉት ዕውቀቶች እንዲሁም ወደ ፊት በሚገጥሙን ተግዳሮቶች የምናሸንፍበትን መንገድ የምንረዳበት ዐቅም ነው፡፡ እርግጥ ብቃት ሁሉ ከላይ ከሰጪው ነው፡፡ "ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው እንጂ፤በገዛ እጃችን እንደሚሆን አንዳችን እንኳ ልናስብ ራሳችን የበቃን አይደለንም፤..."2ቆሮ3፡5 ስለዚህም በሁሉ ብቃትን ይሰጠን ዘንድ በመለመን አእምሮአዊ ብቃታችንን በማዳራጀት ራሳችንን ብቁ በማድረግ ለቅዱሱ ጋብቻ ልንበቃ ይገባል፡፡ አካላዊም ሲባል የጤና እና የሥነ ልቦና በቂ የሆነ ዝግጅት ሊኖረን ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ በምናደርገው ሩካቤ ሳይቀር በመቸገር አጋራችንን ወዳልተፈለገ ኃጢአት ልንመራው እንችላለንና በዚህ ጉዳይ በቂ የሆነ የአእምሮም ሆነ የአካላዊ ብቃት ላይ ስንደርስ የምንጀምረው ቅዱሱ ጋብቻ በፍሬዎቻችንም ሳይቀር ያማረና ደስ የሚያሰኝ ኑሮን እንድንኖር እንሆናለን፡፡

    የአእምሮ ብቃታችን በተለይ እግዚአብሔርን የማወቅ እርከን ላይ ከፍ የሚያደርገን ከሆነ ከጥፋት ድነን ሌሎችንም የምናድን ቤተሰባችንን እንደፍቃዱ የምናስተዳድር ታማኝ አገልጋዮች ለመሆን እንችላለን፡፡ሆሴ 4፡6 በአእምሮ ብቃት ውስጥ የኢኮኖሚው ብቃትንም ማየት እንችላለን ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉ ሆነው ይህንን ቅዱስ ጋብቻ መፈጸማቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ እንዲኖሩ ስለሚያደርጋቸው በአካላዊውም ሆነ በአእምሮአዊው እንዲሁም በኢኮኖሚያዊው በቂ የሆነ የብቃት ደረጃ ላይ ሊሆኑ ይገባል፡፡
    6. የንስሐ አባት ምስክርነት ያስፈልጋል፡፡
    ማንኛውም አማኝ በሥርዓተ ተክሊልም ይሁን በሥርዓተ ቁርባን ምሥጢረ ተክሊልን ለመፈጸም ሲዘጋጅ የንሰሐ አባቱን አማክሮ እና ምስክርነትን ሲይዝ ብቻ ነው በዚህ ቅዱስ ጋብቻ ሊሳተፍ የሚችለው፤ በመሆኑም ስለ ቅዱሱ ጋብቻ አባቶችን በመጀመሪያ ሊያማክሩ እና ከእነርሱ በሚያገኙት መልካም ምክር ጋብቻቸውን ሊመሰርቱ ይገባል ይህ ካልሆነ ግን በዘፈቀደ የምናደርገው ጋብቻ እግዚአብሔር የሌለበት እና በራሳችን የምንመራው ይሆንና ውሉ ይጠፋብናል እንዲህ ከመሆን እርሱ ይጠብቀን፡፡

    አንድ ወንድማችን የተሐድሶ መናፍቃን እምነት ተከታይ ነው ይህ ልጅ የሚያገባት ደግሞ ኦርቶዶክስ ናት ይህ መናፍቅ አባቶችን ቢጠይቅ እሺ እንደማይሉት ስለተገነዘበ ደብርን ቀይሮ ለማግባት ተገደደ ይህም ሆኖ በሄደበት ደብርም አባት አጣ በኋላም ገንዘብ ሰጥቶ "ከመጠምጠም መማር ይቅደም" እንዲሉ ሆዱ አምላኩ የሆነበት አባት ይህንን ልጅ የተክሊል ሥርዓት እንዲፈጽም አደረጉ፡፡ እንዲህ ልናይ እና ልንሰማ እንችላለን ይህን በተሳሳተ መልኩ ከምንፈጽም እና ለሰዎች ስንል ብቻ አክሊሉን ከምናጠልቅ ገብቶን ተረድተን እና አባቶችን ጠይቀን አማክረን ማግባቱ ለሕሊናችን እረፍት እናገኝበታለን፡፡

            ምሥጢረ ተክሊል  ክፍል ዘጠኝ
               
    የምትናፍቁኝ እና የምናፍቃችሁ ወዳጆቼ እንደምን ቆያችሁ የወደደን እስከ ሞት ድረስ ያፈቀረን የፍቅር መምህራችን እግዚአብሔር ስለማይነገር ስጦታው ሁሉ ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤ የአምላክ እናት ቤዛዊተ ዓለም ድንግል ማርያም በትውልዱ ሁሉ አንደበት ምስጋና ይድረሳት፤ ለስሙ ለተለዩ ቅዱሳን፤ ለስሙ ለሞት ተላልፈው ለተሰጡ ሰማእታት፤ መናፍቃንን ድል ለነሱ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፤ ስለ ስሙ ለተሰደዱ ጻድቃን ምስጋና ይሁን፡፡ አሜን፡፡

    ቅዱስ ጋብቻ አንድ ለአንድ የሚፈጸም ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ኤፌ5፡32 አንድ ለአንድ ብቻ በቅዱስ ጋብቻ ልንፈጽም እንደሚገባ ሲገልጽ፡- "ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት፡፡" 1ቆሮ7፡2 ይህንን ሰማያዊ ትሕዛዝ ስንመለከተው ባሎች ወይም ሚስቶች የሚል ሐሳብ አለመኖሩ አንድ ለአንድ የሆነውን ጋብቻ ብቻ መፈጸም እንዳለብን ያስገነዝበናል፡፡ ከአንድ በላይ ማግባት አለመፈቀዱን ለመረዳት ሌላው የመጀመሪያዎቹ አዳምና ሔዋን ያደረጉትን ልዩ ጋብቻ ማየቱ በቂ ነው፡፡ዘፍ 2፡23
    በቤተክርስቲያናችን ሁለት ዓይነት የጋብቻ ሥርዓትን በሐይማኖት ለጸኑት፤ቀኖናቸውን ለፈጸሙት እና ስርዓቱን አክብረው ተዘጋጅተው በፍቃዳቸው ጋብቻን ለመፈጸም ለቀረቡት ሁሉ ትፈጽማለች፡፡ "የባል እና የሚስት ፍቅር አጥጋቢ ፍሬን ይሰጣል፡፡ " እንዲሉ ይህንን የፍቅር መሰረት ለማጽናት እና በክርስቶስ ዓለትነት ላይ ለመጀመር የምንፈጽመው ቅዱስ ሥርዓት በምሥጢርነቱ ምሥጢረ ተክሊል ፤ በሚደርሰው ጸሎት ጸሎተ ተክሊል በመባል ይታወቃል፡፡ ሁለቱ ዓይነት የጋብቻ ሥርዓቶች የምንላቸው ፡-
    1ኛ. በተክሊል የሚፈጸም እና
    2ኛ. ያለ ተክሊል የሚፈጸም ሥርዓቶች ናቸው፡፡ 

    1ኛ. በተክሊል የሚፈጸም ፡- ይህ በድንግልና ላሉ ጥንዶች የሚፈጸም ሥርዓት ሲሆን ስለ ድንግልናቸው ክብር የሽልማት ምልክት የሆነውን የድል አክሊል ይጭናሉ፡፡ የክብርን ካባ ይለብሳሉ፤በዚህም ሌሎች ድንግልናቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸውና ለዚህ ክብር እንዲበቁ ለማስተማሪያ ትጠቀምባቸዋለች፡፡ ይህ ምሥጢር የሚፈጸመው በተክሊል ነው፡፡ እግዚአብሔር ለዚህ ክብር ሁላችንን ያብቃን፡፡ አሜን
    2ኛ. ያለ ተክሊል የሚፈጸም ፡- ይህ ደግሞ ድንግልናቸውን በፍላጎታቸው በማወቅም ባለማወቅም ያጡ ጥንዶች የሚፈጽሙት ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ ጥንዶች የሚያደርጉት ጋብቻ እንደ ቤትክርስቲያን ስያሜ የማስባን ጋብቻ ይባላል፡፡ ይህ ምሥጢር የሚፈጸመው በቁርባን ነው፡፡

    ሰው እምነቱ ሲላላ ለሥርዓቱ ለሐይማኖቱ ግዴለሽ ይሆናል፤ ነገር ግን እምነታችንን ጠንካራ እንዲያደርግልን መጸለይ ሲገባን በግዴለሽነት የትዳርን ሕይወት በመጀመራችን ስንቶቻችን ነን ትዳራችንን እንደወደድነው፤ እንደተመኘነው ሆኖ በአሁኑ ሰዓት ያላገኘነው? የውስጣችን እምነት ጠንካራ ከሆነ የውጭው ፈተና እኛን አያሸንፈንም፤ ሰልስቱ ደቂቅን እሳቱን እንዳይፈሩ ያደረጋቸው የውስጣቸው የእምነት ጽናት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ጽናት ይስጠን፡፡

    ማንኛውም ሰው ወደ ትዳር ዓለም ከመግባቱክርስቶስ ለቤተክርስቲያን ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ወንድም ራሱን አሳልፎ ለሚስቱ መስጠት ይገባዋል ፤ ሚስትም ፍቃዷን ሁሉ ለባሏ አሳልፋ ልትሰጥ ይገባታል፡፡ እንዲሁም በመጠን ለመኖር እና በግልጽነት ልባቸው አንድ ለመሆን ፍቃደኝነት ያስፈልጋል፡፡ ትዳር በቤተክርስቲያን ትምህርት ከዚህ ቀደም በነበሩት ክፍሎች እንዳየነው ተቋም ነው፤ ቅዱሳን ይወጣሉ፤መሪዎች ይወጣሉ፤ነገስታት ይወጣሉ... ይህ ትውልድ የሚመጣበት ምንጭ ደግሞ መሰረቱ የቀና ሊሆን ይገባል፡፡ ሁላችንም ልናውቀው የሚገባን በዚህ ቅዱስ ጋብቻ ሦስቱ ጉልቻዎችን በማሟላት ትዳራችንን መጀመር እንዳለብን ነው፡፡
    በማንኛውም ጊዜ ከእነዚህ ሦስት ጉልቻዎች አንዱ የሚጎድል ከሆነ ጤናማ የሆነ ትዳርን መምራት እንዳንችል ያደርገናል፡፡ እነዚህም 1. ለመረዳዳት 2. ከዝሙት ለመራቅ 3.ዘር ለመተካት ናቸው፡፡ አንዳንዶች ለመረዳዳት ብቻ በማሰብ ትዳርን ይመሰርታሉ፤አንዳንዶች ልጅ ለመውለድ ብቻ ዕድሜያቸው እንዳያመልጣቸው በማሰብ ትዳር ይመሰርታሉ ታድያ ያሰቡትን መረዳዳት ወይም ልጅ መውለድ ሲያገኙ ትዳራቸውን ያፈርሳሉ፡፡ ቅዱሱ ጋብቻ ግን እስከ ሕይወት ፍጻሜ የምንኖረው በምድር ላይ ያለ ሰማያዊ ኑሮ ነው፡፡

    ሌላው ልንረዳው የሚገባን መረዳዳትን በሁለት መልኩ ማየት እንዳለብን ነው፡፡ ይኸውም የመጀመሪያው ልናስቀድመው የሚገባን ቅዱሱ ጋብቻ ሰማያዊውን ኑሮ የምንኖርበት ሕይወት እንደመሆኑ መጠን በመንፈሳዊ ሕይወት መረዳዳት፡- ለጸሎት፤ ለጾም፤ ለስግደት፤ለምጽዋት፤ለንሰሐ ፤ ሱባኤ ለመግባት፤ቅዱስ ሥጋውን እና ክቡር ደሙን ለመቀበል፤በዓላትን እና ሰንበትን ለማክበር ሙሉ ፍቃደኛነታችን አንድ በመሆን ራሳችንን ቅድመ ዝግጅት አድርገን ወደ ተቀደሰው ጋብቻ ልንገባ ይገባል፡፡ ሌላው በሥጋዊ ሕይወታችንም ቢሆን በጊዜውም ያለጊዜውም ችግሮችን ባለመፍራት እርስ በእርሳችን ለመረዳዳት ከችግራችን በላይ የሆነውን የመፍትሄ ቁልፎች በእጁ የያዘውን እግዚአብሔርን በጋራ ለማምለክ የተዘጋጀን ከሆንን የተባረከው ቅዱስ ጋብቻ ገብቶን ነውና የጀመርነው አንድ ሥጋ እንጂ ወደ ፊት ሁለት አንሆንም፡፡ 

    ሥርዓተ ተክሊል

    ከሰርጉ ቀን አስቀድሞ ከቤተክህነት የተሰጣቸውን(በአሁኑ ከቤተክርስቲያን) ማስረጃ በአቅራቢያቸው ላለው የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ አቅርበው ቃልኪዳናቸውን በቤተክርስቲያን መፈጸም ይገባቸዋል፡፡ በዚሁ ቀን ሙሽራውና ሙሽራይቱ ከነዘመዶቻቸው በቤተክርስቲያን ተገኝተው ለቃል ኪዳን በተሰጠው ሕግ መሠረት የቀለበቱን ሥነ ሥርዓት ይፈጽማሉ፤ በመተጫጨት የሰጡትንም የፈቃድ ቃል በመሐላ ያጸናሉ፡፡ 
    በሠርጉ ቀንም ከሌሊቱ በ9 ሰዓት ሙሽራው ከዘመዶቹ ጋር ሙሽራይቱም ከዘመዶቿ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን ሔደው ሙሽራውና ዘመዶቹ በሰሜናዊ መዓዝን ሙሽራይቱና ዘመዶቿ በደቡባዊው መዓዝን ሥፍራ ሥፍራቸውን ይዘው ይቆማሉ፡፡ ከዚህ በኋላ በምዕራብ በኩል ከመካከለኛ ክፍል ማለት ከቅድስቱ በቤተመቅደስ ፊት ለፊት ካለው ዓውደ ምሕረት ላይ ሊቀዲያቆናቱ ሙሽራውና ሙሽራይቱ ሥርዓተ ተክሊል የሚፈጽሙበትም ምንጣፍ አንጥፎ ለሁለቱ የሚሆን አንድ አግዳሚ ወንበር እንዲሁም አንድ ጠረጴዛ በላዩም ሙሽሮቹ ቃል ኪዳናቸውን የሚፈጽሙበትንና አንድ ሆነው ሥጋውን ደሙን የሚቀበሉበትን ነጭ መጎናጸፊያ የሚቀቡበትን ዘይት የሚቀዳጅዋቸውን አክሊላት ያዘጋጃል፡፡ መጽ.ተክ.ገጽ 76

    ከዚህ በኋላ ሙሽራውና ሙሽራይቱ ሥፍራቸውን ይዘው ይቆማሉ፤ካህናቱም ሥርዓተ ተክሊሉን ይፈጽማሉ፤በመጨረሻም አስቀድሰው ሥጋውን ደሙን ተቀብለው፤ቃል ኪዳናቸውን በሥጋ ወደሙ ያጸናሉ፤ ይፈጽማሉ፤ያለ ቁርባን ግን፤ ተክሊል ተክሊል ሆኖ ሊቆጠር አይችልም፡፡ የጋብቻ አንድነት ካህናት ከሌሉበት፤ ጸሎተ ተክሊል ካልደረሰለት ሊፈጸም አይገባም፡፡ ተክሊልም በደረሰላቸው ጊዜ ሁለቱ አንድ የሚሆኑበትን ቅዱስ ቁርባንን ያቀብሏቸው፡፡ በሥጋ ወደሙ አንድ ይሆናሉና፡፡ መጽ.ተክ.ገጽ 76-77
    ይቆየን... ይቀጥላል ፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ምሥጢረ ተክሊል ምዕራፍ ፫ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top