• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    “እንዲህ ያለ ነገር እግዚአብሔር አያምጣብኝ!” ፩ኛ ነገ ፳፥፫        

     ለኢይዝራኤሉ ሰው ለናቡቴ በሰማርያው ንጉሥ በአክዓብ ቤት (ቤተ መንግሥት) አጠገብ የወይን ቦታ ነበረው። አክዓብም ናቡቴን፦ “ለቤቴ ቅርብ ነውና የተክል ቦታ ይሆነኝ ዘንድ ይህንን የወይን ቦታህን ስጠኝ፥ ከሱ የሚበልጥ ሌላ የወይን ቦታ እሰጥሃለሁ፥ ዋጋውንም ትወድ እንደሆነ የዚህን የወይንህን ቦታ ወርቅ እሰጥሃለሁ፥ የተክል ቦታ ይሁነኝ፤” አለው። “ወይቤሎ ናቡቴ ለአክዓብ ኢያምጽእ ሊተ እግዚአብሔር ከመ አሀብከ ርስተ አበውየ። ናቡቴም አክዓብን የአባቶቼን ርስት እሰጥህ ዘንድ እንዲህ ያለ ነገር (ክፉውን ኅሊና) እግዚአብሔር አያምጣብኝ፤” ሲል መለሰለት፡ ናቡቴ ይኽንን የመለሰው፦ “ምድርም ለእኔ ናትና፥ እናንተም በእኔ ፊት እንግዶችና መጻተኞች ናችሁና ምድርን ለዘለዓለም አትሽጡ።” በሚለው የእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርቶ ነው። ዘሌ ፳፭፥ ፳፫።

              ምርጫው ከሰማዩ፥ ከዘለዓለሙም ንጉሥ ትእዛዝ እና ከምድራዊው ንጉሥ ትእዛዝ መካከል ነው። ናቡቴ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ አንጻር የሚያወዳድረው ወይም የሚያነጻጽረው ምንም ነገር ስለሌለ፦ “እንዲህ ያለውን ክፉ ኅሊና እግዚአብሔር ያርቅልኝ፤” ብሏል። ንጉሡ፦ ሊያሥረው ወይም ሊገርፈው ወይም ሊገድለው እንደሚችል ያውቃል። ነገር ግን እግዚአብሔርን ከሚያሳዝን ይልቅ ንጉሡን አሳዝኖ መታሰርን፥ መገረፍን፥  መገደልን መርጧል። ምክንያቱም ስለ ሃይማኖት በሃይማኖት የሚቀበሉት መከራ ክብርም ሕይወትም እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም የአባቶቹን ርስት አልሸጠም፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ አልጣሰም። “የመንግሥት ትእዛዝ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም፤” ብሎ በቀቢጸ ተስፋ አልተንበረከከም። በሌላ በኵል ደግሞ ንጉሡ “እሰጥሃለሁ፤” ያለው ወርቅና ብር አላጓጓውም። “ስለዚህ ከወርቅና ከዕንቍ ይልቅ ትእዛዝህን ወደድሁ፤” እንደተባለው ሆኖ ተገኘ። መዝ ፻፲፰፥ ፻፳፯።

              ንጉሡ አክዓብ ወደ ድሀው ርስት እንዲመለከት ያደረገው ስግብግብነቱ ነው። ብዙ ያላቸው ሰዎች ላይበሉት፥ ነገ ጥለውት ሊሄዱ ዓይናቸው አይጠግብም። “አንተ ሰነፍ! በዚች ሌሊት ነፍስህን ከሥጋህ ለይተው ይወስዷታል፥ እንግዲህ ያጠራቀምኸው ለማን ይሆናል፤” ተብሎ በወንጌል የተጻፈውን ንቀውና ጠቅጥቀው ድሀውን ከቤቱ፥ ከርስቱ ይነቅሉታል። “መሬት የመንግሥት ነው፤” እያሉ “ምድርም ለእኔ ናት፤” ያለውን እግዚአብሔርን ይገዳደሩታል። እግዚአብሔር “የእኔ ነው፤” ቢል የእርሱ ስለሆነ ነው። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ፤” ይላልና። ዘፍ ፩፥፩። ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ ስለሆነ “መሬት የመንግሥቴ ነው፤” አላለም። ሰማዩም ምድሩም የእግዚአብሔር መሆኑን ስለሚያውቅ፦ “ምድር በሞላዋ የእግዚአብሔር ናት፤” ብሏል። መዝ ፳፫፥፩።

              እግዚአብሔር የነገረን፥ ካለን ብዙ ነገር ከፍለን ለድሆች እንድናካፍል እንጂ ያለቻቸውን ትንሽ ነገር እንድንነጥቅ አይደለም። ለድሆች በማካፈላችንም በረከት ይትረፈረፍልናል። ዘዳ ፲፭፥፩-፲፮። ድሃው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ቢሸጠው እንኳ በኢዮቤልዩ ሕግ ወደ ርስቱ እንዲመለስ ታዟል። ዘሌ ፳፭፥፳፭-፴። ኢዮቤልዩ ከአርባ ዘጠኝ ዓመት በኋላ የሚመጣው ሃምሣኛው ዓመት ነው። በዓለ ሃምሣ ይባላል፥ ብዙ የበግ መሥዋዕት የሚሠዋበት ዕለት በመሆኑ የበግ ጠቦት ተብሎም ይተረጐማል። ቀንደ መለከት የሚነፋበት በዓል በመሆኑም ቀንደ መለከት እየተባለም ይጠራል። በዚህ ዘመን ለባሪያዎች ነፃነት ይሰጣል፥ ርስት የተያዘባቸው ሰዎች ወደ ርስታቸው ይመለሳሉ፥ ምድሪቱም በዚህ ዘመን አትታረስም። (ታርፋለች)።

              ናቡቴ ቸግሮት ልሽጥ፥ ልለውጥ ብሎ የተነሣ ሰው አይደለም። እስከ ችግሩ የአባቶቹን ርስት አክብሮ አስከብሮ ለመኖር የመረጠ ሰው ነው። ነገር ግን በቀላጤ ሳይሆን በቀጥታ መጥቶ ንጉሡ ሊያስገድደው ሞክሯል። ናቡቴ ከፍ ብሎ ለእግዚአብሔር ሕግ፥ ዝቅ ብሎ ለኅሊናው ተገዥ ስለሆነ አልተቀበለውም። አንድም በኅሊናው የተቀረጸ፥ በልቡናውም በመዓልትና በሌሊት የሚያሰላስለው የእግዚአብሔር ሕግ ጠበቀው። ሰውን ሰው የሚያሰኘው እንዲህ ኅሊናው ሲገዛው ነው። ኅሊናቸውን ለሸጡ ሰዎች ግን ይህ ሰለማይገባቸው፥ ወይም እንዲገባቸው ስለማይፈልጉ ኅሊና ባላቸው ሰዎች ይበሳጫሉ። አክዓብ አዝኖ ወደ ቤቱ የተመለሰው፥ በብስጭት ብዛት ፊቱን ተከናንቦ የተኛው፥ እህል ውኃም አልቀምስም ያለው ለዚህ ነው። ግፈኞች ድሀውን ካላስለቀሱ ደስታ የላቸውም። እንደ ሙዚቃ የሚያዝናናቸው የድሀው ጩኸት ነው። ጠቢቡ ሰለሞን፦ “ድሃውን በግድ አትበለው፥ ድሃ ነውና፤ ችግረኛውንም በበር አትግፋው፥ እግዚአብሔር ፍርዱን ይፈርድለታልና።” ያለው ለድሆች መራራት እንጂ በድሆች ላይ መጨከን ስለማይገባ ነው። ምሳ ፳፪፥፳፪። ዛሬ ሥልጣንም፥ ጉልበትም፥ ገንዘብም ስላለን የድሀውን ቤት ያውም በክረምት በላዩ ላይ ልናፈርስበት፥ የእርሻ መሬቱንም ልንነጥቀው እንችላለን፥ ነገር ግን ሰው ዝም ቢል እግዚአብሔር ዝም አይልም። ትናንት፦ “መሬት ላራሹ፥ የከተማ ትርፍ ቤቶች ለድሃው፤” እንዳልተባለ፥ ድሆችን ያለ አማራጭ ሜዳ ላይ መበተን በእውነት ስለ እውነት ግፍ ነው። አክዓብ እንኳ ተለዋጭ መሬት ወይም በቂ ብርና ወርቅ ልስጥ ብሏል።

              የግፈኛው የአክዓብ ሚስት ኤልዛቤል ወደ ንጉሡ ገብታ “እህል የማትበላው ምን ሆነህ ነው? የሚያሳዝንህስ ምንድር ነው?” አለችው። ይህች ሴት ባሏ አክዓብ በኣል የተባለውን ጣኦት እንዲያመልክ የገፋፋችው ናት። ፩ኛ ነገ ፳፥፳፬። የእግዚአብሔርን ነቢያት ትገድል፥ አራት መቶ ሃምሣ የሚሆኑ የጣኦቱን ነቢያት ትቀልብ ነበር። ፩ኛ ነገ ፲፰፥፩-፲፱። ነቢዩ ኤልያስንም ለመግደል አሳድዳዋለች። ፩ኛ ነገ ፲፱፥፩-፪። ከደጋግ ሰዎች ጀርባ ደጋግ ሚስቶች እንዳሉ ሁሉ ከክፉ ሰዎች ጀርባም ክፉ ሚስቶች አሉ። ንጉሡ አክዓብ ሚስቱ ኤልዛቤል ለጠየቀችው ጥያቄ፦ “የኢይዝራኤል ሰው ናቡቴን የወይንህን ቦታ በዋጋ ሽጥልኝ፥ ትወድም እንደሆነ ስለሱ ፈንታ ሌላ እሰጥሃለሁ ብዬ ብናገረው የአባቶቼን ርስት አልሰጥህም ብሎኛልና ስለዚህ ነው፤” አላት። በዚህን ጊዜ፦ “ዛሬ እንዲህ የምታደርግ አንተ የእስራኤል ንጉሣቸው ነህን? አሁንም ተነሥተህ እህል ብላ፥ ራስህንም አፅና፥ ልቡናህንም ደስ ይበለው፥ የኢይዝራኤል ሰው የናቡቴን ቦታ እኔ እሰጥሃለሁ፤” ብላ ለበቀል አነሣሣችው። የናቡቴን መሬቱንም ነፍሱንም ልትነጥቀው ተዘጋጀች። ለባሏ እህል አብልታ ናቡቴን ግን አፈር ልታበላው ተቅበዘበዘች። የሚገባው፦ “እኛ ብዙ አለን፥ ይኽ ድሃ ምን አደረገህ?” ማለት ነበር። ዛሬም ሰውን ለበቀል የሚያነሣሱ ሰዎች ብዙ ናቸው። እርሷ “የአንተ ንጉሥነት ለመቼ ነው?” እንዳለች፥ የአንተ ሊቀ መንበርነት፥ አለቅነት፥ ሥራ አስኪያጅነት፥ ሚኒስትርነት፥ ለመቼ ነው?” እያሉ ሰውን ወደ ጥፋት የሚገፋፉ ቍጥራቸው ቀላል አይደለም።

              ኤልዛቤል በባሏ ስም የምትነግድ ስለሆነ፥ አንድም ንግሥት በመሆኗ በአክዓብ ስም ደብዳቤ ጽፋ፥ በማኅተሙም አትማ፥ ያቺን ደብዳቤ ወደዚያች ሀገር አለቆች፥ ከናቡቴ ጋር ወደሚኖሩ ወደዚያች ሀገር መኳንንቶችም ላከቻት። የዚያችም ደብዳቤ ቃል፦ “ጾምን ጹሙ፥ ናቡቴንም በሕዝቡ ፊት አስቀምጡት። የሐሰት ምስክሮች ሁለት ሰዎችን አስነሡበት፥ (አሠልጥኑበት)፥ እግዚአብሔርን ሰደብከው፥ ንጉሡንም ረገምከው ብለው ይመስክሩበት፥ ከከተማም ወደ ውጭ አውጥታችሁት በደንጊያ ቀጥቅጣችሁ ግደሉት።” የሚል ነው። የዚያችም ሀገር ሰዎች፥ አለቆች፥ መኳንንቶችም ኤልዛቤል እንዳለቻቸው አደረጉ። ነገሩን እውነት ለማስመሰል ጾምን አወጁ፥ በአደባባይም በሐሰት አስመስክረውበት በደንጊያ ቀጥቅጠው ገደሉት። “የቤተ መንግሥቱን መመሪያ ተግባራዊ አድርገናል፤” ብለውም ለኤልዛቤል ላኩባት። “ለምን?” የሚል ከሽማግሌዎች እንኳ አንድ ሰው አልተገኘም። ለመንግሥት መመሪያ ሲሉ የሐሰት ምስክሮችን አዘጋጁ፥ ምናምንቴ ዳኞችም በግፍ ፈረዱ። በተቻለ መጠን ግፋቸውን ሕጋዊ ለማስመሰል ሞከሩ። በተለይም በሰው ሕይወት ላይ በሐሰት መፍረድ የግፍ ግፍ ነው። ፍርድ ቤቶችም ለተሾሙለት ሕዝብ ሳይሆን ለሾማቸው ክፍል እንዲህ በገሃድ የሚያደሉ ከሆነ እንግዲህ ምን ኑሮ አለ? ትላላችሁ። በዚህ ዓይነት በዚህች ምድር ላይ ዕድሜ ልክ ወይም ሞት የተፈረዳባቸው ስንት ይሆኑ?

              ኤልዛቤልም አክዓብን፦ “ናቡቴ በሕይወት አለ እንዳትል፥ ሙቷልና፤ በዋጋ መስጠትን እምቢ ያለህ የኢይዝራኤሉ ሰው የናቡቴን የወይኑን ቦታ ተነሥተህ ውረስ፤” አለችው። አክዓብም ናቡቴ እንደ ሞተ በሰማ ጊዜ ይወርሰው ዘንድ ተነሥቶ ወደ ኢይዝራኤሉ ሰው ወደ ናቡቴ የወይን ቦታ ወረደ። በዚህ አይነት ከአያት ከቅድመ አያት ጀምሮ ይዘው የኖሩትን ርስታቸውን በአንድ ጀንበር ያጡ ቍጥራቸው ስንት ይሆን? ሜዳ ላይ የወደቁ፥ በገዛ ሀገራቸው ስደተኞች የሆኑ፥ በዚህም ምክንያት ቀን ከሌሊት የሚያለቅሱ፥ ፍትሕ ላያገኙ ፋይል ተሸክመው የሚንከራተቱ፥ የተደበደቡ፥ የሞቱ፥ ሀገር ለቅቀው የተሰደዱ የብዙ ብዙ ናቸው። አንድስ ሰው ቢሆን ለምን? የዋልድባ ገዳም አባቶችም የዘመናችን ናቡቴዎች ናቸው። በሩቅ ሆነን እንደምንሰማው፦ “የአባቶቻችንን ርስት አንሰጥም፥ የቅድስናውን ስፍራ ለሥጋዊ አገልግሎት አሳልፈን አንተውም፥ ይኼ የምናኔ ቦታ ነው፤” በማለታቸው እየታሰሩ፥ እየተገረፉ፥ እየተሰደዱ ነው። አምልኮተ እግዚአብሔርን የምንፈጽምባቸው አድባራትና ገዳማት በሃይማኖት የወረስናቸው የአባቶቻችን ርስት ናቸው። ባለቤቱ የሁሉ ጌታ  እግዚአብሔር ነው። ስለሆነም በአክዓብና በኤልዛቤል መንፈስ መሄድ ለሥጋም ለነፍስም አይጠቅምም። ለራስም ለሀገርም የሚበጀው በእነ አብርሃ ወአጽብሃ፥ በእነ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ፥ በእነ ዓፄ ዮሐንስ፥ በእነ ዓፄ ምኒልክ፥ በእነ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ መንገድ መጓዝ ነው። ከቀደሙት ነገሥታት መካከል አንዳንዶቹ በግል የተወሰኑ ድካሞች ቢኖርባቸውም ከሀገር አንድነት እና ከሃይማኖት አንጻር እጅግ ጠንካሮች ነበሩ። በጥንታውያን አድባራትና ገዳማት ላይ አሻራቸው አለ። ሀገሪቱን ባለ ታሪክ፥ ባለ ቅርስ አድርገዋታል። በሕይወት እያሉ የወርቅ ዘውዳቸውን፥ የወርቅ ካባቸውን፥ ቤታቸውን፥ መሬታቸውን ለቤተ ክርስቲያን አውርሰዋል። ለአድባራቱ እና ለገዳማቱ መተዳደሪያ ሰጥተዋል። እንጨት ሆኖ የማይጨስ፥ ሰው ሆኖ የማይበድል የለምና ንስሐ ገብተውባታል፥ ሥጋ ወደሙ ተቀብለውባታል። በጠበሏ ተጠምቀው ተፈውሰውባታል። ቤተ ክርስቲያንም ውለታቸውን አትረሳም። ታሪክም ሲያስታውሳቸው ይኖራል።

              ሰው ዝም ቢል እግዚአብሔር ዝም አይልም። እግዚአብሔርም ቴስብያዊውን ኤልያስን፦ “ተነሥተህ በሰማርያ የሚኖረውን የእሥራኤልን ንጉሥ አክዓብን ትገናኝ ዘንድ ውረድ፤ እነሆ፥ ይወርሰው ዘንድ በወረደበት በናቡቴ የወይን ቦታ ውስጥ አለ። እንዲህም ብለህ ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ናቡቴን ገድለህ ወረስኸውን? ስለዚህም ደግሞ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጅቦችና ውሾች የናቡቴን ደም በላሱበት ስፍራ የአንተን ደም ውሾች ይልሱታል፤ አመንዝራዎች በደምህ ይታጠባሉ፥ ብለህ ንገረው፤” አለው። አክዓብም ኤልያስን፦ “ጠላቴ ሆይ፥ አገኘኸኝን?” አለው። የምድር ገዢዎች እንዲህ ናቸው፥ በትክክል እውነቱን የሚነግራቸው ሰው ጠላታቸው ነው። ኤልያስም፦ “አግኝቼሃለሁ፥ ታስቆጣው ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገሃልና እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ክፉ ነገር አመጣብሃለሁ፥ እሳትን ከኋላህ አነድዳለሁ፥ አጥር ተጠግቶ እስከሚሸን ድረስ የአክዓብን ዘር አጠፋዋለሁ፥ በእስራኤል ውስጥ ያሉትንም የሌሉትንም እነቅላለሁ፤ በሥራህም አስቆጥተኸኛልና፥ እስራኤልንም አስተሃልና፥ ቤትህን እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ ብሎሃል።” አለው። አክዓብ ከእግዚአብሔር ከፊቱ ቍጣ የተነሣ ደነገጠ፥ ልብሱንም ቀደደ፥ እያለቀሰም ሄደ፥ በሰውነቱም ላይ ማቅ ለበሰ፥ ጾመም። የሰውን ልጅ ተጸጽቶ መመለሱን እንጂ መጥፋቱን የማይፈልግ አምላክ እግዚአብሔርም፦ “አክዓብ በፊቴ እንደደነገጠ አየህን? በፊቴ በልጁ ዘመን በቤቱ ላይ ክፉ ነገር አመጣለሁ እንጂ በእርሱ ዘመን ክፉ ነገር አላመጣም።” ሲል ለባሪያው ለኤልያስ ነገረው። ስለዚህ ከታች እስከ ላይ ያለን ሁላችንም እግዚአብሔር እየተናገረን ነውና እንደንግጥ፥ ማቅ ለብሰን፥ አመድ ላይ ተኝተን ንስሐ እንግባ፥ የማስመሰል ወይም የልማድ ሳይሆን በእምነት እንጹም፥ እንጸልይ። ያን ጊዜ እግዚአብሔር ባለፈው ይቅር ይለናል፥ ከሚመጣውም ይጠብቀናል። በመጨረሻም እግዚአብሔር በነቢዩ በኤልያስ አንደበት የተናገረበት ሁሉ በአክዓብ ላይ ተፈጸመበት። ፩ኛ ነገ ፳፪፥፴፬-፵። ከዚህም የምንማረው፥ ይዋል ይደር እንጂ ሁላችንም የእጃችንን እንደምናገኝ ነው። ምክንያቱም ሁላችንም እንደየአቅማችን የምንፈጽመው ግፍ አለና። ባል በሚስቱ፥ ሚስትም በባሏ፥ ወንድም በወንድሙ፥ አሠሪ በሠራተኛው፥ ሠራተኛውም በአሠሪው፥ ወላጆች በልጆቻቸው፥ ልጆችም በወላጆቻቸው ላይ የሚፈጽሙት ግፍ አላቸው። ሌላው ቀርቶ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ እንኳ ስንት ግፍ ይፈጸማል። ግፍ ሲፈጸም እያዩና እየሰሙም በእኔ ላይ እስካልደረሰ ድረስ ምን አገባኝ ብሎ ዝም ማለትም ራስ ወዳድነት ነው። የግፈኞችም ተባባሪ መሆን ነው። ስለሆነም እኔ ማንን ነው የምመስለው? ናቡቴን እና ኤልያስን? ወይስ አክዓብንና ኤልዛቤልን? እንዲሁም ኤልዛቤል የላከችውን ደብዳቤ ለማስፈጸም እንደተሯሯጡት ሰዎች? ማለት አለብን። ዛሬውኑ ራሳችንን ፈልገን እናግኝ። እንደ ናቡቴም “ክፉውን ኅሊና እግዚአብሔር ያርቅልኝ፤” እንበል። እንደ ኤልያስም የእግዚአብሔርን መልእክት በትክክል እናድርስ።

    የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን። አሜን።

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: “እንዲህ ያለ ነገር እግዚአብሔር አያምጣብኝ!” ፩ኛ ነገ ፳፥፫         Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top