ዲያቆን አምኃ ልዑልሰገድ
እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረትን በዕለተ እሑድ መፍጠር ጀምሮ በዕለተ ዐርብ የመጨረሻና የፍጥረቱ ሁሉ ገዥ የሆነውን ሰውን በመፍጠር ሥራውን ፈጽሞ በሰባተኛዋ ቀን በዕለተ ቅዳሜ አርፏል/መዝ.2፡3/ ይህችም /ሰባተኛዋ/ ቀን ለሰው ልጆች ሁሉ የዕረፍት ቀን ሆና እንድትቀጥል በሙሴ በኩል ትእዛዝን አስተላልፎአል፡፡ /ዘፀ.31፡15/ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ ሰባተኛውን ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው፡፡በማለት ሥራን ማከናወንና ማረፍን የሰው ልጅ ከአምላኩ ተምሯል፡፡
በዘመነ ኦሪት ከእሑድ እስከ ዐርብ ሰው ወጥቶ ወርዶ ይደክምና በሰባተኛዋ ዕለተ ሰንበት ከሥራው ሁሉ በማረፍ የእግዚአብሔር ሰንበት ዕረፍት መሆኗን በማሰብ ያሳልፋል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔር ዕረፍቱ ለሰው ሁሉ ዕረፍት ሆና ተሰጥታለች፡፡
ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ተረድቶ አባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ ስለ እውነተኛዋ ዕረፍትና የዕረፍቶች ሁሉ ዕረፍት ስለሆነችው ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም እንዲህ ይናገራል፡-
ትመሰል እምኪ ማርያም ዕለተ ሣልስተ ወራብዕተ
ዘወለደት ጽጌ ወፀሐየ ዓለም ብርህተ
ካዕበ ትመስል ሳብእተ ዕለተ
እስመ ፈረየት ኪያኪ ተአምረ ግዕዛን ሰንበተ
ለእለ በሰማይ ወምድር ዘኮንኪ ዕረፍት
ትርጉም፡- ማርያም ሆይ እናትሽ ጽጌያት የተፈጠሩበትን ሦስተኛዋን ቀን ሠሉስን(ዘፍ.1፡11-13)፣ ፀሐይ የተፈጠረችበትን አራተኛዋን ቀን (ረቡዕ) እንዲሁም እግዚአብሔር ሥራውን ፈጽሞ ያረፈባትን ሰባተኛዋን ቀን ትመስላለች፡፡
ምክንያቱም በሰማይና በምድር ላሉ ሁሉ ዕረፍት የሆንሻቸውን አንቺን ወልዳለችና፡፡በማለት በዕለተ ማክሰኞ ቅድስት ሐናን የመሰለው በዚች ዕለት ዕፀዋት ከምድር እንደተገኙ ድንግል ማርያምም ከሐና ማኅፀን ተወልዳለችና ነው፡፡ አንድም ዕፀ ሠሉስ ድንግል ማርያምን ያስገኘች ሐና እንደሆነች ሁሉ ጽጌ ሠሉስ ክርስቶስን የወለደች እመቤታችን ማርያም መሆኗን መናገር ነው፡፡
አንድም ዕፀ ሠሉስ ሐና ጽጌ ሠሉስ ድንግል ማርያምን መውለዷንና ጽጌ ሠሉስ ድንግልም ፍሬ ሕይወት ክርስቶስን እንደወለደችልን መግለጡ ነው፡፡ ነቢዩ ሚልክያስ (ሚል.4፡2) ፟ስሜን ለምትፈሩት ለእናንተ የጽድቅ ፀሐይ ትወጣላችኋለች ፈውስም በክንፎችዋ ውስጥ ይሆናል እናንተም ትወጣላችሁ እንደሰባ እምቦሳ ትፈነጫላችሁ፡፡፟ እንዳለ ፀሐይ ካለመኖር ወደ መኖር በመጣችበት ዕለተ ረቡዕን ለሐና መስሎ ቅድስት ድንግል ማርያምን ፀሐይ ይላታል፡፡ በእርሷ ፀሐይነት ዐቢይ ብርሃን ክርስቶስ ታላቁን ጽልመት አስወግዶ ዘለዓለማዊ ዕርፍትን ሰጥቶናልና፡፡ ይኸውም ገንዘቡ ባደረገው ከርሷ በነሳው ሥጋና ነፍስ ማለትም ፀሐይ በተባለች ፍፁም ሰውነት በትክክል እኛን መስሏልና፡፡ ለእርሱም ማረፊያው አንቺ ነሽ ሲል ነው፡፡
እግዚአብሔር ያረፈባት ሰባተኛዋን ቀን እናትሽ ቅድስት ሐናን ትመስላለች ዕለቷ እናትሽ ዕረፍታችንም አንቺ ነሽና ብሎ ምሳሌውን ይጠቀልላል፡፡ ምክንያቱንም ሲያመጣ ዕለት በራሷ ዕረፍት መሆን አትችልም ምክንያተ ዕረፍትነቷን አንችን አግኝታ ነው፡፡በሰማይና በምድር አንቺ እመቤታችን ዕረፍት ሆንሽን ይኸውም ያቺ የእግዚአብሔር ዕረፍቱ ሰባተኛዋ ቀን አንቺ ነሽ፡፡
በቀዳሚት ሰንበት ፍጥረት የመፍጠር ሥራውን ፈጽሞ ቢያርፍም የመጨረሻ ዕረፍት የሆንሽው አንቺ ነሽ፡፡ምክንያቱም በሐዲስ ተፈጥሮ አዳምን ፈጥሮ (የቤዛነት ሥራውን ፈጽሞ) ያረፈው በአንቺ ነውና፡፡ አንቺ እመቤታችን ዕረፍት ለሆነን ለልጅሽ ዕርፍቱ ስለሆንሽ ዕረፍት ብቻ ሳትሆኚ የዕረፍቶች ዕረፍት ነሽ በማለት ዘለዓለማዊ ዕረፍት ለሰጠን ለዕረፍታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የዘለዓለም ማረፊያ(ማደሪያ) እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗንም ያስገነዝበናል፡፡
ከዕለታት ሰንበትን ለሰዎች ሁሉ የዕረፍት ዕለት አድርጎ የሰጠ እግዚአብሔር ከፍጥረታት ቅድስት ድንግል ማርያምን የዕረፍቶች ሁሉ ዕረፍት አድርጎ ለሰማያውያንና ምድራውያን (በሰማይና በምድር) ዕረፍት ትሆን ዘንድ ሠጥቷል፡፡ ለፍጥረቱ ብቻም ሳይሆን ፈጣሬ ዓለማት ራሱ ለራሱ የዘለዓለም ማረፊያ ትሆነው ዘንድ እንደመረጣት እንደልቤ ባለው በቅዱስ ዳዊት በኩል ተናግሯል፡፡
ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ/መዝ.132፡14/የተናገረውን ማኅሌታዊው አባ ጽጌ ድንግልም ይህን የቅዱስ ዳዊትን ምስክርነት ወስዶ በከመ ይቤ መጽሐፍ ማዕከለ ፈጣሪ ወፍጡራን ለዕረፍት ዘኮንኪ ትእምርተ ኪዳን፣ ሰንበተ ሰንበታት ማርያም ዕለተ ብርሃን፣ብኪ ይትፌስሑ ዘገነተ ጽጌ ጻድቃን፣ወብኪ ይወፅኡ ኀጥአን እምደይን፤ የፈጣሪና ፍጡራን ማዕከል(መገናኛ) መሆንሽ በመጻሕፍት እንደተነገረ የዕረፍታችን ኪዳን ምልክት ሆንሽ፤የእረፍቶች ዕረፍት የብርሃን ቀን (ብርህይት ዕለት) በአንቺ የገነት አበቦች ጻድቃን ደስ ይላቸዋል በአንቺም ኀጥአን ከሲኦል (ከእሳት) ይወጣሉ፡፡
በማለት ቅድስት ድንግል ማርያም በቀደመው በደል ምክንያት በጠብ ተራርቆ የነበረው ፍጥረት ከፈጣሪው ጋር የተገናኘባት ለመዳናችን (ለዘለዓለማዊ ዕረፍታችን) ምልክት ሆና የተሰጠች መሆኗን ገልጾ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመነ ጽልመት የበራብሽ ብርህይት ዕለት አንቺ ነሽ ሲል በቅድስት ትንሣኤው ሞትና መቃብር ድል መነሣቱን በዚህም ዕለት የጨለማ ዘመን አክትሞ ዘመነ ብርሃን ዓመተ እግዚእ እውን መሆኑን በማስረዳት ለዚህ ሁሉ የበቃንበት ልጅሽ ኢየሱስ ክርስቶስ አንቺን ማረፊያ አድርጎ ነው በማለት ያለ እመቤታችን ስለ ድኅነት መናገር እንደማይቻል ያስገነዝባል፡፡ ገነት ርስታችንንና ለዘለዓለም የምንወርሳት መንግሥተ ሰማያትንም ያገኘነው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ነውና፡፡
ገነት ያለ ቅዱሳን አትዋብምና በገነት ያሉ አበቦች ጻድቃን በአንቺ ደስ ይላቸዋል ምክንያቱም መድኃኒታቸውን ከአንቺ ተወልዶ አግኝተዋልና አንድም እውነተኛ መብል ቅዱስ ሥጋውን እውነተኛ መጠጥ ክቡር ደሙን በልተውና ጠጥተው በገነት ያረፉት በአንቺ ምክንያት ነውና፡፡ በምልጃዋ በቃል ኪዳኗ የሚታመኑ ኃጥአንም እንኳ ለንስሐ ፍሬ እንደሚበቁባት ሲያስረዳ ኃጥአን በአንቺ ከሲኦል ይወጣሉ ነማለት ይገልፃል፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ኤፍሬም ዛቲ ይእቲ ኢየሩሳሌም ሀገሮሙ ለነቢያት ወማኅደረ ፍሥሐሆሙ ለኵሎሙ ቅዱሳን ሕዝብ ዘይነብር ውስተ ጽልመት ወጽላሎተ ሞት ብርሃን ዐቢይ ሠረቀ ላዕሌሆሙ፤የነቢያት ሀገራቸው ኢየሩሳሌም ይህች ናት፤ ለቅዱሳን ሁሉ የደስታቸው ማደሪያ ናት፤በጨለማና በሞት ጥላ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው፡፡�
የቅዱሳን ሁሉ የደስታ ማደሪያ፣ በአፀደ ሥጋ በምድር በአፀደ ነፍስ በሰማይ ያሉ አንድም በአፀደ ሥጋም በአፀደ ነፍስም ያሉ ቅዱሳን በአንድነት የሚያርፉብሽ ዘለዓለማዊ ርስታቸው ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አንቺ ነሽ፡፡ በማለት ምስክርነቱን ያጸናል፡፡ አባ ሕርያቆስም €œበቦታ ሁሉ አንቺ ርስት ነሽ፤ ስምሽም በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠነ ነውâ€�/ቅዳሴ ማርያም/ በማለት የቅድስት ድንግል ማርያምን ክብርና በድኅነታችን ውስጥ ያላትን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራል፡፡
ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ዘለዓለማዊ ዕረፍት በተናገረበት መልእክቱ እንግዲህ አንፍራ ወደ እረፍቱም እንድንገባ ትእዛዙን አንተው/ዕብ.4፡1/ በማለት የእግዚአብሔር እረፍቱ እኛም እንገባበት ዘንድ ያለን እንደሆነና ለዚህም እንድንበቃ ትእዛዙን መጠበቅ እንዳለብን ገልጾ ለእኛም የምሥራች ተሰብኮልናል፤ ነገር ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም፡፡ ሥራው ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ምንም እንኳ ሲፈጸም እንግዲህ ወደ ዕረፍቴ አይገቡም ብዬ በቁጣዬ ማልሁ እንዳለ እኛስ ያመንን ወደ ዕርፍቱ እንገባለን የእግዚአብሔር ሕዝብ የሆነ ሁሉ የሚገባበት ጸንቶ የሚኖር ዕረፍት እንዳለ ታወቀ ወደ ዕረፍቱ የገባስ እግዚአብሔር ከሥራው እንደ ዐረፈ እነሆ እርሱ ከሥራው ሁሉ ዐረፈ፡፡
እንግዲህ እንደ እነዚያ እንደ ካዱት እንዳንወድቅ ወደ ዕረፍቱ እንገባ ዘንድ እንፋጠን፡፡ /ዕብ.4፡10/ በማለት የእረፍት ዜና መሆንሽን የሰሙ ብዙዎች በመስማታቸው ያልተጠቀሙ የእግዚአብሔን ዕረፍት አንቺን አያዩም፤ በኪዳንሽ የምናምን በልጅሽ የምንታመን እኛ ግን በአንቺ ከሞት ወደ ሕይወት ተሸጋግረናልና ወደ ዕረፍት እንገባ ዘንድ አለን፡፡ ይህን ቃል በእምነት ጸንተን ከሰውነታችን ጋር ተዋሕዶ ተጠቃሚ ከሆኑት ከቅዱሳን ጋር ወደ ዘለዓለማዊ ዕረፍት ለመግባት በምሥጋና ሕግና ትእዛዙን በመጠበቅ እንፋጠን፡፡ ቅዱስ ያሬድ የአምላክ ልጅ ካንቺ ሰው ስለመሆኑ ባንቺ ከምድር ወደ አርያም (መንግስተ ሰማያት) የቀረብን ሆንን በአንቺና በልጅሽ ስም የቀረብንን ሆንን (አንቀጸ ብርሃን) በማለት የእኛን ሰውነት ሰውነቱ አድርጎ በባሕርይ አባቱ በአብ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ክብር መገኘቱን እኛንም በእርሱ በኩል በጸጋ የክብሩ ተካፋዮች (የመንግሥቱ ልጆች) መሆንን ያገኘነው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምክንያት እንደሆነ በመዳናችን ውስጥ ያላትን ድርሻ ግልጽ አድርጎ ያሳያል፡፡
አባ ጽጌ ድንግልም ሰንበተ ሰንበታት ማርያም ዕለተ ብርሃን፣ የብርሃን ቀን የዕረፍቶች ዕረፍት በማለት የገለጻት ትንሣኤ ዘጉባኤ ሆኖ ጊዜ ሳይቆጠር የምንኖርባትን ሰባተኛዋን ሰንበት ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ አድርጎ የገለጸው ይህንኑ ሐቅ ተረድቶ ነው፡፡
ስለዚህ ሐዋርያው እንግዲህ እንደዚያ እንዳለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ በማለት በሕግ በሥርዓት ኑረን በምግባር በትሩፋት ወደ ዘለዓለማዊ ዕረፍት መንግስተ ሰማያት ለመግባት የበቃን ሆነን እንገኝ፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
0 comments:
Post a Comment