• በቅርብ የተጻፉ

    Friday 6 November 2015

    የጌታችንና የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ በቅዱስ መጽሐፍ ሲነጻጸር


    እግዚአብሔር ሰውን አክብሮና አልቆ በመልኩ በምሳሌው ፈጠረው፡፡ ሰው ግን እግዚአብሔር ባስቀመጠው የክብር ሥፍራ አልተገኘምና ተዋረደ፡፡፡ ከኃጢአቱም የተነሣ ደሃ ሆኗልና ሰው ሆኖ መፈጠር /መወለድ/ የምሬት ርእስ ሆነ፡፡ ሁሉን አይቶ ሁሉን ማጣት የሰው ልጅ የማይለምደው የኑሮ ጥቁር መልኩ ነው፡፡ ሁሉን ያጣ ሁሉን ሲያገኝ የዕድገት ሕግ ያለው፣ የሚናፈቅ ደስታና ሊተርኩት የሚያስቸኩል የኑሮ ገድል ነው፡፡ ሁሉን አይቶ ሁሉን ማጣት ግን የሚያንደረድር የቁልቁለት ጉዞ፣ ጉልበትን እያዛለ ከዕይታ የሚሠውር፣ ልታይ ልታይ ያለውን ሰብእና ደብቁኝ የሚያሰኝ፣ የማይለምዱትና የማይደፍሩት ሥፍራ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ ሀብት ጨብጣችሁ አግኝቶ እንደማያውቅ ብትቸገሩ ሌሊቱን ያመጣ ቀኑን ያመጣልና በርቱ፡፡ ሀብት በማጣታችሁ ስትበሳጩ ሀብት የማያመጣውን ጤና እንደምታጡ አስቡ፡፡ ወልዳችሁ ሞት ልጆቻችሁን ነጥቋችሁ ከሆነ ማዳን ብቻ ሳይሆን መግደልም የእግዚአብሔር ሥልጣን እንደሆነ በመረዳት ከከንቱ አእምሮ ራቁ፡፡ ሊነጋ የጨለመ እንጂ ጨልሞ ሊቀር የመሸ ሌሊት ስለሌለ በእምነታችሁ ጽኑ! ጌታችን ድል ለነሡ ሽልማት የሚሰጥ ንጉሥ ብቻ ሳይሆን ለወደቁትም ትንሣኤ የሚሆን አምላክ ነውና፡፡

    በሥነ ፍጥረት ተመራማሪነቱ የሚደነቅ አንድ የሥነ ሕይወት ሊቅ በባሕር ዳርቻ ዳክዬዎችን እያየ ይመሰጥ ነበር፡፡ ሁል ጊዜ የሚያያቸው እነዚህ ዳክዬዎች በሽታ ገባባቸውና ማለቅ ጀመሩ፡፡ እርሱም መድኃኒት ነበረውና ለማዳን ሲቀርባቸው ይሸሹታል፡፡ ከዚህም የተነሣ ዓይኑ እያየ፣ መድኃኒቱንም በእጁ እንደጨበጠ ዳክዬዎቹ  በሙሉ አለቁ፡፡ በዚህን ጊዜ ታዲያ ‹‹ዳክዬ ብሆን ዳክዬዎቹን አድናቸው ነበር›› ብሎ ቁጭቱን ተናገረ ይባላል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰው ባልሆንኩ ለሚሉት የሰውነትን ዋጋ ሊገልጥ፣ ሰው የለኝም ለሚሉት ጥሩ ሰዋቸው ሊሆን፣ ሰው በሆንኩ ለሚሉትም ሰው ሊያደርጋቸው ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ፣ ሰውነታችንን ተዋሕዶ ሰው ሆነ፡፡ ‹‹በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፡፡ . . .  ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ››  እንዲል /ዮሐ.1÷1/፡፡

    ይኸውም እኛን ከሞት አድኖ የሕይወትን ትንሣኤ ሊሰጠን ነው፡፡ ከጌታችን ሰው መሆን በፊት የነበሩ ጻድቃን ሰዎች ቢኖሩም ከጠባያቸው ብቻ ሳይሆን ከተፈጥሮአቸውም በውርስ ኃጢአት ስለተያዙ /ከእመቤታችን ከቅድስት ንጽሕት ድንግል ማርያም ከተወለደው መድኅን ክርስቶስ በቀር/ እኛን ሊያድኑን አልቻሉም ነበርና፡፡ ሊቁ አቡሊደስ ‹‹ከሰው ወገን ማንም ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፤ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር፣ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲዖል ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው? ብሎ እንደተናገረ /መዝ.8÷8/፡፡ ራሱን ማዳን ያልቻለው ሌላውን ማዳን እንደምን ይችላል? አንድ ራሱን ሊያድን ያልቻለስ ዓለምን ሁሉ ሊያድን እንደምን ይችላል? ኃጢአት በሰው አድሮ ይኖር ነበርና፤ ሞትም ይከተለው ነበርና/መዝ.8÷9/ ብሏል /ሃይ.አበው ገጽ 145/፡፡

    የሠለጠነው ዓለም እንኳ ሰውን በቤተ ሙከራ ለመፍጠር ሲያስብ የሞት ማስወገጃን ለመሥራት ግን ዕቅድ እንኳን የለውም፡፡ ለምን? ቢባል የንጉሡም የምሁሩም አእምሮ ሞትን የሚገዛ ሳይሆን ለሞት የተገዛ ነውና፡፡ ሞት ሁለት ዓይነት መልክ አለው፡፡ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየትና የነፍስ ከእግዚአብሔር አንድነት መለየት የሚሉት ናቸው፡፡ የሰው ትልቁ ሞት ሕይወት ከሆነው ከእግዚአብሔር አንድነት መለየቱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወተ ሥጋ ያሉትን ኃጢአተኞች ‹‹ሙታን›› በማለት የሚጠራቸው ለዚህ ነው /ኤፌ.2÷1/፡፡ መንፈሱ የሞተ ሰው ከእግዚአብሔር  ጋር ያለውን አንድነት ያፈረሰ በመሆኑ የባከነ ሕይወት ይኖራል፡፡ ነፍሱ ከሥጋው ስትለይም ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ፊት በእሳት ባሕር ይጣላል፡፡ የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ አምነው በሕግ በአምልኮ እርሱን የተከተለ፣ በክርስቲያናዊ ምግባር እርሱን የመሰለ ግን ይህ የሞት ኃይል በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፡፡

    በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተጽፎ እንደምናገኘው ሞት ለብዙ ዘመናት ኤልያስን አሳዶት ነበርና ሞትን ከለመኑት መካከል አንዱ ነው፡፡ /2ኛ ነገ.4÷35/፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ኤልያስ ሞትን አቅም አሳጥቶታል/1ኛ ነገ.17÷22/፡፡ በሐዲስ ኪዳንም እግዚአብሔር መንግሥቱን በማስፋፋት ውስጥ ትልቅ ድርሻ (ሓላፊነትን) የተጣለባቸው እነ ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስም በተሰጣቸው የጸጋ ሥልጣን በሞት ላይ መራመድና ሙታንን ማስነሣት ችለዋል /ሐዋ.5÷1-11፣9÷40/፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር አምላክ በጸጋ ያደረባቸው ቅዱሳን ተአምር እና  ይህን ያህል ድንቅ ነገር ካደረጉ በማይወሰነው ፍጹም አካሉ እርሱ ባወቀው ድንቅ ጥበቡ ያደረባት እመቤታችንማ ተአምሯ እንዴት ከዚህ አይልቅ? የእርሷ ሞትና ትንሣኤ ከልጅዋ ሞትና ትንሣኤ ጋር ይነጻጸራል ቢባልስ ምን ይደንቃል? ዳሩ ግን በዕውቀት /በመረጃ/ ያልታገዘ እምነት ጠቀሜታው አመርቂ አይደለምና የጌታችንና የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ ሲነጻጸር /የሚመሳሰልበትንና የማይመሳሰልበትን ምክንያት/ በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡ እመብርሃን ምሥጢሩን ትግለጥልን፡፡

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥድሳ አራት ዓመቷ በእግዚአብሔር ፈቃድ ጥር ሃያ አንድ ቀን ዐርፋለች፡፡ ሐዋርያትም ሥጋዋን ገንዘው ተሸክመው ሊቀብሩ ሲወስዱ አይሁድ አይተው ለምቀኝነት አያርፉምና ቀድሞ ልጇን ከመቃብር ሰርቀው ወስደው ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ ያውኩናል፤ ዛሬ ደግሞ እናቱን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? ብለው ሥጋዋን ለማቃጠል ወሰኑ፡፡ ከዚያም ታውፋንያ የሚባለውን ሰው ከመካከላቸው መርጠው ‹‹አንተ ሂድና ሥጋዋን ከመሬት ላይ ጣለው፣ እኛም ወስደን እናቃጥለዋለን›› ብለው ላኩት፡፡ እርሱም ተደፋፍሮ ሥጋዋን ከመሬት ላይ ለመጣል አጎበሩን ሲጨብጥ የእግዚአብሔር መልአክ ተቆጥቶ ሁለት እጁን ቆርጦታል፡፡ ወዲያው የእመቤታችንን ሥጋ ከዮሐንስ ወንጌላዊ ጋር ቅዱሳን መላእክት እየዘመሩ ወደገነት አሳርገውታል፡፡

    ቅዱሳን ሐዋርያትም ዮሐንስ ያየውን ምሥጢር ለእነርሱም እንዲያሳያቸው ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምረው ጾም፣ ጸሎት ለማድረግ ሱባኤ ያዙ፡፡ ዛሬም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሐዋርያት በወረሰችው ትውፊት መሠረት ለጾመ ፍልሰታ ሥርዓት ሠርታ፣ ከሰባቱ አጽዋማት ተርታ አስገብታ ይህን ታላቅ የበረከትና የምሥጢር መገለጫ ጾም ትጾማለች፡፡ ልክ እንደ ሐዋርያቱ የእመቤታችንን ምሥጢረ ትንሣኤና ዕርገት ይገለጥላቸው ዘንድ በመሻት ሕፃናት፣ ጎልማሶችና አረጋውያን በመንፈሳዊ መነቃቃት ሱባኤ ይገባሉ፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ጾማቸውን በጀመሩ በዐሥራ አራተኛው ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ሥጋ ከገነት አምጥቶ ሰጥቷቸዋል፡፡

    እነርሱም አክብረው በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል፡፡ ከዚያም በተቀበረች በሦስተኛ ቀኗ ተነሥታ በቅዱሳን መላእክት እና በክቡራን ሐዋርያት ዝማሬ ታጅባ ዐርጋለች፡፡ ከዚህም የተነሣ በመቅድመ ተአምረ ማርያም ላይ እንደተገለጸው አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ሊቃነ ጳጳሳት ሠላሳ ሦስቱን በዓላቶቿን እንደ እሑድ ሰንበት እንድናከብር ሲያዝዙን የትንሣኤዋንና የዕርገቷን በዓል በተመለከተ ‹‹ወአመ 16 ለወርኃ ነሐሴ ፍልሰተ ሥጋሃ ሰዱሰ መዋዕለ ይግበሩ በዓለ ከመ ትንሣኤ ወልዳ፤ በነሐሴ 16 ሥጋዋ የፈለሰበት ነውና እስከ 21  ድረስ ለስድስት ቀናት እንደ ልጇ ትንሣኤ አድርገው ያክብሩ›› በማለት ሥርዓት ሠርተዋል፡፡

    ‹‹እንደ›› የሚለው አገባብ መመሳሰልን ለመግለጥ፣ ኃይለ ቃሉን ለማጉላት እና በአጽንኦት ክብርን ለመስጠት ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ አበበ እንደ ከበደ ጎበዝ ተማሪ ነው ብንል የአበበ ጉብዝና የከበደን ያህላል /ይመስላል/ ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳን ምሳሌ «ዘየሐጽጽ፤ ከሚመሰልለት ነገር የሚያንስ» ቢሆንም የእመቤታችን ትንሣኤ ከጌታችን ትንሣኤ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን እንደሚያስገነዝብ ልብ ይሏል፡፡ በመሆኑም የእመቤታችንን ትንሣኤ እንደ ልጇ ትንሣኤ አድርገን እንድናከብር የታዘዝንበትን ምክንያት በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

    ሀ. የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው በመቃብር ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ቆይቶ እንደተነሣው ሁሉ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምም ሥጋ ሐዋርያት ከቀበሯት በኋላ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በመቃብር ቆይታ ተነሥታለች፡፡

    ለ. ጌታችን ከሙታን ተለይቶ ሲነሣ መግነዝ ፍቱልኝ፣ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል በኅቱም መቃብር እንደተነሣ እመቤታችንም እንዲሁ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል በኅቱም መቃብር ተነሥታለች፡፡

    ሐ. ጌታችን ሦስት ሌሊትና መዓልት በከርሠ መቃብር ሲቆይ ሥጋውን ሙስና መቃብር እንዳላገኘው ሁሉ እመቤታችንም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር ስትቆይ ሥጋዋን ሙስና መቃብር ሳያገኘው ተነሥታለች፡፡

    መ. ጌታችን ከሙታን ተለይቶ በተነሣበት ሳምንት ማለትም እስከ ዕለተ ጰራቅሊጦስ ባሉት ቀናት ውስጥ የሚደረሰው ስብሐተ እግዚአብሔር እና የሚሰጠው ትምህርት ሁሉ በሞቱ፣ በትንሣኤው እና በዐርገቱ ላይ እንደሚያተኩረው ሁሉ እመቤታችን ከተነሣችበት ነሐሴ ዐሥራ አራት እስከ ዐሥራ ስድስት ድረስ ያው ሥርዓትና ትምህርት ስለሚከናወን ነው፡፡

    ሠ. ጌታችን ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳይጠብቅ ዳግመኛ ሞት በማያስከትል በሐዲስ ሥጋ እንደተነሣ ሁሉ እመቤታችንም ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ ዳግመኛ ሞት በሌለበት በሐዲስ ሥጋ ተነሥታለች፡፡ እንዲሁም ጌታችን ወደ ሰማይ ያረገው ሞትን ድል ነሥቶ ነው፡፡ እነ ሄኖክና ኤልያስ ሲያርጉ እንዲሁ ሳይሞቱ ነው፤ እመቤታችን ግን ያረገችው እንደ ልጇ ሞት ድል ከተነሣ በኋላ ነው፡፡ ደግሞም ሄኖክና ኤልያስ ቢያርጉ ዕርገታቸው ሞት አለበት፡፡ መሬታዊ ባሕርይ ካለው ፍጥረት ሞትን የማያይ፣ የማይታመምና የማይለወጥ የለምና፡፡ ሆኖም ግን ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ እንዲሁ ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ ከሰው ሁሉ ምስኪኖች ይህ ምሥጢር ተሠውሮባቸው ‹‹ዛሬ እንብላ እንጠጣ ነገ እንሞታለን›› በሚል ብቻ እምነታቸውን የወሰኑ ናቸው /1ኛቆሮ.15÷33/፡፡

    ሄኖክ ወደ ሰማይ ያረገው በምድራዊ ሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው ቅዱስ ሆኖ ስለተገኘ ነው፡፡ ‹‹ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለወሰደው አልተገኘም፡፡ ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና›› እንዲል /ዕብ.11÷5/፡፡ ይሁን እንጂ ሄኖክና መሰሎቹ በሐሳዊ መሲህ ዘመን በአካል ተገኝተው በርትዕት ሃይማኖት ክርስቲያኖች እንዲጸኑ፣ የጌታችንን የባሕርይ አምላክነት በመመሥከርና የመሲሑን ስሑትነት በመግለጥ በሰማዕትነት ይሞታሉ፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን ሄኖክ ቢያርግ የገባው ገነት ነው፤ ኤልያስም ቢያርግ የገባው ብሔረ ሕያዋን ነው፡፡ እመቤታችን ግን ብታርግ የገባችው መንግሥተ ሰማይ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዕርገቷን በዜማው ‹‹እመቤታችን በክብር ወደ ሰማይ ዐረገች›› ሲል ዘምሯል፡፡ ስለዚህ ትንሣኤዋም ሆነ ዕርገቷ እንደ ልጇ መሆኑን እናምናለን፡፡

    የጌታችንና የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ ሲነጻጸር ይመሳሰላል ቢባልም ግን የሚለያይበትም ምክንያት አለው፡፡ ጌታችን ከመቃብር የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ አልፎ አልፎ ‹‹እግዚአብሔር አስነሣው›› የሚል ቃል ይገኛል /ሐዋ.2÷32፣3÷15፣ሮሜ.4÷24፣10÷9፣1ኛ ቆሮ.15÷15/፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቅድስት ሥላሴ በሥልጣን አንድ መሆናቸውን ለማሳወቅ ነው እንጂ ጌታችን እንደ ፍጡር አስነሺ የሚሻ ሆኖ አይደለም፡፡ ራሱ ባለቤቱ «ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀንም አስነሣዋለሁ›› ብሏልና /ዮሐ.2÷19/፡፡ እንዲሁም «ነፍሴን ደግሞ አነሣት ዘንድ አኖራለሁና፡፡ ስለዚህ አብ ይወድደኛል እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ላኖራት ሥልጣን አለኝ ደግሞም ላስነሣት ሥልጣን አለኝ›› ብሏል /ዮሐ.10÷17-18/፡፡ ስለዚህ ጌታችን በራሱ፣ በባሕርይ አባቱ በአብ፣ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድና ሥልጣን ከሙታን ተነሣ፡፡

    እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ግን ከሙታን ተለይታ የተነሣችው በልጇ በወዳጅዋ በፈጣሪዋ በአምላኳ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን በመሆኑ አሥነሽ ትሻለች /ሽቷታል/፡፡ ጌታችን በኩረ ትንሣኤ በመሆኑ ከእርሱ በኋላ የሚነሡ ሁሉ እርሱን አብነት አድርገው በእርሱ ሥልጣን ይነሣሉ፡፡ እመቤታችን ግን ከጌታችን ቀጥላ ልጇን ወዳጅዋን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት አድርጋ ተነሥታለች፡፡ ሌላው የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ ከትንሣኤ ዘጉባኤ በፊት ከሰው ልጆች ሁሉ ቀድማ መነሣቷ ነው፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ ሰፊ ምክንያትና ትንታኔ ያለው ሲሆን ለአብነት ያህል ግን ሁለቱን እናያለን፡፡

    ሀ. የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ጥበበኛው ሰሎሞን ከመዝሙራት ሁሉ በሚበልጠው መዝሙሩ ላይ ‹‹ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይትየ ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኰኵሕ ቅሩበ ጥቅም፤ ወዳጄ ሆይ፣ ተነሺ ውበቴ ሆይ ነዪ፡፡ በዓለት ንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግቤ ሆይ፣ ቃልሽ መልካም ፊትሽም ያማረ ነውና›› /መኃ.2÷14/ ሲል አባቱ ዳዊት ደግሞ ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት›› ብሎ ነበር /መዝ.131÷8/፡፡

    አቤቱ ክርስቶስ ሆይ! ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት  በከርሠ መቃብር አድረህ መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል በኅቱም መቃብር በራስህ፣ በአባትህና በሕይወትህ ሥልጣን ከሙታን ተለይተህ ለምእመናን ትንሣኤ /ዕርገትን/ ወደምትሰጥበት ወደ መንግሥተ ሰማያት ተነሣ፡፡ አንተ ብቻህን አይደለም፤ የመቅደስህ ታቦት ማለት የሰውነትህ ማደሪያ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስን ተዋሕደህ ፍጹም ሰው ሆነህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን አንተ ጽላት ማኅፀኗን ታቦት አድርገህ ያደርክባት ቅድስት እናትህ ድንግል ማርያም ሌሎች በትንሣኤ ዘጉባኤ እንደሚሉት ማለትም መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳትል በኅቱም መቃብር በአንተ ሥልጣን ተነሣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ከጌታችን ቀጥላ ዳግም ምጽአትን ሳትጠብቅ ተነሥታለች፡፡

    ለ. የአዳም ዘር በሙሉ በዚህ ዓለም ለሠራው ደግም ሆነ ክፉ ሥራ ዋጋውን ለመቀበል በጌታችን ፊት ይቆማል /እንቆማለን/፡፡ ‹‹ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን»፤ ‹‹መልካምም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ እያንዳንዱ በሥጋው የሠራውን ብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናል›› እንዲል /ሮሜ.14.10፣2ኛቆሮ.5.10/፡፡ እመቤታችን ግን የፈራጁ አምላክ የኢየሱስ ክርስቶስ እናቱ በመሆኗ፣ ክብሯም ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን በላይ ስለሆነ በልጇ የፍርድ ወንበር ፊት አትቆምም፡፡ ስለዚህ እርስዋ ለአምላክ እናትነት የተመረጠችና የከበረች ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ እንተ አልባቲ ሙስና ናትና በልጇ የፍርድ ወንበር ፊት መቆም ስለማይገባት ትንሣኤዋ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት መጠበቅ አላስፈለገውም፡፡

    ይልቁንም ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ላይ ‹‹ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤ በወርቅ ልብስ ተጎናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች» በማለት ፍርድን ለመቀበል ሳይሆን ምሕረትን ለማሰጠት ስለእኛ እንደምትማልድ መስክሯል /መዝ.44.9/፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ በትንሣኤ ዘጉባኤ የእርስዋ ግብር መነሣት/መቆም/ ሳይሆን የልጇን ፍርድ ማየትና ማድነቅ መሆኑን ልናስተውል ይገባል፡፡ ስለዚህ አሁኑኑ በሃይማኖት በምግባር ጸንተን፣ ጌታችንን በሕግ በአምልኮ ተከትለን፣ እመቤታችንንም ተማጽነን እርስዋ ያለችበትን መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ ዝግጁ መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጣዕሟን በአንደበታችን፣ ፍቅሯን በልቡናችን ታሳድርብን፤ አሜን፡፡

     

                     ወስብሐት ለእግዚአብሔር

     

    ከአባ ሳሙኤል

     በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

    የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ

    አዲስ አበባ

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: የጌታችንና የእመቤታችን ምሥጢረ ትንሣኤ በቅዱስ መጽሐፍ ሲነጻጸር Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top