• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 6 November 2015

    ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም፡፡ መዝ 33/34/፡14

    በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

    ሰላም የሚለው ቃል ሰለመ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም የአእምሮ እረፍት፣ መግባባት፣ ውይይት፣ መመካከር ፣ የተረጋጋ ሁኔታ ያለበት ሲሆን ቅሬታ፣ ረብሻ፣ ሁከት ጦርነት የሌለበት ነው፡፡ ሰላም አንድ ሰው ሳይጨነቅ፤ ሳይታመም፤ ሳያዝን፤ በግሉም ሆነ ከሰዎች ጋር ስምምነት መኖርን ያመለክታል፡፡ ሰላም በንግግር፤ በአካላዊ እንቅስቃሴ ይገለጻል፡፡ ሰላም የተቀደሰ ከመሆኑ የተነሳ ቅዱስ ጳውሎስ በተቀደሰው አሳሳም ሰላምታ ተለዋወጡ እያለ ያስተምረናል፡፡ ሮሜ 16፤16፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሰላም ቅዱስና ከእርሱ የሚሰጥ መሆኑን እንዲህ ብሎ አስተምሯል፡፡ ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፡፡ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፡፡ ዮሐ. 14፤ 27

    በዚህ መሰረት ሰላምን የመሰረተ፤ ሰላምንም የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ፡-

    ሰላም ክርስቶስ ነው፡- 2ተሰ.3፤16 በመሆኑም በእሱ ያለንን እምነት በማጠንከር (ዮሐ.16፤33) አድርጉ ያለውንም በተግባር በመሥራት (1ኛ ጴጥ.12፤18) ሰላምን መጠበቅ ይገባል፡፡ አታድርጉ ያላቸውን አለማድረግ ይገባል፡፡ ኢሳይያስ በአንተ ታምናለችና በአንተ ለምትደገፍ ነፍስ ፈጽመህ በሰላም ትጠብቃታለህ፡፡ ኢሳ. 26፤3 እንዳለ ሰላማችን ክርስቶስን አምነን በትዕዛዙ መኖር ይገባል፡፡

    ሰላም ክርስቶስን መምሰል ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተ እኔን ምሰሉ ብሎ አስተምሮናል፡፡ ክርስቶስ አብነታችን ነውና ክርስቲያን የሆንን ሁሉ ሰላምን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡ በክርስቶስ የሚያምን ሁሉ ሊይዘው የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም ሰላምን የሚመሰርቱ እርቅን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፡፡ ማቴ.5፤9 ብሏልና አምላካችን፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በቅድስና በንጽሕና መኖር ይገባል ( ሮሜ. 15፤13፡ 1ቆሮ.14፤33)፡፡

    ሰላም የክርስቶስ ስጦታ ነው፡፡ በደሙ ያወጀልን ስጦታ ነው፡፡ ቆላ.1፤19 የሰላም ጠላት ዲያብሎስ ክፋትን፤ ተንኮልን ፈጥሯል ዘፍ.3፤1 በዲያብሎስ አማካኝነት የተፈጠረው ክፋትና ተንኮል እንዲጠፋ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም መጥቷል፡፡ ሰላምንም መልሷል፡፡ €œበመስቀሉ ሰላምን አደረገ፡፡ እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ቆላ 1፡19-20 መጠበቅ ስለ ሰላም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የሰላም ጠላቱ ዲያብሎስ በመሆኑ የሰው ልጆችም ጠላት ዲያቢሎስ በመሆኑ በዲያቢሎስ ተንኮል እንዳንወድቅ ሰላምን በእንክብካቤ መያዝና ሰላምን መጠበቅ ይገባል፡፡ ዲያቢሎስ ሰላም ስለሚያስጨንቀው ሰላምን ለማጥፋት ዘወትር ይተጋልና፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔርን ስጦታ ልንጠብቅ ልንከባከብ ይገባል፡፡

    ሰላም ስለሌሎች በማሰብና ለኛ የሚገባውን ለሌሎች በማደረግ ትጠበቃለች፡፡ አብርሃም አባታችን ሰላምን ይንከባከባት ነበር፡፡ አብርሃም ከሎጥ ጋር የነበረው ፍቅር እንዳይቀዘቅዝ፣ ሰላምንም እንዳያጣ ሰላምን ተንከባክቦ የዲያቢሎስንም ተንኮል በጥበብ አሸንፏል፡፡ ዘፍ 13፡5 €œበእኔና በአንተ መካከል ጠብ መነሣት የመለያየትና የመራራቅ መንፈስ መኖር የለበትም፡፡ እኛ ወንደማማቾች ነንና በእኔና በአንተ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ፡፡ . . . ወንድሜ ሆይ ምድር በፊትህ አይደለችምን አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ፡፡ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ግራውን እወስዳለሁ€� በማለት በምድር ከሚገኘው ሀብት፣ ንብረት፣ብዕል በላይ ከወንድም ጋር ሰላም መሆን እንደሚበልጥ አውቆ ሰላምን ጠበቃት፡፡ ያውም ሰው ሳይበዛ የምድር ሀብትም ሳይነካ፡፡

    ሰላም የመንፈሰና የጽድቅ ፍሬ ተብሎ የተገለጸ ነው፡፡ ይህን ፍሬ ያላቸው ሰዎች ለጽድቅ የሚበቁ መሆኑን ተገልጾ በዲያብሎስ የተፈጠረው ተቃራኒው ፀብ፣ ጥላቻ፣ ክፋት ደግሞ የሥጋ ሥራ ተብለው ተገልጸዋል፡፡ ፀብን፣ጥላቻን፣ክርክርን የሚያደርጉ መንግሥተ ሰማይ እንደማይገቡ ይገልጻል፡፡ገላ 5፡19-22

    እንደ ልቤ ተብሎ በእግዚአብሔር የተመረጠውና ገና በልጅነቱ በሰላም ተረጋግርቶ መኖር እና በክፉዎች ምክንያት ደግሞ ሰላምን አጥቶ መንከራተት የተፈራረቁበት ቅዱስ ዳዊት ስለ ሰላም ሲናገር ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ፡፡ ሰላምንም እሻ መዝ34፡14 ሲል የሰላምን ጥቅም የክፋትን ጐጂነት አስረድቷል፡፡

    ሰላም ሲኖር የሰው ልጅ እድሜው በምድር ይረዝማል፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረትም ይኖረዋል፡፡ ሰላም በጋራ ለምንኖርባት ዓለም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊ ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው፡፡ ሰላም ከሌለና ክፋት ከነገሠ፤ ሰው መረጋጋት አይችልም፡፡ ተኝቶ እረፍት አያገኝም፡፡ ሠርቶ አይረካም፡፡ እድሜውም ያጥራል፡፡ ሰዎች የእርስ በእርስ ሰላም ከሌላቸው አንዱ አንዱን ይቀማል፡፡ አንዱ አንዱን ይገድላልâ€Ãƒ‚¦፡፡ የቃየልን ግብር ይፈጸማል፡፡ ጦርነት፣ ስደት፣ ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ዳዊት የክፋት ውጤቱ በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ፣ በሀገር፣ በዓለም ለይ የሚያስከትለውን ጉዳት በዘመኑ ተረድቶ፣ በትንቢት መነጽር ተረድቶ “ሰላምን እሹ ፈልጓትምâ€� ያለው፡፡

    በጥንተ ተፈጥሮ ተሰጥታን የነበረችውን ሰላም፡፡ አዳም አባታችን በዲያብሎስ ሲቀማ ሰላምን ለመመለስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲወለድ ሰላም አጥተውና ተለያይተው የነበሩት ስውና መላእክት ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፡፡ ሰላምም በምድር ለሰውም በጐ ፈቃድ€� ሉቃ2፡14 እያሉ የሰላምን መመለስ አብስረዋል፡፡ ሰላም ቅዱስ ስለሆነ ይዘመርለታል፡፡

    ጌታችን ሐዋርያትን የሰላምንና የወንጌልን መልእክት ይዘው ለዓለም እንዲያበስሩ ሲልካቸው €œወደምትገቡበት ሀገር ሁሉ አስቀድማችሁ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን በሉ፡፡ በዚያም የሰላም ልጅ ቢኖር ሰላማችሁ ያድርበታል€� ሉቃ 10፡5-6 በማለት የእግዚአብሔር ሰላም ለሰው ልጆች አስፈላጊና ለሚፈልጉትና ለሚጠቀሙበት የሚበዛ መሆኑን ያስረዳል፡፡

    ነህምያ ከሀገሩ ኢየሩሳሌም ተማርኮ ወደ ሱሳ ተሰዶ ሳለ ሰላም አጥቶ ይጨነቅ ነበር፡፡ የኅሊና እረፍትም ማግኘትም አልቻለም፡፡ የሀገሩ ናፍቆትና የሀገሩ ፍቅር ሰላም ማጣት አስጨንቆት ሲኖር ሳይማረኩ የነበሩ የይሁዳ ሰዎች እሱ ወዳለበት ሲመጡ €œኢየሩሳሌም እንዴት ናት? ብሎ ጠየቃቸው የተጠየቁት ከምርኮ የተረፉት እስራኤላዊያን €œኢየሩሳሌም ቅጥሯ ፈርሷል፡፡ ሕዝቡም በመከራ ላይ ነው €�ብለው ነገሩት፡፡ነህምያ አለቀሰ መፍትሔው ሰላምን ወደሚሰጠው አምላክ ማልቀስ ማዘን ነውና ለአምላኩ ሐዘኑን በለቅሶ ነገረ፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎቱን ሰምቶት የተማረከበት ሀገር ንጉሥ ኢየሩሳሌምን እንዲሠራ ፈቅዶለት የኢየሩሳሌምን ቅጥር ሠርቷል፡፡ ሕዝቡንም አጽናንቷል፡፡ ሰላምንም አግኝቷል፡፡ ነህ 2፡1-8 ስለዚህ ለምንጊዜም ቢሆን በሀገር በሕዝብ መሐከል ሰላም ሲጠፋ የሰላም ምንጭ የሆነው እግዚአብሔርን መማጸን ተገቢ መሆኑን ያስረዳል፡፡

    የሰላም ጥቅም

    ሰላም ከእግዚአብሔር ይቅርታ የምናገኝበት ነው፡፡ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ የሰማ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ያላችኋል፡፡ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ የሰማይ አባታችሁ ይቅር አይላችሁም፡፡ ማቴ. 6፤14-15 ይህ በመሆኑ ስለሰላም ሲባል ይቅር መባባል ለራስም ከእግዚአብሔር ይቅርታን ያስገኝልናል፡፡ ከሰዎች ጋር ኅብረት አንድነት ሰላም ሲኖረን ስለ ሰላም ስንል ይቅር የምንል ከሆነ እግዚአብሔር እኛም የሠራነውን ኃጢአት ይቅር ይለናል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሰላም ትልቅ ሀብት ስለሆነ ነው ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ ሮሜ.12.18 በማለት አስተምሯል፡፡

    ሰላም አምላክን የምናይበት መነጽር ነው፡-ዕብ.12.14፡፡ ቅዱስ ዳዊት ሕግህ ለመንገዴ ብርሃን ነው እንዳለ ከእግዚአብሔር ጋር ከሆንን ሰላም አለን፡፡ ሰላም ካለን ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ይኖረናል፡፡

    ሰላም ከእግዚአብሔር ብጽዕናን ያሰጣል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብጹዓን ትምህርቱ €œሰላምን የሚመሰርቱ ዕርቅን የሚያደርጉ ብጹዓን ናቸው€� ማቴ 5፡9 በማለት ሰላም ወደ ብጽዕና የሚያደርስ መሆኑን አስተምሯል፡፡ በዚህም መሠረት ቤተክርስቲያን በሕዝቧ መካከል ሰላምን የመመስረት ሥልጣን ስላላት ሰላም እንዲመጣ በመጸለይና ሀብተ ክህነት በሰጠቻቸው ካህናት አማካኝነት ለልጆቿ ብሎም ለዓለሙ ሁሉ የሰላም መልእክት እንዲደርስ ታደርጋለች፡፡

    ሰላም ግጭትን የማስወገጃ መሣሪያ ነው፡፡ ዕርቅና ሰላም ግጭትን የማቆም ታላቅ መሣሪያ ነው፡፡ በጥበብ በደግነት የተነገረች ምላስ /ንግግር/ ቁጣን ታበርዳለች እንዳለ ጠቢቡ፡፡ የአንድ ቀን ጽንስ፣ የአንድ ቀን ልደት የነበራቸው ያዕቆብና ዔሳው በመካከላቸው የነበረው ጠብና አሳዳጅነት መፍትሔ ያገኘው በሰላም ነው፡፡ ዘፍ27፡41-46 ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም €œሰላምን ትቶ ወንድሙን የሚጠላ በጨለማ ይገኛል€� ዮሐ 2፡11 እንዳለው የጨለማን መንገድ ትቶ ወደ ብርሃን መንገድ ወደ ሰላም መመለስ ያስፈልጋል፡፡

    ሰላም ከእግዚአብሔር የተሰጠ ጸጋ ክፋት ደግሞ ከዲያብሎስ የመጣ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የተሰጠንን ጸጋ ጠብቀን የዲያብሎስን ሸንገላ ተቋቁመን በዚች አጭር ዘመናችን ከታመንን በምድር ሳለን የእግዚአብሔር ሰላም አይለየንም፡፡በምድር እድሜያችን ይረዝማል በሰማይም መኖሪያ ይዘጋጅልናል፡፡ ስለ ሰላም ተረድተን በጥንቃቄ ከኖርን የሰላም አምላክ ከእኛ ጋር ይሆናል፡፡ ስለሀገር፣ ስለሃይማኖት፣ ስለማኅበረሰብ ስለ ግለሰብ ሰላምም እንጨነቃለን፡፡ €œበቀረውስ ወንድሞች ሆይ ደህና ሁኑ ፍጹማን ሁኑ ምክሬን ስሙ በአንድ ልብ ሁኑ በሰላም ኑሩ የፍቅርና የሰላም አምላክ ከእናንተ ጋር ይሆናል€� 1ቆሮ፡1-2

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ከክፉ ሽሽ መልካምንም አድርግ ሰላምን እሻ ተከተላትም፡፡ መዝ 33/34/፡14 Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top