• በቅርብ የተጻፉ

    Friday, 13 November 2015

    እንደ ሙሴ ያለ መሪ ክፍል 2


    በክፍል አንድ ለማየት እንደሞከርነው የሊቀነቢያት ሙሴ ህይዎት ለብዙዎቻችን የሚያስተምረው በጎ ነገር እንዳለ ለመረዳት እንደቻልን እገምታለሁ። ዛሬም በክፍል ሁለት ከሱ ህይዎት ተነስተን በእኛ ህይዎት ሊኖር ስለሚገባው ነገር  ለማየት እንሞክራለን ስለሁሉም የአምላክ ቸርነት የወላዲተ አምላክ አማላጅነት ከሁላችን ጋራ ይሁን።

     1/ የሙሴ ትህትና

    ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ከሰው ወገን እንደ ሊቀነቢያት ሙሴ ያለ ትሁት ሰው አልነበረም <<ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅእጅግ ትሑት ሰው ነበረ። ዘኁል 12፥3

    ትሁት ማለት ለበ ጎ ነገር የሚፋጠን ትንሹን ትልቁን በእኩል የሚያይ ማለት ነው። ከዚህም በላይ እራሱን ከሁሉ የበታች አድርጎ የመቁጠር ጸጋ ነበረው። ለዚህም ነው በኦሪት ዘጸ 4፥10  ላይ ለህዝበ እስራኤል መሪ እንዲሆን እግዚአብሔር በመረጠው ጊዜ  <<  ጌታ ሆይ፥ እኔ አፌ ኰልታፋምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ ትናንት ከትናንትወዲያ ባሪያህንም ከተናገርኸኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰውአይደለሁም >> ብሎ የተናገረው። 

    እግዚአብሔር አምላክ የህዝበ እስራኤልን መከራና ስቃይ ተመልክቶ ነጻ ሊያወጣቸው በፈቀደ ጊዜ፤ ሙሴ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ህይዎት ነበረው። ስለዚህም ለህዝቡ መሪ ሆኖ ከግብጽ ባርነት ነጻ ያወጣቸው ዘንድ መረጠው ። በዚህ ጊዜ ወደ ፈጣሪው በትህትና በመቅረብ እራሱን አዋርዶ መሪነት አይገባኝም ከኔ ሌላው ይሻላል እኔ ያንተን የገናናውን አምላክ ህዝብ ለመምራት አቅሙ የለኝም ምላሴም ኮልታፋ ነው የሚጎድለኝ ነገር አለ ብሎ መለሰ ። ከዚያም በኦሪት ዘጸ 4፥11 ላይ ወንድምህ አሮን ነቢይ ይሆንልሃል አንተም በእግዚአብሔር ፋንታ ትሆንለታለህ እኔም ከእናንተ ጋራ እሆናለሁ በፈርኦን ፊት ታላላቅ ተአምራትን የምታደርግባትን በትር በእጅህ ይዘሃት ሂድ ብሎታል።

    የሙሴ ትህትና ለሃይማኖት መሪው፣ ለሃገር መሪው፣ ለቤተሰብ አስተዳዳሪው ወ ዘ ተ የሚያስተምረው ብዙ ነገር አለ ። የሱን ህይዎትመርህ አድርገው ብዙ ቅዱሳን አባቶቻችን እናቶቻችን እግዚአብሔርን በመፍራትና እራሳቸውን ዝቅ በማድረግ እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተዋል ጥበበኛው እንዳለው  <<  ትሕትናና እግዚአብሔርንመፍራት ባለጠግነት ክብር ሕይወትም ነው ምሳ 22፥4  >> በሚለው ቃል ተመርተው ሰማያዊ ክብርንና ባለጠግነትን አጝኝተዋል።

     

    እግዚአብሔር ለሰው ልጆች አስቀድሞ በነቢያቱ እንደተናገረው በህይዎት ስንኖር በትህትና እና በይቅርባይነት ልንኖር ይገባል። ነቢየ እግዚአብሔር ሚክያስ << ሰው ሆይ፥መልካሙን ነግሮሃል እግዚአብሔርም ከአንተዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድአይደለምን? ሚክ 6፥8 >> ይለናል ፤ ዛሬ ከሰው ልጆች ዘንድ የጠፉትን ትህትናን እና ይቅርባይነትን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፦ ከሊቀነቢያት ሙሴ ህይዎት የምንማረው ትህትናንና ስለእግዚአብሔር ክብር ይቅር ማለትን ነው። ይህም በእህቱ በማርያምና በወንድሙ በአሮን የገጠመውን ፈተና በትእግስት፣ በይቅርባይነት እና በትህትና እንዳሳለፈው እናያለን    ዘኁል 12፥1 በዚህም የተነሳ እግዚአብሔር ስለሙሴ ክብር በግልጽ ተናግሮለታል በእሱ ላይ የማይገባ ነገር የተናገሩትንም አሮንን እና ማርያምን ገስጿቸዋል ይህም የሚያሳየው የሙሴ ህይዎት ምን ያህል በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ እንደነበረ ነው።

     

    እንደሙሴ ያለ መሪ ይስጠን ስንል ከእኛም የሚጠበቀውን ለማድረግ በቅንነትና በትህትና ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ ልቦና ይዘን ልንጘኝ ይገባል። ካለፈው ተምረን የንስሃን ህይዎት ልንመርጥ ያስፈልጋል።  << እናንተፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፥እግዚአብሔርን ፈልጉ ጽድቅንም ፈልጉ፥ትሕትናንም ፈልጉ ምናልባት በእግዚአብሔርቍጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል። ትን ሶፎ 2፥3 >>

     

    ህዝበ እግዚአብሔር እስራኤል ለብዙ ዘመናት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ሥራ ሲሰሩ ክፉ መሪ ይነሳባቸው ነበር፤ በንስሃ ወደ እግዚአብሔር ሲመለሱ ደግሞ እንደሙሴ፣ እንደኤልያስ፣ እንደ ሳሙኤል ያሉ መሪዎችን ይሰጣቸው ነበር ከዚህ የምንማረው መልካም መሪ ለማግኘት ለእግዚአብሔር የምንመች ህዝቦች ሆነን መገኘት ይገባናል። አለበለዚያ መልካም መሪ ቢነሳም መልካምነቱ ሊታወቅ አይችልም ። ብዙ ጊዜ በኛ በኩል የሚታየው ችግር የሌላውን ስጦታና ክብር አለመቀበል ነው። የችግራችን ምንጭ ከኔ ይልቅ እሱ ይሻላል አለማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ << ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱይልቅ እንዲሻል በትህትና ይቍጠር፤ ፊልጵ 2፥3 >>    ይላል በኛ ዘንድ ያለውን ችግር ስንመለከት ደግሞ ሁሉ እኔ ብቻ ነኝ አዋቂ ማለቱ ነው። ስለዚህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚመራ ህይዎት ሊኖረን ነው የሚገባው። እንደ ጥንቱ እንደ አባቶቻችን ትህትናንና እግዚአብሔርን መፍራትን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል። ከኔ የሚጠበቀው ምንድነው? ብለን እራሳችንን በመጠየቅ በእድሜያችን ልናደርገው የሚገባውን እንደ ህጉ ማድረግ አለብን። ሁሉ እንደሚገባው ቢያደርግ ሁሉ ነገር ይስተካከላል። <<እንዲሁም፥ ጐበዞች ሆይ፥ ለሽማግሌዎችተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በርሳችሁእየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፥እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፥ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል። 1ኛ ጴጥ 5፥5 >>

     

    ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ስለ ትህትና በቃልም ሆነ በተግባር በሰፊው አስተምሯል  በዮሐ 13፥4  ላይ የሐዋርያትን እግር በማጠብ ትህትናን ካሳያቸው በኋላ እኔ እዳደረኩላችሁ እናንተም እንዲሁ ለሌላው አድርጉ ብሎ አስተምሯቸዋል። እግዚአብሔር በትህትና ሆነን ወደሱ ስንቀርብ በእኛ ደስ ይለዋል። በምህረትም ይመለከተናል  እራሱን ዝቅ አድርጎ ወደ እርሱ የቀረበ ከፍ ከፍ ይላል። በሉቃ 14፥11  ራሱን ከፍ የሚያደርግሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱንም የሚያዋርድ ከፍይላል። ተብሎ  እንደተጻፈው በትህትና የሚገኘው ክብር እጅግ ብዙ ነው።  

     

    ይቀጥላል-----------------

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: እንደ ሙሴ ያለ መሪ ክፍል 2 Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top