• በቅርብ የተጻፉ

    Thursday 5 November 2015

    በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ


    ነሥአ ደዌነ ወፆረ ሕማመነ የእኛን ደዌ ተቀበለ ሕመማችንንና ኃጢአታችንን ተሸከመ ስለ መተላለፋችን ሕጉንና ትእዛዙን በማፍረሳችን ስለ እኛ ቆሰለ፣ ስለ በደላችን ደቀቀ፣ ማለትም ሥጋውን ቆረሰ ደሙን አፈሰሰ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፣ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከሲኦል ወደገነት ከውርደትና ከኃሳር ወደክብር ተመለስን፡፡ የዓለምን ሁሉ መድኃኒት የሁላችን ዕዳ፣ ፍዳና በደል በእርሱ ላይ አኖረ (ኢሳ. 53÷4-5)

    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮቱ ስቃ ሳይኖርበት እኛን ከሥቃይ ለማዳን ሲል በለበሰው ሥጋ ተጨነቀ፣ ተሠቃየ፣ ለመታረድ እንደሚነዳ በግ (ጠቦት) በሽላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል ይህ ሁሉ መከራ በእርሱ ላይ ሲፈጸም ስቃዩ በዛብኝ መከራው ፀናብኝ ብሎ አልተናገረም፣(አፉን አልከፈተም) ይልቁንም ስለሕዝቡ ኃጢአት ተገርፎ ተሰቅሎ ነፍሱን ከሥጋው ለየ፡፡

    ይህን ከባድ ስቃይና መከራ ሲፈጽሙበት በሰውነቱ ስህተት በአንደበቱ ሀሰትና ተንኮል አልተገኘበትም (ኢሳ. 53÷7 ይህን መከራ ሲቀበል በሰውነቱ ስህተት በአንደበቱ ያልተገኘበት አምላክ ከመከራ ከፈተና ያድነን ዘንድ በጐ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ አሜን 

    ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጠን (ቆላ. 2÷13)

    አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ቀርባችኋል በአባታችን በአዳም በደል አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የሰውና እግዚአብሔር ግንኙነት ተቋርጦ ስለነበረ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ሰውና እግዚአብሔር መታረቁን ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተማረ፡፡ ሐዋርያው ያስተማረው ይህን ብቻ አይደለም እርሱ ሰላማችን ነውና ሁለቱን ያዋሐደ የጥልንም ግድግዳ በምቱ ያፈረሰ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ ሁለቱንም በእርሱ አንድ ያደረገ ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን ቀርበው ለነበሩት ሰላምን የምስራችን ሰበከ፣ (ኤፊ. 2÷14–18)፡

    እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሙታን በሆናችሁ ጊዜ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፣ በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ፣ በእኛ ላይም የተጻፈውን የእዳ ደብዳቤ ደመሰሰው፣ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡ (2ቆላ. 13÷15)፡፡

    ከዚህ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ተጠማ በቸርነቱ የሚያጠጣ የደከመውን የሚያበረታ አምላክ ተጠማሁ አለ ለእሥራኤላውያን ከደረቅ አለት ውኃ ያጠጣ አምላክ መናን ከደመና አውርዶ የመገበ አምላክ ስለሰው ልጅ ብሎ ተጠማሁ አለ፡፡ በዚህም ሆምጣጤ የሞላበት መራራ ዕቃ “ተቀምጦ ነበር በሰፍነግ ሞልተው ወደአፉ አቀረቡለት ኢየሱስም ከርቤ የተቀላቀለበት ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ተፈጸመ አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ” (ዮሐ. 19÷28-31)፡፡

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ሳለ ሰባቱ (አጽርሐመስቀል) የተናገራቸው ቃላቶች

     

    ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ፡- ይህ አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውኸኝ ማለት ነው፡፡ (ማቴ. 27÷46)አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው (ሉቃ. 23÷34)፡፡እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ (ሉቃ. 23÷43)፡፡አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ (ሉቃ. 23÷46)ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱን አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ አላት ደቀመዝሙሩን እነሆ እናትህ አለው (ዮሐ. 19÷27)፡፡ተጠማሁ (ዮሐ. 19÷29)፡፡ተፈጸመ አለ ራሱን አዘንብሎ ነፍሱን ሰጠ (ዮሐ. 19÷30)፡፡

     

    ኦ አእዳው እለ ለሐኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል አዳምን የፈጠሩ እጆች ወዮ በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ በገነት የተመላለሱ እግሮች ወዮ በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ፡፡ በአዳም ፊት የሕይወትን መንፈስ እፍ ያለ አፍ ወዮ ከሐሞት ጋር የተቀላቀለ መጠጥንና ከርቤን ጠጣ፡፡

    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ በሰማይና በምድር የተፈጸሙ ሰባት ተአምራት፡-

    በሰማይ የተፈጸሙ ሦስት ተአምራት፡-

    ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ላይ ፀሐይ ጨለመ (ሉቃ. 23÷44)፡፡ጨረቃ ደም ሆነ፣ከዋክብት ረገፉ

     

    በምድር የተፈጸሙ አራት ተዓምራቶች

    የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከሁለት ተቀደደዓለቶችም ተሰነጠቁመቃብሮችም ተከፈቱሞተው ከነበሩት ከቅዱሳን ሰዎች ተነሡ (ማቴ. 27÷51)፡፡

    ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን (ሮሜ.5÷10)፡፡

    እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ አክብሮ በመልኩ ከፈጠረው በኋላ ሕግ ሠራለት፡፡ ሰውም የተሰራለትን ሕግ አፈረሰ፤ በዚህ ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ጥላቻዎች ተመሰረቱ፣ በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ በርደተ መቃብር ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ሲኖር ይቅር ባይና ቸር አምላክ የሰውን ንስሓ ተቀብሎ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጁን ወደዚህ ዓለም ላከው (ዮሐ. 3÷16-18) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነስቶ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለእናት ድኀረ ዓለም ከእመቤታችን ያለአባት ተወለደ በመወለዱ ጥልን አፈረሰ እርቅን መሠረተ፡- “ሐመ ከመ ሕሙማነ ያድኅን” የታመሙትን ያድን ዘንድ ታመመ፡- የተፍገመገሙትም ያጸናቸው ዘንድ የሞቱትንም ያድናቸው ዘንድ ሞትን ይሽረው ዘንድ የሰይጣንን  ማሰርያ ይቆርጥ ዘንድ በፈቃዱ ሁሉም ሆነ፡፡

    በሰውና በእግዚአብሔር እርቅ ተመሠረተ (ዮሐ. 1÷14)፡፡የሰውና የመላእክት ማኅበር ተመሠረተ (ሉቃ. 2÷8)፡፡የሕዝብና አሕዛብ መገረዝና አለመገረዝን እርቅ ተመሠረተ (ቆላ. 2÷11-12)፡፡ሕይወትን ሰጠ፣ ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍስና ሥጋን ለያይቶ ሥጋን በመቃብር አበስብሶ ነፍስን በሲኦል ተቆራኝቶ ለማኖር አስቦ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እነዚህን አንድ አድርጐ በመንግሥተ ሰማያት ለማኖር ፈቀደ (1ኛ. ተሰ. 4÷14)፡፡

    “ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር በሌላ አልመካም/ገላ. 6÷14”

    ትምክሕት፡- “ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር በሌላ አልመካም” ወይም “ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክሕት ከእኔ ይራቅ፤” የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ አነጋገር አንድ ሀሳብና አንድ ግብ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም በክርስቶስ መስቀል ብቻ መመካትና ደስታ ማድረግ ነው፡፡

    በእርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ በሌላ ቦታ በማንና በምን መመካት እንደሚቻል ተናግሯል፤ “በእግዚአብሔር ክብር ተስፋ እንመካለን፡፡” (ሮሜ. 5÷2) “መከራ ትዕግሥትን እንደሚያደርግ፤ ትዕግስትም ፈተናን፤ ፈተናም ተስፋን እንደሚያደርግ እያወቅን በመከራችን እንመካለን፡፡” (ሮሜ. 5÷3) “የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ፡፡” (2ኛ ቆሮ. 12÷9) “ትምክሕት የሚያስፈልግ ከሆነ እኔም በድካሜ እመካለሁ፡፡” (2ኛ. ቆሮ. 11 ÷30) “ተስፋችን ወይም ደስታችን ወይም የትምክሕታችን አክሊል ማን ነው? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እናንተ አይደላችሁምን?” (1ኛ. ተሰ. 2÷19)፡፡

    ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሱት ነገሮች መመካት በክርስቶስ መስቀል ከመመካት መራቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእግዜአብሔርን ክብር ተስፋ ማድረግ፣ መከራን መቀበልና በወንጌል አገልግሎት ሁሉን ትቶ መስቀሉን ተሸክሞ በእውነት መከተል ነው፡፡ በመስቀል ላይ የተፈጸመውን ድኀነት በአንድ ሐዋርያ ላይ  ሊደርስ የሚችለው በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስ በሚሰብክበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሐሰተኞች መምህራንን ለማሳፈር እንደ ዓለማውያን በዓለማዊ ነገር ለመመካት የሞከረበት ጊዜ መኖሩ በሚከተለው አነጋገሩ ይታወቃል፡፡ ብዙዎች በዓለማዊ ነገር ስለሚመኩ እኔ ደግሞ እመካለሁ፡፡ (2ኛ ቆሮ. 11÷18) ይህንንም በግልጥ ሲያስረዳ እንዲህ ይላል እነዚህ ዕብራውያንና እስራኤላውያን፣ የአብርሃም ዘሮች፡-

    እንደዚሁ የተገረዙ ቢሆኑ እኔም እንደ እነርሱ ዕብራዊ፣ እስራኤላዊና የአብርሃም ዘር ነሀን፤ በስምንተኛ ቀን የተገረዝኩ ነኝ ከሁሉም እኔ እበልጣለሁ፤ ኦሪትን ጠብቄአለሁ፤ ለኦሪት ቀናተኛ ነበርሁ፤ በኦሪት ስለሚገኘው ጽድቅ ያለ ነቀፋ ነበርኩ፡፡ (ፊል. 3÷5-6)፡፡

    ነገር ግን ይህ ዓይነቱ ትምክሕት ይላል ቅዱስ ጳውሎስ በተለይ ለመንፈሳዊያን ሰዎች ከእግዚአብሔር አይደለም፤ አይጠቅምም፤ ዕብደት ወይም ስንፍና ነው፤ ከንቱ ወይም ኢምንት ነው፤ እንደ ጉድፍም ነው፡፡ ስለዚህ ከመስቀሉ በቀር በሌላ አልመካም እናከብረው እና እንደፀጋው ባለጠግነት መጠን በደሙ የተደረገልን ቤዛነታችንን አገኘን እርሱም የበደላችን ስርየት ነው፡፡

    በመስቀሉ ላይ በተሰቀለው በእግዚብሐር ወልድ ድነናል (ኤፌ. 1÷7፤ 1ኛ ጴጥ. 1÷19)በመስቀሉ ክርስቶስ ወደ ራሱ አቅርቦናል፤

    በሰማያት ወደ አባቱ አቅርቦናል፤ (ዮሐ. 12÷32፤ ኤፌ. 2÷13፤ ኪዳን፡፡)

    አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በኃጢአት ምክንያት፣ በበደል ምክንያት በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል፡፡በመስቀሉ ደም ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል፤ ሰላምን አግኝተናል፤ (ቆላስ. 1÷20-21፣ ሮሜ. 5÷10)፡፡በጌታችን በአምላካችን ወደቆምንበት ወደዚህ ጸጋ በእምነት አግኝተናልበመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ ጽድቅን፣ ቅድስናንም ቤዛነትን አግኝተናል፤ (ሮሜ. 5÷2፣ 1ኛ ቆሮ. 1÷31፣ ዕብ. 10÷10፣ 13÷12)በመስቀሉ ለዘለዓለም ፍጹማን ሆነናል፣ (ዕብ. 10÷14)በመስቀሉ የዕዳ ደብዳቤያችን ተደምስሶአል፣ (ቆላስ. 2÷14)በእኛ ላይ የነበረውን የተጻፈውን የእዳ ደብዳቤ ጽሕፈት ደምስሶ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፡፡በመስቀሉ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ሞገስን አግኝተናል፤ (ዕብ. 10÷19)በመስቀል ላይ በፈሰሰ ደሙ ከበደላችን ሁሉ ታጥበናል፣ (ራዕ. 12÷11)በመስቀል አዲስ ኪዳን ተመስርቶአል፣ (ሉቃ. 22÷20)ወይቤ ተፈጸመ ኩሉ፡፡ጌታችን ሁሉ ተፈጸመ ብሎ እንደተናገረ ስለ ሰው ልጆች መዳን በመጻሕፍት የተነገረው ሁሉ በመስቀል ላይ ተፈጽሟል፣ (ዮሐ. 19÷18)፡፡ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ ሁለቱን ወገኖች አይሁድና አሕዛብ አንድ አድርጐ ከራሱ ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው፡፡ (ኤፌ. 2÷16)በመስቀል ላይ ስለተደረገልን ነገር የእኛ መልስ ምንድን ነው?

    ከሁሉ በፊት ከእኛ የሚፈለገው በወደደንና ስለ እኛ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ በማመን በሃይማኖት መኖር ነው (ገላ. 2÷20) ምክንያቱም አሁን በሥጋ የምንኖርበት ጊዜ ስለእኛ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ነውና፡፡

    ምንተኑ አዐስዮ ለእግዚአብሔር በእንተ ኩሉ ዘገብረ ሊተስለ ተደረገልን ሁሉ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ (መዝ. 115÷3-4)ይህን ስለአደረገልን ምን ወረታ እንከፍለዋለን ጽናት አግኝተናልና፡፡ከመስቀሉ በቀር በሌላ አለመመካት፣ (ገላ. 6÷14)ከተሰቀለው ክርስቶስ በቀር ሌላ አዳኝ አለመኖሩን በእርግጥ ማመን፣ (1ኛ. ቆሮ. 2÷2)ስለ እኛ በመስቀል ላይ መከራ የተቀበለውን የክርስቶስን ፍለጋ መከተል፣ (1ኛ. ጴጥ. 1÷21)መንፈሳዊውን ነገር በሚያስተምረን የእግዚአብሔርን ቃል የተሰቀለውን ክርስቶስን መስበክ፣ (1ኛ. ቆሮ. 1÷13)ሞቱን እስከ ዳግም ምጽአት ማወጅ፣ (1ኛ. ቆሮ. 11÷26)በመስቀል ላይ ለድኀነት የፈሰሰውን ቅዱስ ምስጢር በእምነት መቀበል ከእኛ ይፈልጋል፡፡ (ማር. 14÷22-25)በሰውና በእግዚአብሔር መካከል እርቅ ተመሰረተ (ዮሐ. 1÷14)የሰውና የመላእክት እርቅ ተመሠረተ (ሉቃ. 2÷8)የሕዝብና አሕዛብ መገረዝና አለመገረዝ እርቅ ተመሠረተ (1ኛ. ቆሮ. 6÷6፣ ሮሜ 8÷6)ሕይወትን ሰጠ፣ ጠላታችን ዲያብሎስ ነፍስና ስጋን ለያይቶ ሥጋን በመቃብር አበስብሶ ነፍስን በሲኦል ተቆራኝቶ ለማኖር አስቦ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን እነዚህን አንድ አድርጐ በመንግሥተ ሰማያት ለመኖር ፈቀደ (1ኛ. ተሰ. 4÷14)አቤቱ የእግዚአብሔር ልጅ ሆይ! ካንተ ጋር በምንኖርበት ጊዜ ምን ያህል ደስተኞች ነን!በዚህ ታላቅ ክብር ያሉ የእግዚአብሔር ልጆች ምንኛ ደስተኞች ናቸው!አብሮን የሚኖር ክብርህ፣የመለኮታዊ ክብርህ ተሳታፊነታችን፣ ደስታችንን ዕጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ ይህን የተናገርህ አንተ ነህ፡፡ “የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳን ሕያው ይሆናል ብለሀልና” ዮሐ. 11÷25፡፡ስለዚህ አንተን በመጥራት እንከተልሀለን፡፡ “በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸነፊዎች እንበልጣለን፡፡” ሮሜ. 10÷32“ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፡፡ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም፡፡ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፡፡” ገላ. 2÷20

    በመስቀል ላይ በተደረገው የማዳን ሥራ ውስጥ መለኮትና ትስብእት በተዋሕዶ ባይገለጥ ኖሮ የተደረገው  የድኀነት ሥራ ከንቱ ይሆን ነበር፡፡ በድኀነት የመለኮትና የትስብእት ድርሻ በተዋሕዶ ምሥጢር ብቸኛ ነው፡፡ ዓለምን ለማዳን ከኀጢአተኞች ጋር ተሰቀለ፡፡ ኢሳ. 93 ሜቴ. 23÷38፡፡

    ባለ ዘመናችን በደላችንና ኃጢአታችን ትዝ እያለን ንስሓ በመግባት የጌታችን ቅዱስ ሥጋውን በመቀበል ክቡር ደሙን በመጠጣት ከእርሱ ጋር ለመኖር ተጠርተናል፣ እርሱ “ሥጋዬን የበላ ደሜንም የጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ እኖራለሁ፡፡” ብሏል (ዮሐ. 6÷56)

    “ከእግዚአብሔር አብ ከመድኃኒታችንና ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን፡፡” ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለቲቶ መልእክት ሲጽፍ በመግቢያው ላይ የሰጠው ቡራኬ (ቲቶ 1÷4-11)

    እግዚአብሔር የሚለው የባሕርይ ስም ምንም እንኳ የሦስቱ የአብ የወልድና የመንፈስ ቅዱስ ስም ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ በሐዋርያው በቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ለአብ ብቻ ተሰጥቶ ይገኛል፡፡ ስለዚህም መነሻ ጥቅስ በሆነው በዚህ ርእስ ሐዋርያው ለቲቶ ቡራኬ ሲሰጥ “ከእግዚአብሔር አብ” ከአለ በኋላ “ከመድኃኒታችን ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ” ብሏል፡፡ ጳውሎስ ይህን ሲጽፍ “ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አይደለም” ሊል ፈልጎ አይደለም፡፡ ጌታ ማለት እግዚአብሔር ማለት ስለሆነ፤ እግዚአብሔር ማለትን ጌታ በማለት ስለተካው ነው፡፡

    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተሰቅሎ ሞቶ ዓለምን ያዳነ ስለሆነ፣ መድኃኒት፣ መድኃኔዓለም፣ ኢየሱስ ይባላል፡፡ ስለዚህም መድኃኒታችን ብሎ አዳኝነቱን በቅጽል ስም አንስቷል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ በባሕርዩ የሰማይና የምድር ንጉሥ ነው፤ ክርስቶስ ተብሏል ክርስቶስ የሚለውም ስም ንጉሥነቱን የሚገልጽ ስም ነውና እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አጻጻፍ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ቅጽል ስም መድኃኒትነቱን የዘለዓለም ንጉሥ መሆኑን የሚገልጥ ስም ነው፤ ጸጋና ምሕረት፣ ሰላምም ይሁን በማለት ቡራኬ ሲሰጥ ሦስት ቃላትን አስቀምጦአል፡፡ እነዚህን ሦስት ቃላት ነጣጥለን በማየት ምንነታቸውን እንረዳ፡፡

    ሀ) ጸጋ፡- ጸጋ ማለት ቸርነት፣ ምሕረት፣ በጎነት፣ ያለ ብድርና ያለ ዋጋ የሚሰጥ ነጻ ስጦታ ማለት ነው፡፡ በተለይ ለሰው የሚሆን የእግዚአብሔር አስተያየት ነው፡፡ (ቲቶ 2÷11፣ ሉቃ. 1÷30፣ ኤፌ. 2÷4-5፣ ሮሜ 5÷6-8)፡፡ እግዚአብሔር በጸጋው ደኅንነትን ፈጽሞልናልና፤ (ኤፌ. 2÷6-8፣ 2ጢሞ. 1÷9)፡፡ የእግዚአብሔርን ጸጋ የምንቀበለው በእምነት ነው፡፡ (ዕብ. 4÷16፣ ኤፌ. 2÷8)፡፡ በሕግ ወይም በሥራ እንጸድቃለን ብንል የጸጋው ተቀባዮች ልንሆን አንችልም (ገላ. 5÷4-5፣ ሮሜ 8÷1-2፣ 5÷1፣ 15-17)፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ ምእመናንን ያጸናል (የሐዋ. 20÷32፣ 2ቆሮ. 9÷14፣ 12÷9፣ 2ጢሞ. 2÷1)፡፡ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ስጦታን ይሰጣል፡፡ (ሮሜ 12÷6-8፣ ኤፌ. 3÷8) ይህን ጸጋ ቸል እንዳንለው መጠንቀቅ አለብን (ሮሜ 6፣ ይሁዳ 4)፡፡

    ለ) ምሕረት፡– ምሕረት ቅጣት ለሚገባው ይቅርታ ማድረግ ነው (መዝ. 50፣ 129÷7-8)፡፡ ለደካሞች፣ ለበሽተኞች፣ ለድሆች ቸርነትና ርዳታ ማድረግ ነው፡፡ (ምሳ. 14÷21-31፣ ሆሴ. 14÷3፣ ሮሜ 5÷6፣ ማር. 10÷46-52)፡፡ እግዚአብሔር ከምሕረቱ የተነሣ ለእኛ ሲል በመስቀል ላይ እንዲሞት አንድ ልጁን ሰጠ (ኤፌ. 2÷4-5፣ 1ጴጥ. 1÷3)፡፡ ምእመናን ምሕረት እንዲያደርጉ ታዘዋል (ያዕ. 2÷1-13፣ ሉቃ. 6÷36፣ ማቴ. 5÷7፣ ሮሜ 12÷19)፡፡ እግዚአብሔር ከማናቸውም ነገር ሁሉ ይልቅ ምሕረትን ይወድዳል፣ (ሆሴ. 6÷6፣ ሚክ. 6÷8፣ ማቴ. 12÷7)፡፡

    ሐ) ሰላም፡– ሰላም ስምምነትና አብሮ መኖር ነው፤ ዕረፍትና ጸጥታ ማግኘት ነው፡፡ ሰዎች ሲገናኙ የሚለዋወጡት የሰላምታ ቃል ወይም የንግግር መክፈቻ ቃል ነው፡፡ (ዮሐ. 20÷19)፡፡ እውነተኛ ሰላም የሚገኘው ሰው በክርስቶስ አምኖ፣ ከኃጢአቱ ነጽቶ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታረቅ ነው፡፡ (ሮሜ. 5÷1፣ ኤፌ. 2÷14-17)፡፡ ሰላም የመንፈስ ፍሬ ነው (ገላ. 5÷22)፡፡ እግዚአብሔር ለሚታመኑበት የራሱን ሰላም ይሰጣቸዋል (ኢሳ. 26÷3-4፣ ዮሐ. 14÷27፣ ፊል. 4÷6-7)፡፡

    አማኞች ከሰዎች ጋር በሰላም እንዲኖሩ ታዘዋል (ሮሜ. 12÷18፣ 1ጴጥ. 3÷11)፡፡ ክርስቶስ ሲመጣ ሰላም ይሰፍናል (ኢሳ. 9÷6-7፣ 11÷6-9)፡፡ ሰላም የእግዚአብሔር መንግሥት ራሱ ነው (ሮሜ 14÷17)፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ጸጋ ተሰጠን ማለት ዋጋ ሳንከፍል የብድር ምላሽ ሳንጠየቅ በእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት ድኅነት ተሰጠን ማለት ነው፡፡

    ከመስቀሉ በቀር ለኔ ሌላ ትምክሕት የለኝም

    የሰው ልጅ ከግዙፍና ከረቂቅ ነገር የተገኘ ታላቅ ፍጥረት ነው፤ በግዙፍነቱ ይጨበጣል፣ ይታያል በርቀቱ ደግሞ እግዚአብሔር ሲፈቅድለት ለማመን የሚያስቸግሩ ብዙ አስደናቂ የፈጠራ ሥራዎችን በረቂቅ አእምሮው ሲሠራ ይታያል፡፡ ይሁንና በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ሲርቅ የረቀቀ አእምሮው በግዙፉ አካል እየተሸነፈና እየተዋጠ ወደ ግዙፉ ነገር ሲያመዝን ይታያል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ የመንፈስን ሳይሆን የሥጋን ሥራ እየተከተለ ፈጣሪውን አሳዝኖአል፡፡ ራሱንም ጎልቶአል፣ (ዘፍ. 6÷6-23)፡፡ እግዚአብሔርም መሐሪ አምላክ ነውና በምሕረቱ እየጎበኘ ግዙፉን ሰው በግዙፍ ምልክት ሲያድነው እናያለን፡፡ ነገር ግን ሰው ዛሬም ድረስ የመስቀሉ ምልክት ተሰጥቶት እያለ በመከራ ሥጋ ተዘፍቆ ይገኛል፤ ለምን ይህ ሆነ? ያልን እንደሆነ መልሱ መስቀሉ እንደሚያመለክተው ሳይሆን በመቅረቱ ነው፡፡ መስቀሉ መዳን የተፈጸመበት ከመሆኑም በላይ በውስጡ ብዙ መልእክቶች አሉት፤ ክርስቶስ በመስቀሉ፣ ኃጢአትን ለማጥፋትና ለመደምሰስ ሞተ (ሮሜ 6÷3-14)፤

    የእስራኤልን ሕዝብ ከግብጽ ባርነት ለማውጣት በግብጻውበያን ላይ ከታዘዘውም መቅሠፍት ለማዳን የደም ምልክት በቤቶቻቸው መቃን እንዲያደርጉ በማዘዝ ከመቅሠፍቱ አድኖአቸዋል፤ (ዘጸ. 12÷12-13)፡፡ እንደዚሁም እስራኤል በምድረ በዳ ኃጢአትን እየሠሩ ባስቸገሩ ጊዜ ተናዳፊና መርዛም እባብ በመልቀቅ ከቀጣቸው በኋላ ንስሓ ገብተው እንዲምራቸው በጠየቁ ጊዜ በሚታይ ቦታ ላይ የእባብ ምልክት በመስቀል እርሱን እያዩ እንዲድኑ አድርጎአል፤ (ዘኁ. 21÷5-9)፡፡ እነዚህ ነገሮች ለጊዜው ከመቅሠፍቱና ከእልቂቱ ለመዳን የተሰጡ ምልክቶች ሲሆኑ በኋላ ዘመን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልና ደም ለሚፈጸመው ድኅነተ ዓለም እንደጠቋሚና አመላካች ቀስት ሆነው  የሚያስተምሩ ነበሩ፡፡ ጊዜው ደርሶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙን በማፍሰስ ሰውን ለፍጹም ድኅነት አብቅቶአል፣ በመሆኑም በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ አምነው ለሚፈሩትና ለሚያመልኩት መስቀሉ የመዳን ምክንያት ሆኖ ተሰጥቶአቸዋል፤ (1ቆሮ. 1÷18)፡፡ ቀድሞ እስራኤላውያን በደሙና በእባቡ ምስል ምክንያት ከመቅሠፍትና ከእልቂት እንደዳኑ ዛሬም ምእመናን ሥጋውንና ደሙን ተቀብለውና መስቀሉን ተሸክመው ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ ይድናሉ፡፡

    ስለዚህ በከበረ ደሙ የገዛን እኛ ሁላችን “ጌታችን በመከራው ከመሰልነው በክብር እንመስለዋለን በሞቱም ከመሰልነው በትንሣኤው እንመስለዋለን” (ሮሜ 6÷50) በሞቱ መስለነው በትንሣኤው እንድንመስለው የእግዚአብሔር ረድኤት አይለየን አሜን!!!

     

    “ስብሐት ለእግዚአብሔር”

     

    ከብፁዕ አባ ሳሙኤል

    በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

    የልማትና ክርስቲያናተራድኦ ኮሚሽን ሊቀጳጳስ

    አዲስ አበባ

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸከመ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top