• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 16 November 2015

    ከልደት በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት


    ከልደት በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት

    እነዚህ ከልደተ በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ ተብለው ይጠራሉ፡፡

    እነዚህ ሳምንታት ነቢያት አምላክ ይህንን ዓለም እንዲያድን ያላቸውን ናፍቆት የገለጡባቸው እና ይህንን አስመልክተው ያስተማሩባቸው ሦስት የተለያዩ መንገዶች እና ጌታችንም ለእነዚህ መልስ የሰጠባቸው ሁኔታዎች ይታሰቡባቸዋል፡፡

    1. ስብከት ( ከታኀሳስ ፯ እስከ ታኅሳስ ፲፫ )

    ስብከት ማለት ማስተማር ማለት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ከሙሴ ጀምሮ የነበሩ ነቢያት በሙሉ አዳኝ /መሲህ/ እንደሚመጣ ማስተማራቸው ጌታችንም እነርሱ ይመጣል ብለው ያስተማሩለት እኔ ነኝ ብሎ ራሱን መግለጡ የሚታሰብበት ነው፡፡
    ሙሴ ለጊዜው የጌታችን ምሳሌ ለሆነው ለኢያሱ ፍጻሜው ግን ለጌታችን በሆነው ትንቢቱ «አምላክህ እግዚአብሔር ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል፤ እርሱንም ስሙት፡፡» ብሎ ለሕዝበ እስራኤል ነግሯቸው ነበር፡፡ /ዘዳ. 18.15/ እግዚአብሔር ወልድም በሥጋ ማርያም በተገለጠ ጊዜ ራሱን ያስተዋወቀው ያ ነቢያት የተናገሩለት አዳኝ /መሲህ/ እንደሆነ ነው፡፡ «ሙሴ እና ነቢያት ሁሉ ስለ እኔ ይናገራሉ፡፡» ይላቸው ነበር፡፡ ትንቢቱን ያውቁ የነበሩ በእግዚአብሔር መንገድ የሚሄዱ እስራኤላውያንም «መሲሁን አገኘነው»፣ «ሙሴ በህግ መጻሕፍት፣ ነበያትም ስለ እርሱ የጻፈለትን የናዝሬቱን ኢየሱስን አገኘነው» እያሉ ተከትለውታል፡፡ /ዮሐ. 1.41፣ ዮሐ. 1.45/ ሐዋርያትና ሌሎቹ ደቀመዛሙርቱም ከጌታችን ሞትና ትንሳኤ በተለይ የተነገሩትን ትንቢቶች ሁሉ ያውቁ ለነበሩት እስራኤላውያን ያስተማሩት እነዚህን የነቢያት ትምህርቶች እና ትንቢቶች እየጠቀሱ ነበር፤ ቅዱስ ጴጥሮስን በቤተ መቅደስ እንዲህ ብሎ አስተምሯል፤ «አሁንም ወንድሞቼ ሆይ አለቆቻችሁ እንዳደረጉ ይህን ባለማወቅ እንዳደረጋችሁት አውቃለሁ፡፡ እግዚአብሔር ግን ክርስቶስ መከራን እንዲቀበል በነቢያት ሁሉ አፍ እንደተናገረ እንዲሁ ፈፀመ» /ሐዋ. 3.17-18/፡፡

    በሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፡- «ወንድሞች ሆይ የቀደሙ ቅዱሳን ነቢያት የተናገሩትን ቃልና ለእኛ ለሐዋርያትም ያዘዘውን የመድኃኒታችንና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ትእዛዝ ታስቡ ዘንድ... ዕወቁ» /2ኛ ጴጥ. 3.1-3/ ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ መግቢያ ላይ እንዲህ ብሏል፤ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዐይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፤ በኋላ ዘመን ግን ሁሉን ወራሽ ባደረገው፣ ሁሉን በፈጠረበት በልጁ ነገረን፡፡» /ዕብ. 1.1-2/

    2. ብርሃን (ከታኀሳስ ፲፬ እስከ ታኅሳስ ፳)

    ነቢያት የአምላክን ማዳን ከጠበቁባቸው እና ከገለጡባቸው መንገዶች አንዱ ብርሃን ነው፡፡ ዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ፣ መከራ ነፍስ የፀናበት፣ ሁሉ ነገር አስጨናቂ የሆነበት፣ ሰው ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት ስለነበር ያሉበትን ዘመን «ጨለማ» ብለው በመግለጥ ይህንን ጨለማ የሚያስወግድና ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራ ብርሃን እንዲመጣ እንዲህ እያሉ ይፀልዩ ነበር፡፡ «ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፣ እነርሱም ይምሩኝ፣ አቤቱ ወደ መቅደስህ ተራራና ወደ ማደራያህ ይውሰዱኝ» /መዝ. 42.3/ ጌታችንም ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ለዚህ መልስ ሰጥቷል፤ «እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ» /ዮሐ. 8.12/ ደቀመዛሙርቱም ስለ ብርሃንነቱ በመመስከር ተባብረዋል፤ - ቅዱስ ዮሐንስ ስለጌታችን ሰው መሆን /ሥጋዌ/ በተናገረበት በወንጌሉ የመጀመሪያ ክፍል ጌታችንን ብርሃን ብሎታል፤ «ሕይወት በእርሱ ነበረ፣ ሕይወትም የሰው ብርሃን ነበረ፤ ብርሃንም በጨለማ ያበራል፤ ጨለማም አላሰነፈውም» /ዮሐ. 1.4-5/ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችን በሚያንፀባርቅ ብርሃን አምሳል እንደተገለጠበት ተናግሯል፡፡ «እኩል ቀን በሆነ ጊዜ በመንገድ በሄደ ከፀሐይ ይልቅ የሚበራ መብረቅ በእኔና ከእኔ ጋር ይሄዱ በነበሩት ላይ ከሰማይ ሲያንፀባርቅ አየሁ፤ ... አንተ የምታሳድደኝ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ አለኝ፡፡» /ሐዋ. 26.13/

    3. ኖላዊ (ከታኀሳስ ፳፩ እስከ ታኅሳስ ፳፯ )

    ኖላዊ ማለት እረኛ ማለት ነው፡፡ ነቢያቱ ራሳቸውን እና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው እና እንደተቅበዘበዙ በጎች በመቁጠር እንዲሰበስባቸውና እንዲያሰማራቸው እንዲህ እያሉ እራሳቸውን ይማፀኑ ነበር» «ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ /እረኛ/ ሆይ፣ አድምጥ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ፡፡» /መዝ. 79.1/ ጌታችንም ለዚህ ጥያቄ እንዲህ ሲል መልስ ሰጥቷል፤ «ቸር ጠባቂ /እረኛ/ እኔ ነኝ፡፡ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል፡፡» /ዮሐ10.11/

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ከልደት በዓል በፊት ያሉት ሦስቱ የጾመ ነቢያት ሳምንታት Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top