• በቅርብ የተጻፉ

    Monday 16 November 2015

    እምፅንሰታ እስከ ልደታ

    በዚህ ሁሉ ትውልድ ደጅ የተጠናችው እመቤታችን የተፀነሰችው ለምህረት ዓመት 15 ዓመት ሲቀረው በ5485 ዓመተ ዓለም በዓመተ ምህረት ዋዜማ ላይ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ህዝቡን ይቅር ሊለው ዘመኑ ሲቃረብ የሰላሟ ርግብ የጥፋቱን መቆም ልታበስር ወደ ዚች ምድር ብቅ አለች፡፡ ያኔ ዓለም የሙታን መንደር በሆነችበት ሠሞን በምድር ላይ የነበረ ስጋዊና ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ወደ ሬሳነት የተቀየረ ጊዜ ውሃ ከታላላቁ ተራሮች ከነ አራራት ከነ ቀርዱ በላይ ሆኖ ለአስራ አምስት ክንድ ወደ ላይ ወጥቶ ይታይ ነበር

    ይህ የጥፋት ውሃ ደግሞ ለመጉደሉ መልስ የሰጠች የሰላሟ መልዕክተኛ ርግብ እንደነበረች ሊቀ ነቢያት ሙሴ ምስክር ነው፡፡ ዘፍ 7፥19 አስተውል ያ ወደላይ ለ15 ክንድ ከፍ ብሎ የታየው ምድሪቱን የከደነው ውሃ ከአዳም እስከ ክርስቶስ መምጣት በምድራውያን ላይ ሰልጥኖ የነበረውን ሐጢአት ይመስላል፡፡ በዚያ ዘመን የወረደው ውሃ ፍጥረትን ሁሉ ጐድቷል ሰውን ብቻም አይደል በምድር ላይ የሚርመሰመስ ስጋዊ ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ተጐድቶበታል ከአዳም የወጣው ሐጢአትም ሰውን ብቻ ሳይሆን እንስሳትንም አራዊትንም ጐድቷል እንኳን ምድራውያኑን ሰማያውያኑን መላዕክትም ሳይቀር ጐድቷል፡፡

    ቅዱሳን መላዕክት በክብር ላይ ክብር 
    ተጨምሮላቸው የሚኖሩት ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ከሰው ወደ እግዚአብሔር በሚያደርጉት አገልግሎታቸው ጭምር ነበርና ይህን አስቀርቶባቸዋል፡፡ በእለተ ልደቱ ከሰው ይልቅ እየዞሩ የምሥራቹን ያሰሙ የነበረውስ ለዚህ አይደል ሉቃ 2፥8-12 ይሔ ፍጥረታትን በሙሉ አንድ አድርጐ የጐዳው ሐጢአት ሁላችንን ሙታን ባደረገበት ዘመን ሊጐል አስራ አምስት ዓመት ሲቀረው ከሞት ላመለጠው ትውልድ ማለትም ለሐዲስ ኪዳኑ ትውልድ ሰላምን ልታበስር ርግቧ ብቅ አለች በእናቷ በኩል ከካህናት፣ በአባቷም በኩል ከነገሥታት ወገን የተገኘች ናት፡፡ ከነገሥታት ዳዊት ሰሎሞን፣ ከካህናትም ታላቁ አሮን አባቶቿ ናቸው፡፡ ከነዚህ የተወለዱት ሐናና ኢያቄም በዘመናቸው ታላቅ የሆነ ችግር ደርሶባቸዋል መካኖች በመሆናቸው ያሽሟጥጧቸዋል፣ ይዝቱባቸዋል ወደ ቤተ እግዚአብሔር መባዕ እንዳያገቡ ይከለክሏቸዋል ምክነት የሐጢአት ውጤት ነው ብለው ያምኑ ነበርና፡፡

    ትዝ አልላቸው ብሎ እንጅ እግዚአብሔር ከብዙ መካን እናቶች ታላላቅ ሥራ የሠሩ ሰዎችን አስነስቷል ከሳራ ይስሐቅን፣ ከኤልሳቤጥ ዬሐንስን፣ ከስምኦንና አቅሌስያ ገብረ መንፈስ ቅዱስን አስገኝቷል፡፡ እመቤታችንም ከእነዚያ አንዷ ናትና ከመካኖቹ እናትና አባቷ ተወልዳ በጐ ነገር መውለድ በተሳናት ዓለም ውስጥ የተገኘች መሆኗን ለማመልከት ከመካኖች ተገኘች ልጅ የበረከት ምልክት ነውና፡፡ ዛፍ ካላፈራ ቅጠሉ ቢያምር ቁመቱስ ቢያድግ ምን ይጠቅማል?ከምንም በላይ የእግዚአብሔር ሐሳብ እንደ ሰው አይደለምና ሐናና ኢያቄም ልጅ በማጣት በሚገቡት ሱባዔ በሚያለቅሱት ለቅሶ ከአዳም እስከ እርሷ መገኘት ድረስ አባቶቻችን የገቡትን ሱባዔ ያለቀሱትን ሱባዔ ለመፈጸም ለመደምደም ነው፡፡ እነ ሙሴ፣ እነ ኤልያስ ለአርባ ቀናት ያለ አንዳች መብልና መጠጥ የጾሙት ዘዳግ 9፥9፣ 1 ነገ 19፥5 እነ ዳንኤል ዝለው እስከ ሚወድቁ ድረስ የተጋደሉት ዳን 10፥1 አባቷ ዳዊት ለዐይኖቹ እንቅልፍን፣ ለሽፋሽፍቶቹ መኝታን ለጐንጮቹ እረፍትን ላይሰጥ የማለው የያዕቆብ አምላክ ማደሪያ እመቤታችንን ለማግኘትም አይደል፡፡ በእውነት ብዙ ነቢያት ሱባዔን  አውጀዋል ጾምን ቀድሰዋል፤ እነ ኤርምያስ በዕለት፣ ሰባቱን ቀን አንድ እያሉ ፣ እነ ዳንኤል ሰባቱን ሳምንት አንድ ሱባዔ እያሉ፣ እነ ሔኖክ በትውልድ ሰባቱን ትውልድ እንደ አንድ ሱባዔ እየጠሩ ብዙ ትንቢትን ተናገሩ ፡፡የሁሉም ሐሳብ ግን አንድ ነው ከድንግሊቱ ዘመን ለመድረስ ነው፤ የነዚህ ሁሉ ጩኸት በሐናና ኢያቄም ጩኸት ተደመደመ፡፡

    እነዚህ ሰዎች ለመስዋት የማይሆነውን ምግብ ሁሉ ከመብላት ተከልክለው በብርቱ ፍለጋ ልጅ ይፈልጉ ነበሩ፡፡ በነርሱ በኋላ እውነተኛ መስዋዕት ክርስቶስን የምታስገኝ እመቤታችን ከእነርሱ የምትወጣ ናትና፡፡ የሚመገቡትን ብቻም ሳይሆን የሚወልዱትንም ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርገው ሊሰጡ ተሳሉ፡፡ የአባቶቻቸው የነ ያዕቆብ ስዕለት እንዲፈጸም የተደረገ ስዕለት ነው፡፡ ዘፍ 28፥21-23 የሐጢአት ውጤት ነው ተብሎ የሚነገርለት መካንነት እንደ ነውር ሆኖ በእነርሱ ተጣብቆ ያ እስኪወገድላቸው ብርቱ ጩኸትን ጮሁ፣ ታላቅ ለቅሶን አለቀሱ፡፡ በህዝቡ ሁሉ ላይ የሆነውን ነውር እግዚአብሔር ከህዝቡ እስኪያስወግድ ድረስ ይህ ሁሉ በእነርሱ ሆነ፡፡ የቀደሙት ወላጆቻችን ከሐጢአት በኋላ ያቀረቡት መሥዋዕታቸው  የጸለዩት ጸሎታቸው ችግር የማይፈታ መሆኑን ለመግለጽ እግዚአብሔር በምስጢር መስዋዕታቸውን እንዳይቀበሏቸው ከለከለ፡፡

    የላይኛው ቤተ መቅደስ አገልጋዬች ቅዱሳን መላዕክት የሰውን መስዋዕት ተቀብለው ወደ ሰማዩ ቤተ መቅደስ የሚያሳርጉበት ጊዜ ገና ነበርና ሃናና ኢያቄምም መሥዋዕት እንዳያስገቡ በምድራዊቷ ቤተ መቅደስ አገልጋዬች ተከለከሉ፡፡ በህይወታቸው ረጅሙን ዓመት በነውር አሳለፉ፡፡ በተለይም ውበት፣ ሙቀትና ልምላሜ የማይታጣበትን በጐውን የልጅነት ዕድሜአቸውን በለቅሶ ጨረሱ፤

    ይህች ዓለምም እንደወጣትነት የሚቆጠር ዕድሜዋን በሐጢአት ጨርሳ 5500 ዘመናት ተቆጥረውላት መሸምገል ከጀመረች በኋላ መስዋዕቷን እግዚአብሔር ተቀበላት፡፡ የታችኛዋ ቤተመቅደስ አገልጋዬች የአረጋውያኑን መስዋዕት እንደተቀበሉ የላይኛዋም ቤተመቅደስ አገልጋዬች ቅዱሳን መላዕክት የአሮጌይቱን ዓለም ልጆች መስዋዕት ተቀብለው ማሳረግ ጀመሩ፡፡ ራዕ 8፥3 ያረጁ ሆነው ሳሉ እናት እና አባቷ ተስፋ ሳይቆርጡ ለመኑ በዕድሜ ለገፋች ዓለማችን የተሰጠች ብቸኛዋን የተስፋ ፍጻሜ ድንግልን እስኪያገኙ በተስፋ ጸኑ፡፡ አንድ ቀን እግዚአብሔር በሌላ በኩልም አይደል በማህጸናቸው ፍሬ ነውራቸውን ከላያቸው እንደሚያንከባልል በማመን ተማጸኑ፡፡ በዚህ ደጅ ጥናታቸው በሰማይና በምድር በሲኦል እና በመቃብር ለነበሩ ነፍሳት ሁሉ መልስ አግኝተዋል፡፡ እኒህ ፍጡራን ለብዙ ዘመናት ደጅ የጠኑትን ጌታን የምትወልድላቸው አምሳያ የሌላት አንዲቷን ድንግል በነሐሴ በሰባት ቀን እንደምትጸነስ በሱባዔያቸው ወቅት ራዕይ አይተው ነበር፡፡ ጸአዳ ርግብ ሠባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በሃና ማህጸን ስትቀመጥ ለእርሷ ኢያቄም ራዕይ አይቶላት ነበር ይህም ሐጢአት ላመከነው ዓለም እመቤታችን እግዚአብሔራዊ ስጦታ ሆና የተሰጠች መሆኗን ያሳያል፡፡ ሰማያዊ ምስጢር የሚገልጥባት ናትና፡፡ ከሠባቱ ሰማያት ስትመጣ በራዕይ ታየች፡፡

    በሌላ መንገድ በተፈጥሮዋ ምድራዊት ሴት ብትሆንም በክብር ከሁሉ የተለየች መሆኗን የሚገልጽ ራዕይ ነው፡፡ በእናቷ በሐናም በራዕይ ከደጃቸው ላይ ሎሚ በቅላ ለምልማ አብባ አፍርታ ለፍጥረት ሁሉ ምግብ ስትሆን ታይታለች፡፡ በዚያችው ሌሊት ፍጥረት ሁሉ የሚመገበውን የህይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ የተገኘችው እውነተኛዋ የጽድቅ ተክል ድንግል በብስራተ መላክ ተጸነሰች፡፡ እውነተኛዋ የጽድቅ ተክል ድንግል በብስራተ መላክ ተጸነሰች፡፡

    ለእስራኤል የሚበላውን የሚጠጣውን ያስገኘችውን ምድራዊት ርስታቸውን ሲያወርሳቸው በመላዕክት መሪነት ነበር ዛሬ ደግሞ ለእስራኤል ዘነፍስ የሚበላውን ያስገኘች እመቤታችን በመላኩ መሪነት ለእስራኤል ዘነፍስ አስረከባት፤ በመላኩ መሪነት ስትጸነስ እናት እና አባቷ መንፈሳዊ ተድላ ደስታን አደረጉ፡፡ ከቀደመው ይልቅ አብዝተው ጾሙ ጸለዩ ድሆች ሳሉ አልናቃቸውምና የልባቸውንም መሻት ፈጽሟልና፡፡ ከሠው ብትወለድም  በህገ መላዕክት የምትኖር እህተ መላዕክት ናትና በጾም እና በጸሎት ተቀበሏት፡፡ የእመቤታችን ምሳሌ የሆነችው ኦሪትን ሲቀበል ሙሴ በዚህ ዓይነት ሥርዓት መቀበሉን የዲያቆናት አለቃ እስጢፋኖስ ይመሰክራል፡፡ ሥራ 7፥53 አማናዊቷ የሙሴ ህግ የተጻፈባት ጽላት እመቤታችን በህገ መላዕክት በሰማያዊ ስርዓት ወደ ዓለም መጣች ከተቀደሰው ጋብቻ የተገኘችው የሃናና የኢያቄም ፍሬ በማህጸንም ሳለች ታላቅነቷን የሚመሰክሩ ታላላቅ ስራዎችን ሰርታለች፡፡ ለእውራን ብርሃንን የሰጠችው ለሰለሉ እጆች ብርታትን ያደለችው ገና በማህጸን ሳለች ነው፡፡ ገና ስትጸነስ ጀምሮ ቅድስት መሆኗን ልብ ይሏል! ከዚያም አልፋ ሃና እርሷን ተሸክማ ጥላዋን ከጣለችበት ሙታን ሳይቀር ይነሳሉ የሞተውን ዓለም ሞትን ገሎ ከሞት ግዞት ነጻ የሚያወጣን ጌታ ከእርሷ የሚወለድ ነውና ሙታንን በማህጸን ሳለች ታነሳ ነበር የሰው ልጆች የትንሳኤ ዘመን የደረሰ መሆኑን ለመመስከር ነው ስትሔድ ሞት ከሙታን ተለይቶ ይሸሽለታል ሙታን ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ነቅተው በማህጸነ ሃና ሳለች ያወድሷታል ይሔን የተመለከተው ሰይጣን ግን ዝም አላለም መቼ እንደሆነ ጊዜውን አያውቅም እንጅ የሚረታበት ጊዜ መኖሩን ያውቃል፡፡ ገና ሳትወለድ ይሔን ካደረገች ስትወለድስ ምን ትሆን? ብሎ በመስጋት ሰልፍ ጀመረ ሠራዊቱን አይሁድን ለሰልፍ አስከትቶ በእናትና በአባቷ ላይ ጠላትነትን አስነሳ ገና በማህጸን ሆና ለሰይጣን አልተመቸችውም ገና ወደ ዓለም ሳትመጣ አስደነገጠችው እውነት ነው ይሔ ከፍጡራን ለማን ተደርጐለታል በታላቁ መጽሐፍ እንደተነገረ ከማህጸን ሳሉ የተመረጡ ነበሩ ኤር 1፥5 በማህጸን ሳሉ በሞት የተከደኑ አይኖችን የከፈቱ በሞት የታሰሩ አንደበትን ያናገሩ ሰዎች ግን የሉም፤

    የዛሬው ጽንስ ሰይጣንን ያስደነገጠው በዚህ ነው ገና በማህጸን የሚሳነው ነገር የሌለ ከሙታን አንደበት ዝማሬን የተቀበለ ይህ ጽንስ እንደምን ያለ ነው?የመጀመሪያው ሠው በእናት ማህጸን በምትመሰለው በገነት ውስጥ ሲኖር ሳለ ነበር የሰይጣን ዓይኖች በክፋት ወደ እርሱ የተወረወሩት በገነት በነበረው ሰው ውጤትን እንዳገኘ በዚህም የሚያገኝ ስለመሰለው ጦሩን ሰበቀ፣ የክፋት አይኑን አጉረጠረጠ የሁላችንን አባት በእባብ አድሮ እንደተዋጋው የጦር መላውን ቀይሮ በሰዎች ልቡና አድሮ የሁላችንን እናት ዳግማዊት ሄዋን ድንግልን መዋጋት ጀመረ ግን አመለጠችው፡፡ መጀመሪያም በክንፉ ላይ ስሎ ለመላዕክት ሲገልጣት የጠባቂነት መዓርግን መስጠቱ ነበርና ከማህጸን ጀምሮ እንዲጠብቃት አደራ በሰጠው መላክ በኩል እንደተናገረው በዘመድ የከበሩ ቢሆኑም ቅሉ ለምትወልደው ህጻን ዘመዶቿ የሰማይ መላዕክት ናቸውና በእነርሱ ተከባ ወደምትወልድበት ስፍራ እንዲሄዱ ተነገራቸው እርሷ ከዓለም አይደለችምና በመወለዷ በቤት ውስጥ የነበሩ ሠዎች ዓለማዊ ተድላ ደስታን እንዳያደርጉ በመንፈሳዊያን ዘመዶቿ በመላዕክት ታጅባ ከቤት ወጣች ከቤቱ ወጥቶ፣ ህገ እግዚአብሔርን ስቶ የነበረው አዳምን የሚፈልግ ጌታ እናቱ ናትና ከቤት ወጥታ ቀድሞ አባቶቿ ነቢያት እሷን በራዕይ ወደ ተመለከቱበት ታላቅ ስፍራ ወደ ሊባኖስ ተራራ ተጓዘች በሊባኖስ ተራሮች ጉያ ስር በአንበሶች ጉድጓድ እንደምትወለድ ትንቢት የተነገረላት የሊባኖስ ሙሽራ እርሷ ናትና፡፡ ከግሩማኑ አንበሶች ከነዳዊት ከነሠለሞን ከታላላቁ ተራሮች ከነ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ አብራክ የተገኘችው እመቤታችን በዚህ ሰው በማይኖርበት ስፍራ ልትወለድ ተወሰነ፡፡ በዚያው ሳሉ በክብሯ ከአድባራት ሁሉ በላይ የሆነ ከቀደሙትም ከኋለኞችም በላይ ስሟ የገነነ ከጸሐይ ይልቅ የምትደምቅ እመቤታችን በግንቦት አንድ ቀን ተወለደች እሷ የሁሉም ፍጥረት ናት እንጅ የሃናና የኢያቄም ብቻ ባለመሆኗ በአንድ ሰው ቤት ውስጥ እንድትወለድ መንፈስ ቅዱስ ከለከለ በዚህ ዕለት ታዲያ ዕፀዋት ያለ ጊዜአቸው ለምልመዋል አፍርተዋል፡፡ ድንጋዬች ህብስት ሆነዋል የክረምቱ ወራት አልፎ የበረከቱ ዘመን ቀርቦ የሰው ዘሮች የጽድቅ ፍሬ የሚያፈሩበት ክርስቶስ ህብስት ሰማያዊ ሆኖ ለአለም የሚሰጥበት ዘመን ደርሷልና ይሔ ምልክት ታየ ከሠማይ ልደቷን ለማክበር ብዙ የሰማይ ሠራዊት ተልከው ወደ ምድር መጥተው ነበርና አካባቢው በበጐ መዓዛ ተሞላ የምድር መዓዛ በሰማያውያን መዓዛ ተተካ አዲሲቷ ህዳን ድንግል ማርያም አባቷ ኢያቄም ከሠራው ዳስ መሳይ ነገር በላይ የመላክ ዑቃቤዋ የቅዱስ ሚካኤል የመላክ ብስራቷ የቅዱስ ገብርዔል ክንፍ በላይዋ ላይ ተዘርግቶላት ነበር የተወለደችው የስደተኛ ስንቁ ይህ ነውና ለሀራሲቱ ሃና የቀረበላት ምግብ ጥሬ ነበርና ዛሬም በሃገራችን በዚህች ቀን ምዕመናኑ ጥሬ አቅርቦ ከቤት ወጥተው በዓለ ልደቷን ያከብራሉ፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: እምፅንሰታ እስከ ልደታ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top