• በቅርብ የተጻፉ

    Saturday 21 November 2015

    ሰሙነ ሕማማትና ምስጢሩ


    በዲ/ን ተመስገን ዘገየ

    ከትንሣኤ በፊት ያለው ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ይባላል፡፡ ይኸውም በነቢዩ ኢሳይያስ ነስአ ደዌነ ወፆረ ሕማምነ፣ በእውነት ደዌአችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንም ተሸከመ፤ በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን፡፡ /ኢሳ. 5፤34-36/ ተብሎ በመንፈስ ቅዱስ ትንቢት የተነገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ሳምንት ውስጥ ለድኅነተ ዓለም ሲል በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ የተቀበለውን ጸዋትወ መከራ ለማስታወስ የወጣ ስያሜ ነው፡፡

    በሰሙነ ሕማማት መስቀል መሳለምና እርስ በእርስ መሳሳም የለም፡፡ ይህም ይሁዳ ጌታን በመሳም አሳልፎ እንደሰጠው ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ሣምንት ውስጥ ያሉት ዕለታት ስያሜያቸውና በየአንዳንዳቸው ዕለታት የተፈጸሙትን ድርጊቶች እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

    ሰኞ፡-

    አንጽሖተ ቤተ መቅደስና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው፡፡ የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ ያድራል፡፡ በማግስቱም ከቢታንያ ሲመጣ ተራበ ወበሳኒታ ወፂኦ እምቢታንያ ርኅበ ወርእየ በለሰ እምርኁቅ ወባቲ ቈጽለ ወሖረ ይርአይ እመቦ ዘይረክብ ፍሬ በውስቴታ ወበጺሖ ኀቤሃ አልቦ ዘረከበ ዘእንበለ ቈጽል ባሕቲቱ እስመ ኢኮነ ጊዜሁ ለበለስ፣ ቅጠል ያላት በለስ ከሩቅ ዓይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፤ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳችም ፍሬ አላገኘባትም፤ ወአውሥአ ወይቤላ ለዓለም አልቦ ዘይበልዕ ፍሬ እምኔኪ እንከ፣ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ /ማር. 11፤11-12/

    በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ናት፡፡ ፍሬ የተባለች ሃይማት ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን ሃይማኖትን ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤል ሕዝበ እስራኤል መባል እንጂ ደግ ሰው አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገም ምክንያት እርሱ ከላያቸው በስተቀር ደግ ሰው ጠፋባት፡፡

    አንድም በለስ ኦሪት ናት፡፡ በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፡፡ እጸ በለስን ፍሬ በአንቺ አይሁን አላት፡፡

    አንድም በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሠፊ እንደሆነች ኃጢአትም በዚህ ዓለም ሥፍራ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል፤ ቆይቶ ግን ይመራል፡፡ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ያሰኛል፡፡ ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ ወደ እርሷ ሄደ ማለትም ከኃጥአን ጋር ዋለ፣ ኃጥእ ከመባል በቀር በመዋዕሉ ኃጢአት አለመሥራቱን ለመመልከት ፍሬ አላገኘባትም አለ፡፡ በአንቺ ፍሬ አይገኝ የሚውሉም በኃጢአት በፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ ስትረገም ፈጥና መድረቋም በአዳም በደል ያገኛትን እዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

    በመቀጠልም ወደ ቤተ መቅደሰ ሄደ፡፡ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምስያጥ /የንግድ ቤት/ ሁኖ ቢያገኘው ቤትየሰ ቤተ ጸሎት ትሰመይ፣ ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች፡፡ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችኋት ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸው፤ ገርፎም አስወጣቸው፡፡ /ማር. 11፤17-19/ ይህም የሚያሳየው ማደሪያ ቤቱ የነበርን የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡

    በሰሙነ ሕማማት ካህናትና ምእመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ወዛቸው ጠብ እስኪል ድረስ በነግህ፣ በሠለስት፣ በስድስት ሰዓትና በተሰዓቱ ሰዓት መላልሰው ሲሰግዱና ሲጸልዩ ይሰነብታሉ፡፡ በተለይም ካህናት በማንኛውም አገልግሎት ጥቁር ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ምክንያቱም የደረሰበትን መከራ ኀዘኑንና 5500 ዘመን የሰው ልጅ በጨለማ ሕይወት ይኖር እንደነበር ለማዘከር ነው፡፡

    ማክሰኞ፡-

    የጥያቄ ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ምክንያቱም ሹመትን ወይም ሥልጣንን ለሰው ልጅ የሰጠ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰኞ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት በዚህ ዕለት ስለ ሥልጣኑ በጸሐፍት ፈሪሳውያን ተጠይቋልና፡፡

    ጥያቄውም ከምድራውያን ነገሥታት፣ ከሌዋውያን ካህናት ያይደለህ ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታት በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? የሚል ነበር ይህንስ ሥልጣን እነዚህን እንዳደርግ እነግራችኋለሁ፡፡ የዮሐንስ ጥምቀት ከወዴት ነበረች? ከሰማይ ወይስ ከሰው? አላቸው፡፡ እነርሱም ከሰማይ ነው ብንል ለምን አልተቀበላችሁትም? ይለናል፡፡ ከሰው ነው ብንል ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስን እንደ አባት ያከብሩታል፤ እንደ መምህርነቱም ይፈሩታልና ሕዝቡን እንፈራለን ተባብለው ወዴት እንደሆነ አናውቅም ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ እኔም አልነግራችሁም አላቸው፡፡ ይህንንም መጠየቃቸው እርሱ የሚያደርጋቸውን ሁሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፡፡ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነው እንጂ፡፡ ከዚህ የምንማረው የእነሱን ክፉ ጠባይና ግብር መከተል እንደማይገባን ነው፡፡

    በዚህ ዕለት በቤተ መቅደስም ረጅም ትምህርት ስላስተማረ የትምህርት ቀንም ይባላል፡፡ ይኸውም ከሃይማኖት የራቁትን፣ ከፍቅረ እግዚአብሔር የተለዩትን አስተምሮ ማቅረብ፣ መክሮ መመለስ እንደሚገባ ሲያስተምር ነው፡፡

    ረቡዕ፡-

    ይህ ዕለት የምክር ቀን ይባላል፡፡ ምክንያቱም የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሓፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚገባቸው ምክር የጀመሩበት ወይም የያዙበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ ምክራቸው ላይ በጣም ትልቅ ጭንቀት ነበር፡፡ ምክንያቱም ወቅቱ የፋሲካ በዓላቸውን የሚያከብሩበት በመሆኑ ብዙውን ሕዝብም በጌታችን ትምህርት የተማረኩ፣ ተአምራቱን የሚያደንቁ ስለነበር ሁከት እንዳይፈጥር ነው፡፡ በዚህ ጭንቀት ሳሉ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ በመካከላቸው በመገኘት የምክራቸው ተባባሪ ሆኖ ጭንቀታቸውን አስወግዶላቸዋል፡፡ /ማቴ. 26፤1-5፣ ማር. 14፤1-2/

    የሐዲስ ኪዳን ካህናት ምእመናን በዚህ ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰብስበው ከእህልና ውኃ ተለይተው፣ መላ ሰውነታቸውን ለእግዚአብሔር አስገዝተው፣ የሞት ፍርዱን በማሰብና በማልቀስ፣ ስለዚህ ታሪክ የሚያወሳውንም በማንበብ እስከ ኮከብ መውጫ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት ተወስነው ይቆዩና ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

    ይሁዳ ማለት ታማኝ ማለት ቢሆንም እንደ ስሙ ግብሩ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ስምና ግብሩ አልተባበረለትም፡፡ እኛ እንደ ስማችን ይሆን ግብራችን?

    መልካም መዓዛ ያለው ቀንም ይባላል፡፡ምክንያቱም ጌታችን በዚህ ዕለት በቤተ ስምዖን ዘለምጽ ተቀምጦ ሳለ መላ ሕይወቷን ለዝሙት አስገዝታ ትኖር የነበረችው ማርያም እንተ እፍረት ከእንግዲህ በኃጢአት ተጎድቶ የኖር የነበረውን ሕይወቴን እንደዚሁ መልካም ሽቶ ዋጋው እጅግ በጣም ውድ የሆነ ከሦስት መቶ ዲናር በላይ የሚያወጣ በአልባስጥሮስ ብልቃጥ የሞላ ሽቱ ይዛ በመሄድ በጠጉሩ /በራሱ/ ላይ በማርከፍከፍ ስላቀረበች ነው፡፡

    የእንባ ቀንም ይባላል፡፡ ይህም ይህችው ሴት በጌታችን እግር ላይ ተደፍታ መላ ኃጢአቷን ይቅር እንዲላት በእንባዋ እግሩን አጥባዋለችና፡፡ /ማቴ. 26፤6-13፣ ማር. 14፤3-9፣ ዮሐ. 12፤1/ ከዚህም እያንዳንዳችን ልንማር የሚገባን ነገር አለ፡፡ ይኸውም የራሱን ኃጢአት በማሰብ ማልቀስና የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ማቅረብን ነው፡፡

    ሐሙስ፡-

    ከስቅለትና ከትንሣኤ በፊት ያለው ሐሙስ በቤተ ክርስቲያናችን የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡

    1.ሕጽበተ እግር ይባላል፡፡

    ይህ ስያሜ የተሰጠው ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ምክንያት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ለማስታወስ ዛሬ ካህናት በተለይም ሊቃነ ጳጳሳት በመካከላችን ተገኝተህ የእኛንና የሕዝቡን ኃጢአት እጠብ ሲሉ በቤተ ክርስቲያናችን የተገኙትን ምእመናን እግር በወይንና በወይራ ቅጠል ሲያጥቡ ያረፍዳሉ፡፡ /ዮሐ. 13፤4-15/

    2.የጸሎት ሐሙስ ይባላል፡፡

    የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ የሚደክም ሥጋን የተዋሐደ አምላክ ፍጹም ሰው መሆኑን ለመግለጽና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ በጌቴ ሴማኒ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ነው፡፡ /ማቴ. 26፤36፣ ዮሐ. 17፤1/

    3.የምስጢር ቀንም ይባላል፡፡

    ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷል፡፡ ይኸውም ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ፡፡ ጽዋውንም አንሥቶ አመሰገነ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ፡፡በማለት እኛ ከእርሱ ጋር አንድ የምንሆንበትን መንገድ ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡

    በዚህ ዕለት ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ የሚቀደሰውም በለሆሳስ ሲሆን እንደ ቃጭል በመሆን የሚያገለግለውም ጽናጽል ነው፡፡ ይህም አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ ሲመጡ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው በለሆሳስ እየተነጋገሩ መምጣታቸውን ለማሰብ ነው፡፡ በቅዳሴውም ኑዛዜ አይደረግም፡፡ ሥርዓተ ቁርባን ግን ይፈጸምበታል፡፡ ይህም ጌታችን የሰጠውን ዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን ለማሰብ ነው፡፡ በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ተዘጋጅቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል ይኖርበታል፡፡

    4.የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል፡፡

    ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳ ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ /ሉቃ. 22፤18-20/ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚሆን የአዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱም ጠጡ በማለቱ ይታወቃል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓማዊ ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት መሆኑን በማሰብ የቃል ኪዳኑ ፈጻሚዎች ጠባቂዎች መሆን እንደሚገባን እንማራለን፡፡

    5.የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡

    ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ራሱም ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባሪያ ጌታው የሚደርገውን አያውቅምና፤ ወዳጆቼ ግን ብያችኋለሁ በማለቱ /ዮሐ.15፤15/ ከባርነት ነጻ የወጣንበት ቀን መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን ከኃጢአት ባርነት በመራቅ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን በቅድስና መምራት ይኖርበታል፡፡ እርሱ ጠላቶቹ ስንሆን ወዳጆቹ አድርጎናል፡፡ /ማቴ 26፤17-19/

    6.አረንጓዴው ሐሙስ ይባላል፡፡
    ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአትክልት ቦታ ስለ ጸለየ፡፡

    ዕለተ ዓርብ፡-

    የስቅለት; ቀን ስቅለት፣ መስቀል፣ መሰቀል፣ አሰቃቀል ማለት ነው፡፡ መስቀል በቁሙ መስቀያ፣ መመዘኛ፣ መሰቀያ፣ መንጠልጠያ፣ ለሞት የሚያበቃ መከራ በማር 8፤34 ወጸውዖሙ ለሕዝብ ምስለ አርዳኢሁ ወይቤሎሙ ዘይፈቅድ ይፀመደኒ ይጽልአ ለነፍሱ ወያጥብዕ ወይፁር መስቀል ሞቱ ወይትልወኒ ከደቀ መዛሙርቱም ጋር ሕዝቡን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፡፡ ሊከተለኝ የሚወድ ሰው ራሱን ይካድ፤ ጨክኖም የሞቱን መስቀል ተሸክሞ ይከተለኝ ይላል፡፡

    ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በ1ኛ ቆሮ. 1፤17 ላይ ወኢኮነ በጥበበ ነገር ከመ ኢንስዐር መስቀሎ ለክርስቶስ የክርስቶስን መስቀሉን ከንቱ እንዳናደርግ ነገርን በማራቀቅ አይደለም ይላል፡፡

    ጌታችን በተሰቀለ ዕለት ከሰድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በምድር ሁሉ ላይ ጨለማ ሆነ፡፡ /ፀሐይ ጨለመ/፣ እነሆም የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ፤ ምድርም ተናወጠች፤ ዓለቶችም ተሰነጠቁ፤ መቃብሮችም ተከፈቱ፤ ተኝተውም ከነበሩት ቅዱሳን ብዙዎች ተነሱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ከመቃብሮች ወጥተው ወደ ቅድስት ከተማ ለብዙዎች ታዩ፡፡ /ማቴ. 27፤51/

    ጌታችን ለዓለሙ ያሰበውን ቤዛነት ሊፈጽም በመስቀል ላይ መሰቀሉ የሚታሰብበት ነውና ለስቀለቱ መታሰቢያ የሚሆን አጎበር ተዘጋጅቶ ከርቤ እየታጠነ ስቅለቱ የሚመለከቱ ምንባባት ሲነበብና ሲሰገድ ይዋላል፡፡ የሰው ልጅ በሙሉ በእግረ አጋንንት ረግጦ ከፈጣሪው ተጣልቶ ለ5500 ዘመን በጨለማ መኖሩን ለማስታወስም መንበሩ ታቦቱ በዚህ ቀን በጥቁር ልብስ ይሸፈናሉ፡፡ ዲያቆኑም በቤተ ክርስቲያን በመዞር የሚያሰማው የቃጭል ድምፅ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለቅሶ አንድም ዋይ ዋይ እያሉ የተከተሉት የኢየሩሳሌም ሴቶችን ሙሾም ምሳሌ ነው፡፡ /ሉቃ. 23፤31/

    በዕለተ ዓርብ ነፍሳት ከሲኦል ወጡ፡፡ አንቀጸ ገነት ተከፈተልን፣ ርስተ መንግስተ ሰማያት ተመለሰችልን፤ አባታችን አዳምም ከፈጣሪው ጋር ታረቀልን በማለት ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃዶ እያልን የተድላ፣ የደስታ ምልክት ወይም መገለጫ የሆነ ልምላሜ ያለውን ቆጽለ ሆሣዕና ወይም ቄጤማ ግጫ ይዘን የምሥራች እንባባላለን፡፡ /ኤፌ. 2፤14-15/ ወዘእንበለ ምሳሌሰ ኢተናግሮሙ፣ ያለ ምሳሌ አልተናገረምና እንዳለ /ማቴ 13፤34-35/ በኖኅ ጊዜም ርግብ ሐጸ ማየ አይኅ፣ ነትገ ማየ አይኅ፣ የጥፋት ውኃ ጎደለ፣ አለቀ እያለች ቈጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ለኖኅ አብስራዋለች፡፡ /ዘፍ. 8፤8-11/

    ርግብ የካህናት፣ ኖኅ የምእመናን፣ ኖኅ እጁን ዘርግቶ ርግብን እንደተቀበላት ካህናትም በየመንደሩ እየዞሩ ክርስቶስ ተመረመረ ዲያብሎስ ታሰረ በማለት ቄጤማ ሲያድሉ ምእመናንም እጃቸውን ዘርግተው መቀበላቸው የዚህ ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢገኝ የወይራ ልምላሜ ቢታጣ ግጫን እየታደልን የምሥራች መባባላችን ነፍሳት ከሲኦል ለመውጣቸው መታሰቢያ ነው፡፡ ይህን ቈጽለ ልምላሜ ይዞ ተድላ፣ ደስታ መግለጽ ከጥንት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ለዚህ በመጀመሪያዪቱ ቀን ከበጎ እንጨት ፍሬን የሰሌንና የተምር ዛፍ ልምላሜ ይዛችሁ በየዓመቱ ሰባት ቀን ተድላ፣ ደስታ ታደርጋላችሁ ብሏል፡፡ /ዘሌ. 23፤40-44/

    በሰሙነ ሕማማት ጊዜ ቤተ ክርስቲያናችን የምታደርገው ትውፊት የሐዋ. ሥራ 1፤3

    ከሆሣዕና እስከ ቀዳም ሥዑር ያሉት ዕለታት የዓመተ ፍዳ መታሰቢያ ናቸው፡፡ ፡፡ ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ በዚህ ሣምንት ውስጥ ለሚሞቱ ምእመናን እግዚኦ ሕያዋን ይደገማልና፡፡ በሰሙነ ሕማማት መስቀል የለም፡፡ ሣምንቱ የዘመነ ኦሪት ምሳሌ ስለሆነ እርስ በእርስ መሳሳም፣ ሰላም መባባልና መልክዐ መልክዕ መድገም የለም፡፡ ይኸውም ይሁዳ ክርስቶስን በሰላምታ ስላስያዘው እርሱን ላለመምሰል፡፡ /ማቴ. 26/

    በዚህ ሳምንት ብሉያትና ሐዲሳት መጻሕፍት ከጠዋት እስከ ማታ ይነበባሉ፡፡ የአምልኮ ስግደት ይሰገዳል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል መስቀልን ተሸክሞ ሲወድቅ ሲነሣ የዋለበትን፣ ይልቁንም ሥርዓተ ስግደትን ራሱ ሰግዶ እኛን ያስተማረንን በማሰብ ነው፡፡ /ሉቃ. 22፤41-45፣ ዮሐ. 4፤22-24/

    ስለዚህም በዚህ ሳምንት ወርኃዊ፣ ዓመታዊ በዓል ቢሆን እንኳ ስግደት አይቋረጥም፡፡ የአምልኮ ስግደት ሳምንት ስለሆነ፡፡ ዲያቆኑ ጥቁር ለብሶ መስቀል ይዞ ቃጭል እያቃጨለ ቤተ ክርስቲያንን ሦስት ጊዜ መዞሩ ዲያቆኑ የዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፣ ቃጭል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆኑ፤ ዮሐንስና እመቤታችን ጌታችን የተሰቀለበትን እግረ መስቀሉን እየዞሩ አልቅሰው ነበርና፡፡

    በዕለተ ዓርብ ሠርክ ሲሆን ምእመናን ወደ ቄሱ እየቀረቡ ስግደት እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ቄሱም በወይራ ቅጠል እየጠበጠበ ተጨማሪ ቀን ሲሰግዱ ከዋሉት ሌላ ስግደት ይሰጣቸዋል፡፡ ጥብጠባ የጌታችን ግርፋት ምሳሌ ነው፡፡ አንድም የተግሣፅ ምሳሌ ነው፡፡ /ማቴ. 26፤27/

    አክፍሎት

    አክፍሎት ማለት ማካፈል፣ ማጠፍ፣ መደረብ፣ ሁለቱን ቀን አንድ አድርጎ መጾም፣ ጌታ ከተያዘበት እስከተነሣበት ድረስ ይህ ሥርዓት የመጣው በቤተ ክርስቲያናችን ልማድ እመቤታችን፣ ያዕቆብና ዮሐንስ የጌታን ትንሣኤ ሳናይ እህልና ውኃ አንቀምስም ብለው እስከ ትንሣኤ በመቆየታቸው ምክንያት ነው፡፡ በሀገራችን ብዙ ሰዎች ሐሙስ ማታ የቀመሱ እሑድ የትንሣኤ ዕለት ብቻ እህልና ውኃ የሚቀምሱት፤ ያልተቻላቸው ግን ዓርብ ማታ የቀመሱ እስከ ትንሣኤ ይሰነብታሉ፡፡ የሁለት ቀን ማክፈሉ እንኳ ቢከብድ ቅዳሜን ማክፈል ሥርዓት ነው፡፡ ቅዳሴው በመንፈቀ ሌሊት ስለሆነ በልቶ ማስቀደስና መቁረብ እንዳይሆን፡፡

    • የተሰጡ አስተያየቶች
    • በፌስቡክ (Facebook) የተሰጡ አስተያየቶች

    0 comments:

    Post a Comment

    Item Reviewed: ሰሙነ ሕማማትና ምስጢሩ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top