• በቅርብ የተጻፉ

    Tuesday 17 November 2015

    አሥሩ የማኅሌት ደረጃዎች ክፍል ፫


    ከባለፈው የቀጠለ….  

    4.  ማንሳት፡-  

    ማንሳት እምንለው መሪው ከመራ በኋላ በቀኝና በግራ ያሉ ሌሎች መምህራን ያንኑ እርሱ ያለውን ቃለ እግዚአብሔር ደግመው እንዲያነሡት ይደረጋል፡፡ ከመሪው ጋር ሦስት መሆናቸው ነው፡፡

    ይህም፡-

     4.1 ክርስቶስ የሞተው በሦስቱ (በጲላጦስ፣ በሔሮድስ፣ በቀያፋ) ፈቃድ መሆኑን የምንገልጥበት ምሥጢር ነው፡፡ አይሁድ ከሀና ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ ወደ ሔሮድስ ሲያመላልሱት አድረው እንደነበረ ለማስታዎስ ሊቃውንቱ ለእለቱ ተስማሚ የሆነውን ቀለም መርጠው በቀኝና በግራ እየተቀባበሉ ያነሡታል፡፡ በአንዳንድ ታላላቅ ቦታዎች ደግሞ ምልጣን ሲመራ መሪውና በቀኝ በግራ ያሉ አንሽዎች መስቀል እንዲይዙ ይደረጋል ይህም የሚሆነው መካከሉ የጌታችን ምሳሌ ስለሆነ በቀኝና በግራው አብረውት የተሰቀሉ ወንበዴዎችን ለማሳየት ነው፡፡

    በቀኝና በግራ ያሉት እንዲያነሱት መደረጉ ጌታችን በተሰቀለበት እለት የሚያልፉት ህዝቡ ሁሉ በቀኝና በግራ የተሰቀሉትን እያዩ ይህ ምንድነው? ይህስ ምንድነው? እያሉ ይጠይቁ ስለነበር ነው፡፡ በመካከላቸው ያለው ክርስቶስም እንደነ እርሱ ወንበዴ የሚል ስም ወጥቶለት ነበርና ሊቃውንቱ ያንን ለመግለጥ አንዱን ቃለ እግዚአብሔር እየተቀባበሉ ያዜሙታል፡፡

      4.2 የዳግም ምጽዓቱን ፍርድ ለማሳየት፡- የጌታችን ዳግም ምጽዓት ቤተ ክርስቲያን የማያልፈውን ዓለም የምትቀበልበት እለት ስለሆነ በተስፋ ስትጠብቀው የምትኖር የተስፋ ቀኗ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በቃልና በተግባር ስትሰብከው ትኖራለች፡፡ በቅኔ ማኅሌት ያሉመምህራንም ጌታ ሲመጣ ያለውን የፍርድ ሂደት ለመግለጥ መሪው መርቶ እስኪጨርስ ድረስ ዝም ይላሉ ከዚያ በኋላ በቀኝና በግራ ያሉት መምህራን በየተራቸው እንዲያነሡ ይደጋል፡፡

    በፍርድ ቀንም ይህ ሊሆን ግድ ነው፤ ማለትም በመላእክት አለቃ አዋጅ፣ በመለከትና በነጋሪትም ድምጽ የሞቱት ሁሉ ተነሥተው በማኅሌት እንዳሉ ሰዎች ሁሉ የትንሣኤያችን መሪ የሆነውን የክርስቶስን ድምጽ እየሰሙ ዝም ብለው ይቆያሉ ከእርሱ ቀጥለው በቀኝና በግራው ለፍርድ የተሰበሰቡ ሕዝቡ ይናገራሉ እሱ የሚናገራቸው በማቴ 25÷34-45 ያሉትን ቃላት ነው፤ እነርሱም ያንኑ መልሰው ለጻድቃንና ለኃጥአን እንደሚገባ አድርገው ይናገሩታል፡፡ ምዕመናን በፍርድ ቀን ተጠይቀው የሚሉትን እንዳያጡ ቅዱስ ሐዋርያ ጳውሎስ እንደተናገረው ሁላችን በፍርድ ዙፋን ፊት የምንቆምበት ቀን መኖሩን እንዳይዘነጉ የምታደርግበት ምሥጢራዊ የምስጋና ጊዜ ነው፡፡

          ሦስቱም መስቀል እንዲጨብጡ መደረጋቸው፡- የመሃሉን ያየን እንደሆነ ክርስቶስ መስቀሉን በፊቱ አድርጎ በመስቀል ላይ የተወጋ ጎኑን የተቸነከረ እጅና እግሩን እያሳየ የወጉት አይሁድ ሳይቀር አይተው እስኪፀፀቱ ድረስ ሆኖ ይመጣል፤ (በእርግጥ አንዲህ ስንል ያን ጊዜ የቆሰለ እጅና እግር፣ የተወጋ ጎን ይኖረዋል ማለታችን እንዳልሆነ ግልጥ ነው እንዲያው በእለተ ዓርብ የተቀበለውን መከራ አምነው የተቀበሉትን ነጻ የሚያወጣበት፣ ያላመኑትን ደግሞ በፍርድ የሚቀጣበት እለት መሆኑን ለመግለጥ ነው እንጅ) በቀኝ ያለው መስቀል ጻድቃን እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ መስቀሉን ተሸክመው ይኖራሉና ‹‹መስቀሌን ያልተሸከመ….›› ማቴ 16÷24 ብሎ ያዘዛቸው ጌታ በመስቀሉ ፋንታ ዘውድ ሊደፋላቸው፣ ደስታን ሊያስታጥቃቸው መምጣቱን ለመግለጥ ነው፡፡ በግራ ያለው ደግሞ፡- ኃጥአን በሕይወታቸው ተደላድለው ተቀማጥለው ስለሚኖሩ በሥጋቸው መስቀል አይሸከሙም ለሥጋቸው በሰጡት አርነት ምክንያት ጻድቃን በሥጋቸው የተሸከሙትን መስቀል ኃጥአን በሥጋቸውም በነፍሳቸውም የሚሸከሙበት ጊዜ እንደደረሰ የሚያሳይ ምሥጢር አለው፡፡

    5 ዝማሜ ፡- ዝማሜ ማለት ሊቃውንቱ በመቋሚያቸው ብቻ በመጠቀም ሌሎችን የዜማ መሳሪያዎችን ሳይጠቀሙ የሚያቀርቡት ምስጋና ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚወደደው የዝማሜ አይነት የተክሌ ዝማሜ ነው ርክርክ ይበዛበታል፣ መቋሚያን ከቀኝ ወደ ግራ ከግራ ወደ ቀኝ እያሉ በብዛት ማወዛወዝን ይጠይቃል፡፡ የሊቃውንቱ መቋሚያ ወደ ላይ ይወጣል ወደታችም ወርዶ መሬቱን ይመታል፤

    5.1 ምድራዊ ኑሯችንን ይገልጣል፡-

          ሥጋና ደምን ተካፍሎ ወደ ዓለም የመጣ ማንኛውም ፍጡር በዚህ ምድር በሚያደርገው ኑሮ ውስጥ መውጣትና መውረድ፣ መውደቅና መነሣት፣ ወደ ቀኝና ወደ ግራ ማለት የተፈጥሮ ግዴታ ነው፡፡ በሥጋ ከወለዱ እናቶች ሁሉ የሴቶችን ልማድ ካራቀላት ከእመቤታችን በስተቀር ሌሎች እናቶች በሙሉ በጭንቅና በምጥ ይወልዳሉ፤ በዚህ ሕግ የተወለደው ሁሉ ደግሞ በኑሮ ምጥ ውስጥ እያማጠ ራሱን ለታላቅ ነገር ይወልዳል፤ ራስን ለትልቅ ነገር ለመውለድ የሚደረገው ጥረት ብዙ ጭንቅን የሚያስከትል በመሆኑ እስከ ቃል ህቅታ ድረስ ጥግልን ይጠይቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ስንወድቅ ስንነሣ፣ ስንዘራ ስንታጨድ፣ ስንበተን ስንሰበሰብ እንኖራለን፤ ይህንንም በዝማሬያችን የዝማሜ ክፍል ለመግለጥ ሊቃውንቱ መቋሚያቸውን ወደላይ አውጥተው መሬት ያወርዱታል፣ ወደ ቀኝ ወደ ግራ ያመላልሱታል::

          በዚህ ሥርዓት ውስጥ በእደ እግዚአብሔር የተያዘችው የሰው ልጆች ነፍስ መቋሚያው ወደላይ እንዲወጣ በንስሐ በተመስጦ ወደ ላይ ወደ ፈጣሪያዋ ትነጠቃለች የዓለምን እስራት ለማምለጥ ትፍገመገማለች፤ ነገር ግን ምድራዊ ባሕርዩአ እየከበዳት ሥጋና ደም እየጎተታት መልሶ መሬታዊ ግብር ያሠራታል፤ ተመስጦዋን ዝምታዋን የዓለም ጫጫታ ይቀማታል፡፡ አንዳንድ ጊዜም በክፉና በበጎ ሀሳብ ተከበን እናማጥናለን ንድ ጊዜ ወደ ቀኝ ሌላ ጊዜም ወደ ግራ ስንል እንኖራለን፤ ሊቃውንቱ ምስጋናቸውን በዚህ መንገድ ማቅረባቸው በኃጢአት እየወደቅን በንስሐ እየተነሣን፣ በሁለት ሀሳብ እያመነታን ምስጋናን እናቀርብልሀለን ለማለት ነው፡፡

          አንድም፡- በኃጢአት ብንሰነካከል አንሥተኸናል፣ ወደግራ (ገሐነም) ብንጣል ወደ ቀኝ መልሰኸናልና ላንተ ምስጋናን እናቀርብልሀለን ማለታቸው ነው፡፡

    መቋሚያቸውን ብዙ ጊዜ ይወዘውዛሉ፣ ዜማውን በብዙ ርክርክ ያዜማሉ፤ ርክርክ በበዛበት ኑሮ ውስጥ እየኖርን፣ በጽድቅና ኃጢአት እየተወዛወዝን፣ ደረትና ድፋት፣ ጭረትና ጎሽምጥ፣ ሂደትና ርክርክ፣ አንብርና ድርስ በሚበዛበት ኑሮ ውስጥ እያለፍን እናመሰግነው ዘንድ የተፈቀደልን እድሜ ወደ መቃብር እስክንወርድ ያለው ብቻ በመሆኑ ‹‹መኑ በመቃብር ዘይሴብሆ ለልዑል፤ በመቃብር ውስጥ ታላቁን አምላክ የሚያመሰግነው ማነው›› እያልን ከማድነቅ ጋራ በተሰጠን እድሜ እንዲህ እናመሰገናለን፡፡

    መቋሚያቸውን ሊቃውንቱ በቀኝ በኩል እንዳሳረፉት መጨረሳቸው ደግሞ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ነው፤ ምንም እንኳን ሥጋውያን ደማውያን ፍጥረት በመሆናችን ላይና ታች፣ ቀኝና ግር ስንል ብንኖርም መጨረሻችን ግን በአምላካችን ቀኝ መቆም መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አሁን በዚህ ምድር ላይ በብዙ መከራ ራሷን ታማጥናለች፣ የፈተና ማዕበል ትንገላታለች የዚህ ሁሉ ነገር ፍጻሜው ታዲያ በቀኝ በኩል እንደ ተጣለው መረብ ከመቃብር ስንወጣ ብዙ ዓሣን (ክብርን) ታቅፎ ለመገኘት ነው፤ስለዚህም የመምህራኑ መቋሚያ በቀኝ በኩል እንዲጨረስ ይደረጋል የቤተ ክርስቲያን መጨረሻ በእግዚአብሔር ቀኝ ነውና፡፡

    5.2 የእለተ ዓርቡን የክርስቶስን መከራ ለማስታወስ፡- አይሁድ ጌታ በእጃቸው ከገባ በኋላ ያለ አንዳች እረፍትና ርህራሄ ነው ከወዲያ ወዲህ ፣ ከወዲህ ወዲያ ያመላለሱት፡፡ ሊቃውንቱም እጃቸው ላይ ያለውን መቋሚያ ከወዲያ ወዲህ፣ ከወዲህ ወዲያ ያወዛውዙታል፣ ከታች ጫፉን ይዘው ከሚያራራ ዜ ጋር ደፋ ቀና እንዲል ያደርጉታል፤

          ለቤተ ክርስቲያን ስትል እንዲህ ያለ መከራ ተቀብለሀል፣ ወድቀሀል ተነሥተሀል፣ በመውደቅህ እኛን ስተመስል በትንሣኤህ ደግሞ እኛ አንተን እንድንመስል አድረገኸናል እያሉ ሊቃውንቱ መከራውን በዐይነ ኅሊና እየተመለከቱ እንደ ብዙ ውኃ ድምጽ ባለ ብዙ ድምጽ ተግተው ያመሰግናሉ፡፡ ጌታችን ይህን መከራ ሲቀበል ስለ እርሱ መከራ ይመጣብናል ብለው ሳይሰቀቁ ከኋላው እየተከተሉ የሚያለቅሱ ሴቶች ነበሩና ያን ድምጽ በመሰለ የኃዘን ድምጽ በእግረ ኅሊና ከኋላው እየተከተሉ የመስቀል ምልክት ከጫፉ ላይ የማይለየው መቋሚያቸውን ይዘው ያዜማሉ እመቤታችን፣ ዮሐንስና ሌሎችም ቅዱሳት አንስት ከመስቀሉ እግር ሆነው ያሰሙትን የለቅሶ ድምጽ ለማስታዎስ ነው፡፡

          ከላይ እንደተናገርነው የዝማሜው መጨረሻ ላይ ሊቃውንቱ መቋሚያቸውን በቀኝ በኩል ማሳረፋቸው በዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ያለፈው ጌታ ከትንሣኤው በኋላ በአባቱ ቀኝ ተቀመጦ የሚኖር ስለሆነ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖቷን በምትገልጥበት ጸሎቷ ዘወትር (ወነበረ በየማነ አቡሁ) እያለች ስታመሰግነው ትኖራለች፡፡ የመጨረሻውን የቤተ ክርስቲያንን መዳረሻ ለማሳየት አሁን ለሚታይላቸው ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ቀኝ ሆኖ ይታያል፤ የሐዋ.ሥራ 7÷54       

    • Blogger Comments
    • Facebook Comments

    2 comments:

    1. Kale hiwot yasemalen gn ke 5 buhala yaluten aletezerezerem ke 5 eseka 10.....

      ReplyDelete
    2. 6 7 8 9 10 ልቀቁልኝ

      ReplyDelete

    Item Reviewed: አሥሩ የማኅሌት ደረጃዎች ክፍል ፫ Rating: 5 Reviewed By: Getahun Amare - ጌታሁን አማረ
    Scroll to Top